አስናቀ ፀጋዬ
የኮሮና ቫይረስ በቻይናዋ ሁቤ ግዛት ሁዋን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተከሰተ በታኅሣሥ ወር መጨረሻ
2019 የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ደርሶታል::ቫይረሱ ቀስ በቀስ የስርጭት አድማሱን በማስፋት ወደተለያዩ ሀገራት በመዛመቱም ድርጅቱ በጥር 2020 አደገኛ የጤና ችግር ሲል አውጆታል::በቫይረሱ ምክንያት የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎም በመጋቢት 2020 ቫይረሱን ‹‹ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ›› ብሎታል::ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ቫይረሱ ዓለም አቀፍ ስጋት ሆኖ እስካሁን ድረስ ቀጥሏል::
ሀገራት ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በሳይንስ ሊቃውንቶቻቸው አማካኝነት ክትባት ለማግኘት ሲሯሯጡ የቆዩ ሲሆን መቶ በመቶ ቫይረሱን የሚከላከል ክትባት ባያገኙም ከ95 በመቶ በላይ የመከላከል አቅም ያላቸውን አዳዲስ ክትባቶችን በምርምር አግኝተዋል::ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ ክትባቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዜጎች እየተሰራጩ ይገኛሉ::
ኢትዮጵያም ኮቫክስ በተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት ጥምረት አማካኝነት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ የመጀመሪያ ዙር ክትባቶችን በቅርቡ አስገብታ ተጋላጭ የሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተከተቡ ይገኛሉ::ክትባቱ ውድ ከመሆኑ አኳያም ኢትዮጵያን ጨምሮ ገና በማደግ ላይ ያሉ በርካታ ሀገራት ክትባቱን በቀጥታ መግዛት የማይችሉ በመሆናቸው ኮቫክስ በተሰኘ ዓለም አቀፍ የክትባት ጥምረት ስር በመሆን ክትባቱን ለማግኘት ተገደዋል::
ክትባቱ ከፍትሃዊ ስርጭት አኳያም ገና ከጅምሩ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱበት ያለ ሲሆን በተለይ ደግሞ ሀብት ክትባቱን በፍጥነት በማግኘት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ መረጃዎች ፍንጭ እየሰጡ ይገኛሉ::የዓለም ሀብታም ሀገራት ከድሆች ሀገራት በ25 እጥፍ ፍጥነት ክትባቱን እያገኙ ስለመሆናቸውም ከሰሞኑ ብሉምበርግ ይዞት ብቅ ያለው መረጃ አመልክቷል::
ዘገባው 5 ከመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ሊከትብ የሚችል የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት የተዘጋጀ ቢሆንም የክትባቱ ስርጭት በታሰበው መልኩ እየሄደ እንዳልሆነና አብዛኛው ክትባትም ወደ ሀብታም ሀገራት እየሄደ እንደሚገኝ አስቀምጧል::
ባለፈው ሐሙስ ብቻ 40 ከመቶ የሚሆነውና ለዓለም ሕዝብ ይሰራጫል ተብሎ የታሰበው የኮቪድ-19 ክትባት 11 ከመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ሊወክሉ ለሚችሉና 27 በሚሆኑ ሀብታም ሀገራት ውስጥ ላሉ ሰዎች መሰራጨቱንም ዘገባው ጠቁሟል::
በብሉምበርግ ክትባት መከታተያ በተሰበሰበው የመረጃ ትንታኔ ውጤት እንደሚሳየው ደግሞ 11 ከመቶ ያህሉን የዓለም የሀብት መጠን የሚወክሉ ሀገራት እስካሁን ከተሰራጨው የኮቪድ-19 ክትባት ውስጥ 1 ነጥብ 6 ከመቶ ያህሉን ማግኘታቸውን አመላክቷል::በሌላ አገላለፅ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ሀገሮች በጣም ዝቅተኛ ከሆኑት ጋር ሲነፃፀሩ በ25 እጥፍ ፍጥነት ክትባት ያገኛሉ እንደማለት ነው ሲል ዘገባው አስቀምጧል::
