መልካምስራ አፈወርቅ
ቀደምት -ታሪክ
የእንግዳው ዓይኖች…
በ1881 ዓ.ም ራስ መኮንን ለጉብኝት ወደ ሀገረ ኢጣሊያ አመሩ። የዛኔ ጣሊያን በዘመኑ በስልጣኔ ከላቁ ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች። ራስ በምድረ ጣሊያን ያዩት ሁሉ አስደነቃቸው። ዓይናቸው የስልጣኔን አሻራ እያስተዋለ፣ልቦናቸው ይማረክ ያዘ። ይሄኔ በቆሙባት ምድር የሚመለከቱትን ድንቅ ነገር ሁሉ ለሀገራቸው ቢሆን ተመኙ።
በወቅቱ ኢትዮጵያን መሰል ሀገራት ስልጣኔ ያሉትን ዘመናዊነት አልሞከሩትም። አደጉ በሚባሉ ሀገራት የሚስተዋለው ቴክኖሎጂም ከደጃፋቸው አልደረሰም። እንደ በርካቶቹ ዕምነት ለእነዚህ አገራት ፈጣን ዕድገትን ማሰብ ሞኝነት ይሆናል። አብዛኞቹ ቅኝ ተገዢዎች ናቸው፣ ህዝባቸው ያልሰለጠነ፣ አስተሳሰቡ ያልዘመነ ነው።
ራስ መኮነን ግን ከተለመደው እሳቤ ራቅ ብለው አለሙ። አዕምሯቸው አንዳች ነገር ሹክ ቢላቸው ውስጣቸውን አዳመጡ። ሀገራቸውን ከኢጣሊያ፣ ህዝባቸውን ከሌላው ዓለም እያቆራኙ ብዙ ወጠኑ፣ አቀዱ። ብልጭ ያለውን ድንገቴ ሀሳብ እንደዋዛ አልገፉትም። ከራሳቸው መክረውና ተማክረው ‹‹ይሁንብኝ ›› ሲሉ
አጸደቁት።
እነሆ! ስልክ ይሉት ቴክኖሎጂ ወደሀገራችን ገባ፤ አጤ ሚኒልክ እጅም ደረሰ፤አጤው ለህዝባቸው ጥቅሙን ለያስረዱ በእጅጉ ደከሙ እጀታውን ጨብጠውም ‹‹ ሀሎ! ሀሎ! ›› ሲሉ የመጀመሪያውን ንግግር በቤተ-መንግስት አሰሙ። ውሎ አድሮ ልፋታቸው ሰመረ። ኢትዮጵያ የስልክ ቴክኖሎጂን ፈጥና ተቀላቀለች። በአፍሪካም ቀዳሚዋ አገር ሆነች።
አዳዲሶቹ የቴሌኮም ግኝቶች አጀብ ማሰኘታቸውን ቀጥለዋል። ዓለም በወጉ ያልደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎች አፍሪካን ተሻግረው በምድረ ኢትዮጵያ መዋል ማደር ጀምረዋል። በርካታ ውጥኖችን ከዓለምአቀፍ እርምጃ ጋር የሚለካው ሀይል ዕንቅልፍ የለውም። ከጀመረው ፍጥነት ለአፍታ መቆም የማይሻው ተቋም የውስጡን ዕቅድ እንደያዘ ‹‹ሙያ በልብ›› እያለ ነው።
ኢትዮ- ቴሌኮም በስኬት ጎዳና…
እነሆ ! ኢትዮ ቴሌኮም ከህዳር 2003 ዓም ጀምሮ በአዲስ ስያሜና በተሻለ አቅም ብቅ ብሏል። አዲሱን ሙሽራ በዘርፉ የተለየ ልምድና ብቃት ያለው የፍራንስ ቴሌኮም በጨረታ አሸንፎ ማስተዳደር ጀምሯል። ከሁለት ዓመት በላይ ቆይታው የውስጥ አደረጃጀቱ መዘመን፣ ይበጃሉ የተባሉ ለውጦችም በፍጥነት መመዝገብ ጀመሩ።
ኢትዮ ቴሌኮም 85 ነጥብ 4 በመቶ የሀገሪቱን የቆዳ ሽፋን በሞባይል ኔትወርክ መሸፈን ቻለ። በአዲስ አበባ ከተማም 400 ሺህ ተጨማሪ አቅም ያለው የ4ጂ ኤልቲኢ ኔትወርክን ገነባ። በመላው ሀገሪቱ ያለውን የኦፕቲካል ኔትወርክ ግንባታ ወደ 21 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማሳደግ አቅዶም ስራውን በስኬት አጠናቀቀ። ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ሆኖም በቴክኖሎጂው ያደጉት አገራትን ቱርፋት ተጋራ።
አሁን አገሪቱ በፖለቲካ ለውጥ ላይ ትገኛለች። ለውጡን ተከትሎም ኢትዮ ቴሌኮም የራሱን አደረጃጀት ይዟል። ይህ እውነት ደግሞ በ 124 ዓመታት ታሪክ ተከስቶ የማያውቀውን የአመራርነት ለውጥ በሴት ስራ አስፈጻሚዋ ጥንካሬ አውን አድርጓል።
ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ በለውጥ ስርዓቱ የተገኙ ዕንቁ አመራር ናቸው። የወጣትነት አቅምና ችሎታቸውን ተጠቅመው ኩባንያውን ለመለወጥ ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ተሳክቶላቸዋል። ከሀምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን ከውነዋል። ፍሬህይወት የአዲሱ ማኔጀመንት ቁንጮ ናቸውና የደንበኞችን ቅሬታና የኩባንያውን ችግሮች እግር በእግር ለመፍታት ሲታትሩ ቆይተዋል። ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትም በክንደ ብርቱዎቹ ሰራተኞች ቅንነት እየታገዘ በርካታ የስኬት ዓመታትን ተሻግሯል።
የአንደኛው ትውልድ መነሻ
በመደበኛ ስልክ ይደርስ የነበረው አገልግሎት በሞባይል ድምጽ የመቀየር ቴክኖሎጂ አውን ሲሆን መነሻው በፈረንጆቹ 1979 ብቅ ያለው የመጀመሪያው ትውልድ (1ጂ) ቴክኖሎጂ ነበር። 1ጂ የስልክ ተለምዷዊ ሰርዓትን ከመደበኛ ወደ ዲጀታል የቀየረ የድምጽ ቴክኖሎጂ ነው። ቀደም ሲል በነበረውና ‹‹ዜሮ ጂ›› በሚባለው ሂደት ተናጋሪዎች እርስ በርስ ለመሰማማት ይቀድማቸው የነበረው ያልጠራ ድምጽና ጩኸት ነበር።ይህ ሂደትም የስልክ አጠቃቀምን አሉታዊ አድርጎት ቆይቷል።
የሁለተኛው ትውልድ በረከት
ከሰው ልጆች ዕድገት ጋር ፍላጎቶች መጨመር ያዙ፤ ይህ አውነታም ከቴክኖሎጂው ጥግ አልራቀም። እ.ኤ.አ. በ1992 ስራ ላይ የዋለው የ2ጂ ሞባይል አገልግሎት ድምጽ ብቻ በነበረው ሂደት አጭር የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎትን አክሎ ተከሰተ። አናሎግ የነበረውን የስልክ ታሪክም ሙሉ ለሙሉ ዲጅታል አደረገ። ቀድሞ የተስተዋሉ የጥራት መጓደል ችግሮች ተወገዱ። የመጀመሪያው ትውልድ ይጠቀምባቸው የነበሩ ትልልቅ የስልክ ቀፎዎች ቀለል ብለው ተዘጋጁ። ይህ በረከት በውስጡ ጂፒ አር ኤስና ኤጅ የተሰኙትን ይዞታዎች ከውስን የዳታ አገልግሎት ጋር ያካተተ ነበር። በሀገራችንም እ.ኤ.አ. 1999 ላይ ደርሶ ቴክኖሎጂውን አበርክቷል። ኢትዮጵያ የሞባይል ቴክኖሎጂውን እግር በእግር እንደመከተሏ የመጀመሪያውን የሞባይል ቴክኖሎጂ
የተገበረችው ዓለም ላይ ዕውን ከሆነ ከስድስት ዓመታት በኋላ ነበር።
የሶስተኛው ትውልድ ስጦታ
ሁለቱን ትውልዶች የተሻገረው የሞባይል ቴክኖሎጂ ሂደቱን አልፎ ከሶስተኛው ትውልድ ዘንድ ደርሷል። ለዚህ ትውልድ የተበረከተው የምስራች ደግሞ 3ጂ የተባለው ቴክኖሎጂ ሆኗል። በዚህ ቴክኖሎጂ የሞባይል ብሮድባንድ ኢንተርኔት የዘመኑበት፣ ስማርት የተባሉ ስልኮች የታዩበትና የድምጽ ጥራትና ፍጥነት የተስተዋለበት ነው። ሀገራችንም ቴክኖሎጂውን የተቀላቀለችው በዓለም ከታወቀ ከስድስት አመታት በኋላ 2014 ላይ ነበር። ቴክኖሎጂውን ተከትሎም በ 2015 የ4ጂ ኤልቲኢ ቴክኖሎጂ መተግበር ጀምሯል።
የአራተኛው ትውልድ ልህቀት
እነሆ! የሞባይል ቴክኖሎጂው ሀይል ረቂቅ ሆኗል። በየትውልዱ ድልድይ የሆነው ዕድገትም አጀብ ያሰኝ ይዟል፤አሁን አራተኛው ትውልድ የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ የተሰኘውን የሞባይል ቴክኖሎጂ እየተረከበ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ እስካሁን ከነበሩት ሁሉ ላቅ የሚልና በሁለቱ የትውልድ እርከኖች የተስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ ነው። እ.ኤ.አ 2020 ላይ ዕውን የሆነው የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ ቴክኖሎጂን ሀገራችን የጀመረችው የዛሬ አመት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 50 ሳይቶች ላይ ነበር።
የቱርፋቱ ልዩነቶች
በ3G ሞባይል ኔትወርክ በሰከንድ ከ5 እሰከ 7 ሜጋ ባይት አንድን ዳታን ለመጫን የሚያስችል ሲሆን፤ ለማውረድ ደግሞ ከ21 እስከ 42 ሜጋ ባይት በሰከንድ ያስችላል። በ4ጂ ኤልቲኢ ቴክኖሎጂ ፍጥነቱ በብዙ እጥፎች ተሻሽሎ በሰከንድ ወደ 150 ሜጋባይት ከፍ ይላል። ሂደቱ ወደ 4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ ሲያድግም ከ300 እስከ 600 ሜጋ ባይት በሰከንድ ፍጥነት ይኖረዋል። ይህ የዘመናችን ቴክኖሎጂ ዳታን የመጫንና ማውረድ ፍጥነትን በአማካይ ስልሳ በመቶ ያሳድገዋል።
በ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ የሞባይል ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ጥራት የቪዲዮ ኮንፍረንሶችን ለማካሄድ ያግዛል። አገልግሎቱ በከፍተኛ ፍጥነትና ባንድዊድዝ የዳታ እና ኢንተርኔት አገልግሎትን ለመጠቀም ያስችላል። በቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ታግዘው የሚከናወኑ ተግባራትን በአስተማማኝ ሁኔታም የማቀላጠፍ አቅም አለው። ይህ በመሆኑም የደንበኞችን ምርታማነት ለማሳደግ የሚኖረውን ድርሻ የላቀ ያደርገዋል። በርቀት ሆኖ ስራዎችን ለማቀላጠፍ ይረዳል። በቀላሉ መረጃዎችን ለማግኘትና ለመለዋወጥ ያለው አስተዋጽኦም የበረከተ ነው። ይህ ፈጣን አገልግሎት ቀደም ሲል በ3ጂ የነበረውን ፍጥነት በእጥፍ ያሻሽላል።
ለ2ጂ እና 3ጂ የሞባይል አገልግሎት የምንጠቀምባቸው መደበኛ ሲም ካርዶች የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎትን ማስጠቀም ስለማያስችሉ በተሻለ አቅም ባላቸው ዩሲም (USIM) ካርዶች ሊተኩ ይገባል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የስልክ ቀፎዎቹ ከአገልግሎቱ የተናበቡ ስማርት ሞባይሎች ሊሆኑ ግድ ነው። ይህን አገልግሎት ስኬታማ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎችን ዕውን ማድረግ ያሻል።
ኢትዮ ቴሌኮም ስማርት ሞባይሎችን ከዘመኑ ኔትወርክ በማናበብ አገልግሎቱን መጠቀም እንዲቻል ለደንበኞች በተመጣጣኝ ዋጋና የጊዜ ገደብ የሽያጭ አማራጮችን አመቻችቷል።
ኢትዮ ቴሌኮም በአጠቃላይ 7300 ‹‹ቢቲኤሶች›› አሉ። ተጨማሪም 769 የሚሆኑ ሳይቶች በግንባታ ላይ የሚገኙ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ 132 ያህሉ በአዲስ አበባ ይገነባሉ። 637 ሳይቶችም ከከተማዋ ውጭ የሚገነቡ ናቸው። 50 በመቶ የሚሆኑት መሰረተ ልማቶች ከሚያገኙት መደበኛ ኃይል በተጨማሪ የመጠባበቂያ ኃይል፤ የጀኔሬተርና የባትሪ ሀይል እንዲኖራቸው ተደርጓል። 21 ከመቶ የሚሆኑት ሳይቶችም ደግሞ የሶላር ኃይል ተጠቃሚዎች ሆነዋል።
በ 4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ ማስፋፊያ 103 ከተሞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የኢትዮ ቴሌኮም ግብና ራዕይ ነው። 1094 ሳይቶችም በተያዘው በጀት አመት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ በጥንካሬ እየሰራ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከተማ በ50 ሳይቶች የጀመረው አገልግሎት አቅሙን በማጠናከር ተጨማሪ 208 ሳይቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴውን በማፋጠን ላይ ነው። በአሁኑ ጊዜም ከ200 በላይ የሚሆኑት ግንባታቸው ተጠናቆ በቅርቡ ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ።
የአምስተኛው ትውልድ መንገድ
በ2020 ላይ ዕውን የሆነው የ5ጂ ሞባይል ቴክኖሎጂ 4ጂ ላይ የነበሩ በረከቶችን በማሻሻል ከፍተኛ የሚባል ለውጥ የታየበት ነው። ይህ ቴክኖሎጂ የሞባይል ብሮድባንድ በእጅጉ የተለወጠበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አዳዲስ ዘመን-ወለድ የሞባይል ቴክኖሎጂዎችን ለመገንባት ያስቻለም ነው። ቴክኖሎጂውን ኢትዮጵያ በ2022 በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነች።
ኢትዮ ቴሌኮም ዓለም የደረሰበትን የሞባይል ቴክኖሎጂ እግር በእግር መከተሉን ይዟል። ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ለመለወጥም ፈጣን ጉዞ ላይ ነው። የ4ጂ ኤልቲኢ አገልግሎት በ2015 በሀገራችን የተጀመረ ሲሆን የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎት በአዲስ አበባ ሀምሳ ሳይቶችም ግልጋሎቱን በ2020 ጀመረ።
ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ምስራቅ ሪጅን
እነሆ! አሁንም አዲስ ብስራት መሰማት ጀምሯል። የካቲት 11ቀን 2013 ዓም በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ማልዳ የወጣችው ፀሀይ ብቻዋን አልደመቀችም። በደቡብ ምስራቅ ሪጂን ለሚገኙ ስድስት ከተሞች አዲስና ታላቅ የምስራችን ይዛለች። አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ዱከም፣ ገላን ሞጆና አዋሽ መልካሳ ታላቁን የምስራች እየተቀባበሉት ነው። መልካሙን ዜና የሰሙ ሁሉ ውስጣቸው በሀሴት ተሞልቷል።
ይህ ቀን ኩባንያው በነዚህ ከተሞች ለሚገኙ ደንበኞቹ 4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የላቀ አገልግሎት መጀመሩን እውን ያደረገበት ነው። በአዳማ ሀይሌ ሪዞርት በተደረገው ብስራት አገልግሎቱ ከፍተኛ ፍጥነትና የዳታ ስርጭት እንዳለው ተነግሯል። መርሀ ግብሩን ለማስጀመር በስፍራው የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩም በእነዚህ ከተሞች ላይ ከፍተኛ የሚባል የዳታ ፍላጎት መስተዋሉን ገልጸዋል። ስፍራዎቹ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያላቸውና የቱሪዝም መዳረሻ መሆናቸውም ለማስፋፊያው መገንባት አንዱ ምክንያት ሆኗል።
ኔትወርክ ማስፋፊያ መደረጉ ብቻ በቂ አለመሆኑን የሚያምነው ኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማቱ ለሚያስፈልገው አቅምና ሽፋን መሟላት አበክሮ ይሰራል። ይህ ጥረት ደግሞ በደንበኞች የሞባይል አጠቃቀም ላይ የሚኖረውን ለውጥ ትርጉም እንዲኖረው ያስችላል። ስራ አስፈጻሚዋ እንዳሉትም ቴክኖሎጂውን በሚገባ የተቀላጠፈ ለማድረግ የሞባይል ቀፎዎች ዘመን ወለድ ቴክኖሎጂውን የመተግበር አቅም ሊኖራቸው ይገባል። እንዲህ መሆኑ ደንበኞች የተሻለ መረጃ እንዲያገኙ፣ ሀሳባቸውን በአግባቡ እንዲገልጹና ከመላው ዓለም በቀላሉ እንዲገናኙ ያግዛል። ለዚህ አባባልም ወ/ት ፍሬህይወት ስማርት ሞባይሎችን ተደራሽ ለሚያደርጉ አካላት በሙሉ አቅርቦትን ከዋጋ ጋር ተመጣጣኝ ያደርጉ ዘንድ መልዕክት አድርሰዋል። ይህ ብቻም አይደል ጠቃሚ የሚባሉ የኢንተርኔት ይዘቶችም የደንበኞችን መረጃ የማግኘትና የመስጠት አቅምን እንደሚያልቅ ተጠቅሷል። እሳቸውም ለይዘት አቅራቢዎቹ ‹‹ዲጂታል ኢኮኖሚውን ትገነቡ ዘንድ በጎነታችሁ አይጥፋ›› ሲሉ ‹‹መልዕክቴ ይድረሳችሁ›› ብለዋል።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በሀገራችን ያለው የኢንተርኔት ትራፊክ ሚዛን የሚደፋው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ነው። እንደ ወ/ት ፍሬህይወት አገላለጽም ይህ ልማዳዊ ተሞክሮ የተሻሉ፣ ሙያዊ የሆኑና መሰል የቢዝነስ ይዘቶች ቢታከሉበት ተመራጭ ይሆናል።
4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ ሲታሰብ ቴክኖሎጂውን ያለዘመናዊ ስልኮች መተግበር ያዳግታል። በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ባለው የኔትወርክ አቅም ላይ 65 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ ስማርት ስልኮች ተገናኝተዋል። 49 ሚሊዮን ደንበኞችም የሞባይል ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ደንበኞቹ ከሚጠቀሙባቸው ስልኮች መካከልም 44 በመቶ ያህሉ የስማርት ስልኮች ናቸው። 23 ነጥብ 3 ሚሊዮን ደንበኞችም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መሆናቸው ተረጋግጧል።
በደቡብ ምስራቅ አካባቢ ያለው መረጃ እንደሚያሳየው 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ደንበኞች የስማርት ሞባይሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው። በደቡብ ምስራቅ ሪጅን ከተሞች 551 የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተዋል። በነበሩት ጣቢያዎች ላይም 110 ያህሉ የፈጣኑ ሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ናቸው።
አገልግሎቱ የደንበኞችን ምርታማነት በእጅጉ የሚያሳድግና የቴሌኮም ተሞክሮን የሚያዘምን ስለመሆኑም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ሲናገሩ በታላቅ ኩራት ነው። እሳቸው ይህን ስኬት የሚያበስሩት ብቻቸውን አልሆነም፡፤ምንጊዜም ለኩባንያው ሰራተኞች፣ የቢዝነስ አጋሮችና ደንበኞች ልዩ አክብሮት አላቸውና የምስራቹን በእኩል ማዕድ ይጋሩታል።
ከፍተኛ ፍጥነት ያለውን የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎት እውን ማድረግ የተቋሙ የሶስት አመታት የዕድገት ስትራቴጂክ ዕቅድ አካል ነው። በዚህ መሰረትም ኩባንያው በአዲስ አበባና በሌሎችም ክልሎች የዳታ ትራፊክ ዕድገትና የደንበኞችን ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የማስፋፊያ ስራዎችን አቅዷል። አዳዲስ የቢዝነስ አማራጮችን ጨምሮ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን ለመጀመር በሂደት ላይ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ያለበትን የፋይናንስ አቅም ይበልጥ ለማጠናከር አበክሮ ይሰራል። የኔትወርክ ማስፋፊያው ሀገራችን ለጀመረችው የዲጂታል ኢኮኖሚ የሚኖረውን ድርሻ የላቀ ያደርገዋል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ኤኮኖሚውን ከሚዘውሩት ተቋማት መሀል አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ትውልድና ከባቢን አካታች በማድረግ የራሱን ሚና በመወጣት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይ ወራትም በጀመረው ፍጥነትና በበረታ ትጋት ተመሳሳይ ስኬቶች እንደሚያስመዘግብ ወ/ት ፍሬህይወት አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2013