አዲስ አበባ፦ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማናቸውም ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት፣ በጊዜ የሚፈቱትን ፈጥኖ መፍታት፣ በሂደት የሚፈቱት ላይ ቀነ ገደብ በማስቀመጥና ግልጽነት በመፍጠር የሚከሰቱ አለመረጋጋቶችን መቀነስ እንዲሰሩ ተጠየቀ፡፡
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አሊ ሁሴን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስጠበቅ ግልጽነት፣ አሳታፊ የሆነ ስርዓት መዘርጋት፣ ተማሪዎችን የመፍትሄ አካል ማድረግና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በጋራ መስራት ይገባል፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ግልጽ የግንኙነት መስመር በመዘርጋት ተማሪዎችን የመፍትሄ አካል ማድረግ ከተቻለ ችግሮች ቢኖሩም ምላሽ እስኪገኝ እንዲታገሱና ከድንጋይ ውርወራ እንዲቆጠቡ ያደርጋል፡፡
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በሰላም ማስቀጠል የተቻለው፤ ግልጽነትና አሳታፊ ስርዓት መዘርጋት በመቻሉ መሆኑን ጠቁመው፤ ተማሪዎች እንዲያውቁ የሚገባቸው ጉዳዮችን ማሳወቅ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ በጎ ተጽእኖ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ሁሴን፤ ማህበረሰቡ ለአጥፊ ተማሪዎች ከለላ የማይሰጥ፣ ጥሩ ተማሪዎችን የሚያበረታታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ በሰመራዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡ ለአጥፊዎች ከለላ የማይሰጥ ሲሆን፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ለተገኙ ተማሪዎች ፍቅር የሚለግሱ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
መምህራንን በመልካም ስነ ምግባር በማነጽ ከፍተኛ ሚና ይወጣሉ ያሉት አቶ አሊ፤ ተማሪዎችና መምህራን መልካም ግንኙነት እንዳላቸው፣ የአስተዳደር ሰራተኞችም ኃላፊነታቸውን ባግባቡ የሚወጡበት ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡ ለተማሪዎች ፍትሃዊ አገልግሎት እንደሚያቀርቡ፣ በብሄር፣ በሃይማኖትና በአካባቢ ሳይለያዩ እንደሚያገለግሉ ጠቁመዋል፡፡
አድሎአዊ አሰራሮችን የመከላከል ስራዎች እንደሚሰሩና፤ ካፍቴሪያ ወይም ሌሎች አገልግሎት መስጫ ላይ ፍትሃዊነት ከተጓደለ ለረብሻ መነሻ ስለሚሆን ጥንቃቄ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ማስጠበቅ እንዲቻል የጊቢው አመራር፣ መምህራንና ሰራተ ኞች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የአካባቢው ጸጥታ አካላት፣ ታዋቂ ሰዎች የሃይማኖት አባቶች ሚና ወሳኝነት እንዳለው በመጠቆምም፤ የሃይማኖት አባቶች በየቤተ ዕምነቶቹ ስለ መቻቻል፣ ስለ ሰላም እና ተማሪዎቹ የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲመለሱ የማድረግ ሚና እንዲጫወቱ መክረዋል፡፡
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት መጥተው በአንድ ማዕድ ዕውቀት የሚገበያዩበት መድረክ መሆኑን በመጠቆምም፤ የየራሳቸውን ባህል፣ ዕምነት፣ ወግና ሌሎች ልዩነቶችን ይዘው የመጡ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይቸው እንደ አንድ ቤተሰብ በመተባበር ዓላማቸውን እንዲያሳኩ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎቹ ዕርስ በእርስ የሚተዋወቁበት የባህል ቡድን፣ የባህል ማዕከልና አልባሳት አላቸው፡፡
ይህ ተማሪዎቹ እንዲፋቀሩ፣ እንዲከባበሩና ተቻችለው እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን የግቢ ህይወት ለመፍጠር እንደተቻለም ነው አቶ አሊ የጠቆሙት፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ዘላለም ግዛው