አስመረት ብስራት
ልጆች ከሀገራችን ተረቶች ስብስብ ውስጥ በአባባ ኢብራሂም ሸሪፍ የተተረከውን ለዛሬ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ። በማንበብ ብዙ ነገሮችን እንደምትማሩ ተገንዝባችሁ አንብቡ እሺ። መልካም ንባብ።
በአንድ ወቅት አንድ በጣም ሐብታም ሰው ነበር። ታዲያ አንድ ቀን ሐብትና ንብረቱን በሙሉ ሰብስቦ ወደ ሌላ ከተማ ሄዶ ለመኖር ጉዞ ጀመረ። በመንገዱም ላይ አንድ እንግዳ ሰው አግኝቶ ሠላምታ ከተለዋወጡ በኋላ አብረው መጓዝ ጀመሩ።
እንግዳው ሰው ሠላማዊ መንገደኛ ቢመስልም ከጥቂት ቆይታ በኋላ አንድ ፀጥ ያለ ቦታ ሲደርሱ እንግዳው ሰው ሐብታሙን ሰው “አሁን ልገድልህ ነውና የሚያድንህ ማነው?” አለው። ሐብታሙም ሰው ግራ ቀኙን ቢያይ ምንም ሰው የለም፤ ቀና ብሎ ሲመለከት አንዲት እርግብ ዛፍ ላይ ተቀምጣ ሲያይ “ይህች እርግብ ታድነኛለች።” አለ።
እንግዳውም ሰው በጣም በመደነቅ ከት ብሎ ከሣቀ በኋላ ሐብታሙን ሰው ገድሎ ንብረቱን በሙሉ ከዘረፈ በኋላ ወደ ከተማው ሄዶ እዚያ መኖር ጀመረ። በጣም ሐብታም ሰው ስለሆነም ቤተመንግሥት ውስጥ ድግስም ሆነ ስብሰባ በተደረገ ጊዜ ተጋብዞ ይሄድ ጀመር። ከዕለታት አንድ ቀን ንጉሱ በጣም ትልቅ ድግስ ደግሶ ሕዝቡን ሁሉ እንግዳውንም ጭምር ጋበዘ። ግብዣው በብዙ የምግብ ዓይነቶች የተትረፈረፈ ስለነበረ ሁሉም የፈለገውን ይመገብ ነበር። እንግዳውም የወደደውን ምግብ ይመርጥ ጀመር። በዚህ ጊዜ አንዲት የተጠበሰች እርግብ አየ። ሐብታሙን ሰው እንዴት እንደገደለው አስታውሶ ሲስቅ ንጉሱ አየውና በእርሱ የሚያሾፍ መስሎት ወታደሮቹ ይዘውት እንዲገድሉት አዘዘ።
በዚህ ጊዜ እንግዳው ሰው መሞቱ ስለማይቀርለት ለምን እንደሣቀ ለመናገር ወሰነ። ንጉሱም ምክንያቱን ከሠማ በኋላ አስገደለው። የእንግዳውም ሰው ሐብትና ንብረት በሙሉ ለሐብታሙ ሰው ህጋዊ ወራሾች ተመለሰ። ልጆች ማንም አያየንም ብላችሁ ሰዎች ላይ መጥፎ ነገር ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ከዚህ ተረት እንማራለን።
የራሳችሁ ያልሆነን ሀቅ አትመኙ፤ እሺ መልካም ሣምንት።
አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም