ጽጌረዳ ጫንያለው
ኢትዮጵያነት ለሳቸው ሁሉ ነገራቸው ነች። ስለ ሀገራቸው ተናግረው የሚጠግቡ አይደሉም። ደረት ኪሳቸው አካባቢ የኢትዮጵያ ባንዲራን ቀለም የያዘ ቁልፍ ሁሌም የሚለያቸው አይደለም። ሰዓታቸውም ቢሆን በኢትዮጵያ ቁጥር ማለትም እኛ በተለምዶ ግዕዝ በምንለው የሚቆጥር ነው። ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ጡረታም ወጥተው እንኳን ከእርሱ ውጪ አጥልቀው እንደማያውቁም ይናገራሉ። በጨዋታቸውና በንግግራቸው ኢትዮጵያ ሀገሬ ማለት ከአፋቸው አይጠፋም ።
በተዘዋወሩበት ሁሉ ኢትዮጵያ ስንቃቸው ነች። እርሷን አለማንሳት አይችሉም። ለንባብ ባበቋቸው 14 መጽሀፎቻቸው ውስጥ የእርሷ ስም ያልሰፈረበት አይታይም። ‹‹ ውቧ ኢትዮጵያ›› የሚለው የፎቶ ግራፍ አልበም መጽሀፍ ደግሞ ሙሉ እርሷን የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያን ገጽታ ለአለምም ያሳዩበት ነው። በዚህም ሹመቱ ባይሰጣቸውም የኢትዮጵያ አንባሳደር ናቸው።
ዶክተር ጌታቸው ተድላ በእርሻ ምርምር አንቱታን ያተረፉ የምርምርና የሥራ ልምዶችም ባለቤት ናቸው። በተለይም ለ34 ዓመታት በሰሩበት የተባበሩት መንግስታት በዘርፉ ያላቸውን ብቃት ለአለም ያሳዩበት ነበር። በእርሻ ምርምር ከስምንት በላይ መጸሐፍት በእንግሊዝኛ ያሳተሙ ሲሆን፤ ታዋቂ የአፍሪካ ሰዎች በሚመዘገቡበት ‹‹አፍሪካ ሁ ኢዝ ሁ›› ላይ ስማቸውና ታሪካቸው ከሰፈሩት መካከል አንዱ ናቸው። በልዩ ልዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ በንቃት የሚሳተፉና የሚያግዟቸውን ልጆች ጭምር ያፈሩም ናቸው ። በዛሬው ‹‹ የህይወት ገጽታ›› አምድ እትማችን እኚህን ስመ ጥርና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይዘንላችሁ ቀርበናልና ተጋበዙልን።
በራስ መተማመን ከልጅነት
የተወለዱት አዲስ አበባ አራዶቹ መንደር በተለምዶ አራዳ ጊዮርጊስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ብዙም የልጅነት ትዝታ ሳይኖራቸው እናታቸው ወደ ጅማ በማቅናታቸው እርሳቸው ወደ ጅማ ተጉዘዋል። የልጅነት ጊዜያቸው በእናትነት ስሜት ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸው እና በጥሩ ስነምግባር ተኮትኩተው አሳልፈዋል። እድሜያቸው ለትምህርት በሚደርስበት ጊዜ ደግሞ አባት እና እናትን አስፈቅደው ወደ አሰላ የወሰዷቸው ሲሆን፤ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜያቸውን በዚያ እንዲያሳልፉ ሆነዋል። ከስድስት ዓመታቸው ጀምሮ 12ኛ ክፍልን እስኪያጠናቅቁ ድረስም በዚያ ቆይተዋል።
አሰላ ለእርሳቸው የልጅነት ጣዕምን ያወቁባትና የኖሩባት ከተማ ነች። የፈለጋቸውን እያደረጉ ከጓደኞቻቸው ጋር የቦረቁባት ፤ የእርሻ ሥራ የለመዱባት፤ በእናታቸው የለመዱትን ይበልጥ በአባታቸውና በእንጀራ እናታቸው ያዩበት ነች። ከሁሉም በላይ ዛሬ ድረስ የማይለዩዋቸውን፤ ያልተለወጡትን ብሔርን ሳያስቡ ፍቅርን ማንነታቸው ያደረጉ ብዙ ጓደኞቻቸውን ያፈሩባት ከዝችው ከተማ ነው። የብዙ ትዝታቸው መሰረትም ነች -አሰላ ።
ዶክተር ተድላ ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። አባታቸው በአካባቢው ሀብታም ከሚባሉ ነዋሪዎች አንዱ ናቸው። ያሳደጓቸው ግን ከሰራተኞች እኩል እያሰሩ ነው። ቤቱ የተትረፈረበትና ዘመናዊ እርሻ የሚከናወንበት ቢሆንም ሁሉ ነገር ተመጥኖ እየተሰጣቸው ነው በራስ ሰርቶ መለወጥን የተማሩት። ይህ አስተዳደጋቸው በራስ ሰርቶ መለወጥን እንዲለምዱ ከማድረጉም በላይ በራስ መተማመናቸውን እንደገነባላቸው ይናገራሉ። በባህሪም ቢሆን የተሻሉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ዘመኑ ጎረቤት የሰፈር ልጅ የመቅጣትና የመቆጣት መብት ባለቤት ስለነበር ፤ በተሻለ ስነ ምግባር እንዲያድጉ የተሻለ እድል ፈትሮላቸዋል። ዛሬ በሚኖሩበት ስሜት ውስጥ እንዲሆኑም ይህ መሰረታቸው እንደነበር አጫውተውናል።
ብሔር እና ሀይማኖት የማይለይበት፤ ለሰው ልጅ ክብር የሚሰጥበት ፤ የአገር ፍቅር ከምንም በላይ እንደሆነ የሚነገርበት ዘመንን አለማስታወስ ከባድ ነው። ስለዚህም በጎረቤቶቻቸው ምክርና ተግሳጽ ልጅነቴን ሳስብ እነዚህ ነገሮች ፈጥነው ወደ አዕምሮዬ ይመጣሉም ይላሉ። የመምህሮቻቸው ጉዳይም የልጅነት ትውስታቸው እንደነበር ያወሳሉ። እነርሱ ለእርሳቸው የባህሪ አራቂ ነበሩ፤ የወደፊት ህልማቸው የስኬት ምንጭም እንዲሁ።
ከሁሉ በላይ ግን አልረሳውም የሚሉት ሁለት ነገሮችን ነው። የመጀመሪያው የባንድራ ማውጣትና ማውረዱ እንዲሁም የሚሰጠው ክብር ነው፤ ዛሬን ሲያዩ ግን እጅግ ያዝናሉ። እንደውም አንዳንዴ ‹‹ምነው ያ ጊዜ ዳግም በመጣ›› ያስብላቸዋል። ሁለተኛው አርፍደው የሚቀጡት ቅጣት ነው። ይህንን ለማስቆም የወሰዱት አማራጭ ደግሞ የበለጠ ብዙ ትዝታ የፈጠረባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ምክንያቱም በጠዋት ተነስተው ሲሄዱ መንገድ ላይ ጓደኝነት ይጠናከራል፤ ጨዋታው ይደምቃልና ነው።
በባህሪያቸው ሰፈር ውስጥና ትምህርት ቤት በጣም ይለያያሉ። በትምህርት ቤት ውስጥ ረባሽ የሚባሉ አይነት ልጅ ነበሩ ፤ በቤት ግን ከ11 በኋላ ውጪ የማይቆዩ ጨዋና ታዛዥ ልጅ ናቸው። በእችላለሁ ስሜት ሁሉን ለመስራት የሚጥሩም ነበሩ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አባታቸውና የእንጀራ እናታቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። እንጀራ እናታቸው ከእናት የማይለዩ ልጆቻቸውን በእኩል አይን የሚያዩ እንደሆኑም ይናገሩላቸዋል። በተለይ እናታቸው እርሳቸው ብቻ እንደሆኑ የሚያስቡ እናት መሆናቸውንም አጫውተውናል።
አባታቸውም ቢሆኑ ጥሩ ልጅ እንዲሆኑላቸው የማያደርጉት ነገር አልነበረም። እንደ ሀብታም ልጅ እንዲሞላቀቁ አይፈልጉም። ከዚያ ይልቅ ልክ እንደሰራተኛው በራሳቸው ጥረው ግረው ገንዘብ እንዲያገኙ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ያደርጓቸዋል።
ከአሰላ ሀሁ እስከ ሲዊዲንና ሀንጋሪ
መጀመሪያ በግቢያቸው ውስጥ በአካባቢው ከሚኖሩ ልጆች ጋር የቄስ ትምህርት የሚያስተምር መምህር ተቀጥሮላቸው ፊደልና ቁጥሮችን መቁጠር ጀመሩ። ከዚያ በዚያው ትንሽ ከቤታቸው ራቅ በሚለው ራስ ዳርጌ ትምህርት ቤት ገቡ። እስከ 12ኛ ክፍልም ያለውን ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በዚያው ነው ። በጣም ጎበዝ ግን ረባሽ ተማሪ ነበሩ። በዚህም ብዙ ጊዜ ይገረፉ እንደነበር አይረሱትም። በተለይ አንድ ቀን የሆነው ቤት ድረስ ደርሶ እንዲገረፉ እንደሚያደርጋቸው አምነው ሲፈሩ ሲቸሩ ነበር። ነገር ግን ጉብዝናቸው ሸፍኖት ሳይመቱ ቀሩ። ነገሩ እንዲህ ነበር የሆነው።
ወቅቱ ካርድ የተሰጠበት ጊዜ ሲሆን፤ ውጤታቸው ከትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ነበር። ነገር ግን በስነምግባራቸው ጥሩ ስላልነበሩ የወላጅ ምክር ያሻዋል ተብሎ ከግርጌ ተጽፎበታል። እንግዳችንም ያንን ካርድ ይዘው ወደ ቤት ነጎዱ። ቤት ሲደርሱም እህቶቻቸውንና እናታቸውን አባታቸው እንዳይገርፏቸው እንዲለምኑላቸው ተማጸኑአቸው። ምክንያቱም አባት አይደለም ቤት ውስጥ ሰፈርተኛው ሁሉ የሚፈራቸውና የሚከብራቸው ናቸው። ስለሆነም እንዴት አድርገው ውጤታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ግራ ገባቸው። በቅጽበት ‹‹ እስኪ ካርዱን አምጣ›› ተባሉም። ላብ አጠመቃቸው። ግን መስጠቱ ግድ ነውና አሳዩ። አባትም ‹‹በጣም ጎበዝ›› ብለው ሌላውን ትኩረት ሳይሰጡ መለሱላቸው። የዚያን ጊዜ ጮቤ ረገጡ። የሆነውንም ሲያስታውሱት ዛሬ ድረስ ያስቃቸዋል።
ባለታሪካችን በአሰላ በሚማሩበት ጊዜ መጀመሪያ ደረጃን ኢትዮጵያዊያንና ህንዳዊያን ፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ የሰላም ጓድ የሚባሉ መምህራን አስተምረዋቸዋል። በዚህም ከትምህርት በተጨማሪ በተለያየ ሙያ እንዲሰለጥኑ አግዘዋቸዋል። ለምሳሌ እርሳቸው በፎቶ ሙያ ብቁ ሆነው እንዲወጡ አስችለዋቸዋል። የተለያዩ ክበቦችም ስለነበሩ በተለይም የክርክር ክበቡ ላይ እንዲሳተፉ በማገዛቸው በራስ መተማመናቸውን ከማምጣቱም በላይ ጥሩ የእንግሊዘኛ ተናጋሪም አድርጓቸዋል።
የእንግዳችን የልጅነት ፍላጎት አንትሮፖሎጂስት መሆን ነበር። ታሪክን መመርመርና ማወቅም ህልማቸው ነው። ነገር ግን በእነርሱ ጊዜ የሚማረውን የሚወስነው አባት በመሆኑ የእርሳቸውን ሙያ ይዘው እንዲቀጥሉ አደረጓቸው። በዚህም የእርሻ ትምህርትን እንዲያጠኑ ሆኑ። መጀመሪያ ግን ወደ ትምህርት መስክ መረጣው ከመግባታቸው በፊት ከአባታቸው ነጻ ለመሆን በዚያው አቅራቢያ በመሄድ በሲዊዳዊያን በሚተዳደር ጭላሎ የእርሻ ልማት ድርጅት ውስጥ ተቀጠሩ። ብቃት ያለው ሰራተኛም ሆኑ። ይህ ደግሞ የነጻ የትምህርት እድልን አስገኘላቸው። ስለዚህም አገራቸውን ትተው ወደ ሲውዲን አቀኑ። በዚያም ‹‹ እንስታድ ›› የእርሻ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጥሩ ውጤት አጠናቀቁ።
በሲዊዲን ቆይታቸው የመጀመሪያው ጥቁር በመሆናቸው ብዙ ገጠመኞች አሏቸው። ጋዜጦች የሚዘግቡት በተለይ ሁልጊዜ የሚያስገርማቸው ነበር። እንደውም አንዱ የዘገበውን ሲያነሱ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአህጉርም ወካይ ሆነው ነበር። የታተመው እንዲህ ይላል። ‹‹ ሲውዲን የወደፊቱን የአፍሪቃ የእርሻ ሚኒስትር እያሰለጠነች ነው›› ከትልቅ ፎቷቸው ጋር በፊት ገጽ ላይ። ይህ ውክልና ሌላ የቤት ስራ እንደሆነባቸው አይረሱትም።
ከትምህርት በፊት በሲዊዲኖች ህግ የሁለት ዓመት የእርሻ ላይ ልምምድ ማድረግ ግዴታ ነው። በዚህም እንግዳችን ይህንን እንዲፈጽሙ ተነገራቸው። ነገር ግን ቀደም ብለው በአገራቸው ሲሰሩበት የነበረ ሰው ይህንን ስለነገራቸው ተዘጋጅተው ነበር። እናም በጭላሎና በወላይታ የእርሻ ልማት ድርጅት ላይ የሰሩት እንደልምድ ተወስዶላቸው ሁለት ዓመቱ ወደ ሰባት ወር ወረደላቸው። በዚህም ወደ ኮሌጁ ከመግባታቸው በፊት በቶላርፕ የእርሻ ሥራ ልምምዱን እንዲወስዱ ተደረገ። ከዚያም ሲጠናቀቅ ኮሌጅ ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አጠናቀቁ።
አገራቸው ተመልሰው ሲሰሩ እየሰሩ ሳለ ደግሞ ጋዜጣ ሲያነቡ በማህበራዊ እርሻ ሀንጋሪ የትምህርት እድል እንደምትሰጥ አወቁ። ደውለውም አረጋገጡ። ነገር ግን የምዝገባው ቀኑ አልፏል። ሆኖም የተመዘገበ ሰው አልነበረምና ማመልከት እንደሚችሉ ተነገራቸው። ጊዜ ሳይወስዱም እርሻ ሚኒስቴር ሄደው ጠየቁ። በወቅቱ ሶሻሊስት አገር ማንም ምርጫው አልነበረምና ሌሎች ላይ ቢሄዱ እንደሚሻላቸው ምርጫ ቀረበላቸው። ይሁን እንጂ እርሳቸው አልተቀበሉትም። ሀንጋሪ ሄደው መማር እንደሚፈልጉ ገለጹ። በዚህም በሀንጋሪ ‹‹ በካርል ማርክስ የኢኮኖሚክ ሳይንስ›› ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተማሩ። ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም ቢሆን በዚሁ በእርሻ ኢኮኖሚክስና የእርሻ ህብረት ስራ የትምህርት መስክ እንዲማሩ ሆኑ።
ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ሲማሩ ሁለት ፈታኝ ችግሮች እንደገጠሟቸው ያጫወቱን ባለታሪካችን፤ የመጀመሪያው መንግስት በመቀየሩ ምርምራቸውን ለመስራት አገራቸው መምጣት አለመቻላቸው ነበር። ሁለተኛው ደግሞ የአሁኑ መንግስት ካልደገፈህ ትምህርትህን አትቀጥልም መባላቸው ነበር። ሆኖም ዛሬ ድረስ ምስጋናቸውን የሚቸሯቸው የወቅቱ የእርሻ ሚኒስትር ዶክተር ጸጋአምላክ ወርቁ በፍጥነት መንግስት እንደሚደግፋቸውና ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጻፉላቸው። ስለዚህም በሀንጋሪ በጥሩ ውጤት ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እንዲያጠናቅቁ ሆኑ።
ከአርባ ዓመት በላይ በውጪ ለሥራ
የመጀመሪያ ሥራቸው የተጀመረው በአባታቸው ልምድ ሰጪነት ገና የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በጭላሎ የእርሻ ልማት ድርጅት ውስጥ ነው። እዚህ ድርጅት ውስጥ ለመግባት ብዙ ተፈትነዋል። ምክንያቱም በእነርሱ ጊዜ መቀጠር ልምድንና ብቃትን ይጠይቃል። ስለዚህም መጀመሪያ እየሰራህ ትታያለህ፤ ከዚያ ቃለመጠይቅ ይደረግልሀል ተባሉ። ተጠሩናም ለምን ድርጅቱን መቀላቀል እንደፈለጉ በእንግሊዝኛ ጽፈው እንዲመጡ ተነገራቸው። ይህንን አድርገው ሲመጡ ግን በወቅቱ አልታመኑም ነበር። ምክንያቱም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃታቸው ያስገርማል። በመሆኑም ሌላ ክፍል ወስደዋቸው ዳግም እንዲጽፉ አደረጓቸው። እርሳቸውም የበለጠ ጽፈው አስረከቡ። ይህ ሁኔታቸው የመሰጣቸው የድርጅቱ አስተዳደር እንዲቀጠሩ ወሰኑ። በድርጅቱ ዋና ሥራቸው ሹፍርና እና ማስተርጎም ሆነ።
እንግዳችን አልችልም የሚሉት ሥራ የለም። የተባሉትን በውጤትና በትጋት ይሰራሉ። እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ የማይረሱት ትዝታ አላቸው። ገበሬዎች ጋር ሄደው የሰሩት ሥራ በሪፖርት የሚቀርብበት ጊዜ በመቃረቡና አለቃው ቤተሰብ ችግር ደርሶበት በመሄዱ ሌሎች ቢሰሩም እርሳቸውም እንዲሰሩ ተነገራቸው። ሪፖርት ጽፈው ስለማያውቁ ግን ተጨንቀዋል። ሆኖም አልችልም የሚሉት ነገር አልነበረምና ወደ ጸሐፊዋ ሄደው የቀደመ ሪፖርት ጠየቁ። በርከት ያለ ዶሴም ተረከቡ። አዳራቸውን ሳይተኙ አንብበው በደንብ ተረዱ። ከዚያ መጻፍ ጀመሩ። በጥሩ ቋንቋና የአጻጻፍ ጥበብም አጠናቀቁት። ነገር ግን ለማ እንደሚያስረክቡት ስላላወቁ እጃቸው ላይ ሪፖርቱ ቆየ። በመጨረሻ ጸሐፊዋ ስጠይቃቸው ሁኔታውን አስረድተው ሰጧት።
ዶክተር ኔክቢ የሚባለው ሀላፊም በጥብቅ እንደሚፈልጋቸው ተነገራቸውና ወደ እርሱ አቀኑ። የአዩትንም ለማመን ተቸገሩ። ምክንያቱም እቅፍ አድርጎ አድናቆቱን ቸራቸው። ከሁሉም የተሻለ እንደጻፉም ገልጾላቸው። በዚህ ሳያበቃም ከዛሬ ጀምሮ 275 ብር 500 ብር እንደሚጨመርላቸውም ተነገራቸው። ነገር ግን የእርሻ ሚኒስቴር ሊፈቅድ ባለመቻሉ ቀረ። ይህ ሲሆን ደግሞ አለቃው የትምህርት እድል ሰጥተው እንደሚልኳቸው ቃል ገቡና ወደ ሲዊዲን ላኳቸው።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ዳግም ለሥራ ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን፤ በወላይታ ወላይታ የእርሻ ልማት ድርጅት ውስጥ በጀነራል ማናጀርነት ሲያገለግሉ ቆዩ። በዚህ ሥራቸው ወቅት ለአገራቸው ብዙ ነገር አበርክተዋል። የውጪው ሰራተኛ ለአገራቸው ያለውን አስተሳሰብ የለኩበትም ነበር። ከዚህ ውስጥ የተሰጣቸው አስተያየት በጣም አሳዝኗቸው የነበረው አንዱ ነው። ይህም ‹‹ መዝናኛ የለም፤ መዋኛ የለም፤ ቤትና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችም የሉም። ለምን እዚህ ትሰራለህ ይህ አቅም ኖሮህ›› የሚል ነበር። ነገር ግን እርሳቸው ‹‹ እንኳን አገሬ እና እናንተም አገር ሰርቻለሁ›› ማለታቸው እንዳስደሰታቸው አይረሱትም።
ከሀንጋሪ ትምህርት በኋላ ወደ አገራቸው አልተመለሱም። መመለስ ቢፈልጉም የወቅቱ ሥርዓት የፈለጉትን መስራት እንደማያስችላቸው ስላመኑ ወደ ሲውዲን አቀኑ። በዚያም በተለያዩ ቦታዎች ውስጥ ለስምንት ወር ያህል ሰሩ። ቀጥለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ተቀላቀሉና በተለያዩ ቢሮዎች ውስጥ ለ34 ዓመት ጡረታ እስኪወጡ ድረስ አገለገሉ። ከእነዚህ መካከልም በአለም ምግብና እርሻ ፤ በአለምአቀፍ ሰራተኞች ድርጅት፤ በአለም ሰላም ማስከበር ተልእኮ ያገለገሏቸው በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። 17 አገራት ላይ በመዘዋወር ነው በትጋት ሥራዎችን ያከናወኑት።
የቋንቋ ነገር
ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸውና ከሌላው የምትለይባቸው ነገሮች አንዱ የራሷ ቋንቋና ፊደል ያላት መሆኗ ነው። ነገር ግን ዜጋው ተቀብሎ እውነታውን ለማሳየት በጣሙን ሀፍረት እየያዘው እንደሆነ እንመለከታለን። ይህ የሚሆነውም በአገር ውስጥም በውጪም ነው። በአገር ውስጥ ያለው ከመከፋፈል ባሻገር ለሌላ አገር ቋንቋ ቅድሚያ መስጠት ላይ ያተኩራል። ለዚህም ማሳያው ሆቴሎቻችንን ጨምሮ በርካታ ስያሜዎች የሚወጡት ከ80 በላይ ባሉን ቋንቋዎች ሳይሆን በእንግሊዝኛ መሆኑ ነው።
የልጆቻችን ስምም ጭምር በዚያ ቢሆን እንመርጣለን። በማናውቀው ቋንቋ ልጆቻችንን እያናገርንም አገር ጠል እናደርጋቸዋለን። እንግሊዝኛ ሲናገር ጎበዝ አማርኛ ሲናገር ደግሞ ሰነፍ እያልንም አዕምሮውን በውጪ ፍቅር እንዲማረክ ያደርጉታል። ሌላው የሚያሳዝነው መንግስታዊ የሆኑ ተቋማት ሳይቀሩ የውጪውን ስያሜ ተሰጧቸው ማገልገላቸው ነው። ለምሳሌ ሲቪል ሰርቪስ። ‹‹ ሀገራዊ ቋንቋ አጥተንለት ነው ? ›› ሲሉ ይጠይቁና መልሰው ወደ ቀደመ ሀሳባቸው ይገባሉ። ይህም ይህ በውጪውም የቀጠለ እንደሆነ ይናገራሉ።
እርሳቸው አለምን እንደማጅላን ዞረዋል። ስለዚህም በተዘዋወሩበት ሁሉ ኢትዮጵያዊያንን ሳያገኙ አይሄዱም። በዚህም ያጋጠሟቸው ሰዎች ብዙዎቹ ከ80ዎቹ ቤተሰብ ከሚችለው ቋንቋ አንዱን እንኳን ማስለመድ ያልቻሉ ናቸው። እንደውም የልጆቹ ፍላጎት ቢኖርም ወላጅ የተወለደችው/ው/ እዚህ ምን ይሰራለታል ሲሉ የሚከራከሯቸውም እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ ቅኝ ያልተገዛች አገርን ቅኝ ከማስገዛት አይተናነስምም ይላሉ።
መሰልጠን የመሰላቸው ደግሞ ስልጣኔ የራስን በመተው እንዳልሆነ ማሰብ አለባቸውም ባይ ናቸው። ለዚህም እንደ አብነት የሚያነሱት የታንዛኒያውን ፕሬዚዳንት ኔሬሬን ነው። ቀደም ሲል የሚናገሩት እንግሊዝኛ ነበር። አሁንም ይናገራሉ። ነገር ግን አገሪቱ ነጻ እንደወጣች በተገዛንበት ቋንቋ ያደረጋችሁትን ስያሜ በሙሉ ወደ ኪስዋህሊ አፍ መፍቻ ቋንቋችን ቀይሩ ብለው አስተላለፉ፤ በ24 ሰዓት ውስጥም አደረጉት። ታዲያ እኛ ሳንገዛ ለምን ይህንን አደረግን? አገራችንን ጠላናት ማለት ይሆን ብለው ይጠይቁና መልሱን ለሚያደርጉት ልተወው ብለው ያቆማሉ።
ናይጄሪያዊያንን እወዳቸዋለሁ
ናይጄሪያዊያን መጀመሪያ ጓደኛ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው። ብዙ ያስለፋሉ። ሆኖም አንዴ ጓደኛ ካደረጉ ወንድሜ እንጂ ጓደኛዬ አይሉም። ለሚመጣ ችግር ሁሉ ቅድሚያ ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡም ናቸው። ወንድሜ ነው የሚሉትን በምንም መልኩ አያስነኩትም። ከእነርሱ የተሻለ እንዲያገኝ ይፈልጋሉ እንጂ።
በዚያ ላይ ሰልፍ ቦታ ላይ ሳይቀር ጥቁር ካየ ‹‹ወንድሜ ከነጮች ጋር ትቆማለህ እንዴ ና እዚህ ግባ›› ብሎ ቅድሚያ የሚሰጠው ለጥቁሩ ነው። እኛ አገር ግን ነጭ እንጂ ጥቁር ቦታ አያገኝም። በአፍሪካዊነታቸው በጣም የሚኮሩ ህዝቦች በመሆናቸውም አከብራቸዋለሁ። ይህ ደግሞ እኔ ካደኩበት ትውልድ ጋር በእጅጉ የሚቀራረብ ነው። የኖርኩበትን ህይወት ስለሚመልሱልኝ በጣሙን እወዳቸዋለሁ። ለዛሬው ትውልድም ትምህርት እንዲሆናቸው እፈልጋለሁ።
አሁን ትውልዱ የቀደመ ችግርን በጋራ የመወጣት ነገሩን ረስቷል። ጓደኛዬ ብሎ አብሮ ጠጥቶና አብሮ በልቶ ሲቆይ ደስተኛ ነው። ችግር ሲደርስበት ግን አላውቅህም ይለዋል። እናም የዛሬ ናይጄሪያዊያንን እያየን የትናንት የአባቶቻችንን ጀብዱ እናምጣ። ይህ ከሆነ ነጋችንምም ይስተካከላል ምክራቸው ነው።
ኢትዮጵያ ለእኔና ለእኛ
‹‹ኢትዮጵያ ልብ የሚሰብር ታሪክን ያስተናገደች አይደለችም። ከዚያ ይልቅ ታሪክ ሰሪ፤ ጀግንነትን አብሳሪ፣ በራስ መተማመንን ሰጪ፤ ቀና ብሎ መሄድን አስተማሪ ነች። ከማንም እንደማናንስ አረጋጋጭም ነች። ምክንያቱም የአባቶቻችን ገድል ጥቁርን ሁሉ ያስከበረ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያን የምወዳት ነጻነቷን ጠብቃ አስጠብቃ ለአፍሪካ ጭምር መኩሪያ በመሆኗ ነው ›› ይላሉ። ሰዎች ምንም ቢሏት እርሷ በእኔ ልብ ውስጥ ዘላለም ውብ ናት። ለዚህም ነው ውቧ ኢትዮጵያ ብዬ ስለእርሷ ለመተረክ የተነሳሁትም ብለውናል።
ጥላቻ ዘርቶ በችግሯ ከእርሷ መጠቀም የሚፈልጉ መጥፎውን ይናገሩታል። ለእኔና ለአገሬ ልጆች ግን እነርሱ የሚሏት ኢትዮጵያ የለችም። ምክንያቱም ለእኛ ኢትዮጵያ ደምም፣ አጥንትም ሥጋም ነች። ህይወት የሰጠች አገር ነች። እርሷ ከሌለች እኛ የማንኖር መሆኑን የምትነግረን አገር ነች። ስለዚህም ውቧን ኢትዮጵያ እንጂ ጥላቻ ያረገዘችውን ኢትዮጵያን አናውቃትም። እወቁ ሲሉንም አንቀበላችሁም ማለት አለብን። እኛ ውቧን አገር ነው መስበክ ያለብን። ለዚህም ነው ስለእርሷም እስከህይወቴ ፍጻሜ ስመሰክር የምኖረውም ብለውናል።
እንግዳችን ይህ እውነታቸው በተግባር የተጨበጠ ሥራ በመስራትም እንደሆነ ያሳዩ ናቸው። በአብነት የሚነሱት ‹‹ በአገር ልጅ›› በሚለው መፅሐፋቸው ስለኢትዮጵያ ያዩቱንና የሰሙትን እንዲሁም ያነበቡትን በእኔ ይብቃ ሳይሉ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስረክበው ትውልድ እንዲያነበው ማድረጋቸው አንዱ ነው። ሌላው በዞሩባቸው አገራት የተጠቀሙባቸውን ብሮችና ሳንቲሞች በሙሉ አንዳንድ ኮፒ በማምጣት በአልበም መልክ ትውልድ እንዲያውቃቸው ለማድረግ አሁንም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲቀመጥ አበርክተዋል። ይሁንና ይህንን ማድረጋቸውን የተረዳ አንድ የውጪ ዜጋ ከመቶ ሺህ ዶላር በላይ ልግዛህ ብሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
በእርሳቸው እምነት ግን ‹‹ከአገር የሚበልጥ ገንዘብ የለም›› ነውና አላደረጉትም። በጣም ሌላው አስገራሚ ሥራ የሰሩት ስለ አገራቸው ለመናገር የሄዱበት ርቀት ነው። በየአገሩ ሲዘዋወሩ አንባሳደሮቹ ስለ ኢትዮጵያ ብዙም የሚናገሩበት ግብዓት የላቸውም። እናም እርሳቸው አገራቸው በመምጣት ስምንት ጠቅላይ ግዛትን በመዘዋወር በካሜራቸው ባህልን፤ ትውፊትንና ታሪክን በማስቀረት አለም እንዲያውቃት በፎቶ ትልልቅ ስራዎችን አከናውነዋል።
በውጪው አለም ምሳ ሲበሉ ካገኘናቸው እስክጨርስ ጠብቀኝ እንጂ እንብላ አያውቁም፤ እኛ አገር ግን ተጨማሪ እንኳን ባይኖራቸው ‹‹ጥሩ ላይ ደረስክ ና እንብላ›› ይላሉ። ይህ የሌለበትን አለም ለምን እንደምናደንቅ አይገባኝም። ኢትዮጵያዊነታችንን የምናከብር ከሆነ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምር መልዕክታቸው ነው።
የህይወት ፍልስፍና
ስጸልይ ጀምሮ ‹‹ እግዚያብሔር ሆይ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አታድርገኝ›› እላለሁ። ምክንያቴ ደግሞ በማንም ላይ ጥገኛ ሆኖ መኖርን ስለማልፈልግ ነው የሚሉት ዶክተር ጌታቸው፤ ማንም ሰው ወደ ሥራ ቦታ ሲሄድ መጀመሪያ ራሱን እንዴት እንደሚለውጥ ማሰብ አለበት ብለው ያምናሉ። ከዚያ ሌሎችን እንዴት ልደግፍ ማለት ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ስለዚህም የህይወት ፍልስፍናቸው ራስን መለወጥና ለሌላ መኖር ፤ ለሰጠ መስጠት ያስፈልጋል ነው። አልችልም ሳይሆን እሞክረዋለሁ ማለትም መርሀቸው ነው። በሥራ ከሌሎች ልቆ መውጣትና የአገር አለኝታ መሆንም የህይወታቸው ፍልስፍና ነው።
”ጾም ነው‘ ያማል
በርካታ ገጠመኞች በውጪም በአገር ውስጥም ገጥሟቸዋል። ‹‹ ጾም ነው›› የተባለው ግን እጅጉን ያመማቸውና መኪናቸው ውስጥ ገብተው ያስለቀሳቸው እንደነበር አይረሱትም። ነገሩ እንዲህ ነው። የመኪና ጎማ ፈንድቶባቸው እየቀየሩ ሳለ በሸራ የተወጠረ ቤት ውስጥ የተቀመጠች አንዲት እናት ወጥታ ‹‹ ኑ ቡና ፈልቷል›› ስትል በኢትዮጵያዊነት ባህሏ ጠራቻቸው። እርሳቸው ቡና አይወዱም። አክብሮቷ ግን ገርሟቸው ወደ ውስጥ ይዘልቃሉ። ብዙም ሳይቆዩ ልጅቷን ሲያዩዋት መኪናቸው ውስጥ ብስኩት እንዳለ አስታውሰው ‹‹መጣሁ›› ብለው ይወጣሉ። ብስኩቱንም ይዘው ተመልሰው ለልጅቷ ይሰጧታል። ግን እናት ወዲያው ከእጇ ትነጥቅና ‹‹ ጾም ነው ነገ ትበይዋለሽ›› ትላታለች።
እንግዳችን በሁኔታው ይደናገጡና ‹‹ ለመሆኑ አምስት አመቷ ነው አላልሽኝም እንዴ›› ሲሉ ይጠይቃሉ። እርሷም ‹‹ አዎ ። ግን ነገ የማበላት ስለማላገኝ ጾም ነው ብዬ አልፋታለሁ። ጠዋትም እሰጣታለሁ›› አለቻቸው። እንባቸው አቀረረ፤ አነጋገሯ ልባቸውን ነካውም። ግን በእርሷ ፊት ማልቀስን አልፈለጉም። ኪሳቸው ውስጥ ያለውን ገንዘብ በሙሉ አውጥተው ከሰጧት በኋላ ወደመኪናቸው ገብተው ብሶታቸውን ተወጡ። ከዚያም በኋላ የማይረሷት ልጅ ሆነችላቸው። እናም አገራችን ላይ ብዙ የሚያስለቅሱ ታሪኮች አሉ። ብዙ ችግረኞችም ይታያሉ። ነገር ግን እኛ መች ከፍተን አየንላቸው። ብናያቸው ኖሮ ማንም አይራብም ነበር። ስለዚህ ለችግረኞች እኛ እንጂ ማንም መከታ አይሆናቸውምና እንያቸው መልዕክታቸው ነው።
መልዕክት
የመንግስት የመሬት አስተዳደር ሁኔታ ቢለወጥ የሚለው የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው። ለዚህም በምክንያትነት የሚያነሱት የሚኖርበት መሬት ሳይቀር የመንግስት መሆኑ ሁለት ችግሮችን አምጥቷል ብለው ስለሚያስቡ ነው። የመጀመሪያው አርሶአደሩ መሬቱ የአንተ ነው ብለው የማያወርሱት ልጅ በመፈጠሩ ጠንክሮ የሚያመርት ዜጋ እንዳይኖር አድርጓል የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው በተቆራረሰ መሬት ላይ አርሶአደሩ እንዲሰራ መደረጉ የማህበራዊ እርሻ መስፋፋቱን በመቀነስ አገር ችግር ውስጥ እንድትወድቅ ማድረጉ ነው።
መንግስት አርሶአደሩን በማህበራዊ እርሻ ማደራጀት ቢችል የኑሮ ውድነት በዚህ ደረጃ አገርን ባላተራመሰ ነበር። ዶላር ቢጨምር ጉዳያችን አይሆንም ነበር። ምክንያቱም የሚመረተው በአገር ስለሆነና በመሀል ደላላ ስለማይገባ ገዢው ምንም አይጎዳም። ሆኖም መንግስት በዘመናዊ መንገድ ገበሬው እንዲሰራ አለማገዙና በጅምር ደረጃ ማህበራዊ እርሻ ላይ መስራቱ ችግሩን አምጥቶታል። ስለሆነም ትራክተር ለመግዛት፣ ንግዱን ለመቆጣጠር፣ በመሀል የሚገባውን ደላላ ለማስቀረት፣ የራሳቸውን ነገር ለመገንባት ያስችላቸዋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ አገር በኢኮኖሚው ከማደጓም በላይ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሸጋገር ሁነኛ አማራጭ ያስገኛታልና አሁን ይህንን ማየት አለበት ሌላው መልዕክታቸው ነው።
ሌላው መልዕክታቸው እንደ አገር የሥራ ትልቅና ትንሽን መተውና የአዕምሮ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል። የክብር ጉዳይም ትኩረታችን ሊሆን አይገባም። ከዚያ ይልቅ በሥራ ልቆ ለመውጣት መስራት ሁነኛ መርሀችን ማድረግ አለብን። ለአገራችን ቅድሚያ መስጠትም የእያንዳንዳችን ድርሻ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም ዜጋው አገሩን ከጠላ ማንም ሊወድለት አይችልም። በብሔር ፣ በሀይማኖት መከፋፈላችንንም እንተው። ይህ ለሌላው አለም መጠቀሚያ እያደረገን ስለሆነ። አባቶቻችን ያስተማሩን አንድ ሆነን አገርን ማቆም ነው ኑ የአባቶቻችን ልጆች እንሁን የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም