ዳንኤል ዘነበ
“ከጠንካራ ወንዶች ስኬት ጀርባ ጠንካራ ሴቶች አሉ” የሚለውን በተግባር ካስመሰከሩ ሴቶች መካከል ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ይጠቀሳሉ። ዶክተር ዐብይ አህመድ ለዛሬ ስኬት ለመብቃታቸው ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ።
በመከራ ጊዜ ከባለቤታቸው ጎን በጽናት ከመቆም ባሻገር ቀን እስኪያልፍ ከልጆቻቸው ጋር በሰው ሃገር ተሰደው ታላቅ ኃላፊነትና የመንፈስ ጥንካሬን የሚጠይቁ አስቸጋሪ ጊዜያትን በብቃት አልፈው ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉለትን ዓላማ በድል ማጠናቀቅና ካሰቡት መድረስ የቻሉ ብርቱ ሴት ናቸው። ይሄንኑም ዶክተር ዐብይ አህመድ በአንደበታቸው መስክረውላቸዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ስኬት ጀርባ ከነበራቸው የላቀ አበርክቶ በተጨማሪ ቀዳማዊት እመቤትዋ ዛሬም ያሉበትን ቦታ የሚመጥን በርካታ ታላላቅ አገራዊና ሕዝባዊ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ።
«ከጠንካራ ወንድ ጀርባ…” ከሚለው ተለምዷዊ አባባል አልፈው፤ `ከጠንካራ ወንድ ጎን ጠንካራና ብልህ ሴት አለች› ለሚል አዲስ ብሂል ህያው ተምሳሌት ለመሆን የበቁት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ናቸው።
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ቀዳማዊት እመቤት ሆነው ታላቁ ቤተ መንግስት የገቡት ቀዳማዊት እመቤቷ፤ ከምንፈልገው ደረጃ ደርሰናል ብለው ዝም አላሉም። ቀዳማዊት እመቤቷ ዛሬም እንደ ወትሮው ከባለቤታቸው ጎን ተሰልፈው ታላላቅ ሕዝባዊና አገራዊ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ።
በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በርካታ አኩሪ ተግባራትን ያለ እረፍት እያከናወኑ ይገኛሉ። የትምህርት ዘርፍ ደግሞ ዋነኝነት ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል።
“ለዜጐች ጥራት ያለው ትምህርት፣ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ማድረግ፣ የሃገሪቱን የወደፊት ትውልድ ለማነጽና ለማዘጋጀት ሊፈፀም የሚገባ ቁልፍ ተግባር ነው” የሚል እምነት ቀዳማዊት እመቤቷ በተለይ በገጠር የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ ትኩረት በማድረግ ዘመን ተሻጋሪ ሥራን ሰርተዋል። ወይዘሮ ዝናሽ የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤትን በተረከቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች 20 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በማስጀመር፤ የ13ቱ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ ለመመረቅ በቅቷል።
ይህም ቀዳማዊት እመቤቷ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን በየክልሎች ሁሉ ለማስፋትና ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ጥረት ከመወጣታቸው ባሻገር፤ በኢትዮጵያ ታሪክ በመላ ሀገሪቱ በዚህ ልክ ትምህርት ቤት በማሰራት ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ታሪክ ሰርተዋል። ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሰጥተው ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ ከተጣለባቸው ኃላፊነት ትይይዩ አንድ ትልቅ ምክንያት ነበራቸው።
የትምህርት ቤት ግንባታ ለምን?
ቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤቱን እንደተረከቡ የትምህርት ቤቶችን ተደራሽነትንና ጥራት ማሻሻልን ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ ያደረጋቸው አንድ አጋጣሚ እንደነበር የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፋንታ እንዲህ ይናገራሉ። በቀዳማይት እመቤት ቢሮ ሥር የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም አለ። በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውረው ጉብኝት አድርገው ነበር። በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በተለይ በገጠር በአብዛኛዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአቅራቢያቸው እንደሌለ ለመታዘብ እንደቻሉ ያስታውሳሉ።
«በዚህ ምክንያት ትምህርታቸውን ከስምንተኛ ክፍል የሚያቋርጡ በርካታ ተማሪዎች መኖራቸውን በወቅቱ ተረዱ። በመላ አገሪቱ በብዛት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ቢሆንም፤ ተማሪዎች እስከ ስምንተኛ ድረስ ከተማሩ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመቀጠል በአቅራቢያቸው ወዳለ ከተማ መሄድ አስገዳጅ ይሆንባቸዋል።
ይህም የምጣኔ ኃብት ጫና ያለው በመሆኑ ልጁን ትምህርት ቤት ልኮ ማስተማር የማይችል ወላጅ ልጁን ትምህርት እንዲያቋርጥ ይገደዳሉ። ሴት ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ርቀው በሚሄዱበት ወቅት ለጥቃት የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ እንደሆነ ለመረዳት ቻሉ» ይላሉ አቶ ሙሉቀን።
«ከንፈር መጦ»አለማለፍ
ቀዳማዊት እመቤቷ በጉብኝታቸው ወቅት በተመለከቱትና በሰሙት ልብ የሚነኩ ችግሮች «ከንፈር መጦ» ማለፍን አልወደዱም። በዚህም ለችግሮቹ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ ከውሳኔ ደረሱ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ባሉባቸው እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሌሉባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን ማስገንባት አንዱ መፍትሄ እንደሚሆን ተረዱ።
የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤትን በተረከቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት እቅድ መያዙን ይፋ አደረገ:: በትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ዙር 20 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የሚገነቡ ይሆናል።
በአማራ እና ኦሮሚያ በእያንዳንዳቸው አራት ትምህርት ቤቶች፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ፣ ጌዲኦ፣ ሻኪሶ ሶስት ትምህርት ቤቶች፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳና መተከል ሁለት ትምህርት ቤት፣ ሶማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ ሁለት ትምህርት ቤቶች፣ አፋር አንድ፣ ጋምቤላ አንድ፣ ትግራይ በሽሬ ከተማ አንድ ትምህርት ቤት ለመገንባት እቅድ መያዙን ጽ/ቤቱ አስረዳ።
የእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የግንባታ ዋጋም 20 ሚሊዮን ብር ወጪ ይፈጃል። የ20ዎቹ ትምህርት ቤቶች የግንባታ ወጪ 4 መቶ ሚሊዮን ብር ይፈጃል። በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በባህር ማዶ ካሉ ወዳጆቻቸው በስጦታ መልክ በተገኘ ገቢ እንደሚሸፈን አስታወቀ። ጽህፈት ቤቱ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ሁኔታን ለህዝብ በግልጽ ወደ ቀጣዩ እርምጃ ነበር የተሻገረው።
በዚህም መሰረት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ሚያዚያ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውጫሌ ወረዳ የሚገኘው የኢፋ ሰላሌ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ። በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ ጦሳ ፈላና ቀበሌ አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ለመገንባት ሌላኛው የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ። በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ትምህርት ቤቶቹን ለማስገንባት መሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሶስት፣ አራት፣ አምስት እያለ፤ የ20 ትምህርት ቤቶች መሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።
የትምህርት ቤቶች ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ አብዛኛዎቹ ግንባታቸው ተጀመረ። ቀዳማዊት እመቤቷ ከሚያስገነቧቸው 20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 13ቱ ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለመመረቅ በቅቷል። በመጀመሪያው ዙር እየተገነቡ ከሚገኙት 20 ትምህርት ቤቶች መካከል ቀሪዎቹ ስምንት ትምህርት ቤቶችን በዚህ አመት አጠናቆ ማስመረቁን እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
በቀዳማዊት እምቤት ዝናሽ ታያቸው ቀናኢ እሳቤ ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ፕሮጀክት የመጀመሪያው ዙር 20 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በማከናወን አልተቋጨም ነበር። የሁለተኛው ዙር የትምህርት ቤት ግንባታን በኦሮሚያ በምእራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ ሮጲ ከተማ ለሚገነባው ትምህርት ቤት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ የመጀመሪያው የመሰረት ድንጋይ በቅርቡ በማስቀመጥ፤ ተጨማሪ አሻራን ለማሳረፍ መንገድ መጀመራቸውን ተገንዝበናል።
የቀደሙት ቀዳማዊ እመቤቶቻችን
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በኢትዮጵያ ሁልጊዜም የሚታወሱባቸውን ትምህርት ቤቶች እያስገነቡ እንደሆነ በወፍ በረር ከላይ ለመመልከት ሞክረናል። በሀገራችን ያለፉት ቀዳማዊ እመቤቶች እድሉን ቢያገኙትም፤ ከግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ባለቤት እቴጌ መነን አስፋውን ሳይጨምር እንዲህ አይነት ማስታወሻ ሳያስቀምጡ እንዳለፉ ታሪክ ይነግረናል።
እቴጌ መነን አስፋው በቀዳማዊት እመቤት ዘመናቸው፤ የመነን አዳሪ የሴቶች ትምህርት ቤትን በማቋቋም ቀዳሚ ናቸው። ይህ ትምህርት ቤት አሁንም በአዲስ አበባ ሴቶች ብቻ የሚማሩበት ብቸኛው የመንግስት ትምህርት ቤት እንደሆነ ይታወቃል። ትምህርት ቤቱ ለእቴጌ መነን ደግሞ የታሪክ ማስታወሻ በጎነት ሲወሳ ይኖራል። የእቴጌ መነን አስፋውን ፈለግ በመከተል ረገድ ያለፉት ቀዳማዊት እመቤቶች ትምህርት ቤቶችን ሳያስገነቡ ቢያልፉም፤ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አዲስ ታሪክ ተመዝግቧል።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ሶስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 13 ትምህርት ቤቶችን አስገንብተዋል። ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ በመላ ሀገሪቱ በዚህ ልክ ትምህርት ቤት ያሰሩ የመጀመሪያዋ ቀዳማዊት እመቤት ሆነዋል። በተጨማሪም ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በተግባራቸው በትውልድ ቅብብሎሽ የሚነገር፣ የሚዘከር፣ የሚታወሱበት… በጎ ታሪክ ፈፅመዋል። በዚህ ሳያበቃ በቀጣይም በርካታ በጎ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ የብዙዎች እምነት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013