አስመረት ብሰራት
ሴቶች በተሰማሩበት ዘርፍ ሰኬታማ የሚያደርግ ብቃት እንዳላቸው ይታመናል። ነገር ግን የተለያዩ ማነቆዎች ወደኋላ ሲጎቱቷቸው ይታያል። በተሰማሩበት ዘርፍም ከማንም ያላነስ አቅም እያላቸው ዝቅ ሲሉ መመልከት የአደባባይ ሚስጢር ነው።
በርካቶች ደግሞ ትውልድን በተገቢው መንገድ የማሳደግ ኃላፊነትን ይወስዱና የራሳቸው የሚሉት ህይወት ሳይኖራቸው ለልጆቻቸውና ለቤተሰባቸው ኖረው ያልፋሉ።
ሌሎች ደግሞ የቤተሰብ ኃላፊነቱንም የሥራ ኃላፊነቱንም በእኩል መጠን በማስኬድ ካሰቡት የስኬት ጣሪያ ላይ ይቀመጣሉ። ከነዚህኞቹ የጥንካሬ ተምሳሌት ከሆኑ ሴቶች መካከል ደግሞ ወይዘሮ እፀገነት በዛብህ አንዷ ናት።
ወይዘሮ እፀገነት በስራዋ ምክንያት የትዳር አጋሯን አጥታ ልጆቿን ብቻዋን አሳድጋለች። በወቅቱም በውጪ አገር ሥራ ላይ ነበረች። ህይወት በውጣ ውረድ ብትታጀብም ጫንቃዋን አደንድና ወደፊት የተራመደች ጠንካራ ሴት ናት።
ይህች የጥንካሬ ተምሳሌት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከአራት በላይ ሀገራትን በመዞር ያገለገለች ሲሆን አሁን ደግሞ በቱርክ ኢስታንቡል የተሰጣትን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ አጠናቃ አሁን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ወጣቶች ዳይሬክተር በመሆን ኃላፊነትን ተቀብላለች።
ከወይዘሮ እፀገነት ጋር የተገናኘነው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የህፃናት ማቆያ ማዕከል ባስመረቀበት ወቅት ነበር። የሴት ሠራተኞችን ውጤታማነት ወደኋላ ከሚጎትቱት አንዱ ልጆቻቸውን የሚይዙላቸው ሰዎች መታጣታቸው በመሆኑ ችግሩ ለመፍታት መፍትሄው ልጆቹ ከእናቶቻቸው አቅራቢያ መሆናቸው ለእናቲቱ ሰላም ለልጁም ጤና መሆኑ የተመለከተበት ፕሮግራም ነበር።
በወቅቱ ሴቶች የመስራት ፍላጎትም አቅምም እያላቸው፤ ልጆቻቸውን የሚይዝላቸው በማጣት ምክንያት ወደኋላ እንዳይቀሩ መከናወን ካለባቸው ተከታታይ ተግባራት ቀዳሚው የልጆች ማቆያ መገንባት በመሆኑ ይህም ተግባር በቀዳሚነት መሰራቱ በመድረኩ ተጠቅሷል።
እናትነት ሴቶች እንደርስበታለን ብለው ከሚያስቡት አላማ ወደኋላ እንዳያሰቀር የታሰበበት ይህ ስራ ወይዘሮ እፀገነት የብቸኝነት የእናትነት ዘመኗን እንድታስታውስ አድርጓት ነበር። ይህች ሴት በህይወት የገጠማትን ፈተናዎች እንዴት አለፈቻቸው አቅም የሆናትስ ምንድነው የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቼላት እንዲህ ተጨዋውተናል መልካም ንባብ።
ወይዘሮ እፀገነት በአዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አካባቢ በ1970 ዓ.ም ተወለደች። አባቷ አቶ በዛብህ ይመኑና እናቷ ወይዘሮ ፅጌ ባዬ ካፈሯቸው ሰባት ልጆች አምስተኛዋ መሆኗን ትናገራለች። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ፍቅር መከባበርና ሰላም የሰፈነበት፣ ሁልጊዜ ታገሎ ማሸነፍ እንደሚቻል በቂ ትምህርት የሚሰጥበት እና ስነ ምግባርን በማስቀደም ከሰዎች ጋር እንዴት መግባባት እንደሚቻል እየተነገራት ያደገች መሆኗን ታስታውሳለች።
የማያቆም የሚመስል ውብ ፈገግታ ያላት ይህቺ ሴት እውነትም ደስታን አሁን የተለማመደችው ሳይሆን አብሯት ያደገ የእሷነቷ መገለጫ መሆኑን በቆየንባቸው ጥቂት ሰዓታት ለመታዘብ ችያለሁ። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተቀጠረች 23 ዓመታትን አስቆጥራለች። በዚህ ስራ ላይ እያለች ነበር ትዳርንም የመጀመሪያ ልጇንም ያገኘችው። ሦሰት ዓመታትን በመስሪያ ቤቱ ካገለገለች በኋላ በውጭ ባሉ ኤምባሲዎች ለመስራት ተመድባ የሄደችው።
ያኔ የሄደችበት ሀገር ለባለቤቷ ስራ መሰጠት ባለመቻሉ እሷ ስራ ውላ ስትገባ አባወራው ቤት የመቀመጡን ነገር በምንም አይነት መቀበል አልቻለም። የመጀመሪያ የተልዕኮ ሀገሯ በሆነችው በእስራኤል ቴላቪቭ ከተማ ብቻዋን ልጅ እንድታሳድግ ወስኖባት የተለያት ባለቤቷ ከባድ የስራ ኃላፊነትንና እናትነትን አብሮ ለማስኬድ ችግር ፈጥሮባት ነበር።
በቴላቪቭ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ከቆየች በኋላ ብቸኝነት ከእናትነት ጋር ሊያውም የአፍላ ወጣትነት ጊዜ ላይ በጣም ከባድ ሆኖባት እንደነበር ታስታውሳለች። ሁሉ ነገር ባሰበችው ልክ አልቀና ያለት ይህች ሴት በራሷ ጥያቄ ወደ ሀገራ ተመለሰች። በወቅቱ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ለመያዝ ትምህርት ላይ የነበረችበት ወቅት በመሆኑ ‹ወላጆቼ በህይወት እያሉ ስለምን እሰቃያለሁ› ብላ ከወላጆቿ ጋር አብራ ለመኖር ወሰና ወደተወለደችበት ቤት ተመለሰች።
በፈተናው ከመልፈስፈስ ይልቅ አማራጮችን በመመልከት ወደ ውሳኔ የደረሰችው ወይዘሮ ሰኬትን ወደራሷ ለመጥራት የምትችለውን በሙሉ ለማድረግ ትተጋ ጀመር። በዚህም የመጀመሪያ ዲግሪዋን በኢኮኖሚክስ ከመያዟም ባሻገር በተለያዩ ሀገራት በኃላፊነት ስራ ላይ ተመድባ ሀገሯን ለማገልገል ደፋ ቀና ማለት ጀመረች።
ሦስተኛ ምድቧ በካናዳ ኦትዋ ኢትዮጵያ ኢምባሲ ሆኖ ወደዛ ለማቅናት በተዘጋጀችበት ወቅት ሁለተኛ ልጇ አራስ እንደነበረች ታስታውሳለች። ካናዳ ደግሞ ለሞግዚት ቪዛ የማይሰጥ ስለነበር ሁለተኛዋ ልጇን ቢሮ ውስጥ ፍራሽ አንጥፋ ስራዋንም እናትነቱንም ጎን ለጎን እያስኬደች ኃላፊነቷንም እናትነቷንም በብቃት ለመወጣት መቻሏን ትናገራለች።
‹‹በሄድኩበት ሀገር በአብዛኛው ከልጆቼና ከስራዬ መካከል መሆን ሰለሚኖርብኝ መሀል ከተማ ወስጥ ቤት ተከራይቶ መኖር ግድ ይለኝ ነበር።›› የምትለው ወይዘሮ እፀገነት፤ ‹‹በዚህም ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣሁ ለቤት ኪራይ አከራይ ነበር።›› ትላለች። ከገንዘቡም በላይ ግን ልጆቿ አድገው ለስኬት የሚበቁበትን ራዕይ ከፊቷ ሰላስቀመጠች መከራዎቿን በፈገገታ የማለፍ ልምድ አዳብራ እነሆ ትዝታዋንም እየተፍለቀለቀች አውግታለች።
ዛሬ ላይ የመጀመሪያ ልጇ 20 ዓመቷ ሲሆን የካናዳ መንግሥት ለዲፕሎማቶች በሰጠው እድል በመጠቀም የትምህርት ቪዛ ተሰጥቷት የሦሰተኛ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆንዋን ትጠቅሳለች። ሁለተኛ ልጇ ደግሞ አሁን ሰባት ዓመቷ ሲሆን እናቷ በሄደችበት እየተከተለች የመጀመረያ ደረጃ ትምህርቷን እየተማረች መሆኑን ትናገራለች።
ሴቶች በዲፕሎማሲ ዘርፍ ላይ የተለያዩ ምድቦች ላይ ተመድበው ብዙ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ይህም ሲባል እንደ የእውቀታቸው በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና በተለያዩ የዲፕሎማሲ ዘርፍ ተመድበው ከወንዱ እኩል ሊያውም በተሻለ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት ይሰራሉ። ከነዛም መካከል አንዷ መሆኗንም ትናገራለች።
ቀደም ሲል ሴት ዲፕሎማቶች በቁጥር ጥቂት የነበሩ ቢሆንም አሁን ላይ መስሪያ ቤቱ ወጣት ዲፕሎማቶችን በማሰልጠን ወደ ስራው የማስገባት ሁኔታ መኖሩ ሴት ዲፕሎማቶች በበቂ ሁኔታ እንዲፈሩ ለማደረግ የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው ትናገራለች። አሁን በርካታ ሴት ዲፕሎማቶች በመኖራቸውና በብቃት ኃላፊነታቸውን ከመወጣታቸው ባሻገር እያንዳንዷ ሴት በተመደበችበት ሀገር ውስጥ ስትንቀሳቀስ የሀገሯን አልበሳት በመልበስና የፀጉር አሰራር ሀገርኛ በማደረግ የማስተዋወቅ ስራ ይሰራሉ።
በአብዛኛው የኢትዮጵያ ጌጣጌጥን ስለሚጠቀሙ ብዙ ሰዎች ይሄ ምንድነው ብለው ይጠይቃሉ። የኢትዮጵያ ልብስ፣ ጌጥና ፀጉር አሠራር መሆኑን ሲነገራቸው ብዙ ሰዎች አብረው ፎቶ መነሳት እንዲሁም የተለያዩ ጥያቄዎች ሲጠየቁ ኢትዮጵያ በቂ ግንዛቤ ይሰጡ እንደነበር ታመለክታለች።
በአብዛኛውን ጊዜ ግብዣ ሲኖር ቡና በባህላዊ አቀራረብ በማቅረብ ፀጉሯን አፍሮ በማድረግ በጣም ብዙ ሰው ሲማረክበት ማየትና ሰለባህላዊ ቁሳቁሶች ማብራራት የሴት ዲፕሎማቶች ተግባር መሆኑን ወይዘሮ እፀገነት ትጠቁማለች።
ሴት ዲፕሎማቶች በጣም በርካታ ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል። በተለይ ደግሞ በተቀባይ ሀገር ሞገዚት የማያስተናግድ ከሆነ በፈለጉት መጠን ባላቸው አቅም ተጠቅመው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ይቸገራሉ። አብሯት የሚሄድ ሰው ካልኖረ ደግሞ ከባድ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ የትዳር አጋሮች ድጋፍ ማድረግ የሚገባቸው መሆኑን ወይዘሮ እፀገነት ትገልፃለች።
‹‹በመጨረሻ የነበረኩበት በኢስታምቡል የኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራል ፅህፈት ቤት ቆንስል በመሆን በፐብሊክ ዲፐሎማሲ ዘርፍ አገልግያለሁ።›› የምትለው ወይዘሮዋ ‹‹በስራዬ አራት ሀገራትን ማለትም በእስራኤል ቴላቪቪ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁለተኛው በህንድ ኒው ደለሂ እና ሦሰተኛው ደግሞ በካናዳ ኦትዋ ኢትዮጵያ ኤምባሲ በመቀጠል አሁን ወደዚህ እስከምመጣ ድረስ በኢስታንቡል ቆንሰል ጀነራል ቆንስል ነበርኩ።›› ትላለች።
ብቸኛ ለሆነች እናት የሚገጥማት ተግዳሮቶችን ስትገልፅ፤ ቤት ውስጥ ያሉ ኃላፊነቶችን የሚወስድ ሰው ማጣት፤ ሁሉም ነገር በተለይም የውጭውም የውስጡንም ኃላፊነት በሴቲቱ ጫነቃ ላይ ብቻ ሲወድቅ፣ አንዳንዴ ደግሞ የተለያዩ የስራ ጉዞዎች ሲኖሩ በሰው ሀገር ልጆችን ባዶ ቤት ጥሎ የመሄድ ነገር ጭንቅ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ። በነበረችባቸው ሀገራት አለቆቿ ሴቶች ሊያውም ቀድመው የነቁ በምንም መልኩ ተበረታተው የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ የሚያግዙ መሆኑን ትጠቅሳለች።
‹‹ ይህ በመሆኑ ስራ ሲኖረኝ፤ በስራ ጉዳይ የግድ ከቦታ ቦታ መጓዝ ሲኖርብኝ አለቆቼ ቤት አስቀምጬ የምሄድበት ሁኔታ ነበር። ስራሽ በሌላ ሀገር ሲሆን፤ በተለይም እናት ብቸኛ ስትሆን ከኢኮኖሚያዊ ችግር በላይ ብቸኝነቱ በራሱ ችግር ወደኋላ የሚያስቀር ጉዳይ ነው።›› በማለት በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆና ላለችበት ደረጃ እንደደረሰች ታስረዳለች።
‹‹ዛሬ የተገናኘንበት ማዕከል ራሱ ሴቶችን በጣም የሚደግፍ ነው። ማዕከሉ መኖሩ እናቶች ልጆቹ ቤት አንድ ነገር ሆኑ እያሉ ከመሳቀቅ ያላቸውን ሙሉ አቅም ተጠቅመው ስራቸውን እንዲሰሩ ከማድረጉም በላይ ህፃናቱ ቀድመው ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር በቂ ተግባቦት አንዲኖራቸውም ተመራጭነቱ የላቀ ነው።›› ብላለች።
ሴቶች ሲወልዱ ለልጆቻቸው ብለው ስራ ስለሚለቁ በተቋምም ላይ ልምድ ያለው የሰው ሃይል እንዲያጣ ያደርጋል የምትለው ወይዘሮ እፀገነት፤ ሴቶችን ከፍ ያለ ደረጃ ለማድረስ ችግሮቻቸውን በየደረጃው መቅረፍ ከወሬ በዘለለ ተግባራዊ በማድረግ አጋርነትን ማሳየት ተገቢ መሆኑን ትጠቅሳለች።
አሁን በተቀመጠችበት ቦታ ሴቶችን ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ ስለምታከናውነው ተግባር ስትናገር ‹‹ሴት አለቆቼ ትክክለኛውን መስመር ሰላሳዩኝ አሁን በተገኘሁበት የስራ ኃላፊነት ላይ በተግባር የተማረኩትን ተግባራዊ የማድረግ ስራ መስራት አለብኝ ብዬ አምናለሁ።›› ብላለች።
‹‹በእኔ እምነት የፈጠነ ብቻ ሮጦ ይቅደም ሳይሆን ሌሎች ወደ ኋላ የቀሩት ለምንድነው በማለት፣ ምክንያታቸውን በመረዳት፣ ከስራ ቋንቋ በዘለለ በማህበራዊ ግንኙነት በማለሳለስ አቅም ያላቸው ሴቶች በተለያዩ ተፅኖ ስር ወድቀው ወደኋላ እንዳይቀሩ የማድረግ ስራን የመስራት እቅድ አለኝ።›› ትላለች። ከዚህ ቀደም በወሰደችው የአመራርነት ስልጠና ‹‹ብቁ አመራር የሰራተኛውን አቅም አውቆ መጠቀም የሚችል ነው።›› የሚለውን አባባል ተግባራዊ ለማድረግ የምትተጋ መሆኑን ታስረዳለች።
በአጠቃለይ ወይዘሮዋ በስራ ላይ የቆየችባቸውን ዓመታት ልምዶች ቀምራ በእድሜም በስራ ወደ አመራርነት መምጣቷ ለቀጣዩ የስራ ጊዜዋ ስንቅ የሆናት የጥንካሬ ተምሳሌት መሆኗን ተመልክተናል። ጥረትና ትዕግስት በአንድ ላይ ካሉ ሁሉም ነገር በሂደት የሚስተካከል በመሆኑ ሴቶች በምንም አይነት መልኩ ያገኛችሁትን እድል አሳልፋችሁ ሳትሰጡ በትዕግስትና በጥረት ያሰባችሁበት ትደርሱ ዘንድ ምኞቴ ነው በሚል መልዕክት እንሰነባበት።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013