አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች ልዩ ጣዕም በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ «ኢትዮጵያ፡- የጣዕም መገኛ» የሚለው ስያሜ መለያ ሆነ፡፡
በንግድና በቱሪዝም አማካኝነት የአገሪቱን የግብርና ምርቶች ልዩ ጣዕም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት በጋራ ሲንቀሳቀሱ የቆዩት የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲና ቱሪዝም ኢትዮጵያ «ኢትዮጵያ፡- የጣዕም መገኛ» የሚል ስያሜ የተሰጠውን መለያ በትናንትናው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡ ስያሜው «መገኛ» ከሚለው ከዋናው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መለያ ምልክት የተገኘ ሲሆን፤ አገሪቱ የግብርና ምርቶች ተለይተው የሚታወቁበት ዓለም አቀፍ ምልክት ሆኖ እንዲያገለግልም ሁለቱ አካላት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ ወቅት የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ካሊድ ቦምባ እንደተናገሩት፤ መለያ ምልክቱ የአገሪቱ የግብርና ምርቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲጨመርና የወጪ ንግዱንም በማስፋፋት ረገድ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ለኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባአሻገር ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ስሟ ከፍ ብሎ በበጎ እንዲነሳ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው፡፡ በተጨማሪም መለያው በአነስተኛ ማሳ ላይ ተሰማራውን አርሶ አደር ከሃገር ውስጥና ከዓለም አቀፉ የአቅርቦት ሰንሰለት ጋር ለማስተሳሰር ያግዛል፡፡
«ይህም የሃገሪቱ የግብርና ትራንስፎርሜሽን የህዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማሳያ ነው» ብለዋል፡፡
በቱሪዝም ኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱን የተፈራረሙት ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ሌንሳ መኮንን በበኩላቸው፤ በቱሪዝምም ሆነ በንግድና ኢንቨስትመንት ምርቶችን ዓለም አቀፍ መለያ ምልክት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ ሃገሪቱ የበርካታ አስደናቂ ነገሮች መገኛ መሆኗን ለዓለም ህዝብ ለማስተዋወቅ መንገድ ከፋች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ምርቶቹን ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ የሚውለው አዲሱ ዓለም አቀፍ መለያ ምልክት በሁሉም ዋና ዋና የግብርና ውጤቶች ላይ ቀጣይነት ባለው መንገድ በቋሚነት እንዲያገለግል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ በጀርመን፣ በቻይናና በግብፅ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የንግድ ዓውደ ርዕዮች ተሞክሮ በገዥዎችና በጎብኝዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትንና ዕውቅናን አግኝቷል፡፡ ዘንድሮም ኢትዮጵያ ከ120 በላይ በሚሆኑ አምራች ድርጅቶች በምትወከልበትና በቀጣይ ሳምንት ከየካቲት 10 እስከ 13 2011 ዓ.ም በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ዱባይ ላይ በሚካሄደው የገልፍ ፉድ ዓለም አቀፍ የንግድ ዓውደ ርዕይ ላይ «ኢትዮጵያ፡- የጣዕም መገኛ» የኢትዮጵያ ምርቶች ልዩ መታወቂያ ምልክት ሆኖ ይቀርባል፡፡
«ኢትዮጵያ፡- የጣዕም መገኛ» የሚለው የመለያ ስያሜ በሃገር ደረጃ ቱሪዝምን ለማስተዋወቅ ቀደም ሲል ይፋ ከሆነው ‹‹ኢትዮጵያ፡- ምድረ ቀደምት›› የሚለውን ስያሜ መሰረት ያደረገ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ይበል ካሳ