ዳንኤል ዘነበ
ኢትዮጵያ ለትምህርትና ስልጠና ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠቷ ጋር ተያይዞ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በትምህርት ተቋማት ውስጥ ይገኛሉ። የብሄራዊ ፈተና ተፈታኞች ቁጥር ከአመት ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡ በትምህርት ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ከሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ነሐሴ 2012 ዓ.ም በኤጀንሲው ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ታትሞ በወጣው መጽሄት እንደሰፈረው፤ በሀገራችን የዓመቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የተፈታኝ ተማሪዎችን ቁጥር ውጤታማ በሆነ መልኩ ማስተዳደር አዳጋች እየሆነ መጥቷል። የፈተና ደንብ ጥሰትን እየጨመረና እየተስፋፋ ቢሆንም፤ በቁጥጥር ስር ለማዋል አልተቻለም። የችግሩ ቁልፍ መንስኤ ደግሞ የፈተና ስርዓቱ ነው ይለናል።
የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘርይሁን ዱሬሳ በተመሳሳይ፤ በሀገራችን ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ባህላዊ የፈተና ስርዓት እጅግ በጣም ውስብስብ፣ አድካሚና ከፍተኛ ወጪ የሚያሳጣ፤ ለስርቆት፣ ኩረጃና ለሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚዳርግ እንደሆነ ያመላክታሉ።
ኤጀንሲው ከፈተና ስርዓቱ ጋር ተያይዞ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት ባለፉት ዓመታት ጥናቶች ሲያካሂድ ነበር። ከባህላዊ የፈተና /ምዘና ስርዓት በመውጣት ወደ ዘመናዊ ስርዓት መሸጋገር እንደሚገባ ችግሮቹን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ባይቻልም በከፍተኛ ሁኔታ ማቃለል እንደሚያስችል ከውሳኔ መድረስ መቻሉን ያስታውሳሉ።
በኮምፒውተር ላይ የተመሰረተ ፈተና በባህላዊ መንገድ በወረቀትና በእርሳስ ከሚሰጠው የፈተና ስርዓት ጋር ሲነጻጸር በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት የሚገልጹት ዶክተር ዘርይሁን፤ የመጀመሪያው የፈተና ደህንነትን ከማስጠበቅ አኳያ ያለው ጠቀሜታ ነው። ተማሪዎች ከክፍል ወደ ክፍል ለመዘዋወር በትምህርት ዘመን ተርም የሚወስዱት ፈተናም ሆነ ሃገር አቀፍና ብሄራዊ ፈተናዎች ግባቸው የተማሪዎችን ብቃት ፈትሾ ማረጋገጥ ነው። የተማሪዎችን ብቃት ማረጋገጥ ግብ ደግሞ የሃገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ ማስጠበቅ ነው።
በየትምህርት ደረጃው ለሚገኙ ተማሪዎች የሚዘጋጅ ፈተና የተማሪዎችን ብቃት በማረጋገጥ የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ዓላማውን ማሳካት እንዲችል ተፈታኙ ተማሪ እጅ እስኪደርስ በምስጢር መጠበቅ አለበት። እያንዳንዱ ተማሪ ፈተናውን ለራሱ ብቻ እንዲሰራ ማድረግም አስፈላጊ ነው። በቅድመ ፈተና ወቅት ፈተናዎች እንዳይሰረቁና በፈተና ወቅት ደግሞ ተማሪዎች እንዳይኮራረጁ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል።
በወረቀት እርሳስ ምዘና አሰጣጥ እያንዳንዱ የፈተና ወረቀት፣ የማስተላለፊያ ሂደት ውስጥ ፈተናው ለአደጋ ሊጋለጥ ወይም ሊሰረቅ የሚችልበት ሁኔታ በመኖሩ ችግሩ እንዳይከሰት ማድረግ አልተቻለም። በሀገራችን በ2008 ዓ.ም እና ከዛ በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተናዎችና የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ሰርቆ በማውጣት በየፌስቡኩ እንደጀብድ ለመናገር የበቃበትን ሁኔታ የሚታወስ ነው። ኮምፒውተርን መሰረት ያደረገ የፈተና ስርዓት መጠቀም ከተቻለ ግን ይህን አይነቱን ችግር አይከሰትም። ይህ የፈተና ስርዓት ከደህንነት ጋር ተያይዞ ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችን የሚቀርፍ በመሆኑ ተመራጭ መሆኑን ያብራራሉ።
ከተለዋዋጭነት አኳያ ያለው ሌላው ጠቀሜታ እንደሆነ የሚገልጹት ዶከተር ዘርይሁን፤ ኮምፒተር ላይ የተመሰረተ ፈተና በምዘና አስተዳደር መስኮች በኩል ተለዋዋጭ ፈተናዎችን ማዘጋጀት ያስችላል።
የፈተና ጥያቄዎችን በማዘበራረቅ የተለያዩ ኮድ ያላቸውን የፈተና ጥያቄ ዓይነቶችን አዘጋጅቶ ለተፈታኞች ለማቅረብ በር ይከፍታል። በባህላዊው የፈተና ስርዓት እራስ ምታት የሆነብንን የፈተና ደንብ ጥሰትን በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚያስችል ይናገራሉ።
«ስለዚህ ኮምፒውተርን መሰረት ያደረገ የፈተና ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ፤ በሀገራችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የብሄራዊ ፈተና ተፈታኞችን በጥራት መመዘን አዳጋች አይሆንም። በተጨማሪም ከአመት ዓመት እየጨመረና እየተስፋፋ የሚገኘውን የፈተና ደንብ ጥሰትን በቁጥጥር ስር በማዋል ጥራት ያለው የትምህርት ስርአት ለመፍጠር ያግዛል» ሲሉ ኮምፒተርን መሰረት ያደረገ የፈተና ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል ያስረዳሉ።
በተጨማሪም ኮምፒተርን መሰረት ወዳደረገ የፈተና ስርዓት የሚደረግ ሽግግር ፈተናን ለሚያስተዳድሩ ተቋማት የሚሰጠውን ጥቅም ያነሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ፈተና መስጠትን፣ ፈተና ማስተዳደርን፣ ውጤት መግለጽን በተሳለጠና ሁኔታ እንዲያከናውኑ ያስችላል።
በነባሩ የአመዘጋገብ ስርዓት ሲፈጠሩ የነበሩና የተፈታኝ ተማሪዎችን የወደፊት እድል የሚያበላሹ በርካታ ችግሮችን መቅረፍ ያስችላል፡፡ ለምሳሌ የስም፣ የጾታና የመሳሰሉ ስህተቶችን እንዳይፈጠሩ የሚያደርግ መሆኑን ይገልጻሉ። በተጨማሪም ለስራው ይወጡ የነበሩ ከፍተኛ ወጪዎችን በማዳን ለሌሎች የልማት ስራዎች እንዲውሉ በማድረግ ውስን የሆነውን የሀገራችን ሃብት ውጤታማ በሆነ መንገድ ስራ ላይ ለማዋል በር ይከፍታል።
በኤጀንሲው የተፈታኞች ምዝገባና የፈተና ውጤት ጥንቅር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ አበራ በበኩላቸው፤ ኮምፒተርን መሠረት ያደረገ የፈተና ስርዓት መጠቀም ለተፈታኞች፣ ለፈታኝ ተቋማት እንዲሁም በሂደቱ ተሳትፎ ለሚያደርጉ ባለድርሻ አካላት በርካታ ጥቅሞች የሚያስገኝ እንደሆነ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች አመላካች እንደሆነ ይገልጻሉ። የቴክሎሎጂውን ፋይዳዎች ከግንዛቤ በማስገባት ይህን መሰል ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ማዋል የግድ የሚል መሆኑን ይናገራሉ።
በእርግጥም ኮምፒውተርን መሠረት ወዳደረገው ስርዓት ዘው ብሎ የሚገባበት እንዳለመሆኑ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግና የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በጥልቀት መመርመር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ተግባራዊነቱም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማስማማት ስራ ላይ ማዋል የሚገባ መሆኑን ያመላክታሉ።
ኤጀንሲው ይሄንኑ መሰረት በማድረግ ወደ ተግባር ለመሸጋገር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ዮሴፍ፤ ኮምፒውተር ላይ የተመሰረተ ምዘና በመጠቀም ተማሪዎችን በመመዘን እጅግ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ሀገራትን ተሞክሮ የተወሰደ መሆኑን ይናገራሉ። በዋናነትም ናይጄሪያ፣ ግብጽ እና ኢንዶኔዥያ ያሉ ሀገራት በተሞክሮነት የተወሰዱ ሀገራት ሲሆኑ፤ እነዚህ ሀገራት የተመረጡበት ምክንያትም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ የህዝብ ብዛት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ እና የምጣኔ ሀብት ደረጃ ስላላቸው መሆኑን ነው ያብራሩት።
ኮምፒተርን መሰረት ያደረገው የፈተና አሰጣጥና ምዘና ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት ተጠናቋል ያሉት አቶ ዩሴፍ፤ «በ2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙከራ ደረጃ የተጀመረው የኦንላይን ምዝገባ ስርዓት በ2012 ዓ.ም የ12 ኛ ክፍል ተፈታኞች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ነው ያስታወቁት። ኮምፒውተርን መሰረት ባደረገ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚደረገው ሀገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ብቃት መመዘኛ ፈተና ለመውሰድ እስከ አሁን 311 ሺህ 421 ተማሪዎች ተመዝግበው የፈተናውን ጊዜ እየተጠባበቁ ይገኛሉ» ሲሉ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።
የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ ደግሞ፤ መንግስት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም ትምህርት ሚኒስቴር እና ኤጀንሲው በመቀናጀት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ – የ12ኛ ክፍል ፈተናን በኦንላይን ለመፈተን መደረግ የሚገባቸውን ቅድም ዝግጅቶች እያጠናቀቀ መሆኑን ይገልጻሉ። ዘንድሮ አዲስ ቴክኖሎጂ ይዘን ወደ ተማሪዎቻችን የምንቀርብ ከመሆኑ አንጻር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኤጀንሲው ባለድርሻ አካላት ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
አዲስ ዘመን ጥር 10/2013