አስመረት ብሰራት
በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት አንዳንድ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ውጣ ውረዶችና ከተዘፈቁባቸው ችግሮች ለመውጣት ሲታገሉ፣ ሌሎች ደግሞ ያጋጠማቸውን ችግር አሜን ብለው በመቀበል ከችግሩ ሳይወጡ የሚዘልቁም ይኖራሉ።
የዛሬዋ ባለታሪካችን ፈቲያ መሐመድ ትባላለች። የፈቲያ መሐመድ ተሞክሮ ቢቢሲ አማርኛ ካሰፈረው ፅሁፍ ላይ የተመለከትነውን ለአዲሰ ዘመን እንዲመች አድርገን አሰናድተነዋል።
ፈቲያ የተወለደችው በምሥራቅ ሐረርጌ በባቢሌ ወረዳ ሲሆን በ12 ዓመቷ ነበር ቤተሰቦቿ ለአንድ ዐረብ ሚሰት ትሆን ዘንድ የሰጧት። ከሳዑዲ ዐረብያ የመጣው ሰው ጋር ለ28 ዓመታት ወልደው ከብደው አብረው ኖረዋል። ያንን ሁሉ ጊዜ ዐረብ ሃገር ስትኖር ስለ ሀገሯ ጥሩ ነገር ሰምታ አለማወቋ በቁጭት ያንበግባት ነበር።
ለ28 ዓመታት ከነበረችበት ሳውዲ አረብያ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ሁለት ጊዜ ብቻ የነበረ መሆኑን የምታስታውሰው ፈትያ በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ ሐረርጌ በባቢሌ ወረዳ፤ በየረር ወንዝ ዙሪያ የአከባቢውን ማህበረሰብ ችግር በሚፈታው የግብርና ሥራ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በአረቦቹ አፍ የምትነሳው በረሃብና በስቃይ በመሆኑ ይህን መስማት ለአንዲት ዜጋ ህመምን በህመም ላይ የሚደርብባት ነበር። ̋እኔንም ‘ከረሃብ ሃገር ነው የመጣሽው’ ሲሉኝ ውስጤ በጣም ይታመም ነበር። እኔ ግን ሃገሬን የማውቃት በተፈጥሮ ሃብት የተሸለመች መሆኗን ነው።
ስለ ድህነቴ በሚሰድቡኝ ጊዜ በዓይኔ የሚመጣብኝ ዙሪያው ለምለም የሆነው ቀየዬ ነው።” የምትለው ፈቲያ ከአሸዋ ሌላ አፈር እንኳን የማይታይበትን ሀገራቸውን አያየች “ከሀገሩ የወጣ ሀገሩ እስኪመለስ፣ ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ” ነውና ነገሩ ዝምታን መርጣ ቆይታለች።
̋ሃገራቸው አሸዋ እንጂ ለሰብል የሚሆን መሬት እንኳን የለም። ከአሸዋው ውስጥ የሞቀ ውሃ አውጥተው አቀዝቅዘው እና አፈር ደግሞ ከሌላ ሃገር እያስመጡ ነው የሚጠቀሙት። ሃገሬ ግን በተሄደበት ቦታ ሁሉ የተሰጣትን የምታፈራ ሃገር ናት።” በማለት ይህችን ለምለም ምድር በአገባቡ አልምቶ ማሳየት ይኖርብኛል ብላ ትወስናለች።
ለእቅዷ መሳካትም በሰው ሀገርም ቢሆን የቅንጦት ኑሮዋን ትታ ገንዘብ መቋጠር ጀመረች። እጇ ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ገንዘብ በሙሉ በማስቀመጥ ለማጠራቀም ትታትር ጀመር።
በዚህ መልኩ ብሩ ተሰብስቦ ወደ 20 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ሲጠጋ ወደ ሀገሯ እንድትመለስ የሚገፋፋትን ቀልቧን ተከትላ ጨርቄን ማቄን ሳትል ያጠራቀመቻትን ገንዘብ ቋጥራ ወደ ሀገሯ ለመምጣት በቆረጥችበት ሰዓት ነበር የኢትዮጵያ መንግሥት ሰው በሃገሩ ሠርቶ እንዲበለጽግ ጥሪ ያቀረበው። እንኳን ተጠርታ ሂጂ ብረሪ እያለ አላስቀመጥ ያላትን ቀልቧን ለመከተል አቆብቁባ በነበረችበት ወቅት ይህ መልካም ዜና መሰማቱ ብርታት ሆናት።
