ለምለም መንግሥቱ
ባሌ ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክና ወፍ ዋሻ፤ ኢትዮጵያ ካሏት ከብዙዎቹ ፓርኮችና ጥብቅ ደኖች መካከል ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሥፍራዎች የየራሳቸው ታሪካዊ ዳራ ያላቸው ሲሆን፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውም የጎላ ነው።ባሌ ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክ በብዝኃ ህይወት የታደለ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ እንስሳትና ዕፅዋት ያቀፈ፣ ደመና፣ጭጋግና ዝናብ የማይለየው የቱሪስት መዳረሻ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ባሌ ተራራዎች ላይ ለመውጣት ብዛት ያላቸው ቱሪስቶች ከየሀገሩ ይመጣሉ።
ወፍ ዋሻም እንዲሁ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ አንኮበር ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ መስህቦች መካከል የሚጠቀስና በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙትን ብርቅዬ አዕዋፋት ጨምሮ የተለያዩ ሀገር በቀል ዕፅዋትን በውስጡ የያዘ ነው። ለጎብኝዎች ሀሴት የሚያደርጉና ለሀገርም የገንዘብ ምንጭ የሆኑትን እነዚህን መስህቦች ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ ፓርኮችና ጥብቅ ደኖች ላይ የእሳት አደጋ ደርሶ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተለባቸው ይታወሳል።በ2012 ዓ.ም በጀት አመት በባሌ ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክ፣በያዝነው በጀት አመት ደግሞ በቅርቡ ወፍ ዋሻን ጨምሮ በተለያዩ ጥብቅ ደኖችና ፓርኮች ላይ በደረሰው ቃጠሎ የውድመቱን መጠን ትክክለኛ መረጃ ማወቅ ባይቻልም ከፍተኛ መሆኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸው ይታወሳል።በደን ውስጥ የዱር እንስሳትን ጨምሮ የተለያዩ ብዝኃ ሕይወት ስለሚኖሩ ጥበቃው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያስገኛል። ደንን ለትውልድ የማሸጋገር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለውን ትውልድም የሚፈትን በመሆኑ በቸልታ የሚታለፍ ጉዳይ መሆን የለባትም።
ኢትዮጵያ የደን መቃጠል ሲያጋጥማት ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀ ተቋም አለመኖሩም ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም መዘንጋት የለበትም። በዚህ መልኩ ካልታየ ለሶስተኛ ዙር የተዘጋጀው አረንጓዴ አሻራ በአንድ በኩል ማልማት በሌላ በኩል የለማው ሲጠፋ ማየት እንዳይሆን አስፈላጊው ሁሉ ጥንቃቄ እንዲደረግ ህብረተሰቡን ማስተማር ያስፈልጋል።
ደን የተለያየ ተጽዕኖ ሊደርስበት እንደሚችል፤ ነገር ግን በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ ችግር ከሚያደርሱት መካከል ሰደድ እሳት ተጠቃሽ እንደሆነ የኢትዮጵያ የአካባቢ የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ጥር 12 ቀን 2012 ላይ ወቅታዊ በሚለው መልዕክቱ አሳውቋል። እንደመረጃው ከሆነ በዓለም ላይ በየአመቱ በሰደድ እሳት በብዙ ሺ ሄክታር የሚቆጠር ደን ይወድማል። በኢትዮጵያም ወደ አንድ መቶ ሺህ ሄክታር በሚደርስ ደን ላይ ጉዳት ይደርሳል።ለደን ቃጠሎ መንስኤው የተለያየ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን በሰው ሰራሽ የሚከሰተው ይበዛል።በተለይም ከጥር እስከ መጋቢት ያሉት ወራቶች ነፋሻማና ሞቃታማ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በደን ላይ የሚደርሰው ቃጠሎ ከመቸውም ጊዜ የሰፋ ነው።በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣውን ሙቀት ለመከላከል አዳጋች እየሆነ መምጣቱ ደግሞ ችግሩን የከፋ እያደረገው ይገኛል። በመሆኑም በእሳት እየተጎዳ ያለው ደን ለቤትና የዱር እንስሳት ሞትና መሰደድ ምክንያት እየሆነ ነው። ይህ ደግሞ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እየፈጠረ ነው።ቃጠሎው ተደራራቢና በስፋት መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል። በኢትዮጵያ በደን ላይ የሚደርሰው ቃጠሎ ከተፈጥሮአዊ ይልቅ በሰው ሰራሽ የሚከሰተው የበዛ ከሆነ በዚህ ረገድ ምን እየተሰራ ነው? እስከ መቼስ እንዲህ እየተባለ ይቀጥላል? እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎችና በቀጣይ አቅጣጫ ላይ በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፤ ደን ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጀነራል ከአቶ ካብታሙ ግርማ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ዳይሬክተር ጀነራሉ አቶ ካብታሙ ግርማ ከችግሩ በመነሳት እንዲህ ያስረዳሉ።በሀገሪቱ ደረቃማው ወቅት ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቷል። የበልግ ዝናብ በወቅቱ አልዘነበም።ይህ የደረቅ ወቅት ደግሞ ለእሳት መነሳት ምቹ ይሆናል። በቀላሉም ይዛመታል። በተጨማሪ ግን በአርሶአደሩ የተለመደና የሚዘወተር ማሳ የማቃጠል ባህል በመኖሩ በየጊዜው ለእርሻ ዝግጅት የብዕር መዝሪያ ማሳዎችን ያቃጥላል።ሌላው ደግሞ በዚሁ ወቅት ከብቶች መዥገር በሚባለው በሽታ ስለሚጠቁ መዥገሩ በቁጥቋጦዎች አማካኝነት ይከሰታል በሚል አርሶአደሩ ቁጥቋጦዎችን ያቃጥላል። እንዲሁም ንብ የሚያንበው በባህላዊ መንገድ በመሆኑ በማር ቆረጣ ወቅት ጭስ ይጠቀማል። እነዚህ አርሶአደሩ ተገቢ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸው ኩነቶች ጥንቃቄ የጎደላቸው ናቸው።
አርሶ አደሩ የሚመለከተው እሳት መጠቀሙን ብቻ እንጂ በአካባቢው ሊያሳድር ስለሚችለው ተጽዕኖ አያስተውሉም ። በተለይም በተለያየ ምክንያት የእርሻ ማሳና ደን በተቀራረበ ቦታዎች ላይ የሚገኙ መሆናቸው ደግሞ ችግሩን የከፋ አድርጎታል።እነዚህ በምክንያትነት ቢጠቀሱም ቦታ ለማስፋፋትና በተለያየ ፍላጎት ደኑን ለማቃጠል በሚፈልጉ አካላት ቃጠሎ ሊከሰት እንደሚችልም ይገመታል።
አቶ ካብታሙ፤ ችግሮቹንና መንስኤውን በጥናት ለይቶ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚገባና በኮሚሽኑ ተዘጋጅቶ ለውሳኔ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል የተሰጠውና በረቂቅ ደረጃ ላይ ያለው የመሬት ፖሊሲ ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ ለማስቀመጥ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ያምናሉ።ምንም እንኳን ተቋማቸው የማስተባበሩን ሚና የሚወጣ ቢሆንም ቅንጅታዊ ሥራ ወሳኝ ነው ይላሉ።
እርሳቸው እንዳሉት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራ ግንኙነት ያላቸው ባለድርሻ አካላት አሉ።እነዚህ አካላት ተቀናጅተውና ተናብበው በኃላፊነት የሚጠበቅባቸውን ሥራ ካልሰሩ በአንድ ተቋም ብቻ ችግሩ ይፈታል ተብሎ አይታሰብም። የጋራ ሥራ አለመኖሩም እየደረሰ ላለው ቃጠሎ እንደ አንድ መንስኤ ሊወሰድ ይችላል።ምክንያቱም በግብርናው ዘርፍ የሚሰራው ተቋም ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ ካልፈጠረ፣ ከብቱን ከበሽታ ለመታደግ፣የተሻለ ምርት ለማግኘት ሲል ማሳውን በማቃጠል የሚጠቀመውን ዘዴ በሌላ ሳይንሳዊ መንገድ ለመተካት ጥረት ካላደረገ ችግሩ ሊፈታ አይችልም። ስለዚህ ከአርሶ አደሩ ጋርም ተገቢውን ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ የደን ልማት ታሪክ በማልማትም ሆነ በጥበቃ ሥራው ላይ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ለሚለው ጥያቄም አቶ ካብታም በሰጡት ምላሽ፤መንግሥታት ቢለዋወጡም በተቆራረጠ መልኩም ቢሆን ደን ልማትና ጥበቃ ሥራው ወይም የተፈጥሮ ሀብቱን የመጠበቁ ሥራ አልተቋረጠም።ከደርግ ሥርአት ጊዜ ጀምሮ እንኳን ማህበረሰብን በማሳተፍ የሥራ ዘመቻ በሚል ለእርሻ በማይውሉና ውሃ የማይተኛባቸውን አካባቢዎች በባህርዛፍ ተክል የመሸፈን ሥራ ተሰርቷል።በአሁኑ ጊዜም የአማራና የኦሮሚያ የደን ኢንተርፕራይዝ ድርጅቶች የሚያስተዳድሩት በዚሁ ሥርዓት የተተከሉትን ነው።
በየሥርዓቱ የተፈጥሮ ሀብትን የማልማቱና የመጠበቁ ሥራ ቢከናወንም።ጥበቃን ብቻ መሠረት ያደረገ ሥራ ነው ሲሰራ የቆየው። ህዝብ ካለማው ደን ተጠቅሞ ኑሮውን እንዴት ማሻሻል አለበት የሚለው ትኩረት አልተሰጠውም። ምናልባትም ለውድመት ይዳርጉታል ተብሎ ከሚጠቀሰው ወይም ከሚገመተው መካከልም አንዱ ሊሆን ይችላል።በዚህ ረገድም ያለውን ክፍተት ማየት ያስፈልጋል።ደን የሚለማውም ሆነ የሚጠበቀው መልሶ ለሰው ልጅ ጥቅም እንዲሰጥ ነው።መጠበቅን ብቻ መሠረት ያደረገ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ለመጥፋት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች እየተወለዱ የሚሄዱበት አጋጣሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። በተለይም በሌሎች አማራጮች ኢኮኖሚ ማመንጨት የማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ባሉባቸው አካባቢዎች ህገወጥነት ተፈጥሮ ሀብቱ ላይ ሊባባስ ይችላል።ለአብነትም ከሰል በማክሰል ሸጠው ገቢ ለማግኘት ይሞክራሉ።ግዴለሽነቱ እየበረታ ይሄድና ውድመቱ ይጨምራል።እንዲህ ያሉ ነገሮችን መከላከል የሚቻለው ደግሞ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ በማመቻቸት ነው።ደኑንና ማህበረሰቡን አስታርቆ ተቻችሎና ተዋድዶ አብሮ እንዲኖር የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል።የሚሰራው ሥራ ግን ተከታታይነት ሊኖረውና ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መሆን ይኖርበታል።ይህ ሲባል ግን ማህበረሰቡ የደንን ጥቅም አያውቀውም ከሚል እሳቤ አይደለም።ለእርሻ ሥራው ለአካባቢው እንደሚጠቅም ያውቃል።ሌላው ቢቀር ማህበራዊ የሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት የሚመካከረውና የሚያስታርቀው በዛፍ ሥር ሆኖ ነው።የጋራ ሥራ ቢሰራ ግን የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ጥብቅ ደን ተብለው የሚጠሩ አካባቢዎች የትኞቹ አካባቢዎች እንደሚገኙና ስለሚደረግላቸው እንክብካቤም ለአቶ ካብታም አንስቼላቸው‹‹ ጥብቅ ደኖች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ። በተለይ ደግሞ በደቡብ ምዕራብ አካባቢ ባሌ፣ከፋ ይጠቀሳሉ።በዓለም ትምህርት፣የሳይንስ፣ባህል ድርጅት የተመዘገቡ ደኖች ደግሞ አሉ።እነዚህ ደኖች በተለየ ሁኔታ እንዲጠበቁ አሳታፊ የደን አስተዳደር ሥርአት አለ።የአካባቢው ማህበረሰብ በመሳተፍ የደን ጥበቃውን የማጠናከር ነው።ማህበረሰቡ ቀጥታ ከደኑ ባይጠቀሙም በተዘዋዋሪ እንጨት ነክ ያልሆኑ የደን ውጤቶችን ይጠቀማሉ።ለአብነትም የጫካ ቡናና ንብ ማነብ፤ቅመማ ቅመም ይጠቀሳሉ።ማህበረሰቡ በማህበር ተደራጅተው ተጠቃሚ በመሆን ደኑን ይጠብቃሉ።በዚህ መልኩ የተንቀሳቀሱ የማህበረሰብ ክፍሎች ገንዘብ የመቆጠብ ባህል ለማዳበር ችለዋል።ደኑንም ማቆየት ተችሏል።በዚህ ረገድ ከፋ፣ጎደሬ፣ሸካ፣ጥብቅ ደኖች ይጠቀሳሉ።ጣና አካባቢም በተመሳሳይ በጥብቅነት ተይዞ እየተሰራ ነው››በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።ይህ ተሞክሮ ከሃያ አመት በፊት በመሆኑና የነበረው የማህበረሰብ ቁጥርም አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለመቃኘት ስላለባቸው ይህን ማየት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።ማህበረሰቡን ማዕከል ያደረገ ሥራ እንዲጠናከር በኮሚሽኑ በኩልም አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።ለአብነትም ወደ ጫካ መጥረቢያ ይዘው የሚሄዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማስቀረት የኑሮ ማሻሻያ ሥራው አብሮ እንዲታሰብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ የተቀናጀ ሥራ ወሳኝ ነው የሚሉት አቶ ካብታም።ግብርና ህዝቡን ሊመግብ የሚችል ምርት አምርቶ ማቅረብ ሲችል ደን ለመቁረጥ የሚሄድ አይኖርም ይላሉ።በመሆኑም ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ ነው ይላሉ።
ሌላው ያነሱት ደግሞ በኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ካለመኖር ጋር ተያይዞ ጥብቅ ደንን በትክክል ለመግለጽ አስቸጋሪ መሆኑን ነው።እርሳቸው እንዳሉት እስካሁን ባለው የእርሻ፣የውሃ፣የመኖሪያና የደን ተብሎ በዚያ ልክ የተቃኘ የመሬት አጠቃቀም የለም ። በዚህ ምክንያት ትናንት ጥበቅ ደን ተብሎ የተያዘው ለሌላ ተግባር ውሎ ይገኛል።የተቀላቀለ አሰራር ነው ያለው።እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለመፍታት የመሬት ፖሊሲ ረቂቅ ተዘጋጅቷል።ፖሊሲው ጸድቆ ሥራ ላይ ሲውል አንዱ ተካይ ሌላው ደግሞ ነቃይ አይሆንም። የፖሊሲው ዋና ዓላማም መሬት ለታለመለት ዓላማ እንዲውልና በዕቅድ እንዲመራ ለማስቻል ነው።የእርሻ፣የውሃ፣የግጦሽ፣የደን፣እየተባለ ሁሉም ለታለመላቸው ዓላማ ከዋሉ ተመጋጋቢ ሆነው እንዲቀጥሉ ይረዳል።ፖሊሲው የቅንጅታዊ የአሰራር ሥልት ሆኖ ያግዛል።የፖሊሲ ረቂቁ በኮሚሽኑ ሥር ባለው ብሄራዊ የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር ዕቅድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የፖሊሲው ረቂቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ተልኳል።
እንደ አቶ ካብታም ማብራሪያ ክፍተት ቢኖርም ኮሚሽኑ የደን አዋጅ አለው።በአዋጁ የደን ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ የግል፣የመንግሥት፣የማህበርና የማህበረሰብ ተብሎ በአራት ተከፍሎ ተቀምጧል።በአራቱ የደን ባለቤትነት የተቃኘ የደን ይዞታ፤ባለቤት ሲኖረው በደን ሽፋን ላይም ሆነ ቀጣይነት ባለው አጠቃቀም ላይ የጎላ ሚና ይኖራል ተብሎ ይታሰባል።
‹‹ደን ከሰው ልጅ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው።የሰው ልጅ የሚኖርበት አካባቢ ንጹህ አየር እንዲኖረው የሚያደርግ በአጠቃላይ ከህይወት ተለይቶ የማይታይ ነው››የሚሉት አቶ ካብታሙ፤በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የሚሸፍን፣ ቁመቱ አምስት ሜትርና ከዚያ በላይ፣ የጥላ ሽፋኑም 20 በመቶና ከዚያ በላይ፣የግንዱ ስፋት ወይንም ውፍረት ደግሞ አንድ ነጥብ አምስት ሴንቲ ሜትርና ከዚያ በላይ ሆኖ ሲገኝ የደን መስፈርትን እንደሚያሟላ አስረድተዋል።ደን በሰው የሚተከል ቢሆንም በተፈጥሮም ህይወት ያለው ዕጽዋት ሊገኝ እንደሚችልም ገልጸዋል። በተመሳሳይ ደግሞ ከተፈጥሮ የሚገኘውን በማበዛትና በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 7/2013