በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ረጅም ዓመታት ቆይቷል። ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሙሉ ትኩረቱን በእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች ስራ ላይ አድርጓል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን በራሱ አምርቶ ወደ ውጪ ሀገር በመላክም ከኢትዮጵያ ቀዳሚው ድርጅት ለመሆን በቅቷል። በአሁኑ ግዜ ደግሞ ከኬንያ ትእዛዝ ተቀብሎ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን ለመላክ ዝግጅቱን አጠናቋል።
በራስ አቅምና ባለሙያ ጥረት የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በማምረት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጪ ገበያ ውስጥም የገባው ድርጅቱ በሰዓት መቶ ኩንታል የእንስሳት መኖ ማቀነባበር የሚችል ማሽንም ለመስራት ችሏል። በዚህም ከአገር ውስጥና ከአገር ውጪ በርካታ እውቅናዎችንና ሽልማቶችን አግኝቷል።
ለድርጅቱ የመሥሪያ ቦታ ችግር ፈተና ቢሆንም በተከራየው ቦታ ላይ ማሽኖችን የማምረት ጥረቱን የቀጠለበት ሲሆን በቀጣይ የራሱን መሥሪያ ቦታ የሚያገኝ ከሆነ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ከማምረት በዘለለ የእንስሳት መኖንም ጭምር በራሱ በማምረት ለገበያ የማቅረብ እቅድ ይዞም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል- ኢሜክ ኢንጂነሪንግና አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር።
አቶ ኤፍሬም ሃይሉ የኢሜክ ኢንጂነሪንግና አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ባለቤት ናቸው። ውልደታቸውና እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ከተከታተሉ በኋላ በ1970 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ኮሌጅ በኤሌክትሪክ አድቫንስድ ዲፕሎማ አግኝተዋል። በጣና በለስ ፕሮጀክት ውስጥ ገብተውም ለአስራ ሁለት ዓመታት ሰርተዋል። በነዚህ ዓመታት ቆይታቸውም በኢንዱስትሪያል ኤሌክትሪክ ሜካኒካል ስራዎች ጋር በተያያዘ ከተለያዩ የውጪ አገር ዜጎች ጋር የመሥራትና ስልጠናዎችን የመውሰድ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል።
ከማኔጅመንት ኢንስቲትዩትም በኢንዱስትሪያል ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሙያዎች የተለያዩ ሰርተፍኬቶችን አግኝተዋል። ከዚሁ ሙያ ጋር በተያያዘም በተለይ የኤሌክትሪክ ኃይል ቁጥጥር ላይ በኦን ላይን የተለያዩ ሰርተፍኬቶችን ተቀብለዋል። የተማሩት የኤሌክትሪክ ትምህርት ደግሞ በዚሁ ዘርፍ ላይ ገብተው የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ በሩን ከፍቶላቸዋል።
አቶ ኤፍሬም በ1994 ዓ.ም ‹‹ኤሌክትሮ ኢሜክ ኢንጂነሪንግ ሰርቪስ›› የሚባልና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን የሚያከናውን የራሳቸውን ድርጅት በአምስት ሺ ብር መነሻ ካፒታል አቋቋሙ። የራሳቸውን ድርጅት አቋቁመው ለመስራት የፈለጉበት ዋነኛ ምክንያት በኢንዱስትሪያል ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ያላቸውን ልምድና እውቀት በግላቸው ተግባራዊ ለማድረግ በመፈለጋቸው ነበር። በግዜው በኤሌክትሮ ሜካኒካልና በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ብዙ ባለሙያ ስላልነበረ የድርጅታቸው ዋነኛ ዓላማም በዘርፉ ባለሙያ ለማፍራትና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ጥገናዎችን ለማካሄድ የነበረ በመሆኑ በኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች በተለይ በውሃ፣ በኤሌክትሪክና አግሮ ኢንዱስትሪ ላይ ለመስራት ተነስቷል። በዚህም ዘርፍ ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ ሰራተኞችን ማሰልጠን ችሏል። የሪዋይንዲንግ፣ የቦሮን፣ የቁፋሮና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ፓምፖች የጥገናና ተከላ፣ የተለያዩ የኃይል ጄኔሬተሮችን ጥገና፣ የተለያዩ ማሽነሪዎችን የመትከል እንዲሁም ማሽነሪዎችን በትእዛዝ የማምረት ስራዎችንም አከናውኗል።
ላለፉት አስራ ዘጠኝ ዓመታትም በዚሁ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች በርካታ ባለሙያዎችን ካፈራ በኋላ በዛው ዓመት በተጓዳኝ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ማምረት ጀመረ። የሃዋሳና ሲዳማ የዶሮ እርባታ ሥራን በኮንትራት አግኝቶም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዶሮ እርባታና የቀንድ ከብት መኖ ኢንዱስትሪ በመጎብኘትና የጎደሉ ነገሮችን በሟሟላት ማሽኖችን አመረተ። በግዜው ድርጅቱ ለሥራው አዲስ ቢሆንም በሂደት ሥራዎችን በማጥናት ማሽኖቹን አምርቶ አስረከበ። ማሽኖቹ ውጤታማ ሆነው በመገኘታቸውም ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ከደንበኞች ይጎርፉ ጀመር።
ላለፉት አስር ዓመታትም ድርጅቱ ከትናንሽ እስከ ትላልቆቹ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች ድረስ በማምረት እራሱን እያሰፋ መጣ። ይሁንና በነዚህ አስር ዓመታት ውስጥ ድርጅቱ ምርቶቹን ሲያስተዋውቅ በተለይ በአርሶ አደሩ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ አንድም ገዢ አልነበረውም። የግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ በዘርፉ ላይ ያሉ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ቢያማክርም አብዛኛቹ ወደ ድርጅቱ አልመጡም። በዚህ አስር ዓመት ውስጥም በዘርፉ ሰፊ ጥናት ሲያካሂድ ቆየ። ሰባ የሚሆኑ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖችንም ማምረት ቻለ። የግብርና ተረፈ ምርቶችን ወደ እንስሳት መኖ የሚቀይሩ፣ ከእህል ዘር መኖን የሚያዘጋጁ ፣ የሳር ዘሮችን ማድቀቅ የሚችሉ ማሽኖችንም አመረተ።
ድርጅቱ ለአስር ዓመታት በዚህ ዝግጅት ውስጥ ከቆየ በኋላ አንድ ‹‹ናሽናል ዴይሪ›› የተባለ ፎረም በሂልተን ሆቴል ሲካሄድ ተጋብዞ በመገኘት ምርቶቹን አሳየ። በዚህም ከእንስሳት መኖ ባለሙያዎች፣ በግብርናው ዘርፍ ካሉ ሰዎችና በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ካሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር የመገናኘትና የመተዋወቅ እድል ገጠመው። በዚሁ መሰረት የመጀመሪያውን ለፀሐይ የገበሬዎች ዩኒየን አስራ አምስት ኩንታል የእንስሳት መኖ የሚያቀነባበር ማሽን መስራት ቻለ። በመቀጠልም ለአክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ ለሥጋና ወተት ኢንስቲትዩት፣ ለአምቦ የገበሬዎች ዩኒየን፣ እሪኩምና ወደራ የገበሬ ዩኒየኖች ምርቶቹን በስፋት እያቀረበ መጣ።
ቀደም ሲል ድርጅቱ የሚያመርታቸው የእንስሳት ማቀነባበሪያ ማሽኖች የማምረት አቅማቸው በሰዓት ከሶስት እስከ አምስት ኩንታል ማቀነባበር የሚችሉ የነበረ ቢሆንም በሂደት ግን ማሽኖቹ ዘምነው በሰዓት መቶ ኩንታል የማቀናበር አቅም ያላቸው ማምረት ችሏል። በአሁኑ ግዜም ሰባ የሚሆኑ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን ማምረት ደረጃ ላይ ደርሷል። በእያንዳንዱ ደረጃ ዘርፍ ደግሞ በሰአት ከአስር እስከ መቶ ኩንታል ማቀናበር የሚችሉ ማሽኖችንም ያመርታል።
እነዚህን ማሽኖች ሲያመርትም ማሽኖቹን ከማምረት በዘለለ የአገሪቱን ችግርም ከግምት ውስጥ በማስገባት የግብርና ተረፈ ምርቶችን ወደ እንስሳት መኖነት መቀየር አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት የተለያዩ የአገዳ እህሎችን የሚያቀነባብሩ የተለያዩ የመፍጫና መከትከቻ ማሽኖችንም አምርቷል። በዚሁ ዘርፍም ከግብርና ሚኒስቴር፣ ግብርና ምርምርና ከሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየሰራ ይገኛል።
በአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢትዮጵያ ሰፊና ለእንስሳት መኖነት የሚውል ሃብት ቢኖራትም ሀብቱን አቀነባብሮ ወደ እንስሳት መኖነት የመቀየር ፍላጎት በስፋት ባለመኖሩ ድርጅቱም ማሽኖችን በሚፈልገው ልክ እያመረተ አይደለም። ከዚህ በመነሳትም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን በየክልሉ በመዞር በዘርፉ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ያካሂዳል። ከዚህ በፊትም ለስምንት አመት ማሽኖቹን በየክልሉ በማዞር በእንስሳት መኖ ማቀነባበር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥቷል።
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ማሽኖች ጥራት ያላቸውና ስታንዳርዱን ያሟሉ ስለመሆናቸው በሚመለከተው አካል ያስፈትሻል። ሁሉንም ማሽኖች በሳይንስና ቴክኖሎጂና የአእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት እንዲመዘገቡም አድርጓል። ሌሎች ማሽኖችንም በማስመዝገብ ሂደት ላይ ይገኛል። ከሚያመርታቸው ማሽኖች ውስጥ ደግሞ መኖውን ተቀብሎ ፣ ፈጭቶ፣ አጓጉዞና አቀነባብሮ የሚያስቀምጥ ኢንቲግሬትድ ኮምፓውንድ ማሽን አንዱ ሲሆን በሰአት ከአስር እስከ አንድ መቶ ኩንታል የማቀናበር አቅም አለው። በተጨማሪም አገዳንና ሳርን የሚከተክቱ፣ የሚያደቁ፣ በቤለር የታሰሩና ያልታሰሩ ሳሮችን የሚያደቁ ማሽኖችን ያመርታል።
ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በደንበኞች ትእዛዝ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖችንም እያመረተ ይገኛል። የበቆሎ ማሽኖች ከዚህ በፊት በአገሪቱ ተመርተው የነበረ ቢሆንም አቅማቸው ውስን መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት አቅሙን ለማሻሻል በሚል ወደ በቆሎ መፈልፈያ ማሽኖች ማምረት ሥራም ገብቷል። በአግሪ ሴፍ በኩልም ማሽኖቹ በተለይ በደቡብ ክልል አስራ አምስት አካባቢዎች ላይ እንዲገቡ አድርጓል። የድርጅቱ ትንሹ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ዋጋ 210 ሺ ብር ሲሆን በሰአት 10 ኩንታል ማቀናበር የሚችለውና ለሙሉ የተቀናጀ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያነት የሚውለው ማሽን ደግሞ 1 ሚሊዮን 200 ሺ ብር ዋጋ አለው። ይኸው ማሽን በሰዓት መቶ ኩንታል የማምረት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ ከተሰራ ደግሞ ዋጋው እስከ 10 ሚሊዮን ብር ሊጠጋ ይችላል። ማሽኖቹ ከውጪ ምርቶች ጋር ሲወዳደሩም ረጅም ዓመት አገልግሎት መስጠት የሚችሉና አቅማቸውም ከፍተኛ ነው።
ለውጪ ገበያ የሚሆኑ ማሽኖችንም ድርጅቱ የሚያመርት ሲሆን ባለፈው ዓመት ስድስት የእንስሳት መኖ መፍጫ ማሽኖችን ወደ ሶማሌላንድ ልኳል። እንዲህ አይነቱን የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ወደ ውጭ አገር በመላክም ከኢትዮጵያ ቀዳሚው ለመሆን ችሏል። ቀደም ሲል መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከዓለም የምግብ ፕሮግራምና ከእንስሳት መኖ ባለሙያዎች ጋር መስራቱ ደግሞ ወደ ውጪ ገበያ ምርቶቹን በቀላሉለመላክ አግዞታል።
አሁንም በተለይ በአፍሪካ ምርቶቹን እንዲያቀርብ ጥያቄዎች እየመጡለት የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ ምርቱን እንዲያቀርብ ከኬኒያ በኩል ትእዛዝ አግኝቷል። በአገር ውስጥም የድርጅቱን አብዛኛውን ማሽኖች የሚወስዱት የገበሬ ህብረት ስራ ዩኒየኖች ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በየአካባቢው ያሉ የግብርና ድርጅቶች፣ የዶሮ እርባታና በከብት እርባታ ላይ የተሰማሩ ሰዎች፣ ባለሃብቶች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም ይወስዳሉ።
የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራውን ብዙ እየሰራበት ባይሆንም ድርጅቱ በአሁኑ ግዜ በተለይ ደግሞ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ሙሉ ትኩረቱን በእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ማምረት ስራ ላይ አድርጓል። በአምስት ሺ ብር መነሻ ካፒታል ሥራውን ጀምሮም በአሁኑ ግዜ ካፒታሉ 23 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ሰባ ለሚሆኑ ሰዎችም ቋሚ የሥራ እድል ፈጥሯል። ለድርጅቱ እቃ የሚያቀርቡና ከኋላ ባሉት ሌሎች አምስት ድርጅቶች ውስጥ ለሚሰሩ ዜጎችም በተዘዋዋሪ ተጨማሪ የስራ እድል ፈጥሯል። በውጪ የሚያሰራቸው ሥራዎችም በመኖራቸው በተመሳሳይ ሌሎች ዜጎች በተጓዳኝ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። ለዩኒየኖች ማሽን ባቀረበ ቁጥር አባላት መኖን በራሳቸው እንዲያመርቱ አስችሏል። በአካባቢያቸው ያለውን የመኖ ሃብትና የግብርና ተረፈ ምርትም እንዲጠቀሙበት አድርጓል።
በቀጣይም ድርጅቱ የከብት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በስፋት በማምረት ወደ ህብረተሰቡ የመድረስ እቅድ አለው። ማሽኑን በብዛት ማምረት የሚችል ከሆነም ቀደም ሲል በ210 ሺ ብር የሚሸጠውን አነስተኛ ማሽን በሃምሳ ሺ ብር የማቅረብ ፍላጎት አለው። ከውጪ አቅራቢዎች የሚያስመጣቸውን 10 ከመቶ ያህሉን የማሽን ግብአቶች በራሱ ቀጥታ ማምጣት ቢችል ደግሞ በምርቱ ላይ ሃምሳ በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለገበያ የማቅረብ ሃሳብ ነድፏል። የማሽኖቹ ገበያ እንዲሰፋም በእጅና በነዳጅ እንዲሁም በሌሎችም አማራጮች የሚሰሩ ማሽኖችን አምርቶ የማቅረብ ውጥን አለው።
ኢትዮጵያ ከቻይና ይልቅ ለአፍሪካ ገበያ ቅርብ በመሆኗ የአፍሪካ አገራትም ከኢትዮጵያ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ብሎም ኢትዮጵያን ከሌሎች ጎረቤት የአፍሪካ አገራት ጋር የሚያስተሳስሩ መንገዶች በመገንባታቸው ምርቶቹን ወደነዚሁ አገራት በስፋት የመላክ እቅድ ይዞም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ለዚህም ሶስትና ከዛ በላይ የሚሆኑ ፋብሪካዎችን በማቋቋም ምርቱን በስፋት የማምረት ሃሳብ አለው።
‹‹የድርጅቱ ዋነኛ ፈተና የመሥሪያ ቦታ እጦት ነው›› የሚሉት አቶ ኤፍሬም የቅብብሎሽ የማምረት ዘዴን እንደማይከተሉና ነገር ግን በኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፍ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ድርጅታቸው ቦታን የመጠቀም ብቃትንና ማሽኖችን የማምረት ጥበብን በሚገባ እንደተካነ ይናገራሉ። ሆኖም ይህን ለማድረግ የመሥሪያ ቦታ፣ የኃይል አቅርቦትና ልዩ ልዩ መሳሪያዎች እንደሚያግዷቸው ያብራራሉ። በዚህ ሥራ የቦታ ጉዳይ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ድረስ መንግስትን እንዳልጠየቀም ያስረዳሉ። በአሁኑ ግዜ ግን ቦታ ለመጠየቅ የሚያበረታቱ ነገሮች በመኖራቸው ጥያቄዎችን እያነሱ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
ድርጅቱ በቀጣይ የመሥሪያ ቦታ የሚፈልግበት ዋነኛ ምክንያትም ከማሽኑ በዘለለ የእንስሳት መኖን በራሱ ለማምረት ፍላጎቱ ስላለው እንደሆነም ይጠቅሳሉ። ‹‹ኢሜክ ኢንጂነሪንግና አግሮ ኢንዱስትሪ›› በሚል የተቋቋመውም በኢንጂነሪንጉ ዘርፍ በእያንዳንዱ የሥራ ክፍል ውስጥ ሰራተኞችን በመቅጠር የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በብዛት ለማምረትና በአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በኩል ደግሞ የእንስሳት መኖውን በማምረት ለተጠቃሚው ለማቅረብ እንደሆነም ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ ሌሎችም ወደ እንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች ማምረት ሥራ መግባት ለሚፈልጉ በቅድሚያ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ባለሙያ ሆነው ማሽኑን ቢያመርቱ የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከማሽነሪዎቹ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ሆነው ደግሞ ማሽኑን ቢያመርቱ የተሻለ መሆኑንም ይጠቁማሉ። ዋናው ነገር ግን ለሥራው ታማኝ መሆን እንዳለባቸውና ሥራቸውን በእውነት ላይ ተመስርተው ማከናወን እንደሚገባቸው ምክራቸውን ለግሰዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2013