̋እኔም ያንን ዕድል በመጠቀም ማድረግ ስለምፈልገው ኢንቨስትመንት ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ ጥያቄዬን አቀረብኩኝ። በኢትዮጵያ መንግሥት ጋባዥነት በ1998 ዓ.ም ወደ ሃገር ቤት ተመልሼ ለሥራዬ ሁኔታዎችን አመቻቸሁኝ።” በማለት ያኔ የነበረውን ነገር አስረድታለች።
በ1999 አ.ም ደግሞ ወደ ኢትዯጵያ ስትመለስ መንግሥት አዲስ አበባ አካባቢ ኢንቨስት እንድታደርግ መሬት ሰጥቷት የነበረ ቢሆንም እሷ ግን በተወለደችበት አካባቢ ያለውን የማህበረሰብ ችግር በመቅረፍ ለውጥ ማምጣት ትፈልግ ስለነበር ምርጫዋ ሀረር ሆነ።
የተቸገረን መርዳት፣ የተጠማን ማጠጣትና የተራበን ማብላት ትልቁ ህልሟ የነበረ መሆኑን የምትናገረው ፈቲያ መንግሥት “አንቺ ሴት ነሽ፣ ብዙ ገንዘብም ይዘሻል። መሬት ሰጥተንሽ እዚሁ አዲስ አበባ አካባቢ ብትሆኚ ነው የሚሻለው” ቢሏትም ፍቃዷ የተወለደችበትን ማህበረሰብ ማገልገል ብቻ ነበር።
”የተወለድኩበት አገር ህዝብ ውሃ ላይ ተኝቶ ይጠማል፣ ለም አፈር ላይ ተቀምጦ ይራባል። ለዚህ ነው ይህንን ሕዝብ መጥቀም እንደምፈልግ ለመንግሥት ያሳወቅኩት። ሆዴን በጣም የሚበላው ነገር የባቢሌና የሐረርጌ ሕዝብ ወንዝ በመንደሩ እያቋረጠ መጠማቱ ነው። ̋ የምትለው ፈቲያ ̋እንደ እነ ግብፅ፣ ሱዳንና ሳዑዲ ዐረብያ ያሉ አገራትን አይቼም እውቀት ቀስሜያለሁ።
ባገኘሁትም ልምድ የአገሬን ሕዝብ ኑሮ መቀየር እንደምችል አምን ነበር። መጀመሪያ ወደ ባቢሌ ስመጣ ምድሩ አቀበትና ቁልቁለት እንዲሁም ጋራና ገደል የበዛበት ነበር። ሰዎች በቆሎ ከሚያበቅሉባቸው ትንንሽ ማሳዎች ውጪ ምንም አልነበረም።” በማለት ተሞክሯዋን ታስረዳለች።
በወቅቱ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ያሉ ሁሉም የመንግሥት መዋቅሮች ድጋፍ ያደረጉላት መሆኑን ገልፃ ከመጣች ጊዜ አንስቶ የመንግሥት ልማት ቢሮ የሞራል ድጋፍ በማድረግ ለስኬቷ ምክንያት መሆኑን ነው የምትገለፀው።
የኤረር ወንዝ ባለበት አካባቢ መሬት አስፈቅዳ ከወሰደች ወዲያ ከውጪ ሃገር ትራክተሮችንና የእርሻ መሣሪያዎችን በማስመጣት ሥራውን አንድ ብላ ተያያዘችው። ያንን ጋራና ገደል ደልድሎ የእርሻ መሬት ማድረግ በጣም ከባድ የነበረ ቢሆንም የያዘቸው ፈቲያ ናትና ዶዘርና ግሬደር በ2 ሚሊዮን ብር ተከራይታ ቦታውን ሜዳ አደረገችው።
መሬቱን ካደላደለች በኋላ እንዴት ዉሃ ከከርሰ ምድሩ ማውጣት እንደምትችል ማሰብ ጀመርች። ይህንን ያሰበችው ለሕዝቡ ውሃ በቅርበት ለመስጠት ነበር። ውሃ በማውጣት ልምድ ያላቸውን ሰዎች ከሱዳን በማስመጣት ማሠራት ጀምረች። ይህን ስታደርግ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፍቃድ አውጥታና ለእነርሱ ከፍተኛ ዶላር ክፍያ በመፈፀም እንደነበር ታሰታውሳለች።
የመጡት ባለሙያዎችም በአንድ ቀን ውስጥ ከጉድጓድ ውሃ ማውጣት ከመቻላቸውም ባሻገር እግረ መንገዳቸውን ሀምሳ ወጣቶችን በዚሁ መስክ እንዲያሰለጥኑ በማድረግ ሥልጠናውን የወሰዱትን ወጣቶች በአካባቢው ላሉ ሰዎች ዉሃ እንዲያወጡ በማድረግ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የተባለውን የሀገራችንን ብሂል ተግባራዊ አድርጋለች። በዚህ አጋጣሚ የባቢሌ አካባቢ ሰዎች ይገጥማቸው የነበረውን የውሃ ችግር በዚህች ሀገር ወዳድ ጠንካራ ሴት የተነሳ ሊቀረፍ ችሏል።
እንደህልሟ ሕዝቡን ውሃ ማጠጣት መቻሏ ትልቅ ደስታ የፈጠረላት ፈቲያ ̋ውሃ በማግኘቴ እኔም ማሳዬን አስፍቼ እያለማሁ ነው። እስካሁን 5 ሺህ ማንጎ፣ 5 ሺህ ብርቱካን፣ 30 ሺህ ፓፓዬ፣ 1 ሺህ ዜይቱን፣ 2200 ቡና እና 2 ሺህ ሽፈራው (ሞሪናጋ) የሚባል ዘር ተክያለሁ።” ትላለች።
የዚህ አካባቢ ሰው ንፁህ የመጠጥ ውሃ በማግኘቱ ተጠቅሟል። ደግሞም በማሳዋ በመሥራት የእለት ጉርሳቸውን የሚያገኙ ብዙ ሰዎች አሉ። ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ሰዎች በማሳው ላይ በመስራታቸው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን ፈጥራለች።
̋እስካሁን 100 የሚሆኑ ሰዎች ይሰራሉ፤ በቋሚነት ደግሞ ከ60 እስከ 70 የሚሆኑ ሰዎች በዚህ ማሳ ይሠራሉ። ቤተሰብ አፍርተው እዚሁ የሚኖሩም ብዙ ናቸው። በአጠቃላይ የአካባቢው ሕዝብ ማሳውን እንደራሱ ንብረት ነው የሚጠቀምበት።
በተለይ ሴቶች እንደፈለጉ አምርተውና ሽጠው እንዲጠቀሙ ፈቅጄላቸዋለሁ።” የምትለው ፈቲያ ̋ሕዝብ የሚጠቀምበት አንድ የጭነት ፒክ አፕ እና አንድ አይሱዙ አለኝ። እኔ ደግሞ የእራሴ የቤት መኪና እና ደረጃውን የጠበቀ ቤት በዚሁ በማሳዬ መካከል ሠርቼ እየኖርኩኝ ነው።” ትላለች።
̋ልጆቼ በሙሉ በሳዑዲ ዐረብያ የራሳቸውን ቤተሰብ መሥርተው እየኖሩ ነው። ባለቤቴ ሞቷል። ልጆቼና የባለቤቴ ዘመዶች መጥተው ማሳዬን በጎበኙ ጊዜ በኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት ቦታ አለ ብሎ ለማመን ከብዷቸው በጣም ተደንቀው ነበር።” የምትለው ፈቲያ ለምለሟን ሀገሯን ለማሳየት በመቻሏ ኩራትን ፈጥሮላታል።
ዓላማዋም የያዘችውን ይህንን ሰፊ ማሳ በምርት መሙላት፣ እያለሙ መንከባከብ እና በብዛት ለገበያ ማቅረብ እንደሆነ ነው የምትናገረው። በመቀጠልም ፋብሪካ አቋቁማ ከፍራፍሬዎቹ እሴት በመጨመር የተለያዩ ምርቶችን ማውጣት ሌላው አላማዋ ነው። እዚያው ማሳዋ ላይ ለፋብሪካው የሚሆን ቦታም ማዘጋጀቷንም ታሰረዳለች።
̋ለሴቶች አስረግጬ መንገር የምፈልገው ሁሉን ነገር የመሥራት ችሎታ እንዳላቸው ነው። ቆርጠው ከተነሱ ደግሞ ማንኛውንም ነገር ከግብ ማድረስ እንደሚችሉ አምናለሁ። አብዛኛዎቹ ግን ብከስርስ ብለው በመስጋት ያመነታሉ። አንድን ሥራ ሳትጅምሪው ለፍርሃት እጅ ከሰጠሽ በጭራሽ ስኬታማ መሆን አይቻልም።”
ስለዚህ ሴቶች ቆራጥ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ እና ጠንካራ አቋም ካላቸው ከሚፈልጉት ቦታ ይደርሳሉ። የምንሠራውንና ወደ ስኬታችን የሚያሻግሩንን ነገሮች ለይተን ማወቅ አለብን። በተለይ ዐረብ ሃገር የሚኖሩ ሴቶች እዚያ መዝናናቱን ትተው ለሃገራቸው የሚጠቅማቸውን ነገር ለመሥራት ማቀድ ይኖርባቸዋል፤ ለነገ ማሰብ አለባቸው ትላለች።
ከምንም ነገር ተነሰቶ ትልቅ ለመድረስ የአላማ ፅናት አስፈላጊ መሆኑን ፈቲያ ፅኑ እምነት አላት። ከተደላደለ ኑሮዋ ላይ ተነስታ የተወለደችበትን አከባቢ ችግር ለመቅረፍ ደፋ ቀና ያለችው ይህች ጠንካራ ሴት፤ ሰርቶ ማሰራትን፣ አግኝቶ ማስገኘትን አይነት ሀሳብ ለማህበረሰቡ በማጋራት ጠንካራ የስራ ባህልን ለማስረፅ እያደረገች ያለችው ጥረት የጠንካራ ሴቶች ተምሳሌት አድርጓታልና ልትመሰገን ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2013