
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ አበባ፡- የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰ በመሆኑ ቀደም ሲል ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ ። ከለውጡ በኋላ ግድቡ ግንባታ የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱ አስታወቁ።
አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ከበደ ነሜ እንደገለጹት፤ የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ከተወሰዱት መልካም እርምጃዎች አንዱ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የተከናወነው ሥራ ነው፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የግንባታ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ሕዝቡ ያለምንም ልዩነት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ያመለከቱት አቶ ከበደ ፣ ይሁን እንጂ ግድቡ ይጠናቀቃል በተባለበት ጊዜ ባለመጠናቀቁ የሕዝቡ ስሜት ወድቆ እንደነበር አመልክተዋል ። ድጋፉም ተቀዛቅዞ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
የለውጡ መንግስት የግድቡን ግንባታ ለማስቀጠል በወሰዳቸው እርምጃዎችና እየታዩ ባሉ መሻሻሎች የሕዝቡ ተስፋ ተመልሶ ማለምለሙን ጠቁመው፣ እሳቸውም ስለግድቡ ያላቸው ስሜትና መንፈስ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላለም በችግርና በጨለማ መኖር የለበትም ያሉት አቶ ከበደ፤ ምንም እንኳን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተጽዕኖዎች ቢኖሩም አስፈላጊውን ዋጋ በመክፈል የግድቡ ግንባታ እንዲጠናቀቅ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም እና የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል የግድቡ ግንባታ ለፍጻሜ እንዲበቃ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አመልክተው፤ እርሳቸውም ቦንድ በመግዛትና አጭር መልዕክት በመላክ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
ለግድቡ ከስድስት ጊዜ በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የሚገልጹት ወይዘሮ እቴነሽ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ይህ ፕሮጀክት ለመላው ኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም ስላለው ይጠናቀቃል በተባለበት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ቅሬታ ፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ በኋላ በግድቡ ግንባታ መሻሻል በመታየቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ግድቡ ግድብ ብቻ ሳይሆን የአገር ህልውና ጉዳይ፣ ቅርስም ስለሆነ ሁሉም ዜጋ ግድቡን ከፍጻሜ ለማድረስ መረባረብና ቆራጥ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በሚስተዋለው የኃይል እጥረት በተለይ ሴቶች ብዙ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ እቴነሽ፤ የግድቡ መጠናቀቅ ለሴቶች ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ ግድቡ በታለመለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡፡
እንደ ወይዘሮ እቴነሽ ገለጻ፤ ሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት ሊደረግ እቅድ በተያዘበት በዚህ ወቅት ከተለያየ አቅጣጫ ጫና ለማሳደር የሚደረጉ ጥረቶች እየተስተዋሉ ነው። መንግሥት የያዘውን ጠንከር ያለ አቋም መቀጠል፤ ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆን አለበት፡፡
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ኢሳያስ ከበደ በበኩላቸው፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በርካታ የአገሪቱን ችግር ከመሰረቱ የሚቀርፍ በመሆኑ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ይህም በመሆኑ የግንባታ መጓተት በመታየቱ ሕዝቡን ቁጭት ውስጥ ከቶት ቆይቷል ብለዋል፡፡
በቅርብ ዓመታት በተወሰዱ እርምጃዎች የተሻለ አፈጻጸም በመኖሩ የግንባታው አፈጻጸም ወደ 80 በመቶ እየተጠጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ቁጭት ውስጥ ገብቶ የነበረውን ሕዝብ ተስፋ እንዲሰንቅ፤የእኔነት ስሜቱም ከፍ እንዲል ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
አሁን ላይ ግንባታው መጨረሻው ምዕራፍ ላይ ስለደረሰ ሕዝቡ በ8100 ላይም ይሁን በሌሎችም አማራጮች ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተው፤ በተለይ የዚህ ፕሮጀክት ዋና ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ከምን ጊዜውም በበለጠ ትኩረት ሰጥተው የሚጠይቀውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም