ጽጌረዳ ጫንያለው
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ፋካልቲ ዲን ናቸው። በብሔራዊ ደረጃ የሚከናወኑ የተለያዩ ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍም ይታወቃሉ። በጤናው መስክ መምህር፣ አማካሪና ተመራማሪም ናቸው። በአስተዳደር ዘርፉም እንዲሁ በርካታ ቦታዎች ላይ ሰርተዋል። ትምህርታቸውንም ቢሆን ከዲፕሎማ ጀምረው ነው ዛሬ ያሉበት ላይ የደረሱት። በጠንካራ ሥራ ወዳድነታቸው በተደጋጋሚ ከተለያዩ ተቋማት ሽልማትን አግኝተዋል። ይሄም ሆኖ ግን አሁንም ምንም አልሰራሁም፤ ለአገሬ ብዙ የማበረክተው አለኝ ብለው የሚያምኑ ናቸው፤ የዛሬ የሕይወት እንግዳችን ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙሉእመቤት አበራ።
ሴት በመሆኔ የተሰጠኝ ኃላፊነት በምንም መልኩ ሊጎል አይገባውም ብለው የሚያምኑና ራሳቸውን እየጎዱ ጭምር ሀላፊነታቸውን የሚወጡ መሆናቸውንም የሥራ ባልደረቦቻቸው ጭምር የሚመሰክሩላቸው ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙሉእመቤት አበራ፤ ከእዚህና መሰል ተሞክሯቸው ልምድን ትቀስሙ ዘንድ ለዛሬ እንግዳ አድርገናቸዋል። ተማሩባቸው ስንልም ጋብዘናችኋል።
የአባት ልጅ
ተወልደው ያደጉት በአርሲ ክፍለአገር አሰላ ከተማ ውስጥ ነው። እናታቸው በልጅነታቸው ነው ከአባታቸው በመለያየታቸው ምክንያት ብዙ ጊዜያቸውን ከአባታቸው ጋር ያሳለፉት። አባት ልጆቻቸውን በእንጀራ እናት ላለማሳደግ ብዙ የቆዩ እንደመሆኑ፤ ለእርሳቸው አባታቸው አባት ብቻ ሳይሆን እናትም ነበሩ። በዚህም ባለታሪካችን አባታቸውን እናት አድርገው እንዲያዩ ሆነዋል። ምክንያቱም ከቆይታ በኋላ አባታቸው ሚስት አግብተው ነበር። እንግዳችንም ከእርሳቸው ጋር ዓመታትን አሳልፈዋል። የእንጀራ እናታቸውንም በጣም ይወዷቸው ነበር። ይሁን እንጂ እርሳቸውም ቢሆኑ ብዙ አልቆዩም። ቤተሰቡን በሞት ተሰናበቱት። በዚህም ሁሉም ጫና በአባት ላይ አረፈ።
አባታቸው አበራ ወርዶፋ እናትም አባትም እንደነበሩ በእንባ ጭምር የሚገልጹት ባለታሪካችን፤ “እርሱ የራሱን ህይወት ለእኛ የሰጠ ነበር” ይሏቸዋል። ብዙ ወንዶች እንደሚታዩት የእንጀራ እናት አግብተው ልጆች ተሰቃይተው ባልና ሚስቱ ግን ተስማምተው ይኖራሉ። አባታችን ግን ልጄን የእንጀራ እናት ራት አላደርግም፣ ማንም እንዲገላምጠብኝም አልሻም ብለው አኑረዋቸዋል፤ ተንከባክበዋቸዋልም። የውጪውን ሥራ ሰርተው ሲመጡም የቤቱን ሥራ እንደ እናት ያከናውናሉ።
ለሴቶቹም ሆነ ለወንዶች ልጆቻቸውም የቤት ውስጥ ስራዎች እንዴት እንደሚከናወኑ ያስተማራሉ። ስለዚህም እርሳቸውን የሙያ ሁሉ ባለቤት ያደረጓቸው አባታቸው እንደነበሩ ያወሳሉ። ወጥ መስራት እና እንጀራ መጋገር ጥንቅቅ አድርገው የቻሉት በእርሳቸው እንደነበርም ይናገራሉ። ስለዚህም አባታቸው የሙያም የቀለምም መምህራቸው እንደነበሩ ነው ያጫወቱን።
እንግዳችን ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። በዚህም ከአባታቸው ቀጥሎ ሌሎች ልጆችን የሚያስተዳድሩት እርሳቸው ይሆናሉ። ነገር ግን በእነርሱ ቤት ህግ ሁሉም የአቅሙን ይሰራልና ሴት ስለሆንሽ ወንድ ስለሆንክ ብሎ ነገር የለም። በዚህም የሥራ ጫና ውስጥ ገብተው አያውቁም። በሴትነታቸው የደረሰባቸውም ብዙ ጫና የለም። ለዚህ ደግሞ ያገዛቸው አባታቸው መምህር መሆናቸው ነው። በትምህርታቸውም ቢሆን አባታቸውን ላለማሰደብ ሲሉ ጎበዝ ናቸው።
ቤተሰባቸው በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ በመሆኑ በጣም ባይንደላቀቁም የጎደለባቸው እንደሌለ የሚናገሩት ባለታሪካችን፤ በባህሪያቸው አትንኩኝ ባይ፣ ሩህሩህ፣ የተቸገረ አይተው የማያልፉ፣ ታዛዥ እንዲሁም ተጫዋች ሲሆኑ፤ እልኸኝነታቸው ከጓደኞቻቸው ሁሉ ለየት ያደርጋቸዋል። ይህ የመጣው ደግሞ የጀመሩትን ሳያጠናቅቁ በምንም ተአምር መተው ባለመፈለጋቸው ነው። ያሰቡትን ከግብ ሳያደርሱም እንዲሁ እንቅልፍ አይወስዳቸውም። ስለዚህ ተስፋ መቁረጥ እርሳቸው ጋር በፍጹም አይታሰብም።
እንግዳችን ግራኝ ሲሆኑ፤ በባህል ዘንድ ግራኝ የሆነ ሰው የሚበላው አይጠጋውም፣ ብር አይበረክትለትም ወዘተ ይባላል። እርሳቸው ጋር ግን ይህ አይሰራም ነበር። እንደውም ልዩ ስጦታቸው እንደሆነ ይነገራቸዋል። ማንም ግራኝ በመሆናቸው የሚያገልላቸውም አልነበረም። በዚህም በግራቸው የፈለጋቸውን ያደርጋሉ። በተለይም አባታቸው የአዕምሮ አቅማቸው ላይ በስፋት ይሰሩባቸው ስለነበር ሳይጨናነቁ ነው ልጅነታቸውን የኖሩት። በነጻነት የፈለጉትን እንዲያደርጉ መበረታታታቸው የተሻለ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ልጅ እንዲሆኑም አስችሏቸዋል።
የልጅነት ህልማቸው ልክ እንደአባታቸው መምህር መሆን ነው። ምክንያቱም በወቅቱ በሚያዩት ደረጃ መምህር መሆን ያስከብራል፤ በአለባበስም ልዩ ያደርጋል። በዚያ ላይ በእውቀት ደረጃ ከእነርሱ ውጪ ማንም አይኖርም ብለው ያምናሉ። ስለዚህም መምህር መሆን የመጀመሪያ ምርጫቸው አድርገውታል። ከፍ ብለው መማርና ማወቅ ሲጀምሩ ደግሞ ፍላጎታቸው ወደ ሌላ ተቀየረ። ይህም የህክምና ዶክተር መሆን ነበር። በእርግጥ ለዚህ መሰረት የሆናቸው ማወቃቸው ብቻ ሳይሆን ታመው ሆስፒታል መግባታቸውም ነበር። እናም ዶክተሮቹ ከአለባበሳቸው ጀምሮ ለሰው ልጆች የሚሰጡትን ተስፋ ሲመለከቱ ይህንን ወደ መሆኑ ፍላጎታቸውን ቀየሩት። በዚያ ሙያም እስከመጨረሻው ቀጠሉበት። ያው መምህርነቱም እንዳለ ሆኖ።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙሉእመቤት፣ በአኗኗርና በልጅነት ጊዜያቸው የነበረውን መዋደድና ቀረቤታ ዛሬ ድረስ በኖረ ብለው የሚመኙት ነው። ምክንያታቸው ደግሞ አስተዳደጋቸው በቤተሰብ ብቻ ባለመሆኑ፤ አራስ ልጅ ሳይቀር ጎረቤት መቀመጡና እንክብካቤ ሲደረግለት መቆየቱ፤ የአራስ እናት ጡት እየጠቡ ማደጉ ነው። በዚያ ላይ መገረፍና መቆጣትም በጎረቤት የበለጠ ክብርና ፍራቻ ያለው መሆኑ ነው።
ከታች የተነሳው የትምህርት ጉዞ
በትምህርታቸው የደረጃ ተማሪ ብቻ ሳይሆኑ አባታቸውን ላለማሳፈር ሲሉ በመምህራኖቻቸው የሚሰጣቸውን የቤት ስራቸውን ጠንቅቀው የሚሰሩ፤ ትምህርትቤትም መጥፎ ባህሪ የማያሳዩ ናቸው። በተለይ ለየት የሚያደርጋቸው እስከ 12ኛ ክፍል ሲማሩ ከአንድ እስከሦስተኛ ደረጃን የሚይዙ መሆናቸውና በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን መከታተላቸው ነው። ትምህርት ቤቱ ጭላሎ ተራራ የሚባል ሲሆን፤ ካሉበት አከባቢ ሳይርቁም ከ1ኛ እስከ 12ኛ የተማሩት እዚሁ ትምህርት ቤት ነው።
‹‹ማትሪክና ቀበሌ የሰራለትን አያውቁም›› እንደሚባለው ምንም እንኳን የደረጃ ተማሪ ቢሆኑም የ12ኛ ክፍል የትምህርት ውጤታቸው ግን ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸው አልነበረም። በዚህም ሌሎች አማራጮችን እንዲያዩ ግዴታ ተጣለባቸው። ይህም ማስተዋቂያ ተከታትለው በሰርተፍኬት ወይም በዲፕሎማ መማር ነው። እናም መጀመሪያ ላይ የሰርተፍኬት ማስታወቂያ አዩ። ነገር ግን እርሱን በዚያ ውጤት ሊቀበሉት አልቻሉም። እናም ሌላ ማስታወቂያ እስኪወጣ ይጠብቁ ጀመር። እድል ቀናቸውናም ያሰቡት ላይ አደረሳቸው። ይህ እድል የልጅነት ፍላጎታቸውን የሚያሳኩበት ነው። ስለዚህም የዞን ጤና ቢሮ በነርሲንግ በዲፕሎማ መማር የሚፈልግ ተወዳደሩ ሲል ማስታወቂያ አወጣ። እርሳቸውም አይናቸውን ሳያሹ ለውድድር ወደቦታው አቀኑ።
ቦታው ላይ ሲደርሱ ያዩት ግን ለማመን አቃታቸው። ከዚህ ውስጥ እንዴት እንደሚያልፉም ግራ ተጋብተዋል። ምክንያቱም የተመዘገበው ሰው ከሺህ በላይ ሲሆን የሚፈለገው ደግሞ አምስት ሰው ነው። ተስፋ መቁረጥ የእርሳቸው ባህሪ አልነበረምና ለሌሎች ፈተናዎች የሚያበቃቸውን ማንበብ ጀመሩ። ጥናታቸው ውጤት አመጣና መቶ ውስጥ ከዚያ 25 ውስጥ እያሉ በስተመጨረሻ ከአምስቱ መካከል አንዷ ሆኑ። ለትምህርትም ወደ ጥቁርአንበሳ ነርሶች ማሰልጠኛ ተጓዙ።
በጥቁር አንበሳ እየተማሩ ማደሪያቸውን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ያደረጉት ተባባሪ ፕሮፌሰሯ፤ መጀመሪያ አካባቢ ከቤተሰብ ተለይተው በመምጣታቸውና ያለመዱት ነገር ስለገጠማቸው እጅግ አስከፍቷቸው እንደነበር አይረሱትም። በተለይ ተሰልፎ መመገቡ አስለቅሷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ሁኔታውን ሲለምዱት ግን የተለመደ ተግባር እንደሆነ ተረዱ። ትምህርታቸውንም በአግባቡ ወደመከታተሉ ገቡ። ከዚያ በኋላ የነበረው ጊዜም ጥሩ ሆኖላቸው እንዳለፈ አጫውተውናል።
ከምረቃ በኋላ ወደመጡበት አሰላ የሄዱት እንግዳችን፤ በሙያቸው ያስተማራቸውን ማህበረሰብ ለአምስት ዓመታት በሽርካ ጤና ጣቢና በአሰላ ሆስፒታል ከአገለገሉ በኋላ ነው ዳግም በውድድር ወደ ትምህርት የተመለሱት። ይህም ዩኒቨርሲቲዎች ለዞኖች ኮታ ሰጥተው እንደመጀመሪያው ጤና ቢሮ በውድድር የትምህርት እድል በመስጠቱ የመጣ ነው። በዚህም የጤና መኮንንነት ትምህርት ለመከታተል ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት፤ ከሦስት ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በመያዝ ከዩኒቨርሲቲው በማዕረግ ተመርቀዋል።
ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው የጀመረው ደግሞ በአሰላ ነርሶች ማሰልጠኛ ለሦስት ዓመት ከአገለገሉ በኋላ ነው። ይህም እንደቀደመው በውድድር የተገኘ የትምህርት እድል ሲሆን፤ ዳግም ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው ነው ትምህርቱን የተከታተሉት። በዚህም በስነተዋልዶ ጤና የትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰሩ። ይህ ውጤታቸውም በዚያው የሚያስቀራቸው ስለነበር በመምህርነት እያገለገሉ ስድስት ዓመታትን አሳለፉ። በመጨረሻም የሶስተኛ ዲግሪያቸውን የመማር እድላቸው ተመቻቸና በሳንዱች ፕሮግራም በዳድ ስኮላርሽፕ ትምህርቱን መማር ጀመሩ።
ትምህርቱን የተከታተሉት በጀርመን ሉድዊግ ማክሲሚላን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ማንቺ በኢንተርናሽናል ሄልዝ የትምህርት መስክ ነው። በዚህም ቢሆን ውጤታማ ነበሩ። ከዚያም የተለያዩ ስልጠናዎችን መውሰድ ችለዋል። አሁን ባሉበት ደረጃ ደግሞ በሰሯቸው ሥራዎችና ጥናቶች ተባባሪ ፕሮፌሰርነታቸውን ያገኙ ሲሆን፤ ሙሉ ፕሮፌሰርነትን ለማግኘትም እየታተሩ ይገኛሉ።
ስለእናቶችና ህጻናት የተሰጠ ሙያዊ ማንነት
የሥራ ጅማሮዋቸው ‹‹ሀ›› የተባለው በትውልድ ቀያቸው አሪሲ ዞን ሲሆን፤ ሽርካ ወረዳ ከተማ ደግሞ ጎቤሳ ይባላል። የጤና ጣቢያው ሥም ደግሞ ጎቤሳ ጤና ጣቢያ በመባል ይጠራል። በዚህ ቦታ ላይ የእናቶችና ህጻናት ክፍልን እንዲይዙ ተደርገው አገልግለዋል። ከእናትቶችና ህጻናት ጋር የነበራቸውን ቁርኝት በደንብ ስለታየና ውጤታማ ስለሆኑም ብዙ ኃላፊነትን እየወሰዱ ነው ለአንድ ዓመት ያህል የቆዩት። ከዚያ ወደ አሰላ ሆስፒታል በመዛወር ሥራቸውን መስራት ጀመሩ። በዚህም ቢሆን የቀደመ ሥራቸውን ነበር የሚያከናውኑት። ልዩነቱ መጀመሪያ ህጻናት ተኝተው የሚታከሙበት ክፍል ውስጥ በባለሙያነት ለአራት ወር ያህል ማገልገላቸውና ቀጥለው ደግሞ የእናቶችና ህጻናት ክፍሉ አስተባባሪ ሆነው እንዲሰሩ መደረጋቸው ነው። ስለዚህም ከእናቶችና ህጻናት ሳይነጣጠሉ ለትምህርት እስኪሄዱ ድረስ ለአራት ዓመት ያህል አገልግለዋል።
ከመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት በኋላም በአሰላ ጤና ጣቢያ የሰሩ ሲሆን፤ ከዚያ የተሻለ እድል አግኝተው የአሰላ የነርሶች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤትን ተቀላቀሉ። የክሊኒካል ነርሲንግ መምህር በመሆን ተሰማሩ። ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ ጉዟቸውን ዛሬ ወደሚሰሩበትና ብዙዎችን ማፍራት ወደቻሉበት ጅማ ዩኒቨርሲቲ አደረጉ። ጅማ ዩኒቨርሲቲንም ሁለተኛ የቤተሰባቸው ቤት አድርገው በማስተማር፣ በመመራመር፣ በማማከርና አንዳንድ ሀላፊነቶች ላይ በመሳተፍም ሀላፊነታቸውን መወጣት ጀመሩ። አሁንም በተለይ በጤናው ዘርፍ የተሻሉ ነገሮች
እንዲኖሩ በማድረግ የበኩላቸውን እያበረከቱ ይገኛሉ።
እንግዳችን በምርምር ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉት የግልገል ጊቤ የመስክ ምርምር ጣቢያ ላይ ሲሆን፤ በአካባቢው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን በእያንዳንዱ ቀበሌ እየተዘዋወሩ የህዝብ ቁጥርን መረጃ በመያዝ፤ ምን ያህል ሰው ሞተ፣ ከቦታው ተነሳ፣ ምን ያህል ተወለደ፣ ምንስ ያህል ሰው ታመመ የሚለውን በመለየት ተግባር ነው። ከዚያም አልፈው ምርምር ጣቢያውም ሀላፊነት መርተዋል። እስካሁን ድረስም አባል ሆነው ምርምር ያደርጋሉ።
በሌላ በኩል የሥነ ህዝብና ቤተሰብ ጤና ትምህርት ክፍልን በሀላፊነት መርተዋል። የትምህርት ፕሮግራሙን ጥራት ይቆጣጠራሉ። እንደአዲስ በተቋቋመው ጤና ኢንስቲቲውትም የፐብሊክ ሄልዝ ፋካሊቲ ዲን ሆነው በእርሳቸው ሥር ስድስት ትምህርት ክፍሎች ይዘው ያስተዳድራሉ። 13 የሁለተኛ ዲግሪ፣ አምስት የሦስተኛ ዲግሪ እና አንድ የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ይመራሉ። ይህንን በማድረጉ ተግባርም አሁን አራተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል። በተጨማሪም በአቅም ግንባታ ዘርፍ ላይ ፕሮጀክት ቀርጸው በጤና ሚኒስቴር አጋዥነት እየሰሩ ይገኛሉ። ሥራው የጤና ባለሙያው በመረጃ የተደገፈ ስራና ውሳኔ እንዲኖረው የሚያግዝ ነው። እናም ጋምቤላና ኦሮሚያ ላይ በስፋት እየሰሩ እንደሆነ አጫውተውናል።
በዚህ ፕሮግራም ከ50 በላይ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያና ጤና ኬላዎች ላይ በመዘዋወርም ያግዛሉ። ከዚህ ባሻገር በፍላጎትም በሙያም የእናቶችና ህጻናት ላይ ብዙ ጥናቶችን ያደርጋሉ። የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍም እናቶች የሚደገፉባቸውን ሁኔታዎችም ያመቻቻሉ። ለዚህም ማሳያው በአገር ደረጃ የተጀመረውን የእናቶች ማቆያ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ የተሻለ እንዲሆን ማድረጋቸው ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ለሙሉ ፕሮፌሰርነት የሚያበቁ በርካታ ጥናትና ምርምሮች ላይ የተሳተፉ ሲሆን፤ ወደ 30 የሚደርሱ በአለምአቀፍ ሳይንሳዊ መጽሔቶች ላይ የታተሙ የምርምር ሥራዎችም አሏቸው። ሌላው የሰሩበት ቦታ በአካዳሚክ ጉዳዮች ላይ የማስተባበርና የመምራት ሥራ ነው። በብሔራዊ ደረጃ ማህበረሰብን መሠረት ያድረጉ በሽታዎችን በማጥናት ቅድሚያ መከላከል ላይ ይሰራሉ። በተመሳሳይ ለህብረተሰቡ እና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተለያዩ በሽታዎች ዙሪያ ስልጠና ይሰጣሉ። በሥነ ተዋልዶ ዙሪያም እንዲሁ ግንዛቤ በመፍጠር ይሳተፋሉ።
“ዘርፎችን እየቀያየሩ መስራት፣ በፍላጎት ማድረግ ሁለገብ መሆንን ያላብሳል። የእውቀት ልኬትንም ይጨምራል። በማኔጅመንቱ ዘርፍ ለሚኖር ሥራ አቅምም ይሰጣል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በራስ መተማመንንና መከባበርን ከፍ ያደርጋል። አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ለማምጣትና ብዙዎችን ለመጥቀም ያግዛል፤” የሚሉት እንግዳችን፤ አብዛኛውን ሰው ወደራስ ለማምጣትና ለማርካት አቅምን እያሳዩ መጓዝ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን እና እርሳቸውንም ለዚህ ያበቃቸው ይህ እንደሆነም ከሥራ ተሞክሯቸው በመነሳት ይመክራሉ።
ፈተና
በህይወታቸው እንደሌሎች ሴቶች ከባድ ነገር ገጥሞኛል የሚሉት ነገር የለም። ሆኖም አሁን በሥራቸው በራሳቸው የፈጠሩት ነገር እንዳለ ያወሳሉ። ይህም በተሰማሩበት ሥራ ላይ ‹‹ሴት ስለሆነች›› ችግሩ ተፈጠረ የሚባል ነገር ላለመስማት ቀን ከለሊት ይታትራሉ። የእንቅልፍ ጊዜያቸውም በዛ ከተባለ አራት ሰዓት ነው። ይህ ትግል ደግሞ ራሳቸውን እንዲጎዱ አድርጓቸዋል። በተለይ ይህንን ልጨርስ እያሉ የሚፈጁት ጊዜ ምግብ ሳይበሉ የሚያሳልፉበትን ሁኔታ አራዝሞታል። ሥራው ካላለቀና አስቸኳይ ከሆነ ከቤታቸው ምሽት ጭምር ቢሮ ሄደው ይሰራሉ። ይህ ደግሞ በህይወታቸው ላይ ከባድ ጫናን አሳርፎባቸዋል። ከራሳቸው አልፎ ቤተሰባቸውን እንኳን የሚንከባከቡበት ጊዜ እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል።
ሴትነት
ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙሉእመቤት፤ ሴት ልጅ ለህይወት ፣ ለአገር ፣ ለቤትና ለማህበረሰብ ሁለገብ መሪ ነች። ሴት ልጅ ሩህሩህነትን ከአፍቃሪነት ጋር ታድላ የተፈጠረች ለወንድ የህይወቱ ማገር እና ምሶሶ ናት። ወንድ ያለ ሴት ሙሉነት እና የህይወት ጣዕም የለውም። ከዚያ በሻገር ሴት ልጅ ስቃይዋን እና ሃዘኗን መደበቅ ካስፈለጋት መከፋትዋን ሳታሳይ ደስተኛ የምታደርግ እናትም ነች። ሴት ልጅ ከወንድ የጎን አጥንት ብትሰራም በህይወት ዘመኑ የጀርባ አጥንቱ ሆና ብርታትን እና ፅናትን የምትሰጥ ሀይልም ነች። ስለዚህም አለም ይህንን አውቆ የሚሰራ ከሆነ ይጠቀማል የሚል እምነት አላቸው።
ሴት መሆን ሲነሳ በሁለት መልኩ አብራርቶ መመልከትና እድሎችን ማየት እንደሚገባ ይጠቁማሉ። የመጀመሪያው ቀደም ባሉት ጊዜያት ስለሴት ልጅ ያለው አመለካከት ነው። በዚህ ጊዜ ሴት በግልጽ አትችልም ትባላለች። ብዙ ጫና አርፎባትም ነው የምትፈልገው ላይ የምትደርሰው። ያም ሆኖ በስራ በልጣቸው ማመን አይፈልጉም። ሀላፊነትም አይሰጣትም። ሁለተኛው አሁን እኛ ያለንበት ነው። መጀመሪያ ነገሮች ከወሬ ሲያልፉ አይታይም። በጫና ብዛት ነው ሀላፊነትም ሲሰጥ። በእርግጥ አንድ ነገር ሊሸሸግ አይገባውም። ይህም በይፋ ይህ ለአንቺ አይገባም የሚለው አመለካከት ተቀይሯል። ምክንያቱም መጠየቅ ተጀምሯል። ነገር ግን ድብቅ በሆነ መልኩ ክልከላው እንዳለ ነው። ትዝ ልትል የምትችለውም ሰው ሲጠፋ ነው።
ይህንን ግን ሴቶች ራሳቸው ጥንካሬያቸውን እያሳዩ መለወጥ አለባቸው። በየዘርፉ ያለው አካልም ይህንን በየደረጃው አይቶ መፍታት አለበት። ከወሬና ከበዓል ያለፈ ተግባር ያስፈልገናልም ይላሉ። በሴትነት ዙሪያ ከሰጪውም ሆነ ከተቀባዮቹ ጀምሮ ስህተቱ አሉና ይህንንም ማረም ይገባል። ለአብነት ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ 10 ሴቶች ሲመረጡ ‹‹የሴት መንጋ በር አይዘጋ›› እየተባለ ሲቀለድ ነበር። ነገር ግን በሥራ ሲታዩ እውነትም ይችላሉ ወደማለቱ ተመጥቷል። እናም እማይሳሳት እማይሰራ ነውና ከሁለቱም ወገን ይህንን አምነው ወደ ተግባር መግባት አለባቸው ባይ ናቸው። ሞክሮ ያቅተኛል ብሎ መተው እንጂ ሳይሞክሩ አልችለውም ማለት ተገቢነት የለውም። ለሌሎች አሳልፎ መስጠትም አይገባም። ራሳችንን ሆነን መገኘት የሚሰጠን ትልቅ ጉልበት አለና ራስን መሆንን ገንዘብ እናድርግ ይላሉ።
ቀን ጠብቆ የሚከበርና የቀኑ ዕለት ሆይ ሆይ ማለት የትም አያደርስም። ስለሴቶችም መነገርም ተግባራዊ ለውጥ ማምጣትም በየቀኑ በመስራት ነው። በተለይ ልጆቻችንን ከማስተማር አንጻር ትልቅ ሥራ መሰራት አለበት። ሁሉም ስለ ሴት ልጅ ሲያወራ ስለ ሰው ልጅ እያወራ እንደሆነም ማመን ይገባዋል። ሴቶች እኩል ናቸው ሲባልም ልዩነት እንዳለንም ማስረዳት ያስፈልጋል። ልዩነቱ ግን ለማስገንዘቢያ እንጂ የበታች አድርጎ ለማሳያ መሆንም አይገባውም። ለዚህ ደግሞ ማንኛውም ተቋም ሴቶችን ማብቃት ላይ ሊራ ይገባል፣ የሚለው ደግሞ መልዕክታቸው ነው።
የህይወት ፍልስፍና
መስራት ያለብኝ እስከመጨረሻው ሰዓት እንደሆነ ማመን፤ ተስፋ መቁረጥን ለውስጤ አለማሳየት የመጀመሪያው ነው። ሌላው በህይወቴ በራሴ ላይ እንዲሆን የማልፈልገውን ነገር በሰው ላይ ማድረግ አልፈልግም። ሰዎች እንዲያደርጉባቸውም አልፈቅድም። ህይወት አጭር ናት። በዚህች አጭር ጊዜ ደግሞ በመቻቻል ውስጥ፣ ይቅርታን አስገብቶ የማይሞት ሥራ መስራት ቢቻል መልካም ነው። ለአለምም ጥሩ ለውጥ ማምጣት ይቻል፤ የህይወት ፍልስፍናዬም ይሄው ነው። ሁሉም ልጅ ትምህርት የሚያገኝበትን፣ የሚረዳበትን መንገድ ይሻልና እኔም የድርሻዬን ለማበርከት መስራት ነው። እንደውም እግዚአብሔር ቢፈቅድ የመርጃ ድርጅት ከፍቼ ብሰራ የበለጠ ደስተኛ እሆናለሁ።
ሽልማቶች
ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጥሩ የሴት ሪሰርቸር ተብለው ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በአርሲ ዞን ጤና ቢሮም እንዲሁ ታታሪ ሰራተኛ በሚል ሽልማት አግኝተዋል። ከጅማ ዩኒቨርሲቲም እንዲሁ የሴቶችን የመማር አቅም በመጨመርና በማገዝ የተሻልሽ ነሽ በሚል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ከሁሉም የተሻልሽ ተማሪ በመባልም ሜዳሊያ ከዩኒቨርስቲው አግኝተዋል።
ለብሔራዊ አውደ ጥናት ስኬታማ አደረጃጀትና አስተዳደር የኤግዚቢሽንና ማስተዋወቂያ ኮሚቴ አባል በመሆን በኮቪድ -19 ላይ የፈጠራ ምላሽ በመስጠት እና የከፍተኛ ትምህርት እና የሥልጠና ተቋም የዝግጅት ወርክሾፕን እንደገና በመክፈት ላበረከቱት አስተዋዕጾ የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ጅማ ዩኒቨርሲቲ የምስክር ወረቀት አበርክቶላቸዋል። የተማሪ ጥናት ኮሚቴም በዓመታዊ የተማሪዎች ምርምር ሲምፖዚየም ላይ ምርጥ የጤና መኮንን ትምህርትቤት ተመራማሪ በማለት ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
ቤተሰብ
አንድ ልጅ አላቸው። የህይወቴ ማርሽ ቀያሪ ናት፤ የመኖሬም ትርጉም ናት ይሏታል። ምክንያቱም እርሷ ለእርሳቸው እርሳቸው ደግሞ ለእርሷ ይኖራሉ። ልጃቸው ኑሀሚን የምትባል ሲሆን፤ 12 ዓመቷ ነው። ይህንን ስሟን ያወጡላት ሁልጊዜ ደስታን ስለምትሰጣቸው ነው። ጨንቋቸው ከቢሮ ሲመጡ እርሷ መፍትሄ ትሰጣቸዋለች፤ ችግራቸውንም ታቀልላቸዋለች። እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ እናት ትንከባከባቸዋለች። ስለዚህም ደስታዬ ሲሉም ስሟን ሰይመውላታል።
በሥራ ምክንያት እናት የሚሰጠውን ሁሉ እንዳደረጉላት አይሰማቸውም። እንደውም ሲያሳድጓት ጭምር ይዘዋት መጥተው ሶፋ ላይ አስተኝተው ነው ስራቸውን ሲሰሩ የሚውሉት። በተለይ ጠዋት ወደስራ ሲሄዱ እርሷን በጀርባቸው አዝለው ላፕቶፓቸውን በአንድ ጎን ምግባቸውን በአንድ ጎን ይዘው ነው ወደ ቢሮ የሚገቡት። ለዚህ ደግሞ የጅማ ማህበረሰብን በተለይ ከእኔ ጋር የሰሩ ባልደረቦቼን እጅግ አመሰግናቸዋለሁ። ከሁለም በላይ ግን እህቶቼን በጣም ላመሰግን እወዳለሁ ከእኔ ይልቅ ለልጄ እነርሱ ነበር ያሏት። ብዙ ነገር ያደርጉላታል፤ ይላሉ።
ልጃቸውን እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ጎረቤቶቻቸው የልጅ አዋቂ ናት ይሏታል። ለዚህ ደግሞ ያበቋት ሁሉንም አክብራ እንድትኖር በማገዛቸው ነው። እስከ 12 ዓመቷ ድረስም ጨዋታ ብትጫወትም አጥፍታ አታውቅም ። መረበሽም የእርሷ ባህሪ አይደለም። በአስቀመጧት ላይ ሆና የተሰጣትን መጫወቻ ይዛ ነው ደስተዋን የምታጣጥመው። ይህ ደግሞ ለስራቸውም ሆነ ለልጃቸው ጤንነት የተሻለና አምላክ በልጃቸው የካሳቸው ልዩ ሥጦታ መሆኑንም ይናገራሉ።
‹‹ሁሉን አሟልቼ፤ ልጄን ብዬ የምትፈልገውን ሁሉ አድርጌላታለሁ ብዬ አላስብም። ግን የሚቆጨኝንም ነገር አላደረኩም። በጥሩ ሥነምግባር እንድታድግ የእናት ሚናዬን ተወጥቻለሁ። ስለዚህም ልጅ አሳዳጊም በሥራም ብርቱ ነበርኩኝ ብዬ አስባለሁም›› ይላሉ። በተለይ ለልጅ እናት ጓደኛም፣ እናትም፣ አባትም መሆን የተለየ ትርጉም አለው። ልጆች የተሻሉ ሆነው እንዲያድጉ ፤ ራሳቸውን ፣ አገራቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ጎረቤታቸውን እንዲወዱም ትልቅ ሀይል ይሰጣል። ምክንያቱም እናት ልጅን ፈጣሪ ነችና። በባህሪዋ፣ ባደገችበት ባህል ታሳድጋለች።
የተማረች ከሆነች ደግሞ ይበልጥ ከዘመኑ ጋር የሚራመዱበትን እድል ትሰጣለች። በመሆኑም እኔም ይህንን ነው ያደረኩት። ለዚህ ግን አባቴና እህቶቼ ብዙ ነገር ከፍለዋል። እዚህ እንድደርስ ያልሆኑት ነገርም አልነበረም። እናም ለመስዋዕትነታቸው እኔ ቆሜ መክፈል አልችልምና ፈጣሪ በህይወት እያለሁ እንዲያሳየኝ እመኛለሁ ብለዋል።
መልዕክት
ያልሰጠነውን ትውልድ መጠየቅ ያልዘሩትን ማጨድ ነው። እኛ ተሰጥቶን ፍሬያማ ሆነን እየሰራንበት እንገኛለን። ሰጪው ደግሞ ቤተሰብ ብቻ አልነበረም። ማህበረሰቡ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም መንግስትና የሀይማኖት ተቋማት ለትውልዱ ተጨንቀው በስነምግባር ኮትኩተውናል። በግብረገብነትም አሳድገውናል። የዛሬውን ትውልድ ግን ከቤተሰብ ጀምሮ እያስተማርነው ያለነው ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህም ያልዘራነውን ማጨድ አንችልምና ብዙ በትውልዱ ላይ መስራት ያለብን ነገር እንዳለ አምነን ዛሬ ላይ መንቃት አለብን። ማስተማርም መጀመር ይገባናል የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
አሁን አሉ የምንላቸው ትውልዶች ከሌላ አለም የመጡ አይደሉም። እናም እንደ ጥንቱ ሁሉም ጎረቤት ተቆጥቶ የሚያሳድጋቸው ማድረግ ላይ እናቶች ትልቅ ሀላፊነት አለባቸው። ብዙው ሰው ቤት ውስጥ የተነገረውን ነው እየሰማ የሚያድገው። በመሆኑም እናት አባት የድርሻውን መወጣት አለበት። የት ላይ ችግሩ እንዳለም ሁሉም አገር ወዳድ የሆነ አካል ቆም ብሎ የጠፋበትን ቁልፍ መፈለግም ይጠበቅበታል። ከዚያ መፍትሄው ቀላል ይሆናል። ብዙ ጊዜ ወደ ነበረበት እንመለስ ሲባል በባህሪ እንጂ በእድገት አይደለም። ምክንያቱም እድገት ወደፊት ነው። እናም የቀደመውን የቀዳሚነት ተግባራችንን እናጎልብት እንጂ ከዚያ እንውረድ የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2013