አዲስ አበባ፦ ግብር የሁሉም ህብረተሰብ ጉዳይ መሆኑን ማህበረሰቡ እንዲያውቅና የተለያዩ የባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ በታህሳስ ወር የተጀመረው የግብር ንቅናቄ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የተጀመረውን የግብር ንቅናቄ አጠናክሮ ለመቀጠልና በንቅናቄውም ውጤት ለማስመዝገብ የተለያዩ ዝግጅቶች መሰናዳታቸውን ተናግረዋል። የግብር ንቅናቄው ከተጀመረ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም ህብረተሰቡ ግብር የኛ ጉዳይ ነው በሚል አስተሳሰብ አጀንዳው አድርጎ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትብብር እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
እንደሳቸው ማብራሪያ ወደ ንቅናቄው የተገባው ተቋሙን ለማስተዋወቅ ሳይሆን፤ ማህበረሰቡ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታው መሆኑን ተረድቶ ኃላፊነቱን እንዲወጣና ሀገርም እንደ ሀገር እንድትቀጥል ብሎም ጠንካራ መንግስት እንዲኖረን ለማስቻል መሆኑን በመግለፅ፤ ንቅናቄው በአማራና በትግራይ ክልል ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በቀጣይም በደቡብ ክልል በሀዋሳ ከተማ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ሩጫ በማካሄድ የተለያዩ የግብር መልዕክቶች እንደሚተላለፉ ተናግረዋል።
የተጀመረው ንቅናቄ ለግብር ከፋዩ ጥሪ ለማቅረብ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በግብር ስርዓት ውስጥ ያልተካተተው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ስርዓቱ የሚገባበት አጋጣሚ ጭምር በመሆኑ ሊጠቀምበት ይገባልም ብለዋል። በሀገሪቷ ግብር መክፈል ከሚገባቸው መካከል 60 በመቶ ያህሉ ብቻ ግብራቸውን በአግባቡ ሲከፍሉ ቀሪዎቹ 40 በመቶ የሚሆኑት ግን ከግብር ስርዓቱ ውጭ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አሁን የሚደረገው ንቅናቄ ግብር የመክፈል ጉዳይን የህብረተሰቡ ጉዳይ በማድረግ ግብር የሚያጭበረብሩትን ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገቡ በማስቻል፤ ግብር የሚደብቁትም ከህዝቡ ዓይን መሰወር እንደማይችሉ በማመን የህብረተሰቡን ትብብር ለማስቀጠል ነው ያሉት፡፡
ደግሞ ወይዘሮ ምህረት ምናስብ የአቅም ግንባታና የሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ናቸው። በተለይም ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ሀገሪቷ ማግኘት የሚገባትን 70 ቢሊዮን ብር አጥታለች። ይህም መክፈል የሚገባቸው አካላት ባለመክፈላቸውና ግብር ሰብሳቢው አካልም በአግባቡ ባለመሰብሰቡ እንዲሁም ህብረተሰቡም ጠያቂ ባለመሆኑ ምክንያት የመጣ ኪሳራ መሆኑን አብራርተዋል።
የተጀመረው ንቅናቄ ለአንድ ዓመት የሚቀጥል ሲሆን፤ ንቅናቄው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ለማስቻል ከየካቲት 9 እስከ የካቲት 30 ቀን ድረስ ባሉት ተከታታይ ቀናት ስለግብር የሚተላለፉ የተለያዩ መልዕክቶች ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ በማድረግ ግንዛቤ ይፈጠራልም ተብሏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ፍሬህይወት አወቀ