ማህሌት አብዱል
በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር ናቸው። በጥንካሬያቸውና በታታሪነታቸው የሚታወቁት እኚሁ ተመራማሪ ታሪክና ተሞክሮ በጊዜው የነበረውን ዘልማድ የቀየረ እንደሆነ ይነሣል። በተለይም የራስን ምርጫና የሥራ ዓለም በመተው ቅድሚያ ለቤተሠብ የሚለውንና የተፈጥሮ ሣይንስ ዘርፍን ለወንዶች የሚያስቀድመውን ዘልማድ የተሻገሩ ብርቱ ሴት ስለመሆናቸው የሚያውቋቸው ይመሠክራሉ።
አራት ልጆች ካሏቸው ቤተሠቦቿ የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ መኮንን በአሰላ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፤ በአባታቸው የፖሊስ መኮንነት ሙያ ምክንያት በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ለማደግ ተገደዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ እና በጎጃም ፍኖተ ሠላም ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት።
ለሣይንስ ትምህርት ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው እኚሁ ብርቱ ሴት ከክፍላቸው ከፍተኛውን ውጤት በማዝመዝገብ የተማሪዎች ሁሉ ቁንጮ እንደነበሩ ይጠቀሣል። በዚሁም ምክንያት ገና በ16 ዓመታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለመቀላቀል ችለዋል። የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሣሉም በጊዜው የነበረውን የመንግሥት ዕድገት በሕብረት ዘመቻ ተቀላቅለዋል። በትውልድ ቦታቸው ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ውስጥ የተመደቡ ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሥነ ሕይወት ትምህርት በማስተማር ለወገናቸው ያላቸውን አለኝታነት አሥመስክረዋል። ከዘመቻው መጠናቀቅ በኋላም በጊዜው በነበረው የፖለቲካ ትኩሣት ምክንያት ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም። በመሆኑም አራት ዓመታትን ይፈጅ የነበረውን ትምህርት በሰባት ዓመታት ለማጠናቀቅ ተገደዱ።
የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በረዳት መምህርነት በተማሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማስተማር ሥራ ቆዩ። በመቀጠልም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዚኦሎጂ የትምህርት ዘርፍ ከመጀመሪያዎቹ መካከል በመሆን በድህረ ምረቃ ፕሮግራሙ የመጀመሪያዋ ሴት ተመራቂ በመሆን በ1980 አጠናቀቁ። በማስከተልም ጀርመን ሃገር ወደሚገኘው ሐይደልበርግ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በፊዚዮሎጂ ትምህርት ዘርፍ በተለይም የሆርሞኖች ሥነ ሕይወት ላይ በማተኮር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ማግኘት ቻሉ። ወደሃገራቸው በመመለስም ሥነ ህይወት ትምህርት ክፍል ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰር በመሆን ሥራቸውን የቀጠሉት እኚሁ ሴት ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ከዚያም በጥር 2009 ሙሉ ፕሮፌሰር ማዕረግን ለመቀዳጀት በቅተዋል።
ከማስተማርና የምርምር ሥራቸው በተጨማሪም የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የአክሊሉ ለማ ፓቶባዮሎጂ ተቋም ዳይሬክተር እንዲሁም የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ የሥነ -ፆታ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሴቶች ሣይንስና ቴክኖሎጂ ማህበረሰብ እንዲጠነሰስም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይጠቀሣል።
ከ40 ዓመታት በላይ በመምህርነትና በምርምር ሥራ ያገለገሉት እኚሁ ሴት በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ በሥነ ሕይወት ክፍል እየሠሩ ይገኛሉ። ቤተሠብ መሥርተው ልጆች ወልደዋል፤ የልጅ ልጆችንም አይተዋል፤ ብዙዎችን በማስተማር ለቁም ነገርም አብቅተዋል። የተለያዩ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን በመሥራት ያሣተሙ ናቸው። ደከመኝና አቃተኝ የማያውቁት እኚሁ ተመራማሪ በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች አርዓያ በመሆናቸው እኛም በዓመታዊው የሴቶች ቀን እንግዳ አድርገን አቅርበናቸዋል። ከፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ መኮንን ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን:- አሁን ለደረሱበት የሥኬት ደረጃ መንገድዎን ያሣዮት ማን እንደሆነ ይጥቀሱልንና ውይይታችንን እንጀምር?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:- ለእኔ ሥኬት ምክንያት ቤተሠቦቼ ናቸው። መሠረታዊ ነገር አቅርበው በጊዜ ወደ ትምህርት ቤት ስለላኩኝ ነው አሁን የደረስኩበት ደረጃ መድረስ የቻልኩት። በችግር አላደግኩም። አባቴም የተማረ ሰው ነበር። በእርግጥ መጀመሪያ ፊደል እንድቆጥር ያደረጉኝ አያቴ ናቸው። ስለዚህ የእኔ የሥኬት እና የከፍታ ምክንያት የሆኑት ቤተሠቦቼ ናቸው። ምሥጋናም የማቀርበው ለቤተሠቦቼ ነው። ለሥኬቴ ምክንያት አባትና እናቴ ዋናውን ሥፍራ የሚይዙ ናቸው። በመቀጠልም አያቴም ባለውለታዬ ነው። አያቴ ጊዜ ሣያልፍ ፊደል እንድቆጥር በማሠብ ወደ ትምህርት ቤት ልኮኛል።
አዲስ ዘመን:- ባለፉት የህይወት ጉዞዎ የሚያነሱት የህይወት ውጣ ውረዶች እና በአስቸጋሪነቱ የሚያስታውሱት ፈተና ካለ ቢጠቅሱልን?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:- ከልጅነት ጀምሬ በትምህርት ዓለም ነው ያለፍኩት። በመቀጠልም ረጅም ጊዜ የቆየሁት በማስተማር ሥራ ላይ ነው። በርግጥ በእዚህ ውስጥ ሣልፍ ችግሮች አላገጠሙኝም ማለት አይደለም። ለምሣሌ ብጠቅስ የመጀመሪያ ዲግሪዬን እንደያዝኩኝ ወዲያው ልጅ ወልጃለሁ፤ ሁለተኛ ዲግሪዬንም ቢሆን ልጅ ወልጄ እያሣደግኩኝ ነው የተማርኩት። ይህም በራሱ በትምህርቱ ላይ የሚያሣድረው ተፅዕኖ ይኖራል። የእኔ ፍላጎት የማስተማር እና የመመራመር ስለነበር ይህንን አብሮ ለማስኬድና ለማጣጣም የሚከፈለው ዋጋ ቀላል አይደለም። አንዱም እንዳይጎድልና የምፈልገው ደረጃ ለመድረስ የነበረው ፈተና እንደተግዳሮት ሊታይ ይችላል። እንደማንኛው ሴት ልጆች እያሣደጉ፣ ቤተሠብ እየመሩ መማርም ሆነ በሥራ ከወንዱ ጋር ተወዳዳሪ መሆን ከባድ ነው።
ሦስተኛ ዲግሪዬን ለመማርም ወደ ምዕራብ ጀርመን ልጆች ትቼ ነው የተጓዝኩት። እንደእናት ከልጆች አጠገብ መለየት ያሣቅቃል። የሚፈጥረውም ጫና ይኖራል። ነገር ግን አጠቃላይ ውጤቱ ሲታይ ያስደስታል። በሕይወት ውስጥ ይኼንን ሁሉ ለማለፍ ታዲያ በአስተዋይነት የተሞላ አካሄድ መጓዝን ይጠይቃል። እኔ በእዚህ ዓይነት መንገድ ነው አሁንም በፊትም እየተራመድኩኝ ያለሁት። ይኼ ለምን ሆነ ብዬም ልጠይቅ አልችልም። ምክንያቱም ሕይወት እንደዚያ ነው ልትሆን የምትችለው። ሁል ጊዜ ቀጥ ብሎ የሚኬድ የሕይወት ጉዞ ካለ ያስደንቀኛል። ውጣ ውረድ እንደሚኖር እሙን ነው። በመሆኑም ሁሉም ሰው ከሥኬቱ ጫፍ መድረስ ከፈለገ የሚያጋጥሙትን የሕይወት ፈተናዎች በፅናት ማለፍ ይጠበቅበታል። ይሁንና ችግር ቢያጋጥምም ምንም አይደለም መታገል ያስፈልጋል። አስቀድሜ እንደገለፅኩት በሕይወት ጉዞዬ ያጋጣሙኝ ተግዳሮቶች ያለቤተሠቦቼ ድጋፍ ማለፍ ከባድ ነበር የሚሆንብኝ። ለዚህም ነው ከሥኬቴ በስተጀርባ ቤተሠቦቼ አሉ የምለው። ምንአልባት የቤተሠቦቼ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ ለመድረስ አስቸጋሪ ይሆንብኝ ነበር።
አዲስ ዘመን:- ልጆች ወልደው አሣድገዋል፣ የልጅ ልጅ አይተው አያት ሆነዋል። በአጠቃላይ እርስዎ እህት፣ እናትም ሆነው አይተውታል እና እንዲያው በጥቅሉ ሴትነትን በእርስዎ አንደበት እንዴት ይገለጻል?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:- በመጀመሪያ ወንድ ሆኜ ባላየውም ሴት ሆኜ በመፈጠሬ በጣም ደስተኛ ነኝ። አንደኛ ነገር ሰው ተፈጥሮውን ማክበር አለበት ብዬ አምናለሁ። ለሁሉ ነገር ትልቁ ነገር ለምን እንዲህ ሆንኩ ማለት አይደለም። እኔ ሴት ነኝ፣ እንዲህ ሆኜ ነው በሥነ ሕይወት የተቀረጽኩት፤ ስለዚህ ያለኝን ሁሉ መቀበል አለብኝ። ለምን እንዲህ ሆንኩኝ? የሚለው አባባል ትክክል አይደለም። ሕይወት አጭር ናት፤ ስለዚህ በተሠጠኝ ዕድል መሠረታዊ ነገር ተሟልቶልኝ፣ በጊዜ ትምህርት ቤት ሄጄ፣ የምፈልገውን ነገር እየሠራሁኝ ነው ያሣለፍኩት። ብቻ ሴትነት ለእኔ በጣም የሚያስደስት ነገር ነው።
ችግር እንኳን ቢኖር ነገሩን በትዕግሥት አይቶ ማለፍ የሚኖር ይመሥለኛል። በአጠቃላይ የሴትን ነገር ብገልጽ ሃላፊነትን መሸከም፣ ለሌላው ማሠብና መድረስ እና መደጋገፍ የሴትነት ጠባይ ይመሥለኛል። ሀይለኛ ነገር ሲገጥም ያንን ነገር በአስተዋይነት ለማለፍ መሞከር፣ ነገሮችን ፊት ለፊት መግጠም፣ ችግሩን ለማለፍ የብልሃትን መንገድ መከተል ሴትነት ይኼ ይመሥለኛል። በአስተሳሰብ እና በአመለካከትም ሴት እኮ እንዲህ ማድረግ አትችልም የሚለው ትክክል አይደል። ሴት እንደምትችል በተግባር አሣይቶ መግለጽ ይገባል፣ ተሽሎ መገኘትም ያስፈልጋል። ሴቷ ራሷን እስካወቀች ወይንም ከወንድ እንደማታንስ ካመነች የምትሻው ሥፍራ መድረስ አይሣናትም።
ለቤተሠብ የመድረስ፣ ልጆችን የመንከባከብ የእርሷ ነው። በእርግጥ ወንድ ልጆቹን አይንከባከብም ማለት አይደለም። ከእራሴ ሕይወት ተሞክሮ ወስጄ ነው የማወራው። ወንድ ሆኖ እንደ ሴት ነው፣ ሴትም ሆና እንደ ወንድ ናት የሚባል አለ። እንዲህም ይኖራል።
አዲስ ዘመን:- በትምህርት ቤት ባሣለፉበት ወቅት እና በወጣትነትዎ የነበሩ የእርስዎ ዘመን ሴቶችና በአሁኑ ዘመን በትምህርት የሚያገኗቸውን ሴቶች በንጽጽር እንዴት ይገልጿቸዋል?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:- የእኔ ዘመን ሴቶች አሁን ካሉት ጋር በጣም ይለያያሉ። በእርግጥ በቁጥር ባይበዛም በእኔ ጊዜ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት ይሄዱ ነበር። ግን የቤተሠብ ጫና በጣም ጠበቅ ያለ ነበር። ጎበዝ ተማሪዎች ቢሆኑም ትምህርት አያስጨርሷቸውም። ሐብታም ባል ከመጣና ዕድሜዋ 18 ከሆነ ወደ ትዳር ያስገቧታል። ከተማ ውስጥ ሆነውም እንኳን ወደ ትዳር የሚገቡ፣ ትምህርታቸውን ቶሎ ተምረውም ባያገቡም ወደ ሥራ ዓለም የሚገቡም ነበሩ። እንዴት እንዲህ ትሆናለች የሚል የቤተሠብ እና የማህበረሰብ ጫና ነበረ። ሴቷ እንኳን ባታምንበትም ይሉኝታ ያጠቃታል።
አሁን ግን ሣየው ወጣቶቹ ለየት ይላሉ። ምናልባት በከተማ እና በገጠር ልዩነቱ የየራሱ ባህሪ ይኖረዋል። ከተማ አካባቢ ሴቶቹ ከእኔ የወጣትነት ጊዜ ይልቅ አሁን በራሣቸው የመቆም ነገር ይታያል። የቤተሠብ ጫና ቢኖርም እንደ በፊቱ አይደለም። ትዳር እንኳን ሳይዙ ለብቻቸው የሚኖሩ አሉ። ይኼ ራሱ እኔ ወጣት በነበርኩበት ጊዜ እንደ ነውር ነበር የሚቆጠረው። አንድ ሴት ልጅ ከቤት ተድራ ካልወጣች ከተማም ብትኖር ተከራይታ የምትኖር እኔ አላውቅም። አሁን ላይ ለሴቶች ነጻነት መሠጠትና በራሷ መቆም እንደምትችል የመቀበል ነገር በቤተሰቦች አለ። በወጣቶቹም ከእኔ ዘመን ይልቅ በራስ የመተማመን በአሁን ወጣቶች አለ። ምክንያቱም ዘመኑ የውድድር ዓለም ነው። ሕይወትን ለማሸነፍ ብዙ ውድድር ስላለ ወጣት ሴቶችን ሥራ ይዘውም ትምህርት ይማራሉ፣ የተሻለ ሥራ ለማግኘት ይሞክራሉ፣ ሕይወታቸውን ለማሻሻል ይጣጣራሉ። የሚገጥማቸውን ተግዳሮት ለመወጣትም እንደሚተጉ እና የተሣካላቸውን ተመልክቻለሁ። በዚህ ረገድ ብዙ ልዩነት አለ።
አዲስ ዘመን:- በየዓመቱ የሴቶችን ቀንን ከማክበር በዘለለ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሴቶች አሣታፊነት እና ተጠቃሚነትን እንዴት ይመዝኑታል?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:- በኢትዮጵያ ማርች 8 ወይም የዓለም የሴቶች ቀን መከበር ከጀመረ ቆይቷል። መከበሩ ጥሩ ነው። ነገር ግን ለውጥ መጥቷል ወይ? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። ማህበረሰቡ የሴቶችን እኩልነት፣ ለእነርሱ በትምህርት፣ በሥራ መሥክና በያሉበት ደረጃ መሻሻል ቃል ከመናገር እና ሕግ ከማውጣት በተሻለ ምን ለውጥ መጥቷል? የሚለው በደንብ መታየት ያለበት ይመሥለኛል።
እኔ የማውቀውና መናገርም የምችለው በትምህርት ዘርፉ ዙሪያ ላይ ነው። ሴት ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቁጥር እየጨመሩ ሄደዋል። ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመቀላቀል በቁጥር እየጨመሩ መሄዳቸው አንድ ጥሩ ነገር ነው። ግን ዝርዝሩ መታየት ይኖርበታል። ሴቶች ከዝቅተኛው ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ በኢኮኖሚ የማደግ፣ አስተሳሰብ የመበልፀግ ሁኔታ ምን ያህል ደረሠ የሚለው በጥናት መደገፍ አለበት። ተሻሽሏል የሚል መረጃ ካለም ለመሻሻሎቹ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ መቀመጥ አለበት። የግለሠብ ጥረት ከሆነ፣ የመንግሥት ድጋፍ ፖሊሲ በመቅረጽ እና በሌሎች ምክንያቶችም ቢሆን መታየት ያለበት ይመሥለኛል። በዚህ መስክ ምርምር ያደረጉ ካሉ የእነርሱ አስተያየት ቢቀመጥ ጥሩ ይመሥለኛል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴቶች ቁጥር ጨምሯል። ይህንን የምለው ሽፋኑ እስከ 30 በመቶ በመሆኑ ነው። በቁጥር መብዛቱ በከፍተኛ ትምህርት መስክ የሚፈልጉትን የትምህርት ዘርፍ እና ዕውቀት ለማግኘት ፈልገው እዚያ መድረሳቸውን ያሣያል። ግን ምን ያህል ውጤታማ ናቸው? የመጨረሻ ደረጃ የሚደርሱትስ ምን ያህል ናቸው? በትምህርታቸው ባገኙት እውቀትስ ምን ያህል ተጠቃሚ ናቸው? ተብሎ መታየት ይገባዋል። ነገር ግን እኔ የሣይንስ ሰው ስለሆንኩኝ የማምነው በማረጋገጫ ወይም በተሠራ ጥናት ላይ በመመሥረት ነው። እናም በእዚህ ጉዳይ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት በጥናት መታገዝና መቅረብ አለበት።
በርግጥ መሻሻል ይታይበታል። ጅምሩም ጥሩ ነው። ውጤት ለማየት ግን ትንሽ ጊዜ መውሠድ ይኖርብናል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ በምሥራቅ፣ በሠሜን፣ በምዕራብ፣ በደቡብ የተለያዩ ቦታዎች ከ50 በላይ ተከፍተዋል። ወደ እነዚህ ተቋማት የገቡ ሴት ተማሪዎች ዕውቀትን ይገበያሉ። የዕውቀት ጥማት ያለባቸው እንደመሆኑ መጠቀም አለባቸው፣ ደግሞም በገበዩት ዕውቀት እና ክህሎት ራሣቸውን የሚረዱና ለአገርም የሚጠቅሙ ሰዎች ይሆናሉ ብዬ ተሥፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን:- እርስዎ በመማር ማስተማሩ የሚያገኟቸው ሴት ተማሪዎች ከቁጥር በዘለለ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው ይላሉ? ራሣቸውንስ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ምን ያህል ይጥራሉ ?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:- የሚጥሩና ጎበዝ ወጣት ሴቶች አሉ። በተለይም በሣይንስና ቴክኖሎጂ የተሠማሩ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር ውስጥ በብዛት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምርምር ተቋማት ሴት መምህራን እና ተመራማሪዎች አሥደናቂ ሥራ እየሠሩ ነው ያሉት። ከሰባት ዓመታት በፊት የተመሠረተው የዚሁ ማህበር አባላት ቁጥር ከ300 በላይ ደርሷል። የዚሁ ማህበር አባላት በየዓመቱ በሣይንሳዊ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምርምርና በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ ውይይት እናደርጋለን። በዚያ መድረክ ላይ የሚሣተፉ ሴቶችን የሚያቀርቡት፣ አስተያየት፣ ፍላጎታቸው፣ ራሣቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ነው። ይኼ ለእኔ ላለፉት ስድስት እና ሰባት ዓመታት በሴቶች ሥኬት ላይ ለሚታየው ለውጥ ማረጋገጫ ነው። ነገር ግን ድጋፍ እና ማበረታታት ይፈልጋሉ። ተራምደው ወይንም ጥሰው ከአገርም ወጥተው በሥራ መስክና በትምህርት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሂደቱ ጅምር ቢሆንም አሉ። ዕድሜያቸው ከፍ ያለ ደግሞ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች አሉ።
አዲስ ዘመን:- ሴቶችን በማብቃት ረገድ መንግሥት ሚናውን በሚገባ ተወጥቷል ማለት ይቻላል?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:- እኔ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ስመለከት እንዳልኩት ሴቶች እንዲበረታቱ በቁጥርም እንዲጨምሩ፣ በሥራ መስክም ሲሰማሩ ለሴቶች የሚሰጠው ትኩረት ለሴቶች የሚሠጥ ማበረታቻ (affirmative action) ጥሩ ነው። አሁን ላይም ቢሆን ሴቶች ካለባቸው ጫና አኳያ ለማበረታቻ መሰጠቱ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይሁንና ይኼ ይቀጥላል ማለት አይደለም። በቅጥር ላይ ወይንም የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ሲገቡ ለሴቶች ትንሽ የምትሰጥ ድጋፍ እየቀነሠ ነው የሚሄደው። ምክንያቱም ከወንዱ እኩል ተወዳዳሪ መሆን ስለሚገባቸው ነው። ያም ቢሆን ግን ሴት ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ሲገቡ ትርፍ ሰዓት እንዲማሩ የጥናት ጊዜ እንዲኖራቸው ለሴቶች ለብቻ ይሠጣል። የሚፈልጉትን ትምህርት ይመርጡና በፍቃደኛ መምህራን ይማራሉ።
እኔ ለአሥር ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ በሴቶች ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ሆኜ ሴቶችን በማበረታታት ሠርቻለሁ። የሚሠጣቸው ማበረታቻ እንደጠቀማቸውም ተማሪዎቹ ራሣቸው ምሥክር ሆነዋል። ለምሣሌ የምርምር ሥራ ላይ ለሴቶች ድጋፍ የማድረግ ጅምር አለ። በሁሉም ተቋማት ይህ ዓይነቱ ድጋፍ ስለመደረጉ እርግጠኛ አይደለሁም። አቅም በፈቀደ መልኩ ከወረቀት ባለፈ ሴቶችን በተለይም የምርምር ሥራ የሚሰሩትን መደገፍ ይገባል ባይ ነኝ። ምክንያቱም በተፈጥሮ ሴቶች ያረግዘሉ፣ ይወልዳሉ፤ ልጅ በማሣደጉም ሂደት ከፍተኛው ሀላፊነት የወደቀው በእነሱ ላይ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግሥት የወሊድ እረፍት ጊዜን ከሦስት ወደ አራት ወር ማሣደጉ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ።
በተጨማሪም ለጎበዝ ተመራማሪ ሴቶች ለምርምር ሥራ ለየት ባለ መልኩ ጊዜ ቢሰጥ መልካም ነው። ግን በውጤት የተመሠከረ መሆን አለበት። በጣም ጎበዝ ለሆነች፣ ሠርታ የምታሣይ፤ ግን ጊዜ የሚያጥራት ከሆነች መደገፍ መልካም ነው። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ሴት የምታጠባው፣ የምትንከባከበው ልጅና የምትደግፈው ቤተሠብም ይኖራታል፣ ብዙ ሸክም በእርሷ ጫንቃ ላይ ነው የሚያርፈው። ይኼንን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ጊዜ ለመስጠት የተወሠነ የሴቶች የምርምር ጊዜ በተጨማሪነት እንደ ማበረታቻ ጊዜ ተሰጥቷቸው ያቀረቡትን የምርምር ንድፈ ሐሳብ የሚሠሩበት ተጨማሪ ጊዜ መስጠት ጥሩ ነው። በርግጥ ዝም ብሎ እንደ ሥጦታ ይሰጥ ማለቴ አይደለም።
አዲስ ዘመን:- በኢትዮጵያ የሴቶች የአመራርነት ሚና እና የፖለቲካ ተሳትፎ የሚገባውን ያህል አድጓል ማለት ይቻላል?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:- ሴቶች በትምህርቱ ዘርፍ ሚናቸውን እያጎሉ ነው። አሁን ለምሣሌ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሴቶች በሚኒስትርነት ደረጃ እየመጡ ናቸው። ወደሥልጣን የመጡትም ጎበዞች እንደሆኑ ይሠማኛል። ራሣቸውን እያበቁ ለመሆኑ ማሣያ ነው። ባይሠሩ ኖሮ ያስቀመጣቸው መንግሥትም ዝም አይልም። ስለዚህ ይኼ ጥሩ ጅምር ነው ባይ ነኝ። ሌሎችም ይበረታታሉ። በእርግጥ ሁሉንም ሴቶች ወደአመራርነት ማምጣት ባንችልም ባሉበት መስክ ብቁና ተወዳደሪ እንዲሆን ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚል እምነት አለኝ። ድጋፍ መስጠት፣ ጎበዞችን የትምህርት ዕድል በመስጠት፣ በማበረታታትና በመሸለም ጭምር ወደፊት ማምጣት ለአገርም ይጠቅማል።
እኔ በፖለቲካ ተሣትፎ ፍላጎት የለኝም፤ ግን ፍላጎቱ ያላቸው ሴቶች ተሣትፎ ማድረግ አለባቸው። የፖለቲካ ተሣትፎ ለተባለው ግን እኔ ብዙም አትኩሮት ስለማልሠጥ አስተያየት መስጠት አልችልም። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ኖሮኝ እዚያ ላይ ትኩረት አላደረኩም። እናም አሁን ሴቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያላቸው አካሄድ ጉዳይ ምንም የማውቀው የለኝም። ነገር ግን ሴቶች በፖለቲካም ተሣትፎ ማድረግ አለባቸው። በፖለቲካ ብቻ ሣይሆን ወንዶች በሚሣተፉባቸው በማበራዊ፣ በኢኮኖሚም ሆነ ሌሎች የተለያዩ ዘርፎች በመግባት ተሣትፎ ማድረግ አለባቸው። በመሠረቱ በመርህ ደረጀ ሴቶች በስፖርት መስክ፣ በትምህርቱም መስክ፣ በአመራሩም፣ በፖለቲካውም ዘርፍ ይግቡና ይሣተፉ እንጂ የወንድና የሴት ተብሎ መለያየት የለበትም። በመሠረቱ ወንድና ሴት የሚለው በሥነ ሕይወቱ የሰው ልጆች ምሥል የተቀረፀበት ነው። ወንድና ሴት ተሰበጣጥረው አብረው ማህበረሰብ መገንባት አለባቸው ብዬ ነው የማምነው። እንጂ ሴቷ ለምን ይህንን አደረገች? እዚህ ለምን ገባች? መባል የለበትም። የማህበረሰብ አካሄዱም ሁልጊዜ አስተሳሰቡም እየተቀየረ ይሄዳል። እኔ ወጣት በነበርኩበት ጊዜ የነበረውና የአሁኑ ገጽታ አንድ አይደለም። ይኼንን የቀየረው አጠቃላይ የማህበረሰብ ዕድገትና ቴክኖሎጂ ነው። ለውጡ ለጥሩም ለመጥፎም ሊሆን ይችላል። ግን የማህበረሰብ ለውጥ ይጓዛል እንጂ ወደ ኋላ አይመለስም። የሚወጣና የሚገባ ነገር ይኖራል። የሚወሰድ ጥሩ ነገር አለ፣ የሚጣል መጥፎ ነገር አለ። በጥቅሉ በሕይወት ኡደት ጉዞ እንዲህ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን:- ግን ሴቶችን በማበረታታት እና በማብቃት አገር ትጠቀማለች ስንል እንዴት ነው የሚገለፀው?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:- ይህም ማለት እንደሚታወቀው ሴት የማህበረሰቡ ግማሽ አካል ናት። ቀደም ባለው ጊዜ የሴቶች ቁጥር ከፍ እንደሚል አንብቢያለሁ። የአገሪቱን ከሃምሣ በመቶ በላይ የሚወክሉ ስለሆነ በሁሉም መስክ በችሎታቸው እስካረጋገጡ ድረስ በየተሠማሩበት ዘርፍ ሁሉ ሠኬታማ መሆን አይችሉም። ያንን ሀላፊነት መውሰድ አለባቸው። ግን ችሎታ እና ፍላጎት ኖሯቸው በልዩ መልክ ማየቱ፣ ማበረታታቱና መደገፉ ተገቢ ነው። በፊት እንደማስታውሰው ከየክፍሉ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጣ ሠርተፍኬት ይሰጣል። ይኼ ዓይነት ማበረታቻ ሴቶችን ወደአንድ ደረጃ ለመሥፈንጠር ያግዛቸዋል። ወደፊት ለመቀጠል ጉልበት ይሠጣል። ጎበዝ ተብዬ እንዴት ሠነፍ እባላለሁ ላለመባል ለቀጣይ ይሠራል። ተመሣሣይ ማበረታቻዎች መኖር ይገባቸዋል።
ሴቶች በሥነ ተፈጥሮም ያለባቸው ሀላፊነት አለ። በባይዎሎጂው በሥነ ሕይወት ያለው ልዩነት ራሱ በማህበረሰቡ ውስጥ ለሚያደርጉት ተሣትፎ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ስለዚህ የወንዶች ዓለም መሆን በራሱ አይጠቅምም፤ ከዚያ ይልቅም ማሠባጠሩ እና መቀላቀሉ ይበጃል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን:- የአሁኑ ትውልድ የሃይማኖት፣ የብሄርና የአመለካከት ልዩነትን ያለማክበር ሁኔታ ይሥተዋላል። በእነዚህ ልዩነቶችም እርስ በእርስ ያለመግባባት መፈጠር ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር የዓለም ፀሐይ:– በነገራችን ላይ ማህበረሰብ አንድ ቦታ ላይ አይቆምም። ተለዋዋጭ ነው። በአንድ ዘመን ጥሩ የሆነው በአንድ ዘመን ደግሞ መጥፎ ነው የሚሆነው። ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የተለያየ የመንግሥት ሥርዓት ስለነበር የዚያ ውጤት ይመስለኛል። እነዚህን ነገሮች ያመጣው። እኔ እንደሚመስለኝ ይኼ ይበልጣል፤ ያ ያንሣል፤ ይኼ የበላይ ነው፤ ያኛው ደግሞ የበታች የሚለውን አስተሳሰብ ያመጣው ያለፍንበት ሥርዓት ነው። ወጣቶች ደግሞ የጊዜና የአካባቢ ውጤቶች ናቸው። በ20 እና 25 ዓመታት ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች በቤታቸው፣ በአካባቢያቸው፣ በትምህርት ቤት፣ ሲሰሙት የነበረው ትክክል ሊመስላቸው ይችላል። ዋናው ነገር ህብረተሰብ እንዲቀየር መሥራት ነው የሚያስፈልገው። ህብረተሰብ የሚቀየረው በማስተማር በመሆኑ ትክክለኛውን ነገር ከሕጻንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ማስተማር ያስፈልጋል።
ትውልድ የሚቀረፀው ከሕጻንነት ዕድሜ ጀምሮ መሆን ይኖርበታል። አንዱ በአንድ አገር ውስጥ ተከልሎ ያለ እስከሆነ ድረስና የጎሣ ልዩነት ያለባት አገር እስከሆነች ድረስ ሁሉም ተከባብሮ መኖር ይገባል። አንዱ ሌላውን ወደታች መመልከት አያስፈልግም። ይልቁንም የአንዱን ባህል በትምህርት ቤት እና በሥራ ቦታ መማር ይጠቅማል። ከሕጻናት ዕድሜ፣ ልጆች ማገናዘብ ከሚችሉበትና በሚጫወቱበት ከአምስት እና ስድስት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ በትምህርት ቤት፣ በቤት፣ በጎረቤት የሚደረገው ነገር ሁሉ አስተሳሰብ የሚቀርጽ ከሆነ አሁን የሚታየውን የማያስፈልግ መገፋፋትን ያቆማል። አገሪቱ የሁሉም እንደ መሆኗ አንዱ ብዙ ቆርሶ የሚያገኝበት ሌላው ደግሞ የሚቀነስበት ሣይሆን በአስተዳደር ሥርዓት የሚተዳደርበት አገር እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር የአለም ፀሐይ፡- እኔም አመሠግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2013