አዲስ አበባ፡- አፍሪካ በዓለም የፋሽን ኢንዱስትሪ ያላት የገበያ ድርሻ ከአምስት በመቶ በታች በመሆኑ፤ ድርሻውን ለማሳደግና የሥራ ዕድል ለመፍጠር የዘርፉን አቅም ሙሉ ለሙሉ መጠቀም እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ በየዓመቱ የሚካሄደው የፓን አፍሪካ የፋሽን ኢንሺዬቲቭ ትናንትና በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በወቅቱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደገለጹት፤ የፋሽን ኢንዱስትሪው በዓመት ሁለት ነጥብ አራት ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሀብት ይገኝበታል። ከዚህ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ እምብዛም የማይባል እና ከአምስት በመቶ በታች ነው። በመሆኑም የአፍሪካ አገራት ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችለው እና ፈጠራ ላይ የተመሰረተውን የፋሽን ኢንዱስትሪ ማሳደግ ይኖርባቸዋል።
እንደ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ገለጻ፤ አፍሪካ የዓለም ፋሽን ኢንዱስትሪን መቆጣጠር የሚያስችል አቅም አላት። በዘርፉ በአህጉሪቷ ውስጥ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ገበያተኛ ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን ኢንዱስትሪው በአግባቡ ጥቅም ላይ አልዋለም። ፈጠራ በታከለበት መንገድ ተጠቅሞ ባህላዊ አልባሳትን በማዘጋጀት እና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችን የምርት ሰንሰለት በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በአግባቡ መቋደስ ያስፈልጋል።
‹‹አፍሪካውያን ኢኮኖሚያቸው መሰረት እንዲኖረው በፈጠራ ላይ የተመሰረቱ ኢንዱስትሪዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለባቸው›› የሚሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ በዚህ ረገድ የፋሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሰፊ የጨርቃጨርቅ ጥሬ ዕቃዎችን ፈጠራ በማከል ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪ ዘርፉ የእራስን ባህልና ማንነት ለማስተዋወቅ ዓይነተኛ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም እንደ ሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ ከምርት እስከ ስፌት ልብስ የሚያዘጋጁና የገበያ ሰንሰለታቸው ጠንካራ የሆኑ ፋብሪካዎች መስፋፋት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግዙፍ የጨርቃጨርቅ አምራች ኩባንያዎች ወደኢትዮጵያ መምጣታቸው ለዘርፉ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያግዛቸው መሆኑን አስረድተዋል።
የአፍሪካ ህብረት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ማቻንጋ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረግ የእርስ በእርስ የፋሽን ምርቶች ግብይት ሊጠናከር ይገባል። የምሥራቅ አፍሪካን ባህል የሚያንጸባርቁ የፋሽን ምርቶችን ወደ ምዕራቡ አፍሪካ ሲገቡ ብሎም፤ አንዱ ክፍል የሌላውን ሲሸምት የንግድ ግንኙነቱም ይጠናከራል። በመሆኑም ጥራት ያላቸው ምርቶችን በማዘጋጀት የፋሽን ኢንዱስትሪውን እምቅ አቅመ በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል።
የፓን አፍሪካ የፋሽን ኢንሺዬቲቭ በተካሄደበት ወቅት የኢትዮጵያን እና የተለያዩ አፍሪካ አገራትን ባህላዊ አለባበሶች በዘመናዊ መልክ ተዘጋጅተው ለዕይታ ቀርበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011
ጌትነት ተስፋማርያም