
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ አበባ፡- መንግሥት ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ከ344 ቢሊዮን ብር በላይ ለነዳጅ ግዥ ወጪ መደረጉን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የዋና ሥራ አስፈፃሚ አማካሪ አቶ ደመላሽ ዓለሙ አስታወቁ። የስኳር ፕሮጀክቶች ስኬታማ አለመሆን ኢታኖልና ቤንዚል ቀላቅሎ ለመሸጥ በታሰበው ፕሮጀክት ላይ ጫና መፍጠሩን አመለከቱ ።
አቶ ደመላሽ ዓለሙ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ መንግሥት እ.ኤ.አ ከ2017 እስከ 2021 መጋቢት ወር ድረስ 344 ቢሊዮን 227 ሚሊዮን 231 ሺህ ብር ለነዳጅ ግዥ ወጪ አድርጓል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ 17 ሚሊዮን 348ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል።
እ.ኤ.አ በ2017 የነበረው የነዳጅ ግዥ 43 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ያመለከቱት አቶ ደመላሽ ፣ እ.ኤ.አ በ2020 ደግሞ 86 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ይህም በየጊዜው የነዳጅ ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል። ፍላጎቱን ለማሟላትም መንግሥት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ እያፈሰሰበት እንደሆነም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ቤንዚን፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ነጭ ናፍታ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ የሚውሉ ቀላል ጥቁር ናፍታ እና ከባድ ጥቁር ናፍታ የተሰኙ አምስት የነዳጅ ዓይነቶችን ከውጭ የምትገዛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከሐምሌ 2012 ዓ.ም እስከ የካቲት 2013 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 428ሺ965 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል። በዚህ ወቅት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ታቅዶ የነበረው 399ሺ261 ሜትሪክ ቶን ነበር። ግዥው ከእቅዱ ሰባት በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
በ 2012 ዓ.ም ተመሣሣይ ወቅት አኳያ የቤንዚን አቅርቦት 16 በመቶ ብልጫ እንዳለው የጠቆሙት አቶ ደመላሽ፣ እንዲህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት የቤንዚን እጥረት እየተከሰተ ነው ፤ ለእጥረቱ ሕገ ወጥ አሠራር መበራከቱ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ አስታውቀዋል።
የነዳጅ እጥረትን ለማቃለል ይረዳ ተብሎ ተስፋ ከተጣለባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አመልክተው፤ የፕሮጀክቶቹ ስኬታማ አለመሆን የስኳር ተረፈ ምርት የሆነውን የኢታኖል ምርት ከቤንዚን ጋር ቀላቅሎ ወደ ገበያ ለማስገባት የነበረውን ተስፋ ፍሬ አልባ አድርጎታል ብለዋል።
ኤታኖልን ከቤንዚን መደባለቁ ለተወሰነ ጊዜ ተሰርቶበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደመላሽ፤ በሂደት የኢታኖል ማጓጓዣ፣ ኢታኖል ምርት መጠን ማነስ፣ አጠቃላይ ያለው ሂደት ወጪ መጨመር፣ ዋጋ ትመና ላይም ቅሬታ መኖር፣ ለወጪ ማካካሻም የተመደበውም ገንዘብ በቂ አይደለም በሚል ቅሬታ ሥራው መስተጓጎሉን አመልክተዋል።
ሥራ ሲታሰብ በግንባታ ላይ የነበሩ ስኳር ፋብሪካዎችን ታሳቢ ያደረገ እንደነበር እነዚህ ወደ ሥራ ሲገቡ 10 በመቶ ኢታኖል የመቀላቀል እቅድና የውጭ ምንዛሪ የማዳን ውጥን እንደነበር ያመለከቱት አቶ ደመላሽ፣ የስኳር ፕሮጀክቶቹ አለመጠናቀቅ የታሰበው ስኬታማ እንዳይሆን ማድረጉን አስታውቀዋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአሁኑ ወቅትም በመላ ሀገሪቱ 950 የሚሆኑ የነዳጅ ማደያዎችም ይገኛሉ።
የስኳር ፋብሪካዎች ኢታኖል አቅርቦት ማነስና የመሳሰሉት ሥራው በታሰበው መጠን እንዳይቀጥል አድርጓል። በመሆኑም ከሁለት ዓመት ተኩል ወዲህ ሥራው መቋረጡን አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም