አዲስ አበባ፡- ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከተመደበው 10 ቢሊዮን ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ የተጠቀሙ ከተሞች ጥቂት መሆናቸውን የፌዴራል የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ በብድር አመላለስ ላይም ክፍተት መኖሩን ገልጿል፡፡
በኤጀንሲው የስትራቴጅክ ዕቅድ ዳይሬክተር ወይዘሪት መነን መለሰ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ አማራና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የተመደበላቸውን ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ሙሉ ለሙሉ ተጠቅመዋል፡፡ ኦሮሚያ ክልል ከተመደበለት ገንዘብ አብዛኛውን ተጠቅሟል፡፡ ሶማሌ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ሐረሪና ጋምቤላ ደግሞ የተመደበላቸውን ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ያልተጠቀሙ ክልሎች ናቸው፡፡ የብድር አሰጣጡም እንደየክልሎቹ የአገልግሎት ስፋት የተለያየ ነው፡፡
እንደ ወይዘሪት መነን ማብራሪያ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሥራ ላይ እንዲውል ከለቀቀው ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ በከተሞች 25 ሺ 746 ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ለ146 ሺ ወጣቶች አራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ተሰራጭቷል፡፡ 980 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ደግሞ ሥራ ላይ አልዋለም፡፡
የብድሩ ተጠቃሚዎች የብድር መመለሻ ጊዜ የደረሰ ቢሆንም ዘርፉን የሚመራው አካል ተከታትሎ በወቅቱ አስመልሶ ለቀጣይ ተበዳሪዎች በማመቻቸት በኩል ክፍተት መኖሩንና ‹‹ብድሩ አይመለስም›› የሚል አመለካከት በተበዳሪዎችም ዘንድ መፈጠሩ ሥራውን ያጋጠመው ተግዳሮት ሆኗል፡፡ በብድር አመላለስ ላይ ያለውን ክፍተት የፌዴራል የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ የቴክኒክና ሙያ እና የማይክሮፋይናንስ ተቋማት ተቀናጅተው ሊፈቱት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታደሰ ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት የተፈቀደውን አንድ ነጥብ 67 ቢሊዮን ብር ሙሉ ለሙሉ መጠቀሙንና የብድር መመላሻ ጊዜያቸው የደረሰውንም ለይቶ በማስመለስ ለቀሪ ሥራ ፈላጊዎች እንዲውል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ገለታ በበኩላቸው፣ ለክልሉ ከተመደበው ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ውስጥ ያልተጠቀመው አራት ሚሊዮን ብር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ቀሪውን ገንዘብ በቀጣይ ጊዜያት ለመጠቀምና ብድር የማስመለሱ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
ለምለም መንግሥቱ