የተዛባ ታሪክና ባህል ማረም በሚል ርዕስ በሰሜን ሸዋዋ ደብረብርሃን ከተማ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። መድረኩ የሸዋን ታሪካዊና ባህላዊ ምንነት በኢትዮጵያዊነት መቃኘት በሚል ላይ ያተኮረ ነበር። የሸዋን ታሪካዊ ይዘት ወደነበረበት ለመመለስ ያለመም እንደሆነም አዘጋጆቹ ይናገራሉ። በወቅቱ የተለያዩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፤ በተለይ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የቀረበው ጥናት ብዙዎችን ያስደመመ ነበር።
ጥናቶቹ የሸዋን ምንነትና የኢትዮጵያን መገለጫነት በሚገባ ያሳዩ ናቸው። ለአብነት ጥቂት ነገሮችን አንስተን እንመልከት። ከ1268 ዓ.ም የይኩኑ አምላክ ዘመን ጀምሮ የሸዋ አማራ ሚና እያደገ የመጣበት፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ትስስሮችን ሳይነጣጠሉ የተተገበሩበት፣ ኢትዮጵያ ወደ ውህደት የመጣችበትና የቤተ ክርስቲያን ኢኮኖሚያው ኃይልና የፖለቲካ ሚና የተጠናከረበት ወቅት ነበር። ሃይማኖት በመንግሥቱ ውስጥ ሰፊ ቦታ ነበረውም።
በሸዋ የጸሐፊ ትዕዛዝ ሹመት የተጀመረበት፣ ሥነ-ጽሑፍ ያበበበት፣ የተማከለ የፖለቲካ አስተዳደር እንደ እነ አጼ ዘርአያዕቆብ አይነት የተፈጠሩበት፤ ቤተ ክርስቲያንን ለአንድነት ፖሊሲ የመጠቀም ስልት የተጀመረበት፤ ሀገር በቀል ልምድ ወደ እውቀት የተለወጠበትም ነው። ባህልና ሃይማኖታዊው እውቀቶች በስፋት የተተገበሩበትም ነበር።
ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲጠፉና ሃይማኖታዊ እሴቶች እንዲዳብሩ፣ ሴቶች በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እውነተኛ ተሰሚነትና ታላቅ ሚና እንዲጫወቱ የተደረገበት፤ የፌዴራሊዝም ፖለቲካዊ ሥርዓት ትግበራ የተጀመረበትም ነው። ለምሳሌ በአጼ በዕደማርያም ማለትም የዘርአያዕቆብ ልጅ ማንሳት ይቻላል። ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር የነበራት ግንኙነት ሰፊ ለመሆኑም አንዱ ማሳያው የሸዋ ኃያልነት በሌሎች አገራት ጭምር መታወቁ እንደነበርም ጥናቱ ያነሳል።
ከምሥራቁ ክርስቲያንና ከአጎራባች ሙስሊም ሀገሮች ጋር ሸዋዎች ጥብቅ ቁርኝት ነበራቸው። ከሌሎች ነገሥታት ውጪ በራሳቸው የውጭ ግንኙነትን በመፍጠር ይታወቁ ነበር። ለአብነት ከግብጽ የማምሉክ ገዥዎች የሰላም ትብብር ነበራቸው። በልብነድንግል አማካኝነት ከፖርቱጋል ጋር ግንኙነት ነበራቸው፤ የጦር ድጋፍ ትብብር፣ የንግድ ልውውጥም እንዲሁ በዚህ ዘመነ መንግሥት የነበረ መሰረት ነው።
ጥናቱ እንደሚለው ሸዋ ተመልሶ የጠፋበት ምክንያት መሰረቱ፤ ጣሊያኖች ለአድዋ ተሸናፊነታቸው ተጠያቂው እርሱ ነው ብለው አምነው የጥላቻ መርዝ በመዝራታቸው ነው። ቅኝ ገዥዎችን ያልተቀበለ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ያስተባበረና ትልቅ ጦርነት ያስተናገደ ነው ይሉታል ጣሊያኖች። በዚህም ኢትዮጵያን ለማዳከም መጀመሪያ መጥፋት ያለበት ሸዋ ነው ይላሉ። በዚህም የሸዋ መከፋፈልን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እንዲመጣ አደረጉ። ይሁንና ከ1941 እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ ሸዋ እንደገና አንሰራርቷል።
የቀድሞ የግዛት ወሰን መልሶ ያስተዳደረበት፣ የህዝብ አሰፋፈሩ እና ቁጥሩ የተስፋፋበት ነገር ግን በትንንሽ አስተዳደሮች የተከፋፈለበት ጊዜ ነበር። በደርግ ዘመን ለምሳሌ መንዝና ግሼ፤ ይፋትና ጥሙጋ፤ ተጉለትናቡልጋ፤ ከንባታና ሃዲያ ወዘተ እየተባለ ተከፋፍሏል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ሸዋ በክልል እና በዞን እንዲከፈል ሆነ። በሸዋና በአዲስ አበባ ላይ ዳግመኛ ከፍተኛ የመከፋፈል አጀንዳ ተዘረጋ። ይህ ደግሞ በሸዋ ላይ የጥፋት አለንጋውን እንዲዘረጋ አደረገው። ሰሜን ሸዋ ደግሞ የነበራት ታሪክ በእጅጉ ጎድፎ እንዲቀርብባት ሆኗል። አንዱ ገዢ ሌላው ተገዥ፡ አንዱ ወራሪ ሌላው ተወራሪ እንዲሁም ፈላጭና ቆራጭ እየተደረገ የሚሰነዘር ታሪክ አልባ ተግባርም መከወን የጀመረው ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር።
የጥናቱ አቅራቢና የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ መምህሩ አቶ ይጥና ገብረ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያን በሸዋ ውስጥ ወይም ሸዋን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማየት ታሪክን ወደኋላ መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል። ምክንያቱም በኢትዮጵያዊነት ስሪት ውስጥ የሸዋ ሕዝበ አሻራ ቀላል አይደለምና። ሁለንተናዊ የስሪቱ መነሻ የሆነውን ፖለቲካ፤ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ጥበብ፣ ታሪክ እና ባህል ይዞ በመጓዝ ታሪክ ሠርቷል። ለዚህም በአብነት የምናነሳው ከአጼ ይኩኑ አምላክ እስከ አጼ ምኒልክ ድረስ ያለውን ዘመነ መንግሥት ነው።
በሸዋ መሪዎች ኢትዮጵያን በኢትዮጵያኖች መሥራት እውን ሆነ፤ በማዕከላዊ መንግሥት ስር ሆኖ ሁሉም ጎሳ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ሥርዓትም ተዘረጋ። ይህ ደግሞ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በሀገሩ ላይ የአንድነት መሰረት እንዲገነባ አድርጓል። ለዚህም አድዋ ምስክር እንደሆነ ያስረዳሉ።
የቀድሞዋ ሸዋ 85 ሺ ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት፣ 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን የህዝብ ብዛት የነበራት ነች። ይሁንና ተከፋፍላ ሰሜን፣ ደቡብ እና ምዕራብ ተብላለች። ይህ ደግሞ አማራና ኦሮሞ እያለ የመከፋፈልን አንድምታ አመጣው። አንዱ የአንዱን ታሪክ እያጎደፈ እንዲመጣ አደረገው። አንድነቱን በመከፋፈል ገነባው። የኦሮሞና አማራ ታሪክ ግን የተጋባ የተዛመደ ለመሆኑ ታሪክ ይናገራል። ለዚህም ሰሜን ሸዋን ብቻ ማንሳት ይቻላል። ግለሰብ ከግለሰብ እንኳን በዘር ጉዳይ ቢጣላ በቤተሰብ እርቅ ነው የሚያልቀው። የቤተሰብ ጸብ ደግሞ በአገሪቱ ፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ ላይ እንዲሁም ማህበራዊ ህይወት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ መገንዘብ ቀላል ነው።
አማራና ኦሮሞ ከሌላው ክልል ይልቅ ብዙ የሚያስተሳስራቸው የቦታ ወሰን አላቸው የሚሉት መምህር ይጥና፤ የአንድ ሸዋ ማንነት ተነካ ማለት ኦሮሞ አማራ ሳይሆን ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ገባች ማለት ነው። ስለሆነም የታሪክ አሻራው የተገመደና የማይነጣጠለውን ሸዋ በአንድነት መገንባት ለነገ የማይባል መሆኑን መገንዘብ ተገቢ እንደሆነ ይናገራሉ።
በብሔር ፌዴራሊዝም ምስረታ ታሪክ ተዛብቷል፤ የቦታ ክፍፍልም ተደርጓል። ይህ ደግሞ ለአንድነት መሥራት እንዳይኖር በር ከፍቷል። ስለዚህም ይህንን ለመመለስ ባህልንና ታሪክን ማስተዋወቅ አስፈላጊ ነው። ወደ ኋላ መመለስም ይገባል። ለዚህ ደግሞ አዋቂና ታሪክ ተመራማሪዎች ኃላፊነት አለባቸው ይላሉ።
«ሸዋ አካባቢ ብቻ አይደለችም፤ ሸዋ የሚባል ህዝብና ቋንቋም ከመኖሩም በላይ የስበትም ማዕከልም ነበር። ማዕከሉ ደግሞ በእምነት፣ በባህል፣ በፖለቲካና ፈርጀ ብዙ በሆኑ ጉዳዮች የታጠረ ነበር። የሸዋ ተጽዕኖ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በአራቱም ማዕዘናት ይታያል። ሸዋ የሴቶችን እኩልነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከም ነው። ባንዲትን ማንሳት ይቻላል። የሸዋ ንግሥት ነበረች» ያሉት ደግሞ የታሪክ ተመራማሪው ዘመነወርቅ ዮሐንስ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ሸዋ ሀገረ መንግሥት ነበረች። ሦስት ዋና ዋና የመንግሥት አይነቶችን አስተናግዳለች። የክርስትና እምነትን የሚከተሉ መንግሥታትን፣ የእስልምና እንዲሁም ጣኦታትን ወይም አገር በቀል እምነቶችን የሚከቱ መንግሥታትና መሪዎች በአገሪቱ እንዲኖሩና እንዲያስተዳድሩ እድል ሰጥታለች። ነገር ግን ይህ ግዙፍ ታሪኩ በጥሩ ያልተያዘበትና ያልተመዘገበበት ዘመን በመምጣቱ፤ ሸዋ እንዲከፋፈል አድርጎታል። ምዕራብ ሸዋ (ኦሮሚያ)፣ ምስራቅ ሸዋ (ኦሮሚያ)፤ ሰሜን ምዕራብ ሸዋ (ኦሮሚያ)፣ ሰሜን ሸዋ አማራ እና አዲስ አበባ ተብሎ ተመደበ።
አልጋስክን የሚባል አውሮፓዊ በጻፈው ጽሁፍ ሸዋን ኢትዮጵያስ ፐርሽያ ይላታል። መልዕክቱም ለጀርመን አንድ መሆን ፐርሽያ ትልቅ ማዕከል እንደነበረች ሁሉ ለአገሪቱ አንድ መሆንም ሸዋ ማዕከል እንደነበረች ለመንገር ነው ካሉ በኋላ፤ የማዕከላዊ መንግሥቱ መቀመጫ ሆኖ የቀጠለ ከአዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫ እየሰፋ ያለ አስተዳደር ግዛት ሸዋ ነውና ይህንን አጋጣሚ መጠቀም ይበጃል ባይ ናቸው።
የንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣበት፣ ለምሳሌ ሞጆ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ዝዋይ፤ ወንጂ ፤ ደብረብርሃን ወዘተ ብዙ ብሔሮች የተከማቹበትና ከተሞች የሰፉበት ነውና ሁሉንም አማራጭ ማየት ይገባል። ይህ ደግሞ ባህልና ታሪክን ለትውልዱ በማሳወቅ የሚመጣ በመሆኑ የተዛባውን ታሪክ በማቃናት ትውልዱን ዘርና ጎሳ መራጭ ሳይሆን ለአንዲት ኢትዮጵያ የሚቆም ማድረግ ይገባልና በተለይ ባለሥልጣናቱ ይህንን ሊመለከቱት እንደሚገባ አበክረው ይናገራሉ።
ሸዋ በአዲስ ቅርጽ እንደገና ይገነባልና ወደ ታላቅነቱ በመምጣት ለኢትዮጵያ አንድነት መልሶ መገንባት ሚናውን እንዲወጣ ማድረግ ላይ ምሁራን የላቀ ሥራ ሊሠሩ ይገባል። ከዚያ ባሻገር የጎደፉ ታሪክና ባህሎችን ማረም ያስፈልጋል። የአማራና ኦሮሞ የኢኮኖሚ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ውህደት የበለጠ የሚገነባው በባህል ትስስር መሆኑን ተረድቶ መሥራትም ይገባል።
እንደ የታሪክ ተመራማሪው ማብራሪያ፤ የማንኛውም ህዝብ ማንነት መከበር ለአገር ገጽታ ግንባታ ፋይዳ መኖሩ ግልጽ ነው። በተለይ የሸዋ ማንነት መታደስ ደግሞ ይበልጥ ለአገር እድገት የማይተካ ሚና አለው። የሕዝቦች ውህደትን ያመጣል። ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ህሊና እንዲታሰብ ያደርጋል። ይህም ለኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ትስስርና እድገት የላቀ ሚናን ይጫወታል። ነገር ግን አምኖ የሚተገብረውን ይሻልና የሚመለከታቸው አካላት ልብ ይበሉት።
ሰሜን ሸዋ ደግሞ ለሸዋ መጠንከር ወሳኝ ቦታ ነችና ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ ለማሳየት በባህል ሲምፖዚየሙ ጠንካራ አቅሟን ማሳየት ይኖርባታል። የጠፋውን እና የጎደፈውን ታሪክ ማስተካከልና ማውጣት፤ የሸዋ ታሪክ፤ ባህል በኢትዮጵያዊነት ምስረታ ላይ የነበረውን ሚና ማሳየትም አለባት። ከዚያ ባሻገር የቀደሙትን በማሰብና እነርሱን በመምሰል የቀደመች ኢትዮጵያን ማሳየት የዛሬው ትውልድ ኃላፊነት ነውና የቀደመች ኢትዮጵያን፤ ሰላምና ፍቅር የበዛባት፤ መተሳሰብና አብሮነት ልምዷ የሆነችውን ኢትዮጵያን ማምጣት ለነገ የማይባል ነውና ታሪክና ባህልን በመንገር ልንመልሳት ይገባል መልዕክታቸው ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው