ሰላማዊት ውቤ
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እና በማህበራዊ መስኩ ከወንዶች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል በየዓመቱ ይከበራል። ጾታዊ ጥቃትን ለማስቆምና የህግና የሰብዓዊ መብታቸውንና ነፃነታቸውን ለማስከበር ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ለዚሁ ዓላማ ትግል ያደረጉ ሴቶችን በመዘከር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1975 በይፋ እንዲከበር እያደረገ ሲሆን፣ ዓለማቀፋዊ ይዘቱ የተጠናከረው በዓሉ እ.ኤ.አ ከ1911 ጀምሮ ነው። ቀኑ ዘንድሮም በዓለም ለ110ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
ይሄን በሀገራችን “የሴቶችን ሁለንተናዊ መብት የሚያከብር ማህበረሰብ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን እየተከበረ ያለው ይህ ቀን የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ዓላማዎቹን መሰረት በማድረግ ማክበር የጀመረው ከየካቲት 21/2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ይናገራሉ።
ሚኒስትሯ እንደሚሉት፤ አለም አቀፉ የሴቶች ቀን ወሩን ሙሉ በአራት መርሐ ግብሮች የሚከበርበት ስርዓት ተዘርግቶ እየተከበረ ነው። ከእሁድ የካቲት 21 እስከ የካቲት 28/2013 በነበረው የሣምንት ዕድሜ ‹‹ሴቶችና አመራርነት›› በሚል ርዕስ ሴቶች በአመራርነትና በውሳኔ ሰጪነት ዙሪያ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመፈተሽና ችግሩን የሚሻገሩበትን ሥራ መሥራት በሚያስችል ሁኔታ በመወያየት የመጀመሪያው መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የሁለተኛው መርሐ ግብር ‹‹ሴቶችና ትምህርት›› በሚልና ከትምህርት ጋር ተያይዞ ታዳጊ ሴቶች ባሉባቸው ማነቆዎችና ታዳጊዎቹን ማብቃትን መሰረት ባደረገ ተግባር ተከናውኗል። ቀሪዎቹ ሁለት መርሐ ግብሮችም በደርዛቸው መከበር ይቀጥላሉ። በዚህ ሳያበቃም አሁን ላይ የአመፅ እንቅስቃሴን መነሻ በማድረግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዕውቅና ለማግኘት የበቃውን ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን በዓመት አንድ ቀን ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ስለ መብቷ እያወሩ፣እየሰሩና እየታገሉ ማክበር ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። ሚኒስቴሩ ይሄን ከስኬት ለማድረስ ባደረጋቸው፣ እያደረጋቸው ባሉና ሊያደርጋቸው ባሰባቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ከሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ለመግቢያ ያህል ስለ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ታሪካዊ አመጣጥ፣ ዓላማውና አከባበሩ በአጭሩ ቢገልፁልን ?
ወይዘሮ ሙና አህመድ፦ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤በዓሉ መከበር የጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተደረገ ትግልን መሰረት አድርጎ ነው።መነሻው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1908 በኒውዮርክ ከተማ ነዋሪ የሆኑ 15 ሺህ ሴቶች የተሻሻለ የሥራ ሰዓትና የደመወዝ ክፍያን እንዲሁም የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር አደባባይ መውጣታቸው ነው።
ዓላማው ሴቶች በኢኮኖሚያዊ በፖለቲካዊ እና በማህበራዊ መስኩ እንዲሁም በጋራ ሀገር የጋራ ግንባታ ከወንዶች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ታሪካዊ ቀን ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረው በአውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድንና ጀርመን እ.ኤ.አ በ1911 ነው።ስያሜውን ያሰጠችውም በዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሀገን በተካሄደ ሁለተኛው የሴቶች ኮንፈረንስ የተገኘችው ክላራ ዜትኪን የተሰኘች ጀርመናዊት እንደሆነች ይነገራል። ይሄን ተከትሎም ቀኑ ዛሬም ድረስ በዓለም ላይ የሚገኙ ሴቶች ዘር፣ ቀለም፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት እንዲሁም መልክዐ-ምድራዊ ድንበር ሳይገድባቸው ሕብረት ፈጥረው ለነጻነታቸው፣ ለሰብዓዊ እኩልነታቸው፣ ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ በአንድነት ድምፃቸውን እያሰሙበት ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፦እንደ ሀገር ያለውን የዘንድሮውን በዓል አከባበር ቢገልፁልን?
ወይዘሮ ሙና፦ ዘንድሮ በዓሉን በተለየ ሁኔታ ወሩን ሙሉ ለማክበር በፌዴራልም በክልሎችም የተለያዩ ሥራዎች ስንሰራ ቆይተናል።ወሩን ሙሉ ሲባል ወሩን ሙሉ ለሴቶች መብት ትኩረት ይሰጣል ማለት ነው። መሪ ቃሉ ‹‹የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበረሰብ እንገንባ›› የሚል እንደ መሆኑ ከምንም በላይ ማህበረሰቡ ለሴቶች ያለውን የተዛባ አመለካከት የሚቀይር ሥራ መሥራት አለብን።
ሁሉም ማህበረሰብ በየደረጃው ሁሌም ስለ ሴቶች መብት እኩል እንዲናገር ማስቻል ይኖርብናል። ወሩን ሙሉ አልኩ እንጂ በዓሉ ዓመቱን ጠብቀን አንድ ቀን ብቻ የምናከብረው አለመሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት እንደሚገባ መናገር እፈልጋለሁ።እስከ አሁን በነበረው ሂደት ሁልጊዜ ቀኑን ጠብቀን አንድ ቀን ብቻ ነበር የምናከብረው።አሁን ላይ ቆም ብለን ስናስበው ለሴት ስለመብቷ አንድ ቀን ብቻ ማውራት ትክክል አይደለም ።ዓመቱን ሙሉ ልናወራላትና ዓመቱን ሙሉ የሴቷን መብት እያከበርን መሄዳችንን ማረጋገጥ አለብን የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል።
አንዱን ወርም ቢሆን ትኩረት እንዲሰጠው አደረግን እንጂ ዓመቱን ሙሉ የሴቶችን መብት ማክበር እንዳለብን በየደረጃው ማሰብ አለብን።እንደ ተቋም እንደ ግለሰብም ከቤታችን ጀምሮ እንዴት ነው የሴቶችን መብት እያከበርን ያለነው በማለት ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ፖሊሲዎች ፣ስትራቴጂዎች ምን ያህል የሴቶችን መብት እያከበሩ ነው ያሉት፣ የሕግ ማዕቀፎች ምን ያህል እየተተገበሩ ነው? የሚለውን መፈተሽ፣ምላሽ እንዲያገኝ መስራትና ምላሽ ማግኘቱንም ማረጋገጥ አለብን።
ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ወሩን ሙሉ ለማክበር አራት አበይት መርሐ ግብሮች ቀርፀን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። በዓሉን ማክበር የጀመርነው ከየካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ነው።ለአራት ሳምንታት የሚከበር ሲሆን የመጀመሪያው ሳምንት የካቲት 21 ‹‹ሴቶችና አመራርነት›› በሚል ርዕስ ሴቶች በአመራርነትና በውሳኔ ሰጪነት ዙሪያ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመፈተሽና ችግሮቹን የሚሻገሩበትን ሥራ መሥራት በሚያስችል ሁኔታ በመወያየት ተካሂዷል።
አራቱ አብይት መርሐ ግብሮች የየራሳቸው ዝርዝር ሥራዎች ያሏቸው ሲሆን በሁለተኛው ሳምንት ያለው መርሐ ግብር ደግሞ ‹‹ሴቶችና ትምህርት››በሚል ርዕስ ታዳጊ ሴቶች በሚገጥሟቸው መሰናክሎች ላይ በማተኮርና መፍትሄ በማፈላለግ ተከብሯል። ሦስተኛው ሳምንት መርሐ ግብር ‹‹ሴቶችና ኢኮኖሚ››በሚል የሚከበር ሲሆን፣ በአራተኛው ሳምንት ላይ የሚካሄደው መርሐ ግብር ዛሬም ያልተሻገርነውን ጾታዊ ጥቃትን መከላከል መሰረት አድርጎ ይከናወናል።
በተለይ በኮቪድና ግጭቶች በተፈጠሩበት ወቅት ሴቶችና ህፃናቶች የጥቃት ሰለባ የሆኑበት አጋጣሚ ስለመኖሩ በመስክ ምልከታ የተደገፈ መረጃ አለን። በቀጣይ ሴቶች ለእዚህ ዓይነቱ ድርጊት እንዳይጋለጡ ማድረግ የሚያስችል ሥራ ይካሄዳል።ይሄ ሲሰራ ከጾታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ የተቋቋመ ግብረ ሀይል /ታስክ ፎርስ/ አለ።የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ጤና ተቀናጅተው በዚህ ላይ ይሰራሉ።
ይሄን መሰረት አድርገን እንደ ተቋም ጾታዊ ጥቃትን ከመከላከል አኳያ ‹ብሄራዊ የጾታዊ ጥቃት ወንጀል› የመረጃ ስርዓት እየዘረጋን ነው። ለዚህ የሰነድ ዝግጅት አጠናቀናል። በቀጣይ ከሚመለከታቸው የተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተፈራርሞ ወደ ሥራ መግባት ነው የቀረን።ሥራው ትልቅና እንደ ሀገር የመጀመሪያ ነው።ዋናው ዓላማው ጥቃት አድራሾች መረጃቸው በትክክል እንዲያዝ ማስቻል ነው።ይሄ ወንጀልን ከመከላከል አኳያ ሕብረተሰቡንም ለማስተማር በእጅጉ ይረዳል። አጥቂዎች ዳግም ጥቃት እንዳይፈፅሙ ለማድረግም አስተዋጽኦው የጎላ ነው። ከጾታዊ ጥቃት መከላከል ጋር ተያይዞ ትልቁ ችግር መረጃ ሲሆን እንደ አንድ የመረጃ ምንጭ በመጠቀም ወንጀሉን መከላከል ያስችላል።
አዲስ ዘመን፦ ለነዚህ ክፍተቶች መንስኤው፣ ክፍተቶቹን ለመሙላትስ እየተወሰደ ያለ መፍትሄ ምንድነው ይላሉ?
ወይዘሮ ሙና፦ አንዱ መንስኤ በህብረተሰብ ውስጥ ለሴቶች ያለው የተዛባና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአመለካከት ችግር ፣የወንዶች የበላይነት መስፈን፣አንዳንድ ሴቶች ለራሳቸው ያላቸውን አመለካከት ዝቅ እያደረጉ ያሉበት ሁኔታ፣ወይም በራስ መተማመን መጥፋት፣የሕግ አተገባበርና የአፈፃፀም ችግር ነው።
ሌላው ራሱን የቻለው መንስኤ በ1985 ዓ.ም የወጣው የሴቶች ፖሊሲ ነው።ይሄ ማለት ሕገ መንግሥቱና የሴቶች ፖሊሲ አይጣጣሙም ማለት ነው።ፖሊሲው ብዙ ነገሮች ይጎሉታል።እንደ ተቋም ጉድለቱን የመሙላቱ ሥራ ተጀምሯል።ድጋሚ እየተከለሰ ያለበት ሁኔታ አለ። አቅጣጫ የማስቀመጥና ክፍተቱን የመፈተሽ፣ ሕጎች እንዴት እየተተገበሩ ነው በማለት በደንብ ተዟዙሮ ማየት ያሻል።
አሁን ዓለም የወንዶች የበላይነት ይታይባታል።ከዚህ አንፃር አንዳንድ የወንዶችን ሀሳቦች ሴቶች የሚጋሩበት ሁኔታ ይታያል፤ እዚህ ላይ በሚገባ መሥራት ያስፈልጋል። እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንሁን ስንል የመብትም ጉዳይ ነው።የመብት ጥያቄያችን በዚህ ደረጃ ነው ወይ የሚታየው የሚለው ሥራ ይፈልጋል። በመሆኑም አስተሳሰብ ላይ በየደረጃው መሥራት ይጠይቃል።በዚህ በኩል ሁሉም መገናኛ ብዙኃን ሊሰሩበት ይገባል።
ሴቶች በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ደረጃ መምጣት አለባቸው የሚለው ከመብትም አኳያ መታየት አለበት ። ወንዶች ሰጪ እኛ ተቀባይ መሆን የለብንም የሚል እምነት አለኝ።በቃ መብታችን ነው! ዕድሉን ብናመቻችላቸው ፣ብንደግፋቸው ብናበቃቸው በእርግጠኝነት ነገ የሀገር መሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሴቶች ማየት እንችላለን ። በዚህ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ሆኖም ደጋግሞ ወደ ታች እየወረድን ስንሄድ ዝቅ እያለ የሚሄድበትን በሚገባ ማየት ያስፈልጋል። ወረዳ ላይ በአስፈፃሚነት ያሉ ሴቶች 25 ነጥብ 9 በመቶ ብቻ ናቸው ።
በፌዴራል ደረጃ ያለው 50 በመቶ የሴቶች ተሳትፎ እንዳይቀንስ ሥራዎችን ተቀናጅቶ መሥራት ይፈልጋል ። በስተኋላ ላይ ቀድመን ያልዘራነውን ማጨድ ስለማንችል ዛሬ ሴቶችን ማብቃት፣ዕድሎችን ማመቻቸት ይገባል።
ሴቶች ሁኔታዎች ስላመቻቸንላቸውና ዕድል ስላልሰጠናቸው ነው እንጂ ይችላሉ ። አሁን ላይ እጅግ ጠንካራ ነገ ሀገር መምራት የሚችሉ ሴቶች እያየን ነው።በቀጣይም በዚህ ደረጃ ውጤት የሚያመጣ ሥራ መሥራት አለብን ብለን እንደ ተቋም ያቀድናቸው አሉ። በተለይ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ ታዳጊ ሴቶች አርአያ የሚሆናቸው ይፈልጋሉ ። ከዚህ አንፃር የተጀመረ መርሐ ግብር አለ ። በቀጣይ ሰፍቶ የሚሄድበት ሁኔታም ተመቻችቷል።
አዲስ ዘመን፦ ሴቶች ምን እየጠየቁ ናቸው ፣እንዴት መታየት አለባቸው? አፈታቱስ እንዴት መሆን አለበት? ጥቅሙ ምንድነው?
ወይዘሮ ሙና፦ የሴቶች ጥያቄ የመብት ጥያቄ ነው፣የተሳትፎ ጥያቄ ነው፣የተጠቃሚነት ጥያቄ ነው ። ጥያቄዎቹን ነጣጥለን ማየት የለብንም ። የመብት ጥያቄ ስለመለስን ሌላው አብሮ ተመልሷል ተብሎ የሚተው አይደለም ። የሴቶች የእኩልነት መብት ጥያቄን ካረጋገጥን ሀብት ምንጮች ላይ የመጠቀም መብት ያገኛሉ ። በኢኮኖሚም ስናበቃቸው ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ይፈታሉ ። በመሆኑም የሴቶችን ጥያቄ ነጣጥለን መመለስ የለብንም ። የሴቶችን ጥያቄ ሁሉንም አስተሳስረን መመለስ ይገባናል። አስተሳስሮ ካልተመለሰ ክፍተት ስለሚፈጠር የማህበራዊ ተጠቃሚነቷን በመመለሳችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷ ተመለሰ ማለት አይቻልም ። የመብት ጥያቄዋ ተመለሰ ማለት አይቻልም ። በመሆኑም እነዚህን ሳንነጣጥል አብረን አስተሳስረን ልንመልስ ይገባል ።
ይሄን ለማድረግ በሴቶች መዋቅር የሚሰራው እንደተጠበቀ ሆኖ በየደረጃው ያለው አመራር በያለበት ለሴቷ ጠብ የሚል ነገር መሥራት አለበት ። የሚደነቁ ጅምሮች ቢኖሩም አሁንም ድረስ ሴቶች በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚያዊውም ሆነ በማህበራዊ መስኩ ተጠቃሚ ነን የሚል የለም ። በመሆኑም ጅምሮቹን አጠናክረን ክፍተቶቹን ሞልተን ለመጪው ትውልድ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንችላለን። ይሄን ማድረግ በየደረጃው ያለውን አካላት ትብብር ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ የወንዶች አጋርነት አስፈላጊነት ምን ያህል ነው?
