የአፍሪካ ልጆች ቀን ለምን ይከበራል?
ልጆች እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ሀገራችን ኢትዮዽያ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ከሚገኙ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንዷ ናት። ስለዚህ የአፍሪካ ሕፃናት ቀንን ከሚያከብሩት ውስጥ ናት ማለት ነው። እናንተም የአፍሪካ ህፃናት ናችሁ። እና ይህ “የአፍሪካ ህፃናት ቀን እንዴት መከበር ጀመረ?” የሚለውን ልንገራችሁ። እ.ኤ.አ1976 በደቡብ አፍሪካዋ ሴዌቶ ከተማ ጥቁር አፍሪካዊያን ልጆች በአገሪቱ የፀደቀውን ኢ-ፍትሃዊ የትምህርት ፖሊሲን ተቃውመው ሰለፍ ይወጣሉ። በወቅቱ ጥቁር አፍሪካዊያን ልጆች በአፓርታይድ ስርዓት ይደርስ የነበረውን ኢፍትሃዊ የትምህርት ፖሊሲ ለመቃወም በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ልጆች ሰልፍ ወጡ። የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ ደግሞ ጥቁር አፍሪካዊያን ልጆች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ለመጠየቅ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ሰልፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጆች በፖሊስ ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆሰሉ።
መብታቸውን ለመጠየቅ የወጡት ህፃናቶች መገደላቸውና መቁሰላቸው እጀግ የሚያሳዝን ነበር። እነዚህ በግፍ የተገደሉት ልጆችን ለማሰብ እ.ኤ.አ 1991 የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ሰኔ 9 በየአመቱ የአፍሪካ ልጆች ቀን ሆኖ እንዲከበር ውሳኔ አሳለፈ። ይህንን ፅሁፍ ለልጆቻችን ይሁን ብለው ያካፈሉን አቶ ብርሃኑ በላቸው አሰፋ (የHolistic Child Development ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ) ናቸው። ባሳለፍነው ረቡዕ በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ መብት የጠየቁ ሕፃናት በግፍ የተጨፈጨፉበትን ሰኔ 9 ቀን የአፍሪካ ልጆች ቀን “ለልጆች የምትመች አፍሪካ” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል።
ልጆች! ዋና ዋና የልጆች መብቶች የሚባሉትን ታስታውሳላችሁ? ካስታወሳችሁ በጣም ጎበዞች ናችሁ ማለት ነው። የዘናጋችሁና የማታውቁ ካላችሁ ደግሞ ዛሬ “የልጆች መብቶች” የሚባሉት ምን ምን እንደሆኑ እንነግራችኋለን።
ልጆች የመኖር፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት አላቸው። ከጉልበት ብዝበዛ፣ ከጥቃት፣ ከመገለልና ከማንኛውም በደል የመጠበቅ እንዲሁም በማህበራዊ ህይወታቸው ንቁ ተሳትፎ የማድረግ መብት አላቸው።
የአፍሪካ ልጆች ቀን ታዲያ በወቅቱ የነበረውን አግላይ የአፓርታይድ ትምህርት ፖሊሲ በማውገዝ አሁን ላይ ደግሞ የአፍሪካ ልጆች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ግንዛቤ በማስጨበጥ ይከበራል።
የአፍሪካ ልጆች ቀን በመላው አፍሪካ ያሉ ልጆች የትምህርት እድል እንዲያገኙ የበለፀጉ ሀገራት እና ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ በመቀስቀስ ይከበራል። ከዚህም በተጨማሪ በጎ ፍቃደኞች በልጆች ትምህርት ቤት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት ተከብሯል። ለልጆች የመፃህፍት እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ታስቦ ውሏል።
ለልጆች ፍሬያማነት ትምህርት ቁልፍ ሚና ስላለው ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይጠበቃል። በተለይም ወላጆች፣ መምህራን፣ መንግስት፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ሌሎችም በልጆች የትምህርት ተሳትፎ እና በትምህርት ጥራት ዙርያ በጋራ ሊሰሩ ይገባል።
ልጆች፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ አህጉራችን አፍሪካ እንዲሁም አለማችንም ጭምር ለእናንተ የምትመች፤ ሁሉም መብቶቻችሁ ተከብረው በተመቻቸ ሁኔታ፣ በንፁህ መንፈስ እንድታድጉ እመኛለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2013