ጽጌረዳ ጫንያለው
ረዳት ፕሮፌሠር መቅደስ ደሴ ይባላሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በተቋቋመው የሴት አመራሮችና መምህራን መረብ ውስጥ ሥራ አሥፈጻሚ ናቸው። የግብርና ምጣኔ ሀብት ምሩቅ ሲሆኑ፤ በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የግብርና ኮሌጅ ዲን በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። በሕይወታቸው በርካታ ውጣ ውረዶችን አሣልፈዋል። በተለይ ለመማርና ያቀዱት ላይ ለመድረስ ያልከፈሉት መስዋዕትነት አልነበረም። ምክንያቱም ከፍተኛ ውጤት አምጥተው እንኳን ዩኒቨርስቲ ገብተው መማር እንዳይችሉ አቅም ገድቧቸው ያውቃል። ስለዚህም ቴክኒክና ሙያ ገብተው ከዲፕሎማ እስከ ሁለተኛ ድግሪ ድረስ ተምረው ነው ዛሬያቸውን ያገኙት። እናም ከዚህ ሁሉ የሕይወት ተሞክሯቸው ልምድን ትቀስሙ ዘንድ ለዛሬ “የሕይወት ገጽታ”› አምድ እንግዳ አድርገናቸዋልና ተማሩባቸው ሥንል ጋበዝን።
የእናት ልጅ
ትውልዳቸው ጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ ከሲና ቀበሌ ውስጥ ነው። አካባቢዋ ገጠራማ በመሆኗ ከእናትና አባታቸው በማይተናነስ መልኩ የጎረቤት ሰው ሁሉ አሣዳጊያቸው፣ ተቆጪያቸው፣ ገራፊያቸው በመሆናቸው በሥነምግባራቸው ምሥጉን ናቸው። በባህሪያቸው ከአካባቢው ልጅ ምሥጉን የሚባሉ ዓይነት ልጅ እንዲሆኑ አሥችሏቸዋልም። መታዘዝ የሚወዱ፣ ያላቸውን የሚያካፍሉና አልችልምን በፍጹም የማይወዱም አድርጓቸዋል። ሲሠሩም አድምተው ነገሮችን ከግብ ሣያደርሱ የማይተዉ እልኸኛ ልጅም የሆኑት በጎረቤትና በእናታቸው ምክር በማደጋቸው እንደሆነም ያስታውሣሉ።
እናታቸው የሚያስፈልጋቸውን እያደረጉላቸው የበለጠ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተከሩ አድርገው ስላሣደጓቸውም በሁሉ ነገር ውጤታማም ነበሩ። በተለይም የማይረሱት ማሥፈራሪያቸው “እንዳልድርሽ”› ነበርና ማግባት ከብዙ ነገር ወደኋላ ያሥቀራል የሚለውን የማህበረሰቡ አመለካከት ልቦና ውስጥ አሥገብተው ብርቱ ተማሪ መሆን እንደቻሉ ይናገራሉ።
ታሪክን መሥማት የሚወዱና የተባሉትን በበጎ የሚተረጉሙት ባለታሪካችን፤ ይህንን አድርጊ ሲባሉም ካልመሠላቸው የማይሆንበትን ምክንያት በደንብ የሚያብራሩና የሚያሣምኑም እንደነበሩ ያስታውሣሉ። በሌላ በኩል ቤተሠባቸውን በተሰጣቸው ሀላፊነት ልክ የሚያግዙ ሲሆኑ፤ በተለይም ልጅ መያዝ፣ ውሃ መቅዳትና ቤት ማፅዳት የእርሣቸው ድርሻ በመሆኑ ቤተሠቡ እንዲደሠት አድርገው ተግባራቸውን ያከናውናሉ። ከዚያ ውጪ ያለውን ሥራ ታላቅ እህታቸው ስላለች እርሷ እንድትሠራ ይደረጋል። ምክንያቱም እንግዳችን ተምረው እንዲወጡ ይፈለጋልና ነው።
ከጨዋታ አሻንጉሊት እየሠሩ ዕቃ…ዕቃ መጫወት የሚያሥደስታቸው እንግዳችን፤ ያልሠሩት የቤት ሥራ ወይም እሠራዋለሁ ብለው ያቀዱትን ነገር ሠርተው ውጤቱን ማየት ካልቻሉ እረፍት አያገኙም። እናም ሁልጊዜ በዚያ ሥራ አዕምሯቸው ይጠመዳል። ይህ ደግሞ ለነገ የሚሉት ሥራ እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል። ስለዚህም በባህሪ ከጓደኞቻቸውም ሆነ ከቤተሠቡ ለየት የሚያደርጋቸው ይህ እንደሆነ አጫውተውናል።
የእንግዳችን የልጅነት ሕልም መምህር መሆን ሲሆን፤ ምክንያታቸውም የሚያሥተምሯቸው መምህራን ናቸው። እነርሱ በእውቀት የሚበልጣቸው ሰው እንደሌለ ያምናሉ። ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ ያሥባሉ። ስለዚህም እርሣቸውም እንደነእርሱ ለማድረግ ስለሚፈልጉ መምህር መሆንን አጥብቀው ይፈልጉታል። ፈልገው ብቻ ሣይቀሩም አሣክተውታል። ለዚህ ደግሞ እናታቸው ትልቁን ድርሻ ይወሥዳሉ። በሚገባ እንዲማሩ ማግባት የሚለውን የማህበረሰብ አስተሳሰብ አዕምሯቸው ውስጥ አስቀምጠውባቸዋልና።
ፈተና አይጥልምን በተግባር
ብዙ ልጅ ለቤተሠቡ ብሎ እንደሚማር ነው የሚረዳው። በዚህም በራሱ ጥሮ ለራሴ ነው የምማረው ብሎ አያሥብም። እንዲያውም ችግር ሲገጥመው ማቋረጥን መፍትሄው ያደርጋል። ምክንያቱም ጠቀሜታውን በአግባቡ የሚረዳው ከፍ ካለና ሥራ ከያዘ በኋላ ነው። እርሣቸው ግን ከልጅነታቸው ጀምሮ ይህንን ተረድተው
ስላደጉ ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ያለው የትምህርት ጉዟቸው ፈተና የበዛበት ቢሆንም አልፈውታል። ወደፊት እንጂ ወደኋላ አላሉምም። እናትም አባትም ሣይኖራቸው በራሣቸው ጥረትም የፈለጉት ላይ መድረስ ችለዋልም።
የእንግዳችን የመጀመሪያ የትምህርት “ሀ ሁ” የጀመረው ከቤታቸው በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው መዝወር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ በትምህርት ቤቱ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረውበታል። ወደ ዘጠኝና ክፍል ሲዛወሩ ግን የመማር ማስተማሩ ሂደት ቀላል አልሆነላቸውም። ምክንያቱም በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት የለም። ስለዚህም በእግራቸው በጣም ሩቅ መንገድ መጓዝ ይኖርባቸዋል። እንዲያውም በሰዓት ሲገልጹት ከ3፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት ድረስ ይፈጃል። ስለሆነም በየቀኑ መጓዝ ባለመቻላቸው ከአምስት የሠፈር ልጆች ጋር ቤት ተከራይተው እንዲኖሩ ሆነዋል።
ትምህርት ቤቱ ጮዛ ሠፈር ወይም በተለምዶ ከሬም ማዶ የሚሠኝ ሲሆን፤ ዘጠነኛና አሥረኛ ክፍልን ተምረውበታል። በዚያው ልክ ደግሞ ብዙ ችግርን ያሣለፉበት ነው። የመጀመሪያው የትምህርት ሥርዓት ተቀይሮ ጀማሪ ተማሪ በመሆናቸው ብዙ የተለዩ ነገሮችን አሥተናግደዋል። ሌላው ደግሞ ከሩቅ በሣምንት አንድ ጊዜ ቤተሠብ ጋር እየሄዱ ሥንቅ በማምጣት ስለሚማሩ ከመንገዱ በላይ ረሀቡ ያሠቃያቸው እንደነበር አይረሱትም። በተለይም ዓርብ እለት ከጾሙ ትይዩ ባዶ ሆዳቸውን መጓዝና ጦማቸውን ማደራቸው የተለመደ እንደነበር ያስታውሣሉ።
በጉራጌ ባህል ቆጮ ትልቁ ምግብ ነው። ምግቡን ለማቆየትና ለመጥበስ የሚያሥችል ማገዶ ለመሰብሰብ ጫካ መውረዱም አንዱ ፈተናቸው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ መጀመሪያ ቆጮና ማባያቸውን ይዘው እሁድ ከቤተሠብ ወደ ትምህርት ረጅሙን መንገድ መጓዙ፣ ዓርብ ትምህርቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ አሁንም ሥንቃቸውን ለማምጣት የአራት ሰዓት መንገዳቸውን በድጋሚ መያዙ በጣም ያሥመርራቸው ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ከሌሎች ጓደኞቻቸው ልጅ ስለነበሩ ሸክም በጣም ይከብዳቸው ነበርና ብዙ ጊዜ እየወደቁ እየተነሱ ሥንቃቸውን ቤታቸው ማድረሱ ያለው ፈተና መቼም የማይዘነጉት እንደነበር ያወሣሉ።
ሌላው ፈተናቸው ሴት ልጅ መሆን በራሱ በርካታ ችግሮች የተጋረጡበት መሆኑ ነው። ምክንያቱም ከአደጋው በላይ መማር የለባትም የሚለው አስተሳሰብ የላቀ ነው። ይሁንና በጉራጌ ባህል ይህ አይደገፍም። ይልቁንም ጥሩ እሴት ያለውና መማርን የሚያበረታታ ስለነበር በዚህ ሕይወት ውስጥ አላለፉም። ነገር ግን ከዚያ በተቃራኒ ገጥሟቸዋል። ይህም ቤተሠብ ጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆንም ብር አውጥቶ ለሴት ልጅ የመሥጠት ባህል የለምና ሴቶቹ እንደ ወንዶቹ ወጥተው እንዲመገቡ አያደርጋቸውም። ረሀባቸውን እንኳን ማሥታገስ ይከብዳቸው ነበር።
የእናታቸው ግፊት የትምህርቱን ውጤታማነት እንዳጎናፀፋቸው የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሠሯ፤ እናታቸው ገና ከትምህርት ቤት ሲመለሱ “ይህንን ኑሮ ከናፈቅሽ አትማሪ፤ መሻገር ከፈለሽ ግን ከትምህርት ውጪ አማራጭ የለሽም” ይሏቸው እንደነበር አይረሱትም። እንደእርሣቸው የገጠሩ አካባቢ ላይ ኗሪ ብቻ ሆነው እንዳይቀሩም ማምለጫው ትምህርት መሆኑን እየነገሩ ስላሳደጓቸውም ቀጣዩን ክፍላቸውን በደንብ እንደተማሩ ይናገራሉ።
እንግዳችን በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ ቢሆኑም የሚገጥማቸው ፈተና ግን ከባድ ነበር። ሆኖም በእናታቸው ተግሣጽ ሁሉን አልፈውታል። ለአብነት እናት ጉብዝናቸውን ተገን አድርገው እንዲንቀባረሩ አይፈቅዱላቸውም። ለዚህም ማሣያው ሽልማታቸውን ይዘው መጥተው በጉጉት ሲያሣዩዋቸው “ሥስራሽ እኮ ነው። እንድትማሪ ተልከሻል፤ ከዚህ የተለየ ውጤትም ልታመጪ ይገባል” መባላቸው ነው። ይህ ግን አላሸማቀቃቸውም። ይልቁንም የበለጠ እንዲበረቱና እንዲሠሩ አድርጓቸዋል። በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ውጤት ካመጡት መካከል የሆኑትም ለዚህ ነው። ነገር ግን መሠናዶን በተለያዩ ምክንያቶች መቀላቀል አልቻሉም።
በጣም ብዙ ርቀው መጓዝ ስለማይችሉና ወልቂጤ ድረስ ሄደው ከተማሩ በተለይ ሴቶች ይበላሻሉ የሚለው የማህበረሠብ አስተሳሰብ የመጀመሪያው ሲሆን፤ ሌላው የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው። ስለዚህም ቤተሠባቸው የመረጠላቸው ትምህርት ቤት መማር ጀመሩ። ይህም በዲፕሎማ ትምህርት የሚሠጥበት በቆጂ ቴክኒክና ሙያ ግብርና ኮሌጅ ነው። በእርግጥ ይህ ይሆናል ብለው መቼም አልመው አያውቁም። ምክንያቱም ከትምህርት ቤቱ የደረጃ ተማሪ ናቸው። በዚያ ላይ የአሥረኛ ክፍል ውጤታቸውም ከፍተኛ ነው። ግን አጋጣሚው የተለየ ሆነና የተባሉት ላይ አረፉ።
“ወደድንም ጠላንም በገባንበት ላይ ውጤታማ መሆን ከቻልን ነገ ያለምነውን እናገኛለን። የተሻለና የመጀመሪያው ሰው መሆናችንም አይቀሬ ነው” የሚል እምነት ያላቸው ባለታሪካችን፤ ግብርና ኮሌጅ በመግባታቸው ሣይቆጩ ውጤታማ መሆናቸው ላይ እንደሠሩ ይናገራሉ። ጥሩ መኝታ በሌለበት ጅባ ላይ እየተኙ በዓላማ ሲሠሩበት የቆዩትን ተግባር አሁን በተፈጠረላቸው ዕድልና ምቾት የበለጠ እንዳጠናከሩትም ያሥረዳሉ። ይህ ነገር ከብዷቸው ከእርሣቸው ጋር የነበሩ ብዙዎቹ ጓደኞቻቸው ትምህርት ማቋረጥ ብቻ ሣይሆን ከዚያም የባሠ ችግሮች ውስጥ ገብተዋል። እንዲያውም የቤት ሠራተኛ እስከመሆን የደረሱም ነበሩ። ሆኖም እርሣቸው ችግርን መቋቋም ወርቅ ያለብሣል ብለው አምነዋልና ትናንትን ተሻግረዋል።
ከችግር ወጥቶ መማር የበለጠ አቅምን ለመጨመር ያግዛልና እርሣቸውም ይህ እንደሆነላቸው ያወጋሉ። ለዚህም ማሣያው አንድ ቢ ብቻ ኖሯቸው በዲፕሎማ መመረቅ መቻላቸውና በአኒማል ሣይንስ የትምህርት መሥክ የሜዳሊያ ተሸላሚ መሆናቸው ነው። ይህ ጊዜ የሚያስደስታቸውና በፈተና ውስጥ ያለፉበት ቢሆንም እንዳስደሰታቸው ግን አልቀጠለም። ሌላ ተጨማሪ
ፈተና ይዞባቸው መጣ። ሥራ ይዤ ለዚህ ያበቃችኝን እናቴን አግዛለሁ የሚለው ሕልማቸው ከተመባቸው። ምክንያቱም ከምርቃት ማግሥት አባትም እናትም ሆነው ያሣደጓቸውን እናታቸውን በሕይወት አጧቸው። በዚህም ቅሥማቸው ተሠበረ።
ማንም የሚያግዛቸው ስላልነበራቸውም መኖራቸውን ሁሉ ጠሉት። ወንድሞች ቢኖራቸውም ለራሣቸው ሕይወት የሚኖሩ ናቸው። ሁሉም ራስ አውጪኝ እያለ የሚታትር ነው። ስለዚህም ነገሮች ከብደዋቸው ትምህርታቸውን ወዲያው ለመቀጠል አቃታቸው። ሆኖም ሁልጊዜ ቀን ጎዶሎ ሊሆን አይችልምና በአንድ አጋጣሚ ነገሮች ተሥተካከሉ። ሚዛን ቴፒ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የመሥራት ዕድል አግኝተው በኮሌጅ ውስጥ እየሠሩ ባሣዩት የሥራ ትጋትና ውጤታማነት እንዲሁም ያላቸው ትራንሥክሪፕት ቀጣዩን የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ አገዛቸው። በዚህም ምርጫቸው ተጠብቆላቸው በግብርና ምጣኔ ሀብት የትምህርት መሥክ እንዲማሩ ወደ ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ተላኩ።
በክረምት ክፍለ ጊዜም ሚዛን ቴፒ ቴክኒክና ሙያ በበጋው እየሠሩ ክረምትን በሐረማያ እየተማሩ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን መያዝ ቻሉ። ከዚያ ወደ ሚዛን ተመልሰው በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ሥራቸውን ጀመሩ። ምክንያቱም በትምህርት ላይ እያሉ ዩኒቨርስቲው ከኮሌጁ ከፍተኛ ውጤት ያላቸውን የሚዛን ቴፒ ቴክኒክና ሙያ መምህራንን ወደ ራሱ መውሠድ በመፈለጉ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበርና እርሣቸው በዚያ ውስጥ ተመራጭ ሆነው ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲን በረዳት መምህርነት ተቀላቀሉ። ይህ ዕድል ደግሞ ከዩኒቨርስቲ ዩኒቨርስቲ ዝውውር እንዲያደርጉ አግዟቸው ሌላኛውን የትምህርት ዕድል አሥገኘላቸው። ይህም በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አማካይነት ያገኙት የትምህርት ዕድል ሲሆን፤ ወልደው የወሊድ እረፍት በወጡበት ሰዓት ነበር የምሥራቹ ቤታቸው ድረስ የደረሣቸው።
በዚህም ገና አንድ ዓመት ያልሞላው ልጅ በመያዝ ለመማር ወደ ዩኒቨርስቲው አቀኑ። ምክንያቱም ትምህርት በእርሣቸው ዘንድ የተለየ ዋጋ አለው። የሚደራደሩበት ጉዳይም አይደለም። ስለዚህም ጊዜ ሣይፈጁ ማቄን ጨርቄን ሣይሉ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ለመማር ልጃቸውን ይዘው የትምህርት ዕድሉን ወዳገኙበት ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ሄዱ። በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲም በተፈጥሮ ሣይንስ እና ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትምህርት መስክ ትምህርታቸውን ተከታተሉ።
ከልጅ ጋር ትምህርት ለብዙዎች ከባድ ቢሆንም ለእርሣቸው ግን ሁሉም ነገር በሥኬት የተጠናቀቀላቸው ሴት ናቸው። እንዲያውም ልዩ የሚያደርጋቸውን ድሎች ተቀናጅተውበትም ነው ያሣለፉት። ከእነዚህ ድሎች ሁለቱ በጣም ዛሬ ድረስ ያሥደስታቸዋል። እነዚህም ውጤታማነታቸው ሣይቀንስ በመመረቂያ ጽሁፍ እጅግ በጣም ጥሩ የሚል ደረጃ ያገኙ ብቸኛ ሴት መሆናቸው አንዱ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከእርሣቸው ጋር የነበሩት ስድስት ወንዶች በመመረቂያ ጽሁፋቸው ሲንጠባጠቡ የመጡ ሲሆን፤ እርሣቸው ግን ጊዜ ያልፈጁ በሁለት ዓመት ውስጥ ውጤታማ ሥራ ያሥረከቡ ሴት መሆናቸው ነው። ከዚህ በኋላ ግን ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም ነበር። ሆኖም የመቀጠል ዓላማው ግን አላቸው። ምክንያቱም በረዳት ፕሮፌሠርነቱ ያገኙት ልምድና በሥራቸው በየጊዜው የሚያዳብሩት ልምድ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ያውቃሉ። ስለዚህም የቀጣይ ዕቅዳቸው ሦስተኛ ድግሪያቸውን መማር እንደሆነ አጫውተውናል።
እናቴ መምህሬም፤ የሥራ መሪዬም ነበረች
ስለ እናታቸው ሲያነሱ ቀድሞ እንባቸው ያቀራል። ምክንያቱም የጥንካሬያቸው ምንጭ፤ የመሥራታቸውና የመለወጣቸው ምሥጢር እርሣቸው ናቸው። እናታቸው ከአባታቸው በላይ ሀላፊነት ያላቸው ሁለገብ ሠራተኛ፣ የልጅ አስተዳደግን ሣይማሩ ያወቁና የሚተገብሩ ስለነበሩ አባት እያለ አባት ጭምር ሆነውም ነው ቤቱን የሚመሩት። ከዚያ ሻገር ሲባልም አባት ግብርናው ላይ ብዙም እውቀቱ ስለሌላቸው እርሣቸው እርሻውን ሣይቀር ከሠራተኛ እኩል ያርሣሉ፣ ያርማሉ። ቤት ውስጥም ቢሆን ሁሉም ሀላፊነት የእርሣቸው አድርገው የሚሠሩ ናቸው። በዚያ ላይ ይነግዳሉም። ስለዚህ ለቤቱ የሚሆነው ገቢ አመንጭ አባት ሣይሆን እርሣቸው ሲሆኑ፤ ልጆችም የፈለጋቸውን የሚጠይቁት እርሣቸውን ነው። እናም እናታቸው በብዙ ነገር መምህራቸው እንደነበሩ ያስታውሣሉ።
ሴት ይህንን አታደርግም የሚለውን አመለካከት በእርሣቸው እንደቀረፉም ያነሣሉ። ምክንያቱም እናታቸው በእርሣቸው እንዲመኩ አሥተምረዋቸዋል። ከሰው ምንም የማይጠብቁ ነገር ግን ሰው ሁሉ ራሱን እንዲያወጣ የሚያግዙ መሆንን አውቀውበታል። የአሠራር ጥበብን፣ እናት መሆንንና ለወደፊት አቅዶ መሥራትን እንዲሁም አለመሸነፍንም ቢሆን ከእርሣቸው ተምረዋል። በመሆኑም ይህንን ለሕይወታቸው መርህ አድርገውታል። ይሁንና በእናታቸው ሞት ብዙ ነገሮች ተደፍነውባቸው ነበር። ሁሉን ነገር መከታተልም የእርሣቸው ድርሻ ሆኖ ያውቃልም። በተለይም ሥራ ለማግኘትና መሠል ነገሮችን ለማከናወን ፈተናው ቀላል አልነበረም። ሐዘናቸው ይበረታ ነበርና ጊዜውን አምላክ አይድገመውም ይላሉ። ነገር ግን የተሰጣቸው ምክር ይበልጣልና በእርሱ አሸንፈውት ዛሬ ላይ ደርሠዋል።
ብርታት የገነባው የሥራ ጉዞ ሥራ ሲታሰብ በእናታቸው ለቅሶ ላይ እንደነበሩ የገጠማቸው ነገርን በሕይወታቸው መቼም አይረሱትም። ምክንያቱም ሥራ ፍለጋ በሚሮጡበት ወቅት ያመለጠ ዕድል ነው። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” የሚሉት ዓይነትም ሆኖባቸው አልፏል። ነገሩ እንዲህ ነው። የተማሩበት ኮሌጅ ማለትም የበቆጂ ግብርና ኮሌጅ ሠቃይ ተማሪዎችን በመለየት እዚያው ኮሌጅ ውስጥ ረዳት መምህር እንዲሆኑ ይፈልግ ነበር። በዚህም ባለታሪካችን ቅድሚያ የሚሰጣቸው ስለነበሩ ተመርጠዋል። ነገር ግን ያሉበት ቦታ ለከተማው ሩቅና በቀላሉ መረጃ የማይደርስበት በመሆኑ ሳይሠሙ አለፋቸው። ነገሩን እንኳን የተረዱት በጣም ቆይተው ነው። ስለዚህም ሌላ ሥራ ማፈላለግ ላይ ተጠመዱ። የማይፈልጉትን ሥራም ለመሥራት ተገደዱ።
ይህም የዲኤነት ወይም የልማት ጣቢያ ሠራተኛነትን ሲሆን፤ በጊዜው ከነበሩበት አካባቢ በታች ወርዶ መሥራቱ በጣም ይሠለች ነበር። ተሥፋ አሥቆራጭም ነው። ብዙ ፈተናዎችም ነበሩበት። በተለይም ውጤታማ ለነበረ ተማሪ በምንም መልኩ የማይታሠብም የማይታለምም ነው። እናም ነገሩን መቋቋም ሲያቅታቸው ከተወሠነ ጊዜ በኋላ በቀጥታ ሥራውን ለቀው ወደ ሐዋሳ ወንድምና እህታቸው ጋር አመሩ።
በሐዋሳ አንድ ሣምንት እንደቆዩ ግን ነገሮች ተቀየሩ። ሚዛን ቴፒ ቴክኒክና ሙያ፤ ዲላ ቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ወላይታ ሶዶ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በረዳት መምህርነት የሚሠራ እንደሚፈልጉ ማስታወቂያ አወጡ። በዚህም እርሣቸው ተወዳድረው አለፉ። ዕጣ ሲያወጡም ሚዛን ቴፒ ቴክኒክና ሙያ ደርሷቸው ለማሥተማር ወደዚያው አቀኑ። ከዚህ በኋላም በትንሹም ቢሆን የተደላደለ የሥራ ሥድሎችን ማግኘት ጀመሩ። በብቃታቸውና በሥራቸው እንዲሁም በውጤታቸው ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነላቸውም።
ሚዛን ቴፒ ሲገቡ ከወንድ ተጽዕኖ ለመውጣት የራሣቸውን ታሪክ እንደፈጠሩና እራሣቸውን ለማሥተካከል እንደጣሩ ያጫወቱን እንግዳችን፤ ጓደኛ ሣይኖራቸው አለኝ ብለው አዲስ ታሪክ ለሁሉም ጓደኞቻቸው ይናገሩ ነበር። በዚህም ማንም ሣይተነኩሳቸው የመማር ማሥተማር ሥራቸውን ማከናወን አሥችሏቸዋል። በዚህ ደግሞ በኮሌጁ ውስጥ ካሉ መምህራን በአቅምም ሆነ ውጤታማ ሥራ በመሥራት የተሻሉ ሆነው እንዲወጡ ሆነዋል። እንዲያውም ሽልማት እስከማግኘት የደረሠ ሥኬት እንዲጎናፀፉም ያደረጋቸው እንደነበር አይረሣቸውም። ይህም ሽልማት የትምህርት ዕድል መሆኑ በሁሉም ቦታ የበለጠ መሥራት ለሥኬት እንደሚያበቃ ያወቁበትም እንደነበር በወጋችን መካከል አንሥተውልናል።
ለመማርና ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ምቹ ሁኔታ ያሥፈልጋል። ከዚያ ይልቅ ደግሞ አጋጣሚን መጠቀም በተግባር የሚደገፍ ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ብለው የሚያምኑት ባለታሪካችን፤ በኮሌጁ ሲሠሩ በመስኩ ቀድመዋቸው የገቡትን ሣይቀር መብለጥ የቻሉት ይህንን መርሀቸውን ይዘው በመጓዛቸው እንደሆነ ያነሣሉ። ቀጣዩም ሥራቸው በዚህ መልኩ የቀጠለና በዩኒቨርስቲው የመግባትና የመመረጣቸው ምሥጢርን ይህ አቋማቸው ያመጣው እንደሆነም ነግረውናል።
ከኮሌጅ ከወጡ በኋላ የሠሩት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ ይህም የሆነው ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ከሚዛን ቴፒ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመቀናጀት በውጤታቸው ሠቃይ የነበሩ መምህራን ዩኒቨርስቲው ውስጥ ገብተው እንዲያሥተምሩ በመፈለጉ ኮሌጁ እርሣቸውን ጨምሮ በመላኩ የተነሣ ነው። ስለዚህም ረዳት መምህር በመሆንም በዩኒቨርስቲው ለዓመታት ሠርተዋል። በአጠቃላይ ሚዛን ቴፒ ለሰባት ዓመት ያህል እንዳገለገሉም አጫውተውናል። ሆኖም አንድ ዓመቱን ግን የሠሩት በኢንስትራክተርነት ነው። ከዚያ ታናናሽ እህቶችና ወንድሞቻቸውን ለማገዝ በመፈለጋቸው መኖሪያቸውን ወልቂጤ ከተማ ላይ አደረጉ። ሥራቸውም ዩኒቨርሲቲው ሆነ።
ወልቂጤ ዩኒቨርስቲን በግብርና ምጣኔ ሐብት ትምህርት መስክ በመምህርነት የተቀላቀሉት ረዳት ፕሮፌሠር መቅደስ፤ በዚህም ሥራቸው በርካታ ተማሪዎችን አፍርተዋል። የማህበረሠብ አቀፍ ሥራዎችንም ሠርተዋል። በምርምሩ ዘርፍም ቢሆን የተለያዩ ሥራዎች ላይ በመሣተፍ ውጤታማ ሥራ እየሠሩ ቆይተዋል። መካከለኛ ደረጃ ማኔጅመንት የሚባለው ላይም ሠርተው አንቱታን ያተረፉ ውጤቶችን አምጥተዋል። በኢንስትራክተርነትም ቢሆን ለዓመት ያህል አገልግለው ውጤታማ ሥራን ያሣዩ ናቸው። ከዚያ ሥራቸው የላቀ በመሆኑና ዋና አስተዳደሩን ቢይዙ የበለጠ ለውጥ እንደሚያመጣ በመታመኑ የግብርና ኮሌጁ ዲን ሆነው እንዲሠሩ ተደረጉ። አሁንም በዚህ ሥራ ላይ ይገኛሉ። ከአስተዳደሩ ሥራ በተጨማሪ የማስተማርና የመመራመር ሥራንም ይሠራሉ። የዩኒቨርስቲው የቦርድ አባልም ናቸው።
እርሣቸው ገደብ ያለበት ሥራ አያውቁም። ግቡ የተባሉት ላይ ገብተው የደማ ሥራ መሥራት የለመዱ ናቸው። በዚህም በአገር ዓቀፍ ደረጃ በተቋቋመው የሴት ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ አመራሮችና መምህራን መረብ ላይ ሥራ አሥፈጻሚ ሆነው ያገለግላሉ። ይህ ደረጃ የሚሰጠው ደግሞ ከ46 ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ከተውጣጡ ሴቶች ሰባት ተመርጦ እንዲያገለግል የሚደረግበት ሀላፊነት ሲሆን፤ በተቻላቸው ሁሉ እየሠሩበት እንደሆነም ይናገራሉ።
የትዳር ሕይወት
የመጀመሪያ ድግሪያቸውን እንደያዙ ነበር ብቸኝነታቸውን ለማሥቀረት ትዳር የመሠረቱት። ምክንያቱም ከዓላማቸው ላለማፈንገጥና የፈለጉት ላይ ለመድረስ የወንዶች ተጽዕኖን ለመቋቋም በሚል ብዙዎችን ሲገፉ ቆይተዋል። ይሁንና የዛሬው ባለቤታቸው ግን ይህንን ሁሉ በማለፉ የትዳር ምርጫቸው አድርገውታል። ወደውትም ነው ያገቡት። እርሱ የት መድረስና ምን እንደሚፈልጉ የሚረዳ ዓይነት ነው። በሥራዎቻቸውም ሁልጊዜ ይደግፋቸዋል።
አታደርጊም የሚላቸውም የለም። እንዲያውም አማራጮችን ሣይቀር ያሣያቸዋል። ስለዚህም ከእናታቸው ቀጥሎ በቅርብ ያለና የሚያማክራቸው ሆኖላቸዋል። በዚህም ቤታቸው በደሥታ የተሞላ ነው። በሁለቱም በኩል ያሉ ቤተሠቦች ጭምር ተዋደውና ተረዳድተው በእነርሱም ታግዘው እንዲሄዱም ያሥቻላቸው የሁለቱ ምልከታ የተመጣጠነ በመሆኑ እንደሆነም አጫውተውናል። በእርግጥ ወደ ወልቂጤ ሲመጡ ባለቤታቸው አብረዋቸው አልነበሩም። ሚዛን ቴፒ ላይ ብዙ ሀላፊነት ስለነበረባቸው በዚያው ነው የቀሩት። በዚህም ብዙውን ጊዜ ብቻቸውን አሣልፈዋል። አሁን ደግሞ በመምጣታቸው ደሥተኛ እንደሆኑና ልጅም ጭምር ከእናት አባት ጋር በደሥታ እየኖሩ እንደሆነ አውግተውናል።
መልዕክት
ከፍተኛ ተቋም ላይ ሲደረስ ለሴት ልጅ የሚሰጠው ክብር የአስተሳሰብ ችግር ያለበት ነው። ሥኬታማ ይሆናሉ ብሎ ማመንን ከፍ እያልን ስንሄድ አናምንበትም። በተለይም በወንዶች በኩል ያለው ቀናይነትና እምነት በብዛት የተሸረሸረና የአመለካከት ችግር ያለበት ነው። ሁሉ ነገር ጨርሰው እዚህ ከእኛ እኩል መወዳደር ከቻሉ ከዚህ በኋላ መታገዝ የለባቸውም የሚል አቋምም አላቸው። ይህ ደግሞ በአመጣጣችን ልክ የሚወሰን ስለሆነ መታየት አለበት። ሰው መደገፍ ያለበት በገንዘብ ብቻ ሣይሆን በምክርም ነው። በቅንት መንፈሥ መሆን የለበትም። በሠራነው ሥራ ልክ ደረጃውም ሊሰጥ ይገባል። ሥራ መመዘኛም ደረጃም መሆን አለበት እንጂ ሴትነት ወይም ወንድነት መሆን አይገባውም፤ መልዕክታቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ነገር ለሴት ልጅ የሚሰጠው ክብርና መሻሻል በድምጽ ወይም በችሮታ መሆን የለበትም። ሁኔታዋ ታይቶና ተመዝኖ በአዕምሮም በሥራም ውጤታማ ሊያደርጋት የሚችል መሆን አለበት። ይህ ሲባል በብዙ ትግል ያለፈችም ብትሆን እኩል መሣተፍ፣ እኩል መሥራት፣ እኩል መናገር የምትችልበት ሁነት ሊመቻችላት ያሥፈልጋል። እየሮጠች ሠርታ እየሮጠች የምትበላ መደረግ የለባትም። ከዚያ ይልቅ ተፈጥሮ ለሰጣት ነገር ተመጣጣኝ ምቾት ሊደረግላት ይገባል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከድምጽ የተሻገረ በተግባር የተደገፈ ሥራ መሥራት ያስፈልገዋል። እኩልነቱና ተሠሚነቱ እኩል እስከሚሆንም በተለይ በከፍተኛ ደረጃዎች ላይ መንግሥት መደገፍ እንዳለበትም ይመክራሉ።
አንድ ሴት ጎበዝ የምትባለው በችግር ውስጥ ሥታልፍ ብቻ ነው። ምክንያቱም ችግር የበለጠ ጥንካሬን ይሰጣል። አቅምንም ያጎለብታል። ከችግሩ መማርና የወደፊት አቅጣጫን እንዴት ማስተካከል እንደሚቻልም ያስተምራል። ስለሆነም ይመቻችልኝን ሣይሆን ችግሩን ልየውና በራሴ ልወጣን ልምዳቸው ሊያደርጉ ይገባል። ተፈጥሮ ከወንዶች የተሻለ የማየት ዕድልም ስላደለን ያንን ተጠቅሞ መሻገርም የሁልጊዜ መርሀችን መሆን አለበት። ማንኛውንም ዕድል በነበረው ጊዜ መጠቀምም ተገቢ ነው። ምክንያቱም ዛሬ ያለው ዕድል ነገ ላይኖር ይችላል። ስለሆነም ዕድሎች ሁሉ መልካም አጋጣሚ በመሆናቸው የተሻለ ነገን እንፍጠርባቸው። በቸልታ ማንኛውም ዕድል መታለፍ የለበትም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2013