
ሙሳ ሙሀመድ
አዲሰ አበባ፡- በሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶች አለአግባብ አሻቅቦ የነበረው የሲሚንቶ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ሲሚንቶ ለመግዛት ወረፋ ይዘው ያገኘናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ። መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት እየሰራ ያለው ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ቢሮው አስታወቀ።
አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው አቶ አሰፋ ካሴ ፣ ሲሚንቶ ቀደም ባለው ጊዜ ከ700 እስከ 800 ብር ይሸጥ እንደነበረው አመልክተው፣ አሁን ላይ ግን በ376 ብር በኩንታል እየተሸጠ ነው ብለዋል።
ዋጋው መቀነሱ እንዳለ ሆኖ በገበያ ላይ የአቅርቦት ችግር እንዳለ ያመለከቱት አቶ አሰፋ ፣ መንግስት ያሉትን ፋብሪካዎች በተገቢው መንገድ ማምረት እንዲችሉ ካደረጋቸው አቅርቦቱ ሊዳረስና ዋጋውም ከዚህም በታች ሊቀንስ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ጎጃም በረንዳ አካባቢ ሲሚንቶ ለመግዛት ሰልፍ ይዘው ያገኘናቸው ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዘውዱ አዱኛ በበኩላቸው በገበያው ላይ የሲሚንቶ እጥረት እንዳለ ገልጸው፣ ዋጋው በተወሰነው ተመን መሰረት እየተሸጠ መሆኑን አመልክተዋል።
ሲሚንቶ በመሸጫ መጋዘናቸው ያላቸው ነጋዴዎች በከተማዋ ውስን በመሆናቸው ምርቱን ለማግኘት መቸገራቸውንና ለመግዛትም ከ30 ኩንታል በላይ ስለማይቻል በየቀናት ልዩነት ስራ አቋርጠው መምጣት የተገደዱበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ፣ “ከዚህ ቀደም ፋብሪካዎች በተለያየ መንገድ ምርት ማምረት ማቆማቸው፣ ምርቱን ለማግኘት ረጅም የደላላ ሰንሰለት መኖሩ፣ አግባብነት የሌላቸው አካላት በሲሚንቶ ንግድ መሳተፋቸው ዋጋ ለመጨመሩ ዋነኛ ምክንያት እንደነበረ አስታውቀዋል።
“ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግስት በተለይም የንግድ ሚኒስቴር በፋብሪካዎች ይታይ የነበረውን የምርታማነት ችግር ለመቅረፍና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የቴክኒክና የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉን አመልክተው ፣ ከዚህ የተነሳም በአሁን ወቅት ፋብሪካዎች ከነበራቸው ዝቅተኛ የማምረት ደረጃ ወደ ተሻለ ደረጃ መሸጋገራቸውን አስታውቀዋል ። የምርት አቅርቦትም መጨመሩን ገልጸዋል፡
ከዚህ በተጨማሪም በግብይት ሥርዓት ውስጥ ኩፖን በመሸጥ የግብይት ሰንሰለቱን በማስረዘም ለማህበረሰቡ ምርት እንዳይደርስ፣ ከገበያ እንዲጠፋ፣ ተገቢ ያልሆነ ግብይት ሲያደርጉ የነበሩ አካላት ከሥርዓቱ እንዲወጡ መደረጉንም አስታውቀዋል።
እንደየፋብሪካዎቹ ነባራዊ ሁኔታ አቅራቢዎች በየክልሎቹ ተለይተው ምርቱን ከፋብሪካዎች እንዲያወጡ ተደርጓል። በአዲስ አበባ ሀምሳ አንድ ቀጥታ ምርት የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ተለይተው ወደ ሥራ ገብተዋል ። የተባሉት ችግሮችና አቅርቦቱም እየተፈታ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል። አሁን ያለውን የሲሚንቶ ፍላጎት ከማሟላት አኳያ እና ያለውን ችግር ለመፍታት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ በንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽንና የኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት አቅራቢ ድርጅት በኩል የሲሚንቶ ምርት ለተገልጋዮች እንዲቀርብ መደረጉን አመልክተዋል።
50ሺ ኩንታል የሚጠጋ የሲሚንቶ ምርት ለአዲስ አበባ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ማቅረብ እንደተጀመረ ፣ በከተማዋ በግንባታና በንግድ ስራ ለተሰማሩ የምርት ሽያጭ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
የዋጋ ተመኑ ምርቱ ከፋብሪካ ከሚወጣበት ዋጋ ያገናዘበ ነው። ሁሉም ፋብሪካዎች መነሻ ዋጋቸውን አሳውቀዋል። ከፋብሪካው ከወጣ በኋላ የሚያልፈውን የቅብብሎሽ ሰንሰለት ሲያልፍ ሊወጣ የሚችለውን ዋጋ ታሳቢ ያደረግ እንደሆነም አስታውቀዋል።
“እጅግ ተጋኖ እስከ 800 ብር ድረስ ይሸጥ የነበረበትን የስግብግብነት የገበያ አካሄድ ለማስቀረት ስራ ተሰርቷል፣ በቀጣይነትም ይኸው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡
“በነበረው ገበያ ከፋብሪካው ዋጋ እስከ 400 ብር ድረስ ጭማሪ አድርጎ የመሸጥ ፣ ምርቱን የመሰወር ሁኔታዎች እንደነበሩ አስታውሰው ፣ መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት እየሰራ ያለው ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቁመዋል። ገበያውን የማረጋጋቱ ስራ በዘፈቀደ ሳይሆን በጥናት ላይ ተመስርቶ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም