በዳንኤል ዘነበ
ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የመማር ማስተማር ሂደት፣ የትምህርት ጥራትን የተመለከተ አስደንጋጭ መረጃን አውጥቷል። ኤጀንሲው ያወጣው መረጃ፤ «በሀገሪቱ የአብዛኛዎቹ ትምህርት ተቋሞች የመማር ማስተማር ሂደት የጥራት መጓደል ያለበት የታየበት እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሆኗል። በአንዳንድ ተቋማት ከ10ኛ ክፍል ላቋረጡ ተማሪዎች ዲግሪ ይሰጣሉ፤ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ሰዎች እንዲሁ ወረቀት እየወሰዱ ይገኛሉ» የሚል ነበር። በዚህ መረጃ ብዙዎች ልባቸው ቀጥ ብሏል። የትምህርት ባለሙያዎች ‹ብለን ነበር› ሲሉ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዛሬ ላይ ለደረሱበት አንገት የሚያስደፋ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ችግሩን ሲጠቁሙ እንደነበር ይታወሳል።
በሀገሪቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥራቸው ቢጨምሩም፤ ጥራትን መሰረት አድርገው እንዳይጓዙ የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲው የፈጠረው ክፍተት እንደሆነ የትምህርት ባለሙያዎች ይናገራሉ። በ1987 ዓ.ም የወጣው አዲሱ የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ መውጣቱ መልካም ቢሆንም፤ በወቅቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ባለሞያዎች ለይስሙላ አስተያየት እንዲሰጡበት መደረጉ ስህተት እንደሆነ በማስታወስ ይሞግታሉ።
በሀገሪቱ ቁጥራቸው እንደ አሸን የፈሉት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች፤ ጥራትን ጉዳያቸው አድርገው እንዳይሰሩ በር ከፍቷል ሲሉ ትችቶችን ያቀርባሉ። በአብዛኛዎቹ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚታየው እንዝህላልነት እየጨመረ በመሄዱ ለተማሪ እውቀትን ለመሸጥ መቋቋማቸውን እስከመዘንጋት አድርሷቸዋል። ከእነዚህ ነጥቦች በመነሳት ባለፉት 20 ዓመታት መንግስት የትምህርት ተደራሽነቱ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መጓዙ፤ በተለይ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ላይ በሥፋት ለሚስተዋለው የትምህርት ጥራት ችግር መሆኑን ለመቀበል ያስደፍራል። ነገር ግን በአብዛኛዎቹ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች በሚተገብሩት እኩይ ተግባር የተነሳ፤ በጥራት የማይደራደሩ፣ የተደራጁበት እና በትምህርት ጥራቱም ሊመሰገኑ የሚገባቸው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ልፋት ገደል እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
ለመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርዐያ እስከመሆን የሚደርሱትን እነኚህ ተቋማት ስም አብሮ የሚያጠለሽ በመሆኑ የተቋማቱን ውጤት፣ ልፋት እንዲሁም ሀብትን ለብክነት የሚዳርግ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በተጨባጭም አንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ሲያነሱት ለመታዘብ እንደተቻለው የችግሩ አይን ማውጣት በእነርሱ ላይ ጭምር አሉታዊ ተጽእኖ አምጥቶብናል የሚሉ ቅሬታዎች እያቀረቡ ይገኛሉ።
መንግስት የሚጠበቅበትን ሀላፊነት አለመወጣቱ እኛን አመድ አፋሽ አድርጎናል። በመሆኑም ጥራቱን የጠበቀ የመማር ማስተማር ሥርዐትን የሚከተሉና ለመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርዐያ መሆን የሚችሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥረት ላይ አሉታዊ ገጽታ አላብሷል የሚሉ ቅሬታዎች መነሳታቸው አልቀረም። የሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ዶክተር ተረፈ ፈየራ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የመማር ማስተማር ሂደት፣ የትምህርት ጥራትን የተመለከተውን መረጃ መሠረት አድርገው ይናገራሉ።
በዚህ ደረጃ ህግን በመጣሥ አለአግባብ የሚሰሩ ተቋማት በግል ዘርፍ ላይ መንሰራፋታቸው በሀገር፣ በትውልዱ ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖው ከፍተኛ ሲሆን፤ ከዚሁ ትይዩ በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ምዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ኢንቨስት እያደረጉ ባሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ኪሳራ የሚያስከትል መሆኑ አያይዘው ያነሳሉ። ስለዚህ «ከተልባ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ» የተባለው ተረት እንዳይደርስባቸው በተለይ መንግስት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ያመላክታሉ። በተለይ ደግሞ ህብረተሰቡ በግል ዘርፍ ላይ እምነት እንዳያሳደር ከማድረግ አኳያ ያለው ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ከሰዋዊ ባህሪ ረገድ ስንነሳ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከተሰራው በጎ ተግባር ይልቅ፤ የተበላሸውን ነገር ጎልቶ የሚታይ እንደሆነ ያብራራሉ።
“ብዙ መልካም ከሰሩት ይልቅ ያልሰሩት ሰዎች ጎልቶ የመታየት፣ መጥፎ ክስተቶች ከፍ ብለው የመሰማት፣ የመታየት ዝንባሌዎች መኖራቸውን እንታዘባለን» ሲሉ ያመላከቱት ዶክተር ተረፈ፤ ‹‹በመገናኛ ብዙሀን በኩል ካለው ልምድ በመነሳት ሥንመለከተው፤ በተለያዩ መስኮች የተሰሩ በጎ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ከመስራት ይልቅ፤ትንሿን ክፍተት አጉልቶና በጎውን ሸፍኖ የመመዝገብ ልምድ ነው በሥፋት ያለው። ይህ አይነቱን ልምድ በደረጃ ሰጪ አካላት ጭምር የተቋማትን ውጤት ሲገልጹ ተመሳሳይ ተግባር ነው የሚስተዋለው›› ይላሉ።
እንደ ዶክተር ተፈራ ገለጻ፤ ደረጃ ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል ስኬታማ የሆኑት ሥራቸውን ጠንቀቅ አድርገው የሚሰሩ አሉ በሚል የሚያልፉት ሲሆን፤ በአፈጻፀማቸው ደካማ የሆኑት ተቋማት ላይ ግን ሰፊውን ሽፋን፣ ልዩ ትኩረት በመስጠት የትኩረታቸውን ዋነኛ ማጠንጠኛ አድርገው ያቀርባሉ። ይህም ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተመለከተ እየሆነ የሚገኘው መሆን ካለበት ይቃረናል። በግል ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑት ተቋማት፤ የተቋማቱ ስኬት መነሻ አድርጎ እውቅና በመስጠት ውድድር ከመፍጠር ይልቅ፤መጥፎ መንገድን ሥለ መረጡ ተቋማት አብዝቶ በማውራት የሚሰራውን እንዳይሰራ የሚያደርግ አካሄድ ነው ያለው። ይህም በግል ዘርፍ ላይም በሀገር ላይም ቀላል የማይባል ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች መካከል ጥሩ እየሰሩ የሚገኙትን ተቋማት ጠቅሶ ተግባራቸውን በዝርዝር መናገር እንደ ማስታወቂያ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ከመኖሩ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ያመላከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቹ ውስጥ ህግን ተከትለው እየሰሩ የሚገኙትን እና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡትን ተቋማት ተግባር መጥቀስ የማይፈለግ መሆኑን ያመላክታሉ። ተቋማቱን መጥቀሱ ማስታወቂያ ይሆናል የሚል ጎታች እሳቤ ምን ያህል ክፍተት እንደፈጠረ አመላካች ይሆናል። ስለዚህ በመልካም ሁኔታ የሚሰሩ የግል ተቋማትን አጉልቶ የማየት፤ተቋማቱን ነቅሶ በማውጣት ለሰሩት ሥራ ተገቢውን እውቅና በመስጠት የማበረታታት ልምድ መዳበር ይኖርበታል።ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት መቻሉ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የተንሰራፋውን የትምህርት ጥራት ችግር እና ህግን ተከትሎ ያለመስራት ዝንባሌን ለማረቅ መንደርደሪያ ይሆናል» ሲሉ ዶክተር ተረፈ ያስገነዝባሉ።
በዘርፉ ጥፋት የሰሩ ተቋማት ተግባር መታየት የለበትም የሚል ሀሳብ የለኝም። ትምህርት ተቋማቱ ትውልድ የሚታነጽባቸውና የሰው ልጅ አንዴ ከመንገድ ከወጣ መመለሱ አደገኛ ሥለሚሆን ልዩ ትኩረት ተደርጎ መወገዝ ያለበት መወገዝ አለበት፤እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባውም በተመሳሳይ። ነገር ግን መወገን ያለበትን ተቋም አውግዞ፤መበረታታት የሚገባውን ተቋም እውቅና ሰጥቶ እንዲበረታታ ካልተደረገ የሚገኘው ውጤት ሚዛን የሳተ እንደሚሆን ይሞግታሉ። በመልካም ሁኔታ የሚሰሩትን ተቋማት ቦታ በመስጠት በማበረታታት በልዩነት መታየት መቻሉ፤የጥፋት መሥመር ይዘው እየተጓዙ ባሉት ላይ አዎንታዊ ስሜትን መፍጠር ይቻላል። ተቋማቱ ወደ ትክክለኛው የአሰራር መንገድ እንዲገቡ የራሱ ሚና ይኖረዋል። ስለዚህ የቁጥጥር ብቻ ሳይሆን ፤የማበረታታት አስተሳሰብ መምጣት እንደሚገባ መፍትሄ ያሉትን ሀሳብ ያቀርባሉ።
በአጠቃላይ በሀገራችን በአብዛኛዎቹ የግል ከፍተኛ ተቋማቶች ላይ ትርፍን እንጂ እውቀትን መሰረት አድርጎ የመጓዝ ዝንባሌዎች ጎልተው እንዲታዩ ያደረገ መሆኑን አምኖ መቀበል ያስችላል። በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ላይ የሚታየውን እንዝላልነት ለማረቅ ከተፈለገ፤ የተቋማት አካሄድን መፈተሽ የሚገባ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። ከዚሁ ትይዩ ግን የቁጥጥር ብቻ ሳይሆን፤ የማበረታታት አስተሳሰብ መኖር አለበት፡፡ ይህም ትርፍን እንጂ እውቀትን መሰረት አድርጎ የመጓዙን ዝንባሌ ለማረቅ አንዱ መንገድ ይሆናል። ይህም ‹‹ከተልባ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ…” የሚሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከቅሬታ ያወጣል ባይ ነን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/ 2013 ዓ.ም