አዲስ አበባ፡- አርሶ አደሩ ባመረተው ምርት በገበያ ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆንና የመደራደር አቅሙን ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ደግሞ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገለጸ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ፣ 6ኛው አገር አቀፍ የህብረት ሥራ ኤግዚቢሽንና ባዛርን ትናንት ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ መንግሥት በግብርና ምርት ግብይቱ ላይ የሚታየውን የተወሳሰበና ፍትሐዊነት የጎደለው አሠራር ከህገወጥ የግብርና ምርቶችን ግዥ ችግር ጋር አጣምሮ መፍታት የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት አርሶአደሩ ባመረተው ምርት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን የተለየዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የአምራች አርሶአደሩ የግብርና ምርት ለመጨረሻ ተጠቃሚው ሸማች ህብረተሰብ የሚደርስበትን የተንዛዛ ሰንሰለት በማሳጠር አርሶ አደሩና ሸማቹ ትክክለኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎች ቢከናወኑም በተጨባጭ የአርሶአደሩን ህይወት በመቀየር ረገድ ብዙ ርቀት መሄድ አለመቻሉን አስገንዝበዋል፡፡
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትና እቅዶችን ተናቦ በመሥራት ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ በሚኒስቴሩ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የህብረት ሥራ ማህበራት የሃገር ብልጽግና ማረጋገጫ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገትን ማሳኪያ ዋነኛ አማራጮች መሆናቸው ሊሰመርበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ «በመሆኑም ሁሉም የአገሪቱ ህብረት ሥራ ማህበራት ከጠባቂነት መንፈስ በመላቀቅ የአባሎቻቸውን የላቀ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለአገር ሰላምና ብልጽግና የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል» ብለዋል፡፡ የዘርፉ አቅም ገንቢ አካላትም ለዚህ ስኬት ከዚህ ቀደም ከሚያደርጉት ድጋፍ በተለየ ሁኔታ የማህበራቱን ውጤታማነት የሚያሳድግ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው፤ ማህበራቱ መንግሥት የፈጠረውን ምቹ የፖሊሲ ምህዳር አሟጦ በመጠቀም የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ኤጀንሲው ይህንን የዕድገት ብልጭታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያስችለው ዘንድ የጋራ የትኩረት መስኮችን ከፌዴራል ጀምሮ በተዋረድ ያሉ የህብረት ሥራ ማስፋፊያ አካላት ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ኡስማን ማብራሪያ፤ ማህበራቱ የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ቀጣይነት እንዲረጋገጥ፥ የአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የቅድመ ድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ባህል እንዲጎለብት እንዲሁም በገበያ የመደራደር አቅሙን ለማሳደግ በዚህም ሀገራዊ ዕድገት እንዲሻሻል ባደረጉት ጥረት ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ በማህበራዊ ልማት ዘርፍም ሸማቹን ካላስፈላጊ የኑሮ ውድነት ከመታደጋቸው በተጨማሪ የባህል የምርትና የማህበራዊ ግንኙነት ትስስር እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
ኤጀንሲው ለዚህ ዓላማ ከነደፋቸው የማስፈፀሚያ ስልቶች መካከል አገር አቀፉ ኤግዚቢሽንና ባዛር አንዱ መሆኑን አቶ ኡስማን ጠቅሰው፤ የዘንድሮው ኤግዚቢሽንና ባዛርም ዋና ዓላማም ማህበራቱንና ሌሎች የግብይት ተዋናዮችን ገፅ ለገፅ በማገናኘት ቀጣይነት ያለው የግብይት ትስስር እንዲፈጥሩ ማስቻል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም የግብይት ስርዓቱን አዘምኖ የማህበራቱን ምርቶች ለሸማቾች ከማሳወቅ ባለፈ በብዛት፥ በጥራትና በተመጠጣኝ ዋጋ በማቅረብ የአምራችና የሸማቹን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የማጠናከር ሚና እንፈደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
የኤጀንሲው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የህብረት ሥራ ማህበራት ግብይት ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 1 እስከ 6 በሚካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛር ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ 225 የህብረት ሥራ ማህበራት ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ለግብይት አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ማህሌት አብዱል