አዲስ አበባ፡- በአህጉሪቱ የሚከሰቱ መፈናቀሎችን ለመከላከል ሀገራት ዘላቂ መፍትሄ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር አሳሰቡ።
ኮሚሽነሯ ሙለታ ሳማቲ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት፣በአህጉሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ የሀገር ውስጥ መፈናቀሎችን ስደትንና የስደት ተመላሽ ችግሮችን ለመፍታት ስትራቴጂያዊ የሆኑ ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።
አፍሪካ ህብረት ከአባል ሀገራት ከቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የልማት አጋሮች ጋር በቅርበት መስራትም እንዳለበት አብራርተዋል። ግጭቶችን በመከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባልም ብለዋል። ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ ደግሞ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትሉ መስራት ከመፍትሄዎቹ አንዱ ነው ብለዋል።
እንደ ኮሚሽነሯ ማብራሪያ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት እኤአ በ1969 የወጣውን የስደተኞች ስምምነትና እ.አ.አ በ2009 የተፈረመውን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ስምምነት እንዲፈርሙ እንዲያጸድቁና ገቢራዊ እንዲያደርጉ ግፊት መደረግ አለበት።
በ2020 ለማሳካት የታቀደውን ከተኩስ ድምፅ ነጻ የሆነችና የጦርነት ዜና የማይሰማባት አህጉር እውን ለማድረግ የተቀመጠውን ፍኖተ ካርታ ለማሳካት ጥረት ማድረግ ከስትራቴጂያዊ መፍትሄዎቹ ተጠቃሽ ነው። የአፍሪካ ሀገራትም ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅም አላቸው ብለዋል።
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት አብዛኞች በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶች በሀገራት መካከል ነበር ያሉት ኮሚሽነሯ በአሁኑ ወቅት ግን አብዛኞቹ ግጭቶችና የመፈናቀል መንስኤዎች በሀገራት ውስጥ የሚከሰቱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ናቸው ብለዋል ። እንደ ኮሚሽነሯ ማብራሪያ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ስድስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመያዝ ከአለም ተፈናቃዮች ምጣኔ ውስጥ የአንድ ሶስተኛው መኖሪያ ነች ። በተመሳሳይ 14 ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችም አሉ፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/201