አዲስ አበባ፡- የአህጉሪቱን የሳይበር ደህንነት ተግዳሮቶችን ለመከላከል የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች ቡድን በማቋቋም ላይ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማትና ኤነርጂ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር አቡዛይድ አማኒ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት፤ የሚቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን በሳይበር ደህንነትና ሳይበር ጥቃቶች ዙሪያ የሚያማክር ይሆናል፡፡ በዓለም ላይ ከሳይበር ጋር ግንኙነት ያላቸው ምርጥ ተሞክሮዎችንም እየቀመረ ለኮሚሽኑ ያቀርባል፡፡
የሳይበር ጥቃት መከላከል የሚያስችሉ ህጎች መውጣታቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሯ፤ 42 የአፍሪካ ሀገራት ህጉን ለመተግበር መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም የመረጃ አጠባበቅና ቁልፍ የኢንተርኔት መሰረተ ልማት ደህንነት ዙሪያ መመሪያዎችን አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሯ፤ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ከሳይበር ጋር ተያያዥ የሆኑ ፈተናዎችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነሯ ማብራሪያ፤ አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግል መረጃ አጠባበቅ፤ ህዝቡ በሳይበር ላይ ያለውን አመኔታ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራትን በማከናወን፤ እንዲሁም በመላ አህጉሪቱ የሳይበር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም በማጎልበት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ነው፡፡
የአፍሪካ ሀገራትም የሳይበር ክህሎትና የሳይበር መሰረተ ልማት ዙሪያ በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሟቸውም ቢሆን የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል ያላቸው ፍላጎት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መጥቷል ያሉት ዶክተር አቡዛይድ አማኒ፤ ሀገራቱ የጀመሩትን ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር አቡዛይድ አማኒ ገለጻ፤ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገት ሌለው አማራጭ ነው፡፡ በመሆኑም የሳይበር አጠቃቀም ባህልን ማጎልበትና በሳይበር ላይ ማህበረሰቡ ያለው አመኔታ እንዲያድግ መሥራት ለነገ የማይባል ነው፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በአህጉሪቱ የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ቁጥርና ቴክኖሎጂ ነክ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በአስር እጥፍ ጨምሯል ያሉት ኮሚሽነሯ፤ በአሁኑ ወቅት በአህጉሪቱ ከ200 በላይ የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች መኖራቸውን በመግለጽ አፍሪካ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዲጂታላይዜሽንና ፈጠራ ሊኖራት የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ አመራር መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
መላኩ ኤሮሴ