
ዋለልኝ አየለ
አዲስ አበባ፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 10ኛ ዓመት የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን ጠብቆ እንደሚከበር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለጸ ። ለግድቡ ግንባታ ከሐምሌ ወር እስከ የካቲት ወር መጨረሻ አንድ ቢሊዮን 283 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ ።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሃም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 10ኛ ዓመት በኮቪድ-19 ምክንያት በሰፊ የአዳራሽ ውስጥ ዝግጅት አይከበርም።
የግድቡ ግንባታ 10ኛ ዓመት በዓል በቦታው ባይከበርም ከጥር ወር ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ኃይሉ፣በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ፣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በምሁራን ውይይትና በኪነ ጥበብ መድረኮች መከበሩን ጠቁመዋል ።
እንደ አቶ ኃይሉ ገለጻ፤ የውሃ ሙሌቱ ከተጀመረበት ከሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ በነበሩት ወራት የሕዝቡ ተሳትፎ ጨምሯል ። በዚህም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል ።
ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪም ከውሃ ሙሌቱ ወዲህ በተለያዩ ዓለም አገራት የሕዝብ ዲፕሎማሲው ጨምሯል። ኢትዮጵያ ላይ አድሎዓዊ ውሳኔ ሲወሰን በተቃውሞ ሰልፍ የኢትዮጵያን አቋም አሳይተዋል። ለዲፕሎማቶቻቸውም አቤቱታ አስገብተዋል። ምሁራንም ከሌላው ጊዜ በተለየ ሙያዊ ማብራሪያ ሲሰጡ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
አርሶ አደሩም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጉንም የጠቆሙት አቶ ኃይሉ ፣አርሶ አደሮች በአማካኝ በዓመት 30 ቀን በነፃ አፈርና ውሃ ጥበቃ ላይ ሰርተዋል። የአርሶና አርብቶ አደሩ ጉልበት በገንዘብ ሲተመን ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆንም ጠቁመዋል ።
ከዚህ በፊት 300 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን፣ ከ400 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት የመገናኛ ብዙኃን እና የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች የህዳሴ ግድቡን መጎብኘታቸውን የገለጹት አቶ ኃይሉ፤ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ጉብኝቱ መቀዛቀዙንና የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ቀን በቦታው ማክበሩ እንደቀረ ገልጸዋል።
ምሁራን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጆርናል ላይ እየሰሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኃይሉ፣ በተለይም ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በጮቄ ተራራ ላይ በተደረገው የምሁራን ውይይት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ስምምነት አድርገዋል ብለዋል።
የውሃ ሙሌቱ ከተጀመረበት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ከተደረገው ድጋፍ በታህሳስ ወር የተሰበሰበው 230 ሚሊዮን 970 ሺህ ብር ይህም ከፍተኛው መሆኑን አስታውቀዋል። ዝቅተኛው ደግሞ በጥር ወር የተሰበሰበው 90 ሚሊዮን ብር እንደሆነም ገልጸዋል። አሁን ላይም ለግድቡ ግንባታ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደቀጠሉ አስታውቀዋል ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም