ከትዝብት
አንዳንድ ነገረኞች ዕንቅልፍ ይሉትን አያውቁም። እጃቸው ረጅም ምላሳቸው ስል ነው። ድርጊታቸው ረቂቅ ሃሳባቸው እቡይ ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ የክፋት ክሮች ሥራቸው በዋዛ ይነቀል አይምሰላችሁ። አናታቸው ሲጎተት እግራቸው አፈር ይዞ ይወጣል። አፈሩ ደግሞ ገራምና ንጹሕ ነው። ዘር የሚፈራበት፣ ትውልድ የሚበቅልበት ለም አፈር።
ለም አፈር የሰጡትን ይቀበላል። ምርጥ ዘር ካገኘ ደግሞ ፍሬው የጎመራ ፣ ውጤቱ ያማረ ይሆናል። በእኔ እሳቤ የትውልዱም አዕምሮ ልክ እንደ አፈሩ ይመሰላል። ትውልድ መልካሙን ትርክት ይሰማል፣ መጥፎውንም ቀርጾ ይይዛል። እዚህ ላይ መልካም ገበሬውን የሚከተል ያተርፋል።
መቼም ሁላችንም ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በታሪካችን የሆነውን እውነት አንረሳም። አገር እርቃኗን እስክትቀር፣ ወገን በድህነት አስኪማቅቅ ፣አንገታችንን ደፍተናል። ህዝብ በተዋለበት ክፉ ድርጊት ከልብ ሲያዝን ሲያለቅስ ኖሯል። ግፍና መከራ የተቀበለበው ማንነቱ ቀጥና ባልተቆረጠች እስትንፋሱ ቢቆይም በማንነቱ በደልን ተሸክሞ ታሪኩ ሲጎድፍ፣ ህይወቱ ሲመር ኖሯል። ባሳለፍናቸው ዓመታት ወንበር የተቆናጠጡ ኃይላት ከቀኝ ኪስ ወደግራ ኪስ የማቀበል ያህል ስልጣንን እንዳሻቸው ሲያፈራርቁብን ቆይተዋል።
ወዳጆቼ! እውነት እላችኋለሁ እነዚህ ቡድኖች እጅግ ክፉዎች ነበሩ። ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሰበብና ምክንያት እየፈለጉ የብዙዎችን ህይወት ያወኩ፣ በዚህ ማንነታቸውም ከሌሎች ተጣብቀው ንጹሕ አዕምሮን ያቆሸሹ ክፉዎች ነበሩ። በእጅጉ የሚገርመው በዚህ የረከሰ ማንነታቸው ሞተው ከተቀበሩ በኋላ እንኳን እንዲንፈራገጡ መታሰቡ ነው።
አዎ! እነዚህ ክፉ እፉኝቶች ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ታውጆ፣ ወዳጅ ዘመድ አልቅሶ ቀብሯቸዋል፤ አፈርና ድንጋይ ተመልሶባቸውም የነበር። ታሪካቸው ሲወሳ ከርሟል። ዛሬም ግን ተላላኪ ቡችሎቻቸው በሙት ዘመዶቻቸው ሙት ታሪክ ላይ አሳፋሪውን ታሪክ ይዘሩት ጀም ረዋል።
በአውሮፓና አሜሪካ ያሉና የግፈኞቹን ሞት አምነው ያልተቀበሉ ጋጠወጦች ያን ክፉ ዘመን ለመመለስ የማይችሉበትን ፉከራና ቀረርቶ እያሰሙ መዘባበትን ሽተዋል። ዛሬም እንደትናንቱ አገር ቤት ከሚኖሩ ዘራፊ ቤተሰቦቻቸው የሀገር ሀብትና ገንዘብ እየተቦጨቀ ቢላክላቸው ይመኛሉ።
ለነገሩ ምን ያድርጉ! ‹‹ውሻ በበላበት ይጮሀል›› እንዲሉ ነው። ትናንት ከድሀዋ አገር እየተነጠቀ በሚሰጣቸው ዳረጎት ዘመናዊ ኑሮን ሲንፏለሉበት ቆይተዋል። ከምስኪኑ ህዝብ የላብ ወዝ እየጠረጉ ባዋጧቸው ወፍራም ጉርሻም በቁንጣን ሲጨነቁ ኖረዋል።
ወዳጆቼ ! ለእነሱ እኮ የቅንጦት ህይወት ብርቃቸው አልነበረም። ሲሻቸው በሚኖሩበት ቦታ፣ ሲፈልጋቸው ደግሞ በአገር ቤት ምድር ሀብትና ንብረት ሲያከማቹ ነበር። ምን ሲያከማቹ ሲቆልሉ ነበር እንጂ። ከእነሱ አልፎም ለሚቀጥለው ትውልዳቸው የሚተርፍ የሀብትና ዝና ማማ ላይ ለመድረስ በሩጫ ላይ እንደነበሩ ድፍን ዓለም ያውቀዋል።
ዛሬ የነበረው እንዳልነበር ሆኖ ‹‹ያዙኝ ልቀቁኝ›› ቢሉ አይደንቅም። በማያበራው ጩኸት ታግዘው ለአፍታ የማይገቱትን ስድብ ቢወረውሩም ልክ ናቸው። እርግጥ ነው! ተስፋ መቁረጥ አያደርገው የለም። ማንነትን ያስታል፤ አንደበትን ይቀይራል፣ ባስ ካለም ራስን እስከመግደል ያደርሳል።
ብዘዎች ስለነዚህ የእፉኝት ልጆች ድርጊት ሲያስቡ ከልብ ይስቃሉ። አሁንም የግፈኞቹን ጁንታዎች ትንሳኤ ማለማቸውና በቁም መቃዠታቸው ያስገርማቸዋል። እናም ባሻገር እያዩ እንዲህ ይሏቸዋል።
‹‹እናንት ርዥራዥ የእፉኝት ልጆች ሆይ ! ግፈኞቹ አባቶቻችሁ ከነክፉ ታሪኮቻቸው ሞተው እስከወዲያኛው ተቀብረዋል። ይህን እውነትም ልትረዱት ልታምኑት ይገባል›› ይሏቸዋል። ግን መስሚያ ጆሮ ያላቸው አይመስሉም።
ስሙኝማ ውዶቼ ! አሁን ከአገርቤት የሚጫን ከድሀው ህዝብ የሚዘረፍ ሀብት ንብረት የለም። ዛሬ ከእናንት የሚጠበቀው ነጠላ አሸርጣችሁ ፣ ፎጣ ጥላችሁ፣ ጸጉራችሁን መንጨት፣ ፊታችሁን መላጥ ብቻ ነው። ወይንም ደግሞ በአሜሪካ ጎዳናዎች ላይ የተቃውሞ ሰልፍ በሚል እንዳደረጋችሁት መሬት ላይ መንደባለል ነው ምርጫችሁ። ለምን ካላችሁም ለሙት የሚደረገው ወግና ስርዓት ይህ ስለሆነ።
‹‹አይይ ! በእውነት ከልብ ያሳዝናል…›› ልል ፈለግኩና መልሼ ዋጥኩት። እንዴ! ሆ !! ደግሞ ብዬ ብዬ ለእነሱ ልዘን? እንደው ለምዶብኝ እኮ ነው። ግን ግን ! ለአንዳንዶች ልካቸውን ማስታጠቅ ሳያስፈልግ አይቀርም። ‹‹ንገሩኝ ባይ›› አለች አክስቴ እውነቷን ነው። አዎ ! እናንሳው ካልን ደግሞ በደንብ እናንሳው። ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል አሉ። ስትነካኩን እኛም ሃጢያታችሁን መነካካታችን አይቀርም።
የዛሬን አያድርገውና ግፈኞቹ አባቶቻችሁ ብዙሀን ኢትዮጵያውያንን የደም ዕንባ ሲያስነቡ ኖረዋል። በድሀው ትከሻ እንደመዥገር ተጣብቀውም በወዙ ያፈራውን ንጹሕ ሀብት በመላና በዘዴ ሲዘርፉት ቆይተዋል። ሰብዓዊነቱን ነጥቀው ፣ታሪኩን አጉድፈው፣ እርስ በእርስ ሲያጣሉት ሲያናክሱትም ነበር።
አዎ ! ንገሩን ካላችሁማ በደንብ እንንገራችሁ። ዛሬ እናንተ አልሞቱም፣ አሉ እያላችሁ የምታላዝኑላቸው ግፈኞች እኮ ትናንት ከስልጣን ማማ ፊጥ ብለው ክፉ ታሪክ ሲዘሩ የሀሰት ትርክት ሲያራቡ ነበር።
እስቲ የሁላችሁም ህሊና የማይክደውን አንድ አውነት እናስታውሳችሁ። የማንም ባዕዳን እጅ፣ ሳይገባበት፣ የየትኛውም አገር ዕርዳታና ብድር ሳይታከልበት እውን የሆነውን የህዳሴ ግድብ ገንዘብ ማነው ቅርጥፍጥፍ አድርጎ የበላው ? እናንተ? ወይስ ህዝቡ ?
ህዝቡማ ከቤት ከጓዳው አጉድሎ ፣ከልጆቹ አፍ ነጥቆ፣ከገንዘብ ከደሞዙ ቆርጦ ስለ ሀገሩ ዋጋ ከፍሏል። ጉልት ቸርቻሪዋ እናት፣ቅጠል ሻጯ ሴት ፣ከጉያ ከመቀነቷ ሳታስቀር የእጇን አራግፋለች። ተማሪው ገበሬው፣ ወዝአደሩ፣ ሊስትሮው፣ ቀንሠራተኛው ፣ ምስኪን ድሀው ሁሉ ስለነገዋ ኢትዮጵያ ብርሃን ካለው አጉድሏል። ልብ በሉ ! የእናንተው ጉዶች ግን ለነዚህ ወገኖች ‹‹ቫምፓየሮች›› ነበሩ። ደማቸውን ሲመጡ፣ አጥንታቸውን ሲግጡ ኖረዋል። ዙምቢዎቹ ብሎ የሚጠራችሁ ማን ነበር? እውነትም ዙምቢዎች።
አሁንም ልብ በሉ የእናንተው ሙቶች ማር በተቀባ ምላሳቸው እየሸነገሉ ከደሞዝ ሲቆርጡ፣ ከመቀነት ሲፈቱ፣ ከጓዳ ሲቆርሱ፣ እፍረትና መሸማቀቅን አላወቁም። ከዓመት ዓመት በሚያቀርቡት የሐሰት ሪፖርትም በዓለም አደባባይ ስማቸውን ከፍ አድርጎ ለመስቀል ሮጠዋል። እመኑን፣ ታመኑን ሲሉም በመላው ህዝብ ህሊና ቀልደዋል።
እስቲ ዛሬ ወግ ደርሶን እንጠያየቅ። እንደሜቴክ ያለ ታላቅ ኩባንያን እርቃን አስቀርቶ አይሮፕላን ከመርከብ የሸጠ ፣ ገንዘቡን እንደዕቁብ ዕጣ የተካፈለ ማን ነው ? ‹‹ሙት ወቃሽ አያድርገኝና›› ዛሬ ‹‹እሪ፣ እዬዬ እያላችሁ የምታለቅሱላቸው የጁንታው ቡድን አባላት ነበሩ እኮ። ዋሸሁ እንዴ ?
አሁን ግን እወቁት። ዛሬ እንዲያ የቀለዱበት ታሪክ አልፎ በሌላ ታሪክ ተለውጧል። በሰፈሩበት ቁና ሊሰፍሩ ጊዜው ሆኖም ዕዳቸውን ይከፍሉ ይዘዋል። እናንተ ሀቁን አናምን አንቀበል ብትሉም ዕዳው የተከፈለው ሞተው በተቀበሩበት እውነት ስር ሆኗል። እስቲ አንከራከር። እነሆ ! ዛሬ በግፈኞች የመቃብር ሀውልት ላይ እንዲህ የሚል ታሪክ ጎልቶ መጻፉን ብዘዎች አንብበው አወቁ።
‹‹በዚህ መቃበር ውስጥ ህዝባቸውን የካዱ፣ ለዓመታት ወገናቸውን የገደሉ ፣አገርን የዘረፉ፣ ህዝብን ያበጣበጡ፣ ታሪክን ያዛቡ፣ የኢትዮጵያን ህልወና አሳልፈው የሰጡና የሸጡ፤ በደል የፈጸሙ፣ ዕንባና ደም ያፈሰሱ፤ የሰውን ዘር በጅምላ የገደሉና የቀበሩ ግፈኞች አርፈዋል። እነሆ ! በደላቸው በሞት ይከፈል ዘንድ ግድ ሆኖም እስከመጨረሻው በዚህ አሸልበዋል። በእነሱ ሞት ለኢትዮጵያ ህዝብ ትንሳኤ፣ ለተበዳዮች ብርሃን ሆኗል››
ይህን የመቃብር ላይ ጽሑፍ እሰከጫፉ አነበብኩት። የበደለኞች መጨረሻ የከፋ ሞት መሆኑን ይናገራል። ግፍ የተዋለባቸው ወገኖች ታሪክ እንደሚከፍላቸው፣ ጊዜ እንደሚበቀልላቸውም ይመሰክራል።
እናንተ ግን ይህን እውነት እያያችሁ ማመን አልቻላችሁም። ግፈኞቹ ወገኖቻችሁ ሥጋ ለብሰው፣ ነፍስ ዘርተው ይመጡ ዘንድ አፈራቸውን ልታራግፉ አጥማቸውን ልታቆሙ ሙከራ ላይ ናችሁ። ‹‹ አከከከ… አከከከከ ›› አለች ዶሮ ! የማይሞከር ሲሞከር፣ የማይታሰብ ሲታሰብ ምንታድርግ።
አይ! እናንተ በእጅጉ አሳዛናችሁኝ ‹‹ሙት ለሙት ያለቅሳል›› እንዲሉ ሆኖባችሁ እንጂ አሳፋሪው የወያኔ ህይወት ታሪክ ፣ ከግፍ መራሹ ሰርዓት ጋር እስከወዲያኛው መቀበሩን ልቦናችሁ ያውቃል። መጨረሻው ያላማረው የጁንታው ማንነት ዳግም ላይንሰራራም በኢትዮጵያ ህዝቦች ጥምር ክንድ ትልቀ ቋጥኝ ተጭኖበታል። እናም የመቃብር ላይ ድርሳናችሁን እያነበባችሁ የግፈኞቹ ሞት ዕውን መሆኑን እመኑ። አርስ በርስም ተማመኑ።
ሰሞኑን ደግሞ እዚያው ካለችሁበት የሰው አገር ምሽግ አዲስ ዜማ ለቃችሁ ማላዘን ይዛችኋል ‹‹ድንቄም›› አለች ሴትዬዋ ፤ ኢትዮያዊነትን ባነወራችሁበት አንደበት የዓድዋ ጉዳይ አሳስቧችሁ ‹‹የእኛና የእናንተን›› ስትጫወቱ አለማፈራችሁ። ጉዳችሁ የሚያልቀው መቼ ይሆን ?
እውነቱን እንውቀው ካላችሁ ደግሞ ዓድዋ በእናንተ ሰብዕና የሚገለጽ፣ በርጉም ምላሳችሁ ከንቱ ውዳሴ የሚገነባ አይደለም። ትውልድና ታሪክን ከማያከብር አንደበትም ቁምነገር ይሉት ታላቅነት አይጠበቅም። የተስፋ መቁረጣችሁ ጥግ ዓለም ያደነቀውን፣ መላውን ጥቁር አፍሪካ ያስከበረውን ወርቃማ ድል ‹‹አፈታሪክ›› አስባላችሁ።
እንደው እናንተዬ የኢትዮጵያውያንን አኩሪ ገድል እኮ ፈጽሞ እናንተ አትመሰክሩም። በኢትዮጵያውን ደም የተከፈለውን የዓድዋ እውነት እንካደው፣ እንርሳው ብትሉ እንኳን የቆማችሁበት ምድር ሳይቀር ያፌዝ፣ ይቀልድባችኋል። የሰማችሁ ሁሉ በንግግራችሁ ዝቅጠት ያፍር፣ ይሸማቀቅባችኋል። እኛስ ለእናንተ አፈርን።
እናንተ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ሆናችሁ ‹‹ጀግንነትን መዘከር አይቻልም›› ማለት ይዛችኋል። ይህን የሰማ ጆሮ ሁሉ ሆድ እንደባሳችሁ አውቆ አዘነላችሁ እንጂ ፈጽሞ አላዘነባችሁም። ሌብነትና ዝርፊያን፣ ሰው መግደልና ግፍን ከጀብዱ ቆጥራችሁ ‹‹ጀግንነት የእኛ ብቻ›› ስትሉም ድፍን ዓለም ሆዱን ይዞ ሳቀባችሁ።
የአለማፈራችሁ ጥግ የጁንታዎቻችሁን የመደበቂያ ዋሻ ድንቅ ታሪክ ከተፈጸመበት የጦር ሜዳ ውሎ ልታነጻጽሩት ሞከራችሁ። አሁንም ጉሯችሁ በከንቱ ጨኸት ነቃ እንጂ የሰማችሁ አልተገኘም።
መለስ ብላችሁ ደግሞ ያልከበራችሁበትን፣ ያልኮራችሁበትን ታሪክ ልትመዙ አሰባችሁ ወሬ አሳመርን ብላችሁም የዓድዋ ድል በእናንተና በእናንተ ተጋድሎ ብቻ መገኘቱን ለፈፋችሁ። ለነገሩ አይፈረድባችሁም። ይህን የሚያናግራችሁ የትንሽነትና የውርደታችሁ መነሻ ብቻ ነው።
አሁንም በአውሮፓና አሜሪካ ያላችሁ ተስፈኞች ከዳር ሆናችሁ ጦርነት ልታውጁ፣ ሰላም ልታደፈርሱ ትመኛላችሁ። በየቀኑ የምታላዝኑበት አይጨበጤ ህልም ግን ሁሌም ከቁም ቅዠት አያልፍም። ሞቶ የተቀበረው ስርዓትና ፣አፈር የለበሰው የጡት አባቶቻችሁ መንፈስ ፣ ዕንቅልፍ ነስቶ እያንገላታችሁ ነው።
አዎ! ውሻ በበላት ሊጮህ ፣ ግድ ነው። ጌታው ሲሞት ደግሞ በየቀኑ ማላዘኑ አዲስ አይደለም። የእናንተ ጩኸትና ለቅሶም በምስኪኑ ውሻ ድርጊት ይመሰላል። ትናንት ስትሰለቅጡ ስትውጡት የነበረ ቅባት ጠገብ ጉርሻ ነገ ላይ እንደማይኖር ስታውቁ ብትጮሁም አይፈረድባችሁም። መቼም እንደ ሰው ላባችሁን ጠብ አድርጋችሁ መኖር አታውቁበትም። መዝረፍ የለመደ እጅ መሥራትን ከወዴት አውቆ።
‹‹ነፍሳቸውን ይማረውና›› እነጁንትዬ በህይወት ሳሉ ብዙ መክረው ብዙም አቅደው ነበር። አዲስ አበባን ባግዳድ ሊያደርጉ፣ ህዝቡን በቦንብ ሊያጋዩ፣ አገር ሊያፈርሱና ሊያበጣብጡ። ይህ ውጥን ከዳር ሳይደርስ ግን መገኛቸው ከዋሻና ጉድጓድ ሆነ። በእርግጥ ሰብል አጥፊ ዓይጦች በጠገበ ሆዳቸው ራሳቸውን ሊከልሉ ከጉድጓድ ይመሽጋሉ። ያም ሆኖ ዕንቅልፍና ሰላም የላቸውም። የእነሱን በጉድጓድ መኖር የሚያውቁ አዳኞች ከገቡበት ገብተው አንቀው ያወጧቸዋል።
ይህን ሳስብ አንድ ገራሚ ነጥብ ትውስ አለኝ። ‹‹ማን ይቀብረኛል ብለህ አታስብ ሥራህ ይቀብርሀል›› ይሉት አባባል። የጁንታዎቹ መጨረሻም እንዲሁ ሆነ። ነፍስ አጥፍተው፣ አገር አውድመው የመሸጉበት ጉድጓድ ከባለንስር ዓይኖቹ አሳሾች አላዳናቸውም። እንደ አይጠመጎጦቹ ከተደበቁበት ወጥተው፣ ለፍርድና ለውርደት በቁ። ‹‹እምቢኝ›› ያሉትም ሥራቸው ከጉድጓድ አውጥቶ በአደባባይ ቀበራቸው።
እናንት የሰው አገር ቁራዎች አሁንስ የጁንታውን ሞት አመናችሁ ? ወይስ ሌላ መርዶ ነጋሪ ትሻላችሁ። እንደው ልፉ ቢላችሁ በከንቱ ድካም ዋጃችሁ እንጂ እውነቱን እኮ ታውቁታላችሁ። ይልቁንስ የሙት ቀን መታሰቢያቸውን ሳትዘነጉ ለነፍስ ይማሩ ተዘጋጁ። መቼም የክፉ ሰው ሞት ለኀዘን አይመችም። ቢሆንም ግን እኛ ለእናንተ መጽናናትን ተመኘን። እንግዲህ ፈጣሪ ያበርታችሁ ከማለት ወዲያ ምን ይባላል? ይኸው ከንፈር መጠናል። እንደዚህ ‹‹ምጽጽጽጽ …..››
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2013