
በኃይሉ አበራ
አዲስ አበባ፦ የከተማ ነዋሪዎች በሀገራችን ግንቦት 28 ለሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ ቀረበ። ዜጎች ካርዳቸውን በሚወስዱበት ወቅት አስፈላጊውን የኮቪድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተጠቆመ ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በምዝገባ ጣቢያዎች ተገኝቶ ያነጋገራቸው ፣ ወይዘሮ ኪዳኔ ሰይፉ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ነዋሪ ናቸው፡፡ የ80 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ሲሆኑ የምርጫ ካርድ ሲወስዱ አግኝተናቸዋል ። ከዚህ በፊት በነበሩት ምርጫዎች በሁሉም ተሳትፈዋል፡፡ በቀጣዩ ምርጫ የበለጠ ተስፋ እምነት አለኝ ብለዋል፤
ምርጫ በሚደረግበት ወቅት ግርግር ሳይኖር ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እንዲከናወን የሀገራችን ሰዎችም አንድነታችንን አስጠብቀን መቆየት አለብን የሚሉት ወይዘሮ ኪዳኔ እንዳሉት፣ እርስበርስ ከመጋጨት ከችግር ከድህነት እንድንወጣ፤ በመስማማት ለመኖር ምርጫ አንዱ መሳሪያ ነው ብለዋል።
ገበሬው ያረሰውን አዲስ አበባ ሸምቶ መብላት የሚቻለው ሰላም ሲኖር የሚሉት ወይዘሮ ኪዳኔ፣ ሰላም ከምንም በላይ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ሰላም ሆና እንድትቀጥል፤ ነዋሪዎቿም በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ እመኛለሁ ብለዋል።
“እኔ የምርጫ ካርዴን ወስጃለሁ፤ የምመርጠውንም አውቃለሁ፤ እናንተም የምርጫ ካርዳችሁን በመውሰድ የፈለጋችሁትን ምረጡ፤ ሰላማዊ ምርጫ እናድርግ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጋዲሴ ከበደ በበኩላቸው ፣ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከዚህ በፊት በምርጫ 97 እንደነበረው ዓይነት ችግር ይመጣል ብዬ አላምንም፤ ይልቁንም ኑሮ የሚሻሻልበትን የተሻለ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በምርጫው የተሻለ ሰላም ይኖራል የተሻለ መንግሥት ሀገራችንን ያስተዳድራል ብዬ አምናለሁ የሚሉት ወይዘሮ ጋዲሴ ፤ የምርጫ ካርዳቸውን በመውሰዳቸው ደስተኛ እንደሆኑ በመግለጽ ፣ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ተመኝተዋል።
ከራያ አካባቢ መጥተው ላለፉት ስድስት ዓመታት በአራዳ ክፍለ ከተማ የኖሩት አቶ ሄኖክ ሃይለ ሚካኤል ፣ በሀገራችን ክፍፍል ሳይኖር አንድ ሆነን የሚያስተዳድረንን መንግስት በመቀበል በሀገራችንን በሰላም ሰርተን በሰላም እንድንኖር የሚያደርገን አንዱ መግባቢያችን ምርጫ ነው ብለዋል።
በምርጫ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን ክፍተት ሳንሰጥ በሰከነ ሁኔታ እንድናካሂድ ካለፉት ስህተቶችም መማር አለብን ያሉት አቶ ሄኖክ ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ ማህበረሰቡም ተረጋግቶ እንዲኖር ዜጎች የምርጫ ካርድ ወስደው እንዲመርጡ መልዕክት አስተላልፈው፤ በምርጫ ወቅትም ሰላማዊ የሆነ ምርጫ እንዲሆን ተመኝተዋል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ (በብሔራዊ አጸደ ሕጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚገኘው ምርጫ ጣቢያ) አስፈጻሚ አቶ አብዲ መገርሳ የምርጫ ካርድ ምዝገባ የተጀመረው መጋቢት 20 መሆኑን አስታወቀዋል። እስከ ረቡዕ 7 ሰዓት ድረስም 63 ሰዎች በምርጫ ጣቢያው መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ምርጫ ጣቢያ 7 አስተባባሪ አቶ ያየህይራድ አሰፋ፣ በምርጫ ጣቢያው በቂ ዝግጅት የተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ የሚጠበቀው የማህበረሰቡ ተሳትፎ ነው ብለዋል።
ምርጫ የዜግነት ግዴታ እና ኃላፊነት ጭምር በመሆኑ ማንኛውም እድሜው 18 ዓመት የሞላው ዜጋ ድምጹን ማባከን የለበትም። ህብረተሰቡ በተቀመጠለት ጊዜ ውስጥ የምርጫ ካርዱን በመውሰድ ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ድምጹን እንዲሰጥ ካርድ ያስፈልገዋል፤ የመራጭነት ካርዱን ለመውሰድም የምርጫ ጣቢያ ቢሮዎች ክፍት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ምርጫ ቦርድም ገለልተኛ፣ ፍትሃዊ እና ለማንም የማይወግን መሆኑን እንዲረጋገጥ ተገቢ ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ የገቡ መሆኑን ጠቁመው ፣ ዜጎች ካርዳቸውን በሚወስዱበት ወቅትም አስፈላጊው የኮቪድ ጥንቃቄ ማድረጋቸው እንዳይረሱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ መጋቢት 16 የተጀመረው የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 15 የሚቆይ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም