በአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት ውስጥ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሥ አጼ ኃይለሥላሴ ሐውልት ሥራ ተጠናቆ ለምረቃ ዝግጁ ሆኗል። ንጉሡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) ምስረታም ሆነ የአፍሪካ ሃገራትና ህዝቦች ከቅኝ ግዛት ለመውጣት በተደረገው ትግል እንደ ኢትዮጵያ መሪነታቸው ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 25/1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ32 የአፍሪካ ሃገራት በአዲስ አበባ ሲመሰረት የአስተናጋጇ ሃገር መሪ አጼ ኃይለሥላሴ የመጀመሪያውን የድርጅቱን ጸሐፊ አቶ ክፍሌ ወዳጆን በመመደብ ከፍተኛ ሥራ እንዲከናወን ለማድረግ ችለዋል፡፡ የአፍሪካ ሃገራት የካዛብላንካና ሞኖሮቪያ በሚል በሁለት ቡድን ሲከፈሉ ወደ አንድ እንዲሰበሰቡና በጋራ እንዲቆሙም የንጉሡ ሚና እጅግ የላቀ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ያልወደቀች ሃገር በመሆኗ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት የጎላ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ በዚህ አስተዋጽኦ የአጼ ኃይለሥላሴ ሚና የጎላ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት መስክረዋል፡፡ ለዚህም ነው በህብረቱ ጽህፈት ቤት የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው የተደረገው፡፡ ባለታሪክን ማክበርና ሥራው በትውልድ እንዲዘከር ማድረግ ተገቢ ነውና ለንጉሡ የተደረገው ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ መልካም ለሠራ ለሥራው ክብርና እውቅና መስጠት ሌሎችም መልካም እንዲሠሩ ያበረታታልና፡፡
በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ ቡድኖች ልዩነት መሰረታዊ አለመሆኑ በጥናት በመለየት ወደ አንድ ማምጣት ባይቻል ኖሮ የአፍሪካ ሃገራት ከቅኝ ግዛት ለመውጣት የሚያደርጉትን ትግል ማሳካቱ ረጅም ጊዜ እና ከፍተኛ መስዋእትነት ይጠይቅ ነበር፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን የኢትዮጵያና የወቅቱ መሪዋ ሚና ከፍተኛ ነበርና ሰናይ ውጤት አስገኝቷል፡፡ የአፍሪካ ሃገራት ከቅኝ ግዛት መውጣት ችለዋል፡፡ አፍሪካ እንዲህ ያለ ትልቅ ሚና ለተጫወቱ የሃገራችን መሪ ሐውልት ለማቆም መወሰኑና መተግበሩ ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡
አፄ ኃይለሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለመመስረት ካደረጉት ጥረት በተጨማሪ ሃገራት ከቅኝ ግዛት ለመውጣት የሚያደርጉትን ትግል በቀጥታ በማገዝ ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ለነፃነት በተደረገው ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ትግልም እገዛቸው ላቅ ያለ ነበር፡፡
አፄ ኃይለሥላሴ የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም ቅኝ አገዛዝንና የዘር መድልዎን ከማውገዝ ጎን ለጎን ለነፃነት ተዋጊዎች ተጨባጭና ተግባራዊ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ይህ አቋም ከእሳቸው በኋላም በመንግሥታት መቀያየር ያልተለወጠና እስከአሁን ጸንቶ የቆየ ነው፡፡
ከእነዚህ ድጋፎች መካከል ለኬንያ ነፃነት ይታገል ለነበረው የማኦ ማኦ ንቅናቄ፣ ለደቡብ አፍሪካ የዘር መድልዎ ለማስወገድ ይታገል ለነበረው ለአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ፣ ዛምቢያና ዚምባብዌ ከቅኝ ግዛት ለመውጣት ያደረጉትን የትጥቅ ትግል ለማሳካት ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከመቋቋሙ በፊትም እ.አ.አ 1960 የደቡብ አፍሪካ አስተዳደር ናሚቢያን የሚያስተዳድረው ከኃላፊነቱ/ማንዴቱ/ ውጪ በመሆኑ ሃገራችን ተቃውማለች፡፡ የደቡብ አፍሪካ ህገ ወጥ ይዞታና የዘረኝነት ፖሊሲ እንዲወገዝና የናሚቢያ ህዝብ ነፃነቱን እንዲጎናጸፍ በዓለም ፍርድ ቤት ከላይበሪያ ጋር በመሆንም አቅርባለች፡፡ ይህ ክስ እኤአ 1966 ውድቅ ቢደረግም በ1967 ግን ተመድ ለደቡብ አፍሪካ የሰጠውን ኃላፊነት በማንሳት ደቡብ አፍሪካ የናሚቢያን ግዛት ለቃ እንድትወጣ አሳስቧል፡፡ በዚህ ተግባርም የአፄ ኃይለሥላሴ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡
በአጠቃላይ አፄ ኃይለሥላሴ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤና ንቅናቄ የአፍሪካ ህዝቦች ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡና ህብረት እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው በህብረቱ ጽህፈት ቤት ግቢ የመታሰቢያ ሐውልት መቆሙ ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011