ወይዘሮ ሙና፦ አሁንም በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት አልቆመም።በመሆኑም ከምን ጊዜውም በላይ የወንዶች አጋርነት እጅግ ያስፈልጋል ። ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ካለብን ወንዶችን ማሳተፍ የበለጠ ይጠቅማል ። ሰጪና ተቀባይ ዓይነት ሳይሆን እኩል ዕድል ሊፈጠርልን እንደሚገባ መረዳት አለባቸው። የጋራ ሀገር እስካለን ድረስ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ እኩል መሳተፍ እንዳለብን ማወቅ አለባቸው።
ሴቶች ደካማ ስለሆን አይደለም፤ ከታች ይዘን የመጣናቸው ችግሮችና ድርብ ኃላፊነቶች አሉብን ። ሴቷና ወንዱ በቤት ውስጥ እኩል አይደለንም ። እኛ የቢሮም ሥራ እንሰራለን። እቤትም ስንገባ ልጆችና ቤተሰብ ከመንከባከብ ጀምሮ የቤት ውስጥ ሥራ ይጠብቀናል ።
የገጠር ሴቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በቤት ውስጥ ሥራ ነው።በዚህ ላይ የተደረጉ አንዳንድ ጥናቶችን ሲታዩ የኢትዮጵያ ሴቶች ስንት ሰዓት ነው የሚሰሩት? በማለት ያስደነግጣሉ። በመሆኑም ወንዱ በቤት ውስጥ ይሄን ጫናዋን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን እንድትጠቀም በማድረግ ሊያግዛት ይገባል።
ሴቶች በዚህ ውስጥ አልፈው ነው ከፍተኛ ስልጣን ላይ ሆነው ሀገራቸውን እየመሩ የሚገኙት ። መምራት ታች ከቤተሰብ ከማስተዳደር እንደመጀመሩ እየተለማመድነው ነው የመጣነው ። በግሌ ሴቶችን ወደ አመራርነት የሚያመጣ መንግሥት ወይም መሪ እጅግ የገባው ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ወንዶች ታማኝ አይደሉም እያልኩ ሳይሆን ሴት የበለጠ ታማኝ ነች ። አንድ የቤት ሥራ ከተሰጣት የቤት ሥራው ሳይበላሽ ከግብ እንዲደርስ ትጥራለች ። ይሄ ምን ያህል ኃላፊነት የሚሰማት እንደሆነች ነው ያመለክታል። ከዚህ አንፃር ለሴቶች የወንድ አጋርነት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለምን ማንሳት አስፈለገ ?
ወይዘሮ ሙና፦ ከጾታ ስብጥሩ ስንነሳ ከሕዝቡ ብዛት 50 በመቶው እንዳውም ከዚያ በላይ ሴቶች ናቸው ። እነዚህን ሴቶች በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ተጠቃሚ ካላደረግናቸው እንደ ሀገር ያሰብናቸው የብልፅግና ጉዞና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች ሊሳኩ አይችሉም ። ምክንያቱም 50 በመቶውን ሴቶች ተደራሽና ተሳታፊ ሳናደርግ የሚመጣው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ውሱንነት ይኖርበታል ።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ሀገር በፖለቲካው መስክ በየደረጃው የሴቶች ተሳትፎ ምን ላይ ይገኛል? በተለይ በለውጡ የታየ መሻሻልና የውጪ ተሞክሮ ካለ?
ወይዘሮ ሙና፦ በፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ከለውጡ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ አመርቂ ውጤቶች መጥተዋል። መሻሻሎችም ታይተዋል ።ለምሳሌ፦የሴቶችን አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ብናይ በፌዴራል መንግስት አስፈፃሚ ደረጃ 50 በመቶ የደረሰበት አለ። በክልል ሲታይ 19 በመቶ ነው። ወደ ሕግ አውጭ ሲመጣ በፓርላማ ደረጃ 38 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል ። የክልል ደግሞ 40 ነጥብ 5 ላይ ነው ።
ከሕግ ተርጓሚ አንፃር በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሴቶች ተሳትፎ ቁጥሩ እየቀነሰ የሚመጣበት ሁኔታ ይስተዋላል ። ብዙ ሴቶች ሕግ ተርጓሚው ላይ የማይገቡበት ሁኔታ አለ ። ለአብነት በፌዴራል ደረጃ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ላይ ያለውን የሴቶች ተሳትፎ ብናይ 27 በመቶ ነው ። ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላይ ሲኬድ 18 በመቶ ደርሷል ። በፌዴራል ደረጃ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ያለውን ተሳትፏቸውን ስናይ 60 በመቶ ነው ። ሆኖም ወደ ላይ እየወጣ በመጣ ቁጥር የሴቶች ተሳትፎ ዝቅ እያለ የሚመጣበት ሁኔታ አለ ።
አጠቃላይ ሴቶች በሕግ አውጪ፣በሕግ አስፈፃሚ፣በሕግ ተርጓሚ ያላቸው ድርሻ 30 በመቶ ነው። ይሄ ስሌት የሚያመለክተን ሴቶች በማህበራዊው፣በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊው ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል በአመራርነት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ነው።
በዚህ በኩል ጥሩ ተሞክሮ ተደርጎ የሚወሰደው የስፔን ሲሆን፣ ከፓርላማው 64 በመቶው ሴቶች ናቸው። የእኛም በቀጣይ የማይሆንበት የለም ማለት እንችላለን ። ለዚህም ጅምሮች አሉ ። በተለይ ሴቶችን በሚገባ መልኩ አለማሳተፍ የእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሀገሮችም ችግር ነው ። የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሴቶች በሚፈለገው መልኩ እየተሳተፉ አይደለም ።
አዲስ ዘመን፦በማህበራዊውና በኢኮኖሚያዊው መስክ ያሉበት ደረጃስ እንዴት ይታያል?
ወይዘሮ ሙና፦ ከ50 በመቶው አጠቃላይ የሴቶች ቁጥር አብላጫውን የያዙት ሴቶች ገጠር ነው ያሉት። ከጠቅላላው ሀገራዊ ገቢ ዋናው በሆነው ግብርና የሴቶች ተሳትፎ 45 በመቶ አካባቢ ነው።
በቅርቡ የቀረበ የስራ ዕድል ኮሚሽን የስድስት ወር ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ በስድስት ወሩ ከተፈጠረው ሥራ የሴቶች ድርሻ 35 በመቶ ነው ። ከዚህ አንፃር ሴቶች አሁንም ከወንድ እኩል ተጠቃሚ ያልሆኑበት ክፍተት አለ ። በመሆኑም በኮታ ሴቶችን ማሳተፍ የግድ ነው ። የሀገር ዕድገት እንዲመጣ 50 በመቶውን ሴት ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ ያሻል።
ግብርና ላይ ያሉት መረጃዎችም ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ይጠቁማሉ ።ይሄ በኤክስቴሽንና በብድር አቅርቦት ቢታይ ኤክስቴሽን ላይ ያለው የሴቶች ምጣኔ 11 በመቶ ነው ። በብድር አቅርቦት ደግሞ ዘጠኝ በመቶዎቹ ናቸው ተጠቃሚ የሆኑት ። ግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ሲታይም ሴቶች ያሉበት ደረጃ 27 ነጥብ 4 በመቶ ነው ። ይሄ ግብርና ላይ የሴቶች ተሳትፎ ውሱንነት እንዳለበት በግልፅ ያመለክታል።
እዚህ አካባቢ ቆጥሮ መፍትሔ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ። ከመሬት ባለቤትነት ጋር ማውረስና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውሱንነቶች አሉ ። በአብዛኛው ሴቶች የተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ሲቃኙም ያሉት መደበኛ በሆኑ ዘርፎች አይደለም ። ወደ እዚህ ያመጣቸው ምንድነው የሚለው በቀጣይ በተለይ ከሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዘ ሥራ ይፈልጋል ።
እንደ ፕላን ኮሚሽን ጥናት፤ ሴቶች በኢኮኖሚው ባለመሳተፋቸው ወይም በሴቶችና በወንዶች መካከል ባለው ልዩነት ሀገር ከኢኮኖሚው 3ነጥብ7 ቢሊዮን ብር ታጣለች ። ይሄ አሁንም ሴቶች በኢኮኖሚ ውስጥ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ያመለክታል ።
እንደ ተቋም በታቀደው የ10 ዓመት ዕቅድ ሴቶች በራስ አገዝ ቁጠባ እየቆጠቡ ወደ ሕብረት ሥራ ማህበር እንዲገቡ የተደረገበት ሁኔታ አለ ። በቅርቡ ይፋ የሚሆን ‹‹50 ሚሊዮን ሴቶች ይናገሩ›› የሚል ፕላት ፎረም እንዲኖር ይደረጋል ። ወደ ገቢ ማስገኛ የሚገቡ ሴቶች መረጃ ስለሌላቸው ከአፍሪካ እህቶቻቸው ጋር ይሄን መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ ፕላት ፎርም ተዘጋጅቶ በዓለም የሴቶች ቀን አከባበር መርሐ ግብር ላይ ይፋ ይደረጋል ።
ሴቷን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ ሥራ ይፈልጋል ። ለዚህ በተሰማሩባቸው የስራ ዘርፍ ምንድነው ያለባቸው ውሱንነት የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። ብድር አቅርቦትና ኤክስቴንሽን ላይ ለምን መጠቀም አልቻሉም የሚለውን በዝርዝር አይቶ ከምንም በላይ የሴቷን ጉልበትና ጊዜ የሚቆጥቡ ቴክኖሎጂዎችን መሰረት አድርጎ መሥራት ይጠበቃል ። ከዚህ አንፃር እስከ አሁን የተሰሩ ሥራዎች ቢኖሩም በቀጣይ አዋጪ የሆኑና ጊዜዋን የሚቆጥቡ ሥራዎች ይሰራሉ ። ሥራው በራሳችን ጀምረን የምንጨርሰው ሳይሆን ብዙ ተቋማት ውስጥ የሚገባ ነው ። ከግብርናና ፣ከሕብረት ሥራ ማህበር ጋር የግድ ተቀናጅቶ መሥራትን ይጠይቃል።
