አዲስ አበባ፡- በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አደጋ የተጋረጠበት ‹‹ኮፊ አረቢካ›› የተባለውን የቡና ዝርያ ከጥፋት ለመታደግ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በኮፊ አረቢካ ቡና ላይ የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች ከሦስት ዓመት በፊት ባደረጉት ጥናት በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምክንያት እየተመናመነ ያለው የቡና ዝርያ በዚሁ ከቀጠለ ከነጭራሹ ሊጠፋ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም ዝርያውን ካንዣበበት አደጋ ለመታደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው፡፡
አጥኚዎቹ በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በኩል የጥላ ዘፍ ካልተተከለ እንዲሁም የውሃና አፈር ጥበቃ ሥራ በአግባቡ ካልተከናወነ አሁን ያለው ቡና ምርቱ መቀነሱ ብቻ ሳይሆን ከ50 እና 60 ዓመታት በኋላ ዝርያው የጎላ ችግር ሊደርስበት እንደሚችል ማመልከታቸውን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ባለ ሥልጣኑ የቡና ምርት ዕድገት ንቅናቄ ላይ እየሠራ ሲሆን፤ ስለ ቡና ጥላ ዛፍ ተከላና የአየር ንብረት እንክብካቤ ገለጻ በማድረግ፤ የኮፊ አረቢካ ቡና ዝርያ እንዳይጠፋና ህልውናውን ለመጠበቅ በተለይ በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮችን እያከናወነ መሆኑን፤ ከግንዛቤ ማስጨባጫ ሥራ በተጨማሪ በ100ሺ የሚቆጠሩ የጥላ ዘፍ ተካላና የውሃና የአፈር ጥበቃ ሥራዎችም እንደሚሠሩ አቶ ብርሃኑ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
‹‹የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፋዊ ችግር ነው ኢትዮጵያ የተሻለ ከሠራች አሁን ያላትን የቡና ይዞታ የዛሬ 50 ዓመት በአራት እጥፍ የማሳዳግ ዕድል ይኖራታል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የአየር ንብረት ለውጡ ለኢትዮጵያ ቡና ስጋት ብቻ ሳይሆን መልካም አጋጣሚና ዕድልም እንዳለው፣ ቀደም ሲል ደጋማ የነበሩ አካባቢዎች አሁን ወደ ወይናደጋነት እየተለወጡ ሲሄዱ እንደ ምዕራብ ሸዋ፣ አርሲ፤ ሆሮ ጉዱሩ፣ ሲዳማና የመሳሰሉት ለቡና ምርት ምቹ የሚሆኑ አዳዲስ አካባቢዎች እንደሚፈጠሩ አስታውቀዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጡን በመከተል ጥላ ዛፎችን በመትከል እንክብካቤውን በማስቀጠል፤ከ10 ባላነሱ ወረዳዎች የቡና ምርት በማስፋፋት ዘርፉን ከስጋት መታደግ እንደሚቻል የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮቹን በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎችን በማካተት ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ላሉ ባለሙያዎች መስጠታቸው ይህም ቀጣይነት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
አዲሱ ገረመው