አስመረት ብስራት
በስለሺ ስህን ህንፃ ስምንተኛ ፎቅ ላይ የከተመው የኤውብ ቢሮን በር አንኳኩቼ ስገባ አይኔ ከጥበብ ጋር ተገናኘ። የሰአሊ ደስታ ሀጎስ ስእሎች በግድግዳው ላይ ተሰቅለዋል። በጠረጴዛ ላይ ወፈር ያለ ነጭ ሻማም በርቷል።
በቢሮው ወስጥ ያለው እያንዳንዱ ቁሳቁስ አይን ከመያዙ የተነሳ የቱን አይቼ የቱን ልተው በሚል ሙሉ ቢሮውን እየደጋገምኩ መቃኘት ጀመርኩ። ፀሃፊዋ የተቀመጠችበትን የመጀመሪያውን ክፍል አልፌ ወደሚቀጥለው ክፍል ስገባ ከስፋቱ በላይ በፈገግታ የተሞሉ የሴቶች ፎቶግራፎች ተሰቅለውበታል። እንደማለዳ ፀሀይ በሚያንፀባርቅ ፈገግታዋ በአክብሮት ተነስታ የተቀበለችኝ የኢትዮጵያ ጽኑ ሴቶች ማኅበር (ኤውብ) መስራች ወይዘሮ ናሁ ሰናይ ግርማ ነበረች።
ኤውብ ከዓመታት በፊት በናሁሰናይ ግርማ አማካኝነት የተመሰረተ ሲሆን፤ እጅግ ብዙ ሴቶች የቋንቋና የንግድ ክህሎት እንዲሁም የተለያዩ ስልጠናዎችን አግኝተውበታል። በተጨማሪም ማህበሩ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሴቶች እርስ በርስ ትስስር የሚያደርጉበት፣ በስራቸው የበቁ እና የላቁ ሴቶች እውቅና እና ድጋፍ የሚያገኙበት እንዲሁም በፖሊሲ ደረጃ ተፅዕኖ የሚያሳድሩበት ለመሆን ችሏል፡፡
ከወይዘሮ ናሁ ሰናይ ጋር በቀጠሯችን ሰአት እንደተገናኘን በብዙ ቁም ነገሮች የታጀበ ጭውውት አድርገናል። ወይዘሮ ናሁ ሰናይ ያጫወተችኝን በራሷ አንደበት እነሆ። መልካም ንባብ።
ወይዘሮ ናሁ ሰናይ ግርማ እባላለሁ። ናሁ ሰናይ ማለት አሁን ደስታ አሁን መልካም ማለት ነው። አባቴ የመጀመሪያ ልጃቸው ሴት እንድትሆን የነበራቸው ምኞት ሲሳካላቸው፤ ናሁ ሰናይ ብለው ስም አወጡልኝ። እኔም ስሜን የምመስል ሰው ነኝ ብዬ አስባለሁ። ይህን ስልሽ ብርሃናቸውን ላላገኙ ሰዎች በተለይም ሴቶች የጥበብ ብርሃን ለማሳየት ነበር ሀሳቤ፤ ያም ተሳክቶልኛል ብዬ አስባለሁ።
ስራውን ለመጀመር ሳስብ ቢያንስ አንድ ሰው ያለውን አቅም አውቆና አውጥቶ መሪ እንዲሆን ለማስቻል አስቤ ነበር። ይህን ለማድረግ ስነሳ ፊቴ ላይ የምትመለከቱት የተሳካ ስሜትና ፈገግታ ነው እያልኩ ሁሌ እናገራለሁ። የእኔ ስራ የሴቶችን አይን መክፈት ነው። ያም ስለተሳካ ነው በመጨረሻው ሰአት ፊቴ ላይ ፈገግታ የሚታየው።
በ1944 ዓ.ም ሚያዚያ 21 መቀሌ ላይ ነበር የተወለድኩት። እናቴ ከትግራይ፣ አባቴ ደግሞ ከአርሲ አሮሞ የተገኙ ሙስሊም ነበሩ። በምኒልክ ዘመን ከ12 አሰተዳዳሪ ቤተሰቦች የተወለዱ ሴቶችን አምጥተው አጋብተው ክርስቲያን ካደረጉ በኋላ በግማሽ ጎን አማራ በግማሽ ጎኑ ደግሞ ኦሮሞ የሆኑት አባቴ ከትግራይ ሴት ስለወለዱኝ እኔ ማለት ጥርት ያልኩ ኢትዮጵያዊት መሆኔን የሚያስረዳ ነው። በእኛ ጊዜ እንዲህ እንደዛሬው ዘር የማይቆጠርበት ዘመን መሆኑንም ለማሳየት ብዬ ነው የትውልድ ሀረጌን የምገልፅልሽ።
ከዛ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ኑሯቸውን ካደረጉት ወላጆቼ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ አደኩኝ። እድሜዬ ሰባት አመት ሲሆን የታናሽ እህቴ ደግሞ አምስት አመቷ እንደሆነ ነበር በእቴጌ መነን ያኔ አዳሪ ትምህርት ቤት የገባነው።
ከዛ በኋላ አሜሪካን ሀገር በስነ ምግብ ዘርፍ እንዲሁም በቢዝነስ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዎቼን ካገኘሁ በኋላ በኮርፖሬት ትሬዲንግ የማስተርስ ዲግሪዬን ያዝኩ። በሂዩማን ሪሶርስ ዴቨሎፕመንት ላይም የረጅም ጊዜ የስራ ልምድ ያገኘሁ በመሆኑ ወደ ሀገሬ ገብቼ የኢትዮጵያ ጽኑ ሴቶች ማኅበር (ኤውብ) በመመስረት ሁሉም ሰው መምራት እንደሚችል የማሳየት ስራን እየሰራሁ እገኛለሁ።
ሰው ራሱን መምራት ካልቻለ ቤተሰቡን መምራት አይችልም። አመልካች ጣቴን አውጥቼ ወደ ሌላ ሰው ስመለከት ሶስቱ ጣቶቼ ወደ እኔ ሆነው ራሴን እንድጠይቅ ያደርጉኛል። እኔ ማን ነኝ? ምን ሰራሁ የሚል አስተሳሰብ ያለው መሪ ነው ትክክለኛ መሪ። እራሱን የገራ መሪ ሌሎችን መግራት የሚችል ጥንካሬ ይኖረዋል ማለት ነው።
አዳሪ ትምህርት ቤት ማደጌ ጠንካራ ለመሆን እድል ሰጥቶኛል። ቤት ውስጥም በተለያዩ ክልከላዎች አለማደጌ በጥንካሬ ለመኖር አስችሎኛል። በእኔ እምነት ሴቶች በአዳሪ ትምህርት ቤት ብቻቸውን ማደጋቸው ጥንካሬ ይሰጣቸዋል። አባቴም በልጅነቴ ስለሞተ ከ9 አጎቶቻችንና አክስቶቻችን የተለየ ፍቅርና እንክብካቤ በቂ ነፃነትና ፍቅር ማግኘቴ እንዲሁም የተለያየ አስተሳሰብ እያዳበርኩ ማደጌ ለዛሬው ማንነቴ መሰረት ሆኖኛል። የተማሪዎች የትግል እንቀስቃሴ ውስጥ ስሳተፍ መቆየቴም የሀገር ሀላፊነትን ለማሰብ እንድችል ፍፁም ሀገር ወዳድ እንድሆን አድርጎኛል።
ይሄኛው ወጣቱ ትውልድ ተስፋ የሚጣልበት መሆን ይኖርበታል። በኢትዮጵያ ትውልድ ላይ የተሰራ ወንጀል ብዬ የማነሳው ስርዓተ ትምህርቱ መውደቁን ሳይ ነው። ትምህርት በጣም ወድቋል። ሰዎች ማሰብም መጠየቅም እንዳይችሉ ሆነዋል። ደርግ በጣም በማስፈራራት ውስጥ ስላቆየን መጠየቅ እንዳንችል አድርጎናል። አሁን የሚገኙት ወጣቶች በዛን ጊዜ ከደነገጡ ወጣቶች የተወለዱ ልጆች ናቸው። ስለዚህ ከየትም ሊመጡ ባይችሉም ትምህርት ቤቶች ጠያቂ ትውልድ ማፍራት አለባቸው።
አሁን ያለው ወጣት የተሰጠውን የሚቀበል የሆነው በትምህርት ስርዓታችን ድክመት የተነሳ ነው። መምህራኖቹ እንኳን ጥያቄ የሚጠይቅ ትውልድ ሊፈጥሩ ይቅርና የማስተማር አቅማቸው ከደረጃ በታች የሆኑ ብዙ ተቋማት አሉ።
ለምሳሌ በጋምቤላ 12 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እውቅና ያልተሰጣቸው መኖሩ ለዚህ መሳያ ነው። ሌላው ከአመታት በፊት አስር ሺህ የሁለተኛ ደረጃ አስተማሪዎች የሚያስተምሩትን ትምህርት ተፈትነው አምስት በመቶ ማለፊያ ነጥብ ሲያገኙ ዘጠና አምስት በመቶው ወደቁ። በእነዚህ መምህራን ነው እንግዲህ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ወጣቶች የሚወጡት።
ትውልድ ለማውጣት፣ ሀገር መሪ ለመፍጠር ትምህርትና ጤና ላይ መሰራት ይኖርበታል። ይሄ ሁሉ የማህበራዊ ሚዲያ ጀግና ስለሚፅፈው ነገር ግን ምንም አያውቅም። በቀላሉ ማንም እየመጣ ወዲያ ወዲህ የሚያደርገው ትውልድ ተፈጥሯል ማለት ነው። በአንባገነኖች በቀላሉ የሚመራ ትውልድ የተፈጠረ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ምክንያታዊ ወጣት ትውልድ መገንባት ላይ ሊሰራ ይገባል። እኔም በአቅሜ ትውልዱ ጠያቂ እንዲሆን አስተምራለሁ።
እናትና አባት ልጅ ወልደውና አሳድገው መልቀቅ ሳይሆን ያለባቸው ቀሪ ህይወታቸው የራሳቸው መሆኑን በመንገር ራሳቸውን ችለው ለሌላ ሰው መትረፍ እንዲችሉ ማድረግ ተገቢ ነው። ይህም ሲባል ትውልዱ ለራሱ የሚያስብ ከሆነ ለሌሎችም ይተርፋል። ፈሪ ሰው ነው ራሱን ገሎ ሌሎችንም የሚያጠፋው።
በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2004 ላይ ወላጅ እናቴ ልጆቿ ሞተውባት በብቸኝነት ስትቀር ያለቻትን ጊዜ አብረን ለማሳለፍ ስመጣ የተመለከትኩት ነገር ቢኖር እዚህ ሀገር ሴቶች እንደወንዶች ወጣ የማለት ሀሳብ እንደሌላቸው ነው። ስራ ይዘው ትልቅ ነገር ሰርተው አለም ላይ ለውጥ ለማምጣት አለመቻላቸውን ተመለከትኩ። በስራ አለም ደግሞ ትልቁ ነገር መረጃ ነው። መረጃ ደግሞ ይደበቃል። ሴቶች ሀላፊነት ቦታ ላይ ሆነው ያለውን እሳት ለማጥፋት ከመጣር ውጭ ራሳቸውን የሚያሳድጉበት አጋጣሚ የለም።
አሜሪካን ሀገር ሰዎች በተማሩበት ዘርፍ በየቦታው እየሄዱ የልምድ ልውውጥ ስለሚያደርጉ ጠንካራ ሴቶች ይፈጠራሉ። በዚህም የተነሳ በሀገራችን በስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በወር አንዴ በመገናኘት ከሰው ጋር የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መድረክ ለመፍጠር ታሰበ። ኤውብ ባለፉት አስር አመታት ለሴቶች የውይይት መድረክ በመፍጠሩ ሰው በእውቀቱ ልክ ማወቅ የሚገባውን የሚያሳውቅ ማህበር ለመሆን በቅቷል። ማህበሩ እንደተነሳበት አላማም አቅም ያላቸው ሴቶችን ለመፍጠርም ችሏል።
ከውይይቱ በላይ መሪ ለመሆን የሚችሉ ሴቶች በተሰማሩበት ዘርፍ ትልቅ ልዩነት የሚያመጡ መሆናቸው የሚታይ ሆኗል። ፕሮፌሰር ሂሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሪ በነበረችበት ወቅት ያመጣችው ለውጥ የሚገርም ነበር። ሴት ወልዳም ሆነ ሳትወልድ እናት ነች። ሁሌም ለማህበረሰብ የሚጠቅም ነገር ማሰብ ትችላለች። ስለዚህ ሴቶች መሪ ሲሆኑ ማድረግ የሚገባቸውን ስንቅ ማሰነቅ ነው እንግዲሀ የማህበሩ ተግባር።
ለምሳሌ በየሳምንቱ ቅዳሜ የውይይት ጥበብ የሚል ፕሮግራም አለ። ያንቺ ንግግር ለእኔ ካልጣመኝ አንቺን ከማግለልና ከማሰናከል ይልቅ ይህ ንግግር በምን ምክንያት ሊባል ቻለ በማለት በሰለጠነ መንገድ መነጋገር እና አሳማኝ ከሆነ መቀበል አልያም አሳማኝ ምክንያቶችን በማምጣት ለመግባባት መሞከር ተገቢ ይሆናል።
ይህ ደግሞ ከአባቶቻችን የመጣውን የውይይት ባህል – ዛፍ ስር ሰብሰብ ብሎ መነጋገርና ችግርን የመፍታት ዕሴታችንን – ጥለን እርስ በርሳችን በጥላቻ መንፈስ መተያየታችን በውይይትና በምክንያት የሚያምን ትውልድ እንዳንፈጥር ወደኋላ እየጎተተን ይገኛል።
አንዳንዶች የቤተሰብ ስራ ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት ያልነበራቸው፣ እንደ አዲስ ከመጀመር ይልቅ ባለው ላይ ያላቸውን አቅምና እውቀት ጨምረው በመወያየት ትልቅ ደረጃ የደረሱ አሉ። ከሚፈልጉት ሙያ ውጪ በመስራት የቆዩ ነገር ግን በውይይቱ ወደ እራሳቸው አላማ የመጡ ሴቶችም ተፈጥረዋል።
በሀገራችን ጉድፍን ብቻ የመመልከት ጎጂ ባህልን ትተን ጎበዝ እያሉ ማበረታታትና ማድነቅ፣ ከፍ የመደራረግ ባህልን ማዳበር ላይ ስራ ተሰርቷል። ሌላው ደግሞ አሁን የበጎ ሰው ከሚባለው በፊት አርአያ የሆኑ ሴቶችን የማውጣት ስራም ተሰርቶ ነበር። ከሌላ ቦታ የአመቱ የኤውብ አምባሳደርን የሚመርጡ ሰዎች ተጠርተው በየአመቱም ጠንካራና የላቁ ሴቶች ወጥተዋል።
በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የላቀች ሴት እንድትመረጥ ማስታወቂያ ተነግሮ በትንሹ 35 ሴቶች የሚመረጡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 14 ከተመረጡ በኋላ አምስቱ ታሪካቸው ካሉበት ቦታ ተፅፎ በትልቅ የዝግጅት መድረክ ተዘጋጅቶላቸው ተምሳሌት ለመሆን በቅተዋል። በዚህ ሂደት እስከዛሬ 53 የሚሆኑ ሴቶች ተምሳሌት ለመሆን ችለዋል።
በየአመቱ እንደነዶክተር ተዋበች ያሉ ሴቶች ባላቸው አላማ እየተደገፉ ለሌሎች ብርሃን ለመሆን ችለዋል። በቤተ መንግስት ውስጥም በኤውብ ያለፉ ሴቶች አሉ፤ ለምሳሌ ብለኒ ስዩም ኤውብ ካፈራቻቸው ፍሬዎች አንዷ ናት። ሀገሬን ልይ ብላ የመጣችው ይህች ሴት በአጋጣሚ ኤውብ ገብታ ሀገሯን ለማገልገል ችላለች። በአጠቃላይ ሴት ራሷን አውቃ በፍጥነት ወደምትፈልገው ደረጃ እንድትደርስ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።
ኤውብ ውስጥ ወደ ስምንት መቶ ሰዎች ገብተው ወጥተዋል። በሀገራችን አንድ ቦታ ስንደርስ ጀርባችንን የመመልከት ባህል ባይኖረንም አሁን ላይ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ አባሎች አሉን። ነገር ግን አሁን ማህበሩ አምስት መቶ አባሎች እንዲኖሩት እፈልጋለሁ።
ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ሁለት ልጆች አሉኝ። ወንዱ ሀገር ውስጥ ባይሆንም ሴቷ ግን ሀገሯ መጥታ ሶስት ልጆችን ወልዳለች። እሷም ትልቅ ሀሳብ ያላት ናት። ሴቷ ልጄ በ13 አመቷ ወደ ሀገራችን ስናመጣት ድህነትን አይታ ስለማታውቅ ደንግጣ ሀገሬ ቀርቼ አገለግላለሁ ስትል፤ ወንዱ ደግሞ ተመልሼ በገንዘብ እረዳሻለሁ አለ።
ልጅ የተመኘውን ያደርግ ዘንድ ሆነና ሀርቫርድ የተማረችው፣ ስድስት የተለያዩ ቋንቋዎችን የምትችለው ልጄ ከባለቤቷ ጋር በመሆን ዘለማ ፕሮዳክሽን የተባለን ድርጅት ከፍ ያለ ቦታ ከማድረሷም ባሻገር የሴቶችን የገንዘብ አቅም የሚያሳድግ የራሷን ሀሳብ ይዛ መጣች። ቀዳሜ ማርት የሚባል ሲሆን ሴቶች ገንዘብ በመበደር ቤት ለቤት እየሄዱ የፅዳት እቃ እያዞሩ በመሸጥ ገንዘብ መስራት የሚቻልበት ሃሳብ ያለው ስራ ነው።
በሃገራችን ውስጥ ከ2 እስከ 4 ዶላር የሚያገኝ 25 ሚሊዮን የሚሆን ሰው መኖሩን በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን ይሄን ያህል ሰው ተደራሽ ለማድረግ በእያንዳንዱ የሃገራችን ጫፍ ያሉ ሴቶች ተበድረው ቤት ለቤት እየሄዱ የፅዳት እቃ በመሸጥ የራሳቸው ስራ እንዲኖራቸው ለማስቻል ሁለት ሺህ ሴቶችን በማሰማራት የገንዘብ አቅማቸው እንዲጎለብት የማድረግ ስራም ተሰርቷል።
ወይዘሮ ናሁ ካሰበችው ርቀት በላይ በከፍታ ለመራመድ የቻለች የጥንካሬ ተምሳሌት ስትሆን፤ እሷ እንደምትለው በህይወቷ ልጆቿን ጥሩ ቦታ ማድረስ ስኬቷ ነው። በድርጅቱም ለበርካታ ሴቶች አይን መክፈት መቻል ለኔ የስኬት መጨረሻ ነው ትላለች። ህይወት ቀላል መሆኗን በማሳየት የሴቶችን ህይወት ለማቅለል መስራቷም “ስኬቴ” ነው ትላለች።
ያሰብኩትን ያህል ከኤውብ ወስድው ለሀገራቸው ወይም ለማህበረሰባቸው ሳይሰጡ ለራሳቸው ሆነው የቀሩ ሰዎች መኖራቸው ደግሞ ቅር እንዲለኝ አድርጓል። ለምሳሌ የትምህርት ስርአቱ መድከም ሃገራችን ውስጥ ግበረ ገብነት እንዲጠፋ አስተዋፅኦ አድርጓል።
ሃገራችን እርጉዝ የሚከበርባት ሀገር ሆና ሳለ ሆድን ከፍቶ ፅንስን እሰከማውጣት የደረሰ ጭካኔ ውስጥ መገባቱ በራሱ የአስተሳሰብ ድህነት መኖሩን ያሳያል። የተቀበልነውን ይዞ ዝም ከማለት በሁሉም ዘርፍ ያለውን መካፈልና ትውልድ ላይ መስራት የለውጥ ቁልፍ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013