በማህበራዊው መስክ ሴቶች ያሉበትን ስናይ ቀዳሚው ከትምህርት አኳያ ያለው ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ እጅግ በሚበረታታ ሁኔታ 95 ነጥብ 4 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ ናቸው።ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲመጣ ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍል 28 በመቶ ተጠቃሚ የሆኑበት አለ ። ወደ ላይ እየቀነሰ የሚሄድበት ፒራሚድ ቅርጽ ነው ያለው ። መጀመሪያ ዲግሪ ላይ 36 በመቶ ናቸው ። ሁለተኛ ዲግሪ ላይ ሲመጣ 23 በመቶ በዶክትሬት ደረጃ ሦስተኛ ዲግሪ እየተባለ ሲኬድ የመሳተፍ ምጣኔያቸው እጅግ ዝቅ ብሎ በመቀነስ ስምንት በመቶ ይወርዳል።
እየቀነሰ የሚመጣበትን ሁኔታ ለማስተካከል ታዳጊ ሴቶች ላይ መሥራት አለብን ። ታዳጊ ሴቶች በትምህርት ሂደት ውስጥ የሚገጥሟቸውን ባዮሎጂካል ችግሮች ብንቀርፍላቸው ውጤታማ ይሆናሉ።
ሴት ልጅን ማስተማር ሀገርን ማስተማር እንደመሆኑ ሴት ልጅን ሳናበቃ ስለ ትምህርት መናገር አንችልም። ለማብቃት ምጣኔው ወደ ላይ ከፍ እያለ ሲሄድ ለምንድነው የሚቀንሰው የሚለው ታይቶ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል ። በዩኒቨርስቲም የተጀማመሩ አሉ።
አፈርማቲቭ አክሽን ላይ ከሴቶች አኳያ ከፍተኛ ትምህርት በደንብ ነው የሚጠቀምበት ። ሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጠው አፈርማቲቭ አክሽን ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል አብነት ወሰድን ሥራ ቅጥር ቢታይ አፈፃፀሙ ውሱንነት አለበት ። የዚህ ችግር ምን እንደሆነ እያስጠናን ነው ። ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ ነገሮች ወደ መሬት ሲወርዱ ለምንድነው የሚሸራረፉት የሚለውን በጥልቀት ማየት ይፈልጋል።
በጤናው መስክ የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አኳያ መሻሻሎች አሉ። ሆኖም አሁንም ቤት ውስጥ የሚወልዱና በዚህ ምክንያት ለሞት የሚዳረጉ ህፃናትና እናቶች ስላሉ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል።
የሴቶች መዋቅር ሕብረተሰቡ በቅርብ ባለው ማዕከል እንዲሰራ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሄደ የተሻለ ደረጃ ማምጣት እንችላለን። በትምህርት፣ በጤና የተጀመሩትን መልካም ነገሮች ማስቀጠል ያስፈልጋል ።
ሰሞኑን ሳነብ እንዳየሁት ከእናቶች ጋር ተያይዞ በማህፀን ጫፍ ካንሰር በየዓመቱ 6ሺህ500 ሴቶች ይያዛሉ። ከነዚህ መካከል አምስት ሺውን በበሽታው እያጣን ነው ። እነዚህን ችግሮች ህብረተሰቡን አነቃንቀን የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ግድ ይላል ። በህብረተሰቡ አመለካከት ላይ ለውጥ ለማምጣት መስራት ቀዳሚ ተግባር ማድረግ አለብን ።
አዲስ ዘመን፦በአጠቃላይ አሁን ላይ እንደ ተቋም እየተሰሩ ያሉትን በተለይ ከሴቶች አደረጃጀቶችና ከምርጫ አኳያ ያሉትን ቢያብራሩልኝና መልዕክት ቢያስተላልፉልን ?
ወይዘሮ ሙና፦ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ታሪካዊ ምርጫ ነው ። ታሪካዊ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ብዙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መጥተው የሚፎካከሩበት መሆኑ ነው። እስካሁን ካደረግናቸው ምርጫዎች በዓይነቱ፣ በይዘቱም በጥራቱም የተለየ ምርጫ ነው ብዬ ነው የምወስደው።
የመብትም ጥያቄ ስለሆነ ከሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሴቶች በምርጫ እንዲሳተፉ የተግባቦት ሥራ አድርገናል ። እያደረግንም እንገኛለን። እስከ አሁን ባለኝ መረጃ ከመራጮች 45 በመቶው ሴቶች ናቸው። በመመረጥ ብቻ ሳይሆን በመምረጥ ውስጥ አስተዋጽዖ አለን። 45 በመቶ አስተዋጽዖ ቀላል አይደለም ። ያለንን ድርሻ በደንብ (ኤክሰርሳይስ) ልምምድ ልናደርግበት ይገባል።
መላው ሴቶች በነቂስ ወጥተን መመዝገብ አለብን። በነቂስ ወጥተን የሚበጀንንና የሴቷን ጥያቄ ይመልሳል የምንለውን መምረጥ አለብን። ይሄን ዕድል መጠቀም የምንችለው ለምርጫ ስንመዘገብ ብቻ ስለሆነ ሴቶች የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው መርሐ ግብር መሰረት ሊመዘገቡና የሚወክላቸውን ሊመርጡ በሚወክሉት ደግሞ ሊመርጡ ይገባል። ሁሉም ሴቶች ወጥተው መምረጥ አለባቸው። በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ እኩል መሳተፍ እንዳለብን ማወቅ አለባቸው።
ይሄ ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረክታል። የዴሞክራሲ መብታችንን የምንለማመደው በምርጫም በሌላውም ነው ። ምርጫ ላይ እንሳተፍና እኩል እንወከል ስንል መብታችንን እየጠየቅን መሆኑ መታወቅ አለበት። መብታችን ከወረቀት ባለፈ ሊከበርልን ይገባል።
ጅምሮች አሉ፤ ጅምሮቹ ወደ ታች ዝቅ እያሉ ስለሚሄዱ እያነሱ የሚሄዱበት ሁኔታ ስላለ መታየት አለበት። በተጨማሪም ሴቶች ተደራጅተው ድምፃቸውን ሊያሰሙ ይገባል። ይሄ ሲባል አደረጃጀቶቹ በራሳቸው ያለባቸው ውሱንነት እንደተጠበቀ ሆኖ ነው።
አደረጃጀቶቹን በቀጣይ ሪፎርም ማድረግ ያስፈልጋል። እኛ በተጠናከርን ቁጥር ድምፃችን ይሰማል። ትግል የምናደርገው ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖልን አይደለም። አደረጃጀቶች መንግሥትን የሚሞግቱ ለሴቷ ድምፅ የሚሆኑ ጠንካራ ቢሆኑ ብዙ ነገሮች መስራት ይቻላል። ድምጻቸው ይሰማል።
አንዳንድ ተቋማት ላይ በማኔጅመንት ውስጥ አንዲት ሴት ብቻ ትኖራለች። ሌላው ተቋም ላይ ሰፋ ያለ ቁጥር ሊኖር ይችላል። በበዛን ቁጥር ውሳኔ ማስለወጥ እንችላለን። ሕጉ እንዳለ ሆኖ ስንበዛ አንዳንዴ በድምፃችን እንኳን መሻር፣የሴቶች ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ እንችላለን። እኛ በበዛን ቁጥር የሴቶች ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ እንችላለን ። ተቋማት በዚህ ልክ አስበው ሴቶችን የማብቃት፣ የመደገፍ፣ ሥራ መሰራት አለባቸው።
አዲስ ዘመን በዝግጅት ክፍሉ ስም እናመሰግናለን።
ወይዘሮ ሙና ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2013