ወይዘሮ መዓዛ መንክር ክሊኒካል ሣይኮሎጂስት ሲሆኑ፤ የልጆች አዕምሮ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ይሰራሉ። ለወላጆች ይበጅ ዘንድ ይኼንን ሀሳብ አካፍለውናልና እናመሠግናለን። “በመጀመሪያ ሁላችንም ልጆችን ከጥቃት እንከላከል። በልጆች ላይ ክፉ የሚያደርጉትን ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ድምፃችንን እናሰማ” ከሚሉት ከወይዘሮ መዓዛ ጋር መልካም ቆይታ።
የልጆች የዕድገት ዘርፎች የምንላቸው የአካላዊ ዕድገት፣ የሥሜት ዕድገት፣ የአዕምሮ ዕድገት፣ የማህበራዊ ግንኙነት ዕድገት፣ የቋንቋ/ተግባቦት እና የመንፈሣዊ ዕድገት ናቸው። ከላይ የተገለፁትን የዕድገት ዘርፎች ለማጎልበት የወላጆች፣ የቤተሠብ እና የመምህራን ብሎም የማህበረሰቡ ድርሻ ትልቅ ነው።
ስኬታማ ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲኖር ልጆች ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ነገሮች ከመንገር ይልቅ አርአያ በመሆን ማሳየት ልጆች የሚያደርጓቸውን ጥረቶች ማበረታታት እና መደገፍ። በራስ መተማመን በጣም አስፈላጊ ክሂሎት መሆኑን ማሳወቅ እና ክሂሎቱን እንዲያጎለብቱ ማገዝ። በዕለት-ተዕለት ከሚገጥሟቸው ችግሮችን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው እና ካጋጠማቸው ችግር ምን ሊማሩ እንደሚችሉ ማሳየት። ችግር የመቋቋም ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት። የልጆች ሀላፊነት፣ መብት እና ግዴታ ምንድነው የሚለውን ማሳወቅ ይኖርብናል።
ልጆች ያዩ እና የሰሙትን እንዲያደርጉ ብቻ ሣይሆን የራሳቸው የፈጠራ ክሂሎት እንዲኖራቸው ማበረታታት፤ ስለሚሰማቸው ሥሜት መግለፅ እና ምን ዓይነት ሥሜት እየተሰማቸው እንደሆነ እንዲገልፁ ማበረታታት፤ ከስህተት እና ከውድቀት መማር እንደሚቻል ማሳወቅ፤ ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት ማድረግ እና መደጋገፍ አስፈላጊነቱን ማስተማር፤ ውሳኔ የመወሰን ክሂሎት እንዲዳብር ዕድል መስጠትም ይጠበቃል።
ከልጅዎ ጋር እድሜው/ዋ በሚፈቅደው ጉዳዬች ላይ በግልፅ መወያየት እና ለልጆች ክብር እና ጊዜ መስጠት። ጥፋት ሲያጠፉ መቅጣት ብቻ ሣይሆን መልካም ሲያደርጉ ማበረታታት። ልጆች በቀለም ትምህርት ጥሩ እንዲሆኑ እንደምንለፋው ሁሉ ጠንካራ መንፈሣዊ መሠረት እንዲኖራቸው ትኩረት እንስጥ። እውቀት ያለሞራል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ከምንም በላይ ልጆች የሚያዳምጣቸው፣ የሚረዳቸው እና ባግባቡ የሚመራቸው ሰው ይፈልጋሉ – ወላጆች ይህንን አስቀድሙ። ውብ እና ድንቅ ሆነው በፈጣሪ አምሣል እንደተፈጠሩ መንገር። አቅም በፈቀደ ሁሉ የተመጣጠነ እና ቤት ውስጥ የተዘጋጀ ምግብ እንዲመገቡ እና ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ የወላጅ ግዴታ ነው። ለአካላዊ፣ ሥነልቦናዊ እና አዕምሯዊ ጉዳት እና አደጋ ተጋላጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መጠበቅ እና መከላከልም ይገባል።
የምድር በረከቶች የሆኑ ልጆቻችን በተገቢው መልኩ የተሟላ ዕድገት እንዲኖረው አቅም በፈቀደ የምንችለውን ነገር በሙሉ ማድረግ ይገባናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም