አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግበዓቶች ድርጅት ለግል ባለሀብት፣ ለመንግስት ኢንዱስትሪዎችና ድርጅቶች ለስራ ማስኬጃ ያበደረው 1ነጥብ7 ቢሊዮን ብር እንዳልተመለሰለት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ የድርጅቱን የስድስት ወራት ዕቅድና የመቶ ቀናት አፈጻጸም አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ለግልና የመንግስት ፋብሪካዎች 1ነጥብ7 ቢሊዮን ብር ቢያበድርም አልተመለሰ ለትም፡፡ ፋብሪካዎቹ ብሩን ባለመመለሳ ቸው ድርጅቱ ለስራ ማስኬጃ የሚውል ገንዘብ አጥቷል፡፡
እንደ አቶ ወንዳለ ገለጻ፤ የግል ድርጅቶቹ ብድሩን በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ ባለመመለሳቸው ተጨማሪ የስድስት ወር ጊዜ ገደብ የተሰጣቸው ሲሆን፤ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ብድሩን ባለመመለሳቸው ጉዳዩ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረስ እንዲታወቅ ተደርጓል፡፡ ድርጅቱ በ2006 ለመቋቋሚያ የተፈቀደለትን ብር ጨምሮ በድምሩ 1ነጥብ3 ሚሊዮን ብር ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር አልወሰደም፡፡ በሌላ በኩል ዲ.ኤም.ቪ፣ ዋይ.ኤ.ኤች እና ሀይሌ ኪሮስ ድርጅቶች እዳቸውን ያልከፈሉና ወንጀል የፈጸሙ በመሆናቸው ጭምር ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ችሏል፡፡
ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከመድረሱ በፊት የተወሰኑት ድርጅቶች እዳውን መልሰዋል ያሉት አቶ ወንዳለ፤ ለአብነትም ከጥጥ ግዥ 15 ነጥብ7 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ ጨው አቅራቢ ድርጅትም 286ሺ የሚያወጣ 992 ኩንታል እንዲያስረክብ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በፍርድ ቤት ክስ በመመስረቱ የኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ብር፣ የሀዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ብርና ሀበሻ ታኒንግ 28ነጥብ4 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ በፍርድ ቤት እንደተወሰነባቸው አቶ ወንዳለ ገልጸው፤ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ 9ነጥብ5 ሚሊዮን ብር፣ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ብር መክፈላቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከቢረ ኢንተርፕራይዝ የ30ነጥብ4 ሚሊዮን ብር ክስ የተመሰረተበትና አይካ አዲስ 105 ሚሊዮን ብር እዳ እንዲከፍል ከልማት ባንክ ጋር በመነጋገር ከስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ወንዳለ ተናግረዋል፡፡
‹‹በብዙ አካባቢዎች የድርጅቱን መስሪያ ቦታ የመውሰድና የተቋሙን የስራ ቦታ የማስተጓጎል ዝንባሌ እየተበራከተ መጥቷል›› ያሉት አቶ ወንዳለ፤ በምዕራብ ሀረርጌ ጭፍሮ ከተማ ያለው የድርጅቱ ቅርንጫፍ ባለፉት ሁለት ወራት ምንም አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
ሶሎሞን በየነ