አዲስ አበባ፡- ስኳር ኮርፖሬሽን በስድስት ክልሎች የሚገኙት ትላልቅ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ባለመንቀሳቀሳቸው ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር አለመቻላቸውን ገለጸ፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን የህዝብ ተሳትፎና ልማት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተገኑ ገናሞ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ሊኖራቸው ሲገባ በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊውን ድጋፍ ባለማግኘታቸው የሚታሰበውን ያህል ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር አልቻሉም፡፡
‹‹ሥራ በሌለበት ሥራ መፍጠር አይቻልም›› ያሉት አቶ ተገኑ የአገዳ ልማቱ በተሟላበት ፋብሪካው አለመኖሩ፣ ፋብሪካው ባለበት ደግሞ የአገዳ ልማቱ አለመሟላቱን ፍብሪካዎቹ ተጣጥመው እንዳይሄዱ እንዳደረጋቸው ጠቁመው፤ ለፋብሪካ ሠራተኞች መኖሪያ ቤትና ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ግንባታ የሚውል ቦታ ከማመቻቸት ጀምሮ የሚደረጉ የተለያዩ ድጋፎችም አነስተኛመሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በአፋር ክልል በሚገኘው ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ልማቱ ሙሉ ለሙሉ አለመሠራቱ፣ በከፊል በለማው ላይም በከብቶች ጥቃት መድረሱ፣ እንዲሁም የክልሉ ድጋፍ አነስተኛ መሆኑ ትልቅ ተግዳሮት እንደፈጠረ አቶ ተገኑ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ተንዳሆ ላይ እስከ 25ሺ ሄክታር የአገዳ ልማት ሊኖር ይገባ እንደነበርና በአሁኑ ጊዜም የአገዳ ልማቱ በ9ሺ ሄክታር ብቻ ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተገኑ፣የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻለው የቀረው ሄክታር ተሟልቶ ልማቱን ማከናወን ሲቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የከሰም ስኳር ፋብሪካ በመጀመሪያው ምዕራፍ የአገዳ ልማት 16ሺ ሄክታር ፣በሁለተኛው ደግሞ 20ሺ ሄክታር መሬት የሚያስፈልገው ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በሦስት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ብቻ የአገዳ ልማት እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ተገኑ ጠቅሰው፤ ፋብሪካው በሥራ ላይ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ የአገዳ ልማት እያገኘ አለመኖሩን አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ተገኑ ማብራሪያ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ቢንቀሳቀስ በአማካይ በአንድ ሺ ሄክታር ላይ ለአምስት መቶ ሰው የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከሰም ላይ 10ሺ ሄክታር ቢለማ ደግሞ በአማካይ ለአምስት ሺ ሰዎች የሥራ ዕድል ያስገኛል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
ለምለም መንግሥቱ