የብሉምበርግ የኮቪድ -19 ክትባቶች የመረጃ ቋትበ154 ሀገሮች ውስጥ የተሰራጩ ከ726 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች ላይ ክትትል ያደረገ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የክትባቱን ተደራሽነት ለመገምገም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሀገራትን በሀብት፣ በሕዝብ ብዛት እና በክትባቶች ተደራሽነት የሚለካ አዲስ የመለኪያ መሣሪያ መጠቀሙ በዘገባው ተገልጿል::
ለአብነትም አሜሪካን 24 ከመቶ የዓለም ክትባት ቢኖራትም 4 ነጥብ 3 ከመቶ ያህል ለሚሆነው ሕዝቧ የሚዳረስ መሆኑንና ከዚህ በተቃራኒ ፓኪስታን ከ2 ነጥብ 7 ከመቶ የዓለም ክትባት ሽፋን ውስጥ 0 ነጥብ 1 ብቻ ክትባት እንዳላት ዘገባው በንፅፅር አስቀምጧል::ይህ ሁኔታ በተለይ ሀብታም ሀገራት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ክትባቶችን ቅድመ ግዥ ለመፈፀም የሚያደርጉትን እሽቅድድም ተከትሎ ሕዝባቸውን ብዙ ጊዜ በክትባት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችላቸው አቅም ላይ ስለመድረሳቸውም ተጠቁሟል::
አሜሪካን በቀጣዮቹ ሦስት ወራቶች 75 ከመቶ ያህል ሕዝቧን ለመከተብ መንገድ ውስጥ የገባች መሆኑም በመረጃው የተገለፀ ሲሆን፣ ከዚህ በተቀራኒ ግን የዓለም ግማሽ ያህሉ ሀገራት አሁንም ድረስ 1 ከመቶ ለሚሆነው ሕዝባቸው በክትባት መድረስ እንዳልቻሉ ተነግሯል::ይህ የልዩነት ስሌት በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ደሃ የሆኑትንና ሕዝባዊ የክትባት መረጃ የሌላቸውን ከአርባ በላይ የሚሆኑ ሀገራት እንደማያካትትም ተጠቅሷል::በዚህ ውስጥ ያልተካተቱ ሀገራት ስምንት ከመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ እንደሚወክሉም ታውቋል::
በአሜሪካ የፌዴራል መንግሥት ክትባቶች የት እንደሚላኩ እንደሚወስንና እስካሁን ድረስም እያንዳንዱ የአሜሪካ ግዛቶች እንደያዙት የሕዝብ ብዛት የክትባት መጠን እንደተደለደለላቸው በዘገባው ተጠቅሷል::በክትባት ተደራሽነት ረገድ ከጎረቤት ጎረቤት ልዩነቶች ቢኖሩም እያንዳንዱ ግዛቶች ባሏቸው የነዋሪዎች ብዛት ልክ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የክትባት ስርጭት እንደሚደርሳቸው ተጠቁሟል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሃዊ የክትባት ስርጭት ለማድረግ የሚያስችል መንገድ እንደሌለ ብዙዎች የሚስማሙ መሆኑም በዘገባው ተገልፆ፤ ሁሉም ክትባቶች በሕዝብ ብዛት ላይ ተመስርተው የሚሰራጩ ቢሆን ኖሮ አሜሪካ ብቻዋን በፍትሃዊነት ስድስት እጥፍ የሚጠጋ ክትባት እንደሚደርሳት ተጠቁሟል::በተመሳሳይ እንግሊዝ ከሕዝቧ ቁጥር ጋር በሚመጣጠን መልኩ ሰባት እጥፍ ክትባት ልታገኝ እንደምትችል ተገልጿል::
ቻይና 18 ከመቶ ለሚሆነው የዓለም ሕዝብ ይደርሳል ተብሎ ከታሰበው ክትባት ውስጥ 20 ከመቶ ያህሉን ለሕዝቧ ያዳረሰች ሲሆን ራሷ ባመረተቻቸው ክትባቶችም ሕዝቦቿን እየከተበች ትገኛለች::
በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም ዝቅተኛው ሀብት በሚገኘባት አፍሪካ ትንሽ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ብቻ መከተባቸውንና ከ54 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ሦስቱ ብቻ 1 ከመቶ የሚሆነውን ሕዝባቸውን መከተብ መቻላቸው በዘገባው ተጠቅሷል::ይህ እንዳለ ሆኖ ታዲያ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሀጋራት ደግሞ ከነአካቴው ክትባቱን እንዳላገኙም ተነግሯል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም