መላኩ ኤሮሴ
ጮቄ ተራራ በምስራቅ ጎጃም፤ ከደብረ ማርቆስ ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። የስናን ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው ረቡዕ ገበያ ደግሞ ልዩነቷ 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ነው፡፡ ተራራው አብዛኛውን የምስራቅ ጎጃም ወረዳዎችን እና ከፊል የምዕራብ ጎጃም ወረዳዎችን ያካልላል፡፡ ከተራራው ስር 273 ምንጮች እና 53 ወንዞች ይፈልቃሉ፡፡ እነዚህ ወንዞች በሙሉ ወደ ጥቁር አባይ የሚፈሱ ሲሆን ከአባይ ወንዝ 9 ነጥብ 5 በመቶውን ይሸፍናሉ፡፡
25ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የጮቄ ተራራ ከፍተኛ ቦታ ከባህር ጠለል በላይ 4100 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ ተራራው ዘጠኝ ወረዳዎችን የሚያዋስን ሲሆን በወረዳዎቹ የሚገኙ 43 ቀበሌዎች ይጋሩታል፡፡ የበርካታ የእንስሳት እና እጽዋት ዝርያዎች መኖሪያ የሆነው ተራራው በምስራቅ ጎጃም ውስጥ ከሚገኙ ከፍታማ ቦታዎች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ከፍታማ ቦታዎች ውስጥ አራተኛ ስፍራ ይይዛል፡፡ በአማካይ ከአንድ ዲግሪ ሴንትግሬድ በታች ቀዝቃዛ የሆነው ጮቄ፤ ቃላት ከሚገልጹት በላይ ውርጫማ ነው፡፡
የአካባቢ ነዋሪዎች ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ተራራው በጫካ የተሸፈነ፣ በዱር አራዊቶች እና በተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎች የተሞላ፣ ረግረጋማ እና ውሃ አዘል እንደነበር ይናገራሉ፡፡‹‹ ከአስርት ዓመታት በፊት በተራራው ስር በየቦታው ምንጭ ይፈልቅ ነበር፡፡ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን መመልከት የተለመደ የዘወትር ተግባር ነበር፡፡ ‹‹ጮቄ›› የሚለው ስያሜ የተሰጠውም ከዚሁ ከረግረጋማነቱ ጋር ተያይዞ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ይህ ብዙ የተነገረለት ባለውለተኛ ደን ግን የነበረ ይዘቱንና ውበቱን ጠብቆ አልዘለቀም። በተለይ ከአስርት ዓመታት ወዲህ ተራራ አደጋ ተጋርጦበት ቆይቷል፡፡ በሰው ሰራሽ ችግሮች እና በመንግስት ትኩረት መነፈግ ምክንያት አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ከተራራው ስር የሚፈልቁ ወንዞች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ፣ ምንጮች እየደረቁ፣ አካባቢው እየተሸረሸረ፣ ብዝሃ ህይወቱ እየተመናመነ መጥቷል፡፡ በተራራው አናት ላይ ለወራት ተከምሮ ይቆይ የነበረው የበረዶ ክምር፤ ዛሬ ግን በረዶ የሚታየው በክረምት ወራት ለዚያውም ከቀናት በላይ በተራራው አናት ላይ አይቆይም፡፡ በአጠቃላይ የተራራው ገጽታ ወደ ታሪክነት እየተቀየረ ያለ ይመስላል፡፡
ጮቄ ተራራ እንዲያገግም ለማድረግ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ አካላት ጥረት እያደረጉ ቆይተዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኘው ደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ ተራራው ከዚህ ቀደም ከደረሰበት መራቆት እንዲያገግም እና የበለጠ እንዳይራቆት ለመከላከል ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ስራዎችን መስራት ጀምሯል፡፡ በዩንቨርሲቲው ስር ዳይሬክቶሬት አቋቁሞ ተራራውን የማልማት ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ የጮቄ ተፋሰስ ምርምርና ልማት ዳይሬክተር ዶክተር አረጋ ሹመቴ የተራራውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች በማብራራት፤ ተራራው የበለጠ እንዳይራቆት እና እንዲያገግም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ተራራው የበርካታ ወንዞች፣ ምንጮች፣ እጽዋት እና እንስሳት መገኛ ነው፡፡ ከተራራው ስር የሚፈልቁ ምንጮች እና ወንዞች ሁሉም በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አባይ ወንዝ የሚፈሱበት መሆኑ ተራራውን ለማልማት የሚደረገው ጥረት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደህንነት እና ዘላቂነትን ለማስጠበቅ ከሚደረገው ጥረት ጋር ቁርኝት ያለው መሆኑን ያነሳሉ፡፡
ከተራራው የሚፈልቁ ወንዞች የጥቁር አባይን 9 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው ውሃ ይሸፍናል፡፡ ምንም እንኳ የአባይ ወንዝ በርካታ ገባር ወንዞች ቢኖሩትም ከጮቄ ተፋሰስ የሚፈልቁ ወንዞች የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ለሆነው አባይ ትልቅ ድርሻ ከሚያበረክቱት ቀዳሚው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን ተራራውን የምስራቅ አፍሪካ ታላቁ የውሃ ማማ በማለት ይጠሩታል፡፡
የጮቄ ተራራ ፋይዳ ለአባይ ወንዝ ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር በብዝሃ ህይወትም የታደለ ነው። በኢትዮጵያ የበርካታ ብዝሃ ህይወት መገኛ ተብሎ ከሚጠቀሱ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ የብርቅዬ አእዋፋት ዝርያዎች፣ የአጥቢ የእንስሳትና የእጽዋት መኖሪያ ነው፣ ይህም ተራራውን ልዩ እንደሚያደርገው ዶክተር አረጋ ይናገራሉ። በተለይም በቱሪዝም፣ በደን ልማት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በብዝሃ ህይወት ዙሪያ ጥናት ማካሄድ ለሚፈልጉ ተመራማሪዎች ትልቅ አቅም የመሆን ሰፊ እድል እንዳለውም ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ፡፡
ከተራራው ስር የሚፈልቁ ወንዞች ለአካባቢው አርሶ አደሮች የመስኖ ስራ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን የሚያነሱት ዶክተር አረጋ፤ እነዚህን ወንዞችን በመጠቀም አርሶ አደሮች የተለያዩ ሰብሎችን እንደሚያለሙ ያነሳሉ፡፡ የወንዞቹ ፋይዳ ግን በአካባቢው ብቻ ተወስኖ የማይቀር ነው፡፡ ከአካባቢው የሚፈልቁ ወንዞች አህጉርና ዓለምን የሚያስተሳስረው የአባይ ወንዝ ገባር መሆናቸውን በማንሳት የተራራው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
ተራራው ሀይማኖታዊና ባህላዊ ፋይዳ አለው። ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች ሀይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች የሚገኙበት እንደመሆኑ ትልቅ የመዝናኛና የመስሂብ ቦታ ሊሆንም የሚችል ነው፡፡ በዚህም ለሀገሪቱ ገቢ የማስገኘት አቅም አለው፡፡
ዶክተር አረጋ እንደሚሉት፤ ከአስርት ዓመታት በፊት በነበሩ ጊዜያት የጮቄ ተራራ በክረምት ወቅት ለወራት በበረዶ የተሸፈነ ነበር ፡፡ አሁን ግን በረዶ ከአንድ ሳምንት በላይ አይቆይም፡፡ እንስሳትና የእጽዋት ብዝሃ ህይወት በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኗል፡፡ በአጠቃላይ ተራራ ለአደጋ ተጋልጦ ግርማ ሞገሱን አጥቷል፡፡
ተራራው አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደረጉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች መኖራቸውን የሚያነሱት ዶክተር አረጋ ፤ በተለይም ሰው ተራራውን ለእርሻ፤ ደኑን ደግሞ ለማገዶ መጠቀሙ ተራራው አሁን ባለበት ሁኔታ ላይ እንዲራቆት አድርጓል፡፡
በተለይም ካለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ወዲህ አካባቢው በጣም ተጎድቷል፡፡ በተራራው ላይ የሚደርሰው ጉዳት በተለይም ከ1989 የመሬት ሽግሽግ በኋላ የባሰ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ወዲህ በአካባቢው በሚስተዋለው የመሬት ጥበት ምክንያት ሰዎች በብዛት ተራራውን የማረስ እና በተራራው ላይ ቤት መስራት ቀጥሏል፡፡
ዶክተር አረጋ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ከ250 ሺህ በላይ ህዝብ በተራራው ላይ ተጠልሎ ይኖራል፡፡ እነዚህ ህዝቦች በተራራው ላይ ሰብል ያመርታሉ፡፡ በግና የጋማ ከብትም ያረባሉ፡፡ ተራራው እንዲራቆት ዋነኛው ምክንያት የሆነውም ይሄው ነው፡፡
ከጮቄ ተራራ የሚመነጩና ወደ አባይ የሚፈሱ አብዛኞቹ ወንዞች ከ300 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ወደ ታች የሚፈሱ መሆናቸው በአንድ በኩል አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ እድል ቢኖራቸውም በሌላ በኩል የራሱ አደጋ አለው፡፡ ከጮቄ ተራራ የሚፈሱ ወንዞች ከከፍታ ወደ ዝቅተኛ ቦታ የሚፈሱ በመሆናቸው ለም አፈር በውሃው ለመታጠብና ለመሸርሸር ምክንያት ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተራራው ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ ቢሆንም፤ መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው የሚሉት ዶክተር አረጋ በመሆኑም ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመሆን ተራራውን ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ እየሰራ ነው፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ ተራራው እንዲያገግም እና ደለል ይዞ እንዳይወርድ ለማድረግ ጥልቅ ጥናት ካደረገ በኋላ ተራራውን በስድስት ስነምህዳር ከፍሎታል። በእያንዳንዱ ስነምህዳር ላይ ጥናቶችን እያካሄደ ነው። በእያንዳንዱ ስነ ምህዳር ላይ ምን መሰራት እንዳለበት ለይቷል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ህይወት በከፍተኛ ደረጃ በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ለእንስሳት የሚሆን የሳር ችግር በመኖሩ ምክንያት አርሶ አደሮች እንስሳትን በተራራው ላይ ስለሚለቁ ለአካባቢ መራቆት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ በአካባቢው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የመሬት ጥበት ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ተራራው ላይ ያለውን ጫካ በመመንጠር የቤት ግንባታ እያከናወኑ ነው ፡፡ በዚህም ምክንያት እንስሳት እና እጽዋት ተመናምነዋል፡፡
በመሆኑም ተራራውን ለማልማት ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን በተራራው አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ህይወት ለመቀየር የሚያስችል ስራ መስራት ተገቢ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በተራራው ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ቁርኝት መቀነስ የሚቻለው ህይወታቸውን የሚለውጡ ስራዎችን መስራት ሲቻል ነው፡፡ በዋናነት የሰብል ምርታማነት የሚጨምርበት፣ የእንስሳት አያያዝ፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በማህበረሰብ አገልግሎትና ምርምር ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት፣ በአካባቢው የሚስታዋሉ ችግሮችን ማዕከል ያደረገ ስልጠናና ድጋፍ ለመስጠት፣ በተራራው አካባቢ የሚኖር ማህበረሰብ ህይወትን የሚለውጡ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ፣ የአካባቢውን ብዝሃ ህይወት ለመጠበቅና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እና ከጆን ሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ ጋር እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ በአካባቢው በሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ላይ የተመሰረተ ኑሮውን ለማላቀቅ ነው፡፡
ተራራውን ለማልማትና ለመጠበቅ 45 ከፍተኛ የመንግስት ዩንቨርሲቲዎች የተፈራረሙ ሲሆን ስምምነቱ ተራራው የበለጠ እንዳይራቆት እና እንዲያገግም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ 45 የመንግስት ዩንቨርሲቲዎች የጮቄ ስምምነት በመፈራረም ወደ ስራ ለመግባት መወሰናቸው ሀብታቸውን በጋራ እንዲያለሙ ከማስቻሉም ባሻገር አካባቢው ለህዳሴው ግድብና ለኢትዮጵያ ምን ያህል ወሳኝ ቦታ እንደሆነ ግንዛቤን እንደሚፈጥር ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ይህም ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች ተቋማት ጋር አካባቢውን ለማልማት በትብብር እንዲሰሩ እድልን ይፈጥራል፤ ወደፊትም ወቅቱን የጠበቀ የምሁራን ምክክር እንዲደረግና ስራዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር እንደሚያስችል ዶክተር አረጋ ጠቁመዋል፡፡
ተራራው በአግባቡ ሲለማ ለአካባቢው እና ለዓለም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና የስነ ምህዳር ጠቃሜታዎች እንደሚኖሩት ዳይሬክተሩ ጠቅሰው የተራራው መልማት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለአባይ ወንዝና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በቀጥታ ለአባይ ወንዝ የውሃ ምንጭ በመሆን ትልቅ አስተዋጽ ያበረክታል። ምክንያቱም ከጥቁር አብይ 9 ነጥብ 5 በመቶ ከጮቄ ተራራ የሚፈስ ነው፡፡ ይህንን ተራራ ማልማት የወንዙን 9 ነጥብ 5 በመቶ የውሃ ድርሻ ዘላቂነት ያረጋግጣል ይላሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ከተራራው የሚፈልቁ ወንዞች ለም አፈር እንዳይወስዱ የሚከላከል በመሆኑ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2013