መርድ ክፍሉ
የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ሥራዎችን በመሥራት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሰፊ ወጣት ህብረተሰብ በማስተባበር አገሪቱ ሰላማዊ እንድትሆን እና የዴሞክራሲ ባህሏ የጎለበትና የበለፀገ አገር የመፍጠር ሂደት ውስጥ የወጣት ህብረተሰብ ሚና ከፍተኛ እንዲሆን የሚያስችሉ አዳዲስ ሥራዎችን ለመሥራት ተዘጋጅቷል።
ሊጉ ወጣቱ ህብረተሰብ የመነጋገርና የሙግት ባህሉ ማደግ አለበት የሚል እምነት አለው።
ስለዚህ የንግግርና የሙግት መድረኮች መዘጋጀት ለውጥ ያመጣል በሚል እሳቤ ለማዘጋጀት እቅድ አውጥቷል። የሚዘጋጁት የንግግር መድረኮች ‹‹ምክንያታዊ የሆነ የወጣቶች ውይይት›› የሚል ሃሳብ አላቸው። የመድረከቹ ዓላማ በተማረ ወጣት ውስጥ የመነጋገር፣ የመወያየትና የመከራከር ባህል ለማሳደግ ነው።
የወጣቶች ምክንያታዊ የውይይት መድረክ በየሦስት ወሩ የሚከናወን ሲሆን፤ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች የሚካሄድ ነው። በሂደት የውይይት መድረኩ በገጠር አካባቢዎችም የሚከናወን ይሆናል።
መድረኩ ወጣት ምሁራን የሚሳተፉበት ሲሆን፤ በክልል፣ በዞንና በወረዳ ከተማዎች ውይይቱ የሚከናወን ይሆናል። ውይይቱ በመጀመርያ በክልል ከተማዎች የሚጀመር ሲሆን፤ በመቀጠል በዞን ከተማዎች ላይ እንዲሁም በመጨረሻ በወረዳና በወረዳ መዋቅር ተጠሪ በሆኑ ከተማዎች ላይ እየተካሄደ ይገኛል።
እስከአሁን ባለው ዳሰሳ ከአንድ ሺ አንድ መቶ በላይ ከተማዎች ላይ የውይይት መድረኩን ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጎ በመጀመሪያው ዙር አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን በመድረኩ ለማሳተፍ መድረኮቹ ተጀምረዋል።
የውይይት መድረኩ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ በአንድ ሺህ አንድ መቶ ከተሞች ላይ የሚከናወን ሲሆን፤ ስድስት ክልሎች በከተማዎቻቸው የምክንያታዊ ወጣት መድረክን አካሂደዋል። መድረኩ አሁንም በተለያዩ ክልል ከተማዎች እየተካሄደ ይገኛል። ስለ መድረኩ ሁኔታና የተንፀባረቁ ሃሳቦች ዙሪያ ከብልፅግና ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፅህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት አክሊሉ ታደሰ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡– ምክንታዊ የወጣቶች መድረክ በምን ዓይነት ሁኔታ እየተካሄደ ነው?
ወጣት አክሊሉ፡- ምክንያታዊ የወጣቶች መድረክ የንግግርና የሙግት ባህሪ ያለው ሲሆን፤ ዋና ዓላማው ወጣቱ ህብረተሰብ ምክንያታዊ እና በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማስቻል እንዲሁም ሠርቶ የሚቀየርና ብልፅግና የሚያመጣና በአገሩ አንድነት ላይ የማይደራደር የወጣት ማህበረሰብን የመገንባት ሥራ ነው።
ከዚህ ቀደም እንደዚህ ዓይነት አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎች አይከናወኑም ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ለአገር ፋይዳ ያላቸው ትልልቅ ጉዳዮች ላይ አስተዋፅኦ እናድርግ በሚል እቅድ ይዞ እየሠራ ነው።
መድረኩ በየሦስት ወሩ የሚካሄድ ቢሆንም አሁን ባለው እንቅስቃሴ በየሁለት ወሩ ሊካሄድ ይችላል። አጀንዳው ከላይ የተቀመጡትን ነገሮች ሊያሳካ የሚችል ሃሳብ እየተመረጠ ይካሄዳል። በመጀመሪያው ዙር አንድ ሺህ አንድ መቶ የወረዳ ከተማዎች ድረስ የሚካሄድ ነው። ለሁለተኛውም ዝግጅት የሚደረገው የመጀመሪያው ዙር በሁሉም ከተማዎች ከተካሄደ በኋላ ነው።
በአሁን ወቅት በስድስት ክልሎች እየተካሄደ ሲሆን፤ በቀጣይ በዞንና በወረዳዎች ላይ የሚቀጥል ይሆናል።
በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ በሁሉም ክልል ይጀምራል። ሌሎች ያካሄዱ ክልሎች ደግሞ ወደ ዞን ከተማዎች መድረኩን እያወረዱ ይሄዳሉ። በዚህ መንገድ በሁሉም ከተማዎች የሚካሄዱ ይሆናል። በአንደኛው ዙር አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡– በተካሄዱ መድረኮች ምን ምን ሃሳቦች ተንፀባርቀዋል?
ወጣት አክሊሉ፡- የመጀመርያው ዙር አጀንዳ ‹‹የአገረ መንግሥት ግንባታና የዓለም አቀፍ ልምዶች እንዲሁም የወጣቱ ሚና›› በሚል ርዕስ እየተካሄደ ይገኛል። ከአጀንዳው ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል።
በመድረኩ ምሁራን ወጣቶች እየተሳተፉ ናቸው። ከተነሱት ሃሳቦች መካከል አገረ መንግሥት ምን ማለት እንደሆነ፣ ብሄረ መንግሥት ምን ማለት ነው? እንዲሁም ሁለቱን የሚለያቸው ጉዳይ ምንድነው እናም የኢትዮጵያ የአገረና የብሄረ መንግሥት ምስረታ ምን እንደሚመስልና የሌሎች አገራት ተሞክሮ እንዴት ነው የሚሉት ጉዳዮች ተዳሰዋል።
ለምሳሌ በደንብ መግባባት ላይ የተደረሰበት አገረ መንግሥት ሲባል አገር እንደ አገር እንዲቆም፣ ዜጎችን ከጠላት ወረራ መጠብቅ እንዲቻልና መንግሥት እንደመንግሥት ለዜጎች የሚያቀርበውን አገልግሎት ለማመቻቸት ገቢ የሚያመነጩ ተቋማት ግንባታ ማለት ነው። አንድን አገር ከጠላት ወረራ የሚጠብቅ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት ያስፈልጋል።
መንግሥት ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርጋቸው አገልግሎቶች ማለትም ትምህርትና ጤና ተደራሽ ለማድረግ ገቢ መሰብሰብ ይኖርበታል። ስለዚህ የገቢ ሰብሳቢ ተቋማት እንዲሁም በተሰበሰበው ገቢ ደግሞ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መገንባት ግዴታው ነው።
ዜጎች ሲበደሉ የሚዳኝ የፍትህ አካል፣ የውስጥ ፀጥታን የሚያስጠብቅ የፖሊስ ተቋማት እንዲሁም የሌሎች ተቋማት ጉዳይ የመንግሥት ግንባታ ይባላሉ። የአገረ መንግሥት ግንባታ ተብሎ የሚጠራው በመሰረታዊነት ይህ ነው።
ብሄረ መንግሥት የሚለው አገላለፅ ወይም ብሄር የሚለው አገላለፅ ከተለመደው ይለያል። ‹‹ኔሽን›› ሲባል አንድ የተለየ ብሄርን የሚገልፅ አይደለም። ‹‹ኔሽን›› የሚለው የእንግሊዝኛ አገላለፅ አገርን የሚገልፅ ነው። ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን የያዘ አገርን እየገለጸ ነው። ‹‹ኔሽን ቢውልዲንግ›› ሲባል በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ህዝቦች አገራዊ ማንነት የሚገነቡበት የውስጥ አስተሳሰብና አቋም ነው።
ነዋሪው አገሪቱ የኔ ናት ብሎ የሚያስብበት፣ ባንዲራው የኔ ነው ብሎ የሚመካበት፣ የኔ ባህል ነው፣ የኔ እሴት ነው እናም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ማሰብ እንዲችል የሚያደርገው ነው። በአማርኛ የብሄር ግንባታ ማለት ሳይሆን የጋራ ማንነት ግንባታ ተብሎ ነው የሚተረጎመው። ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዝሀነት ያለባቸው አገር ውስጥ ብዙ ቋንቋዎች፣ ብዙ ሃይማኖቶች፣ ብዙ ባህሎችና ብዝሀነት ቢኖሩም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የጋራ ማንነት የሚገነቡበት አስተሳሰብ ብሄረ መንግሥት ግንባታ ይባላል።
የጋራ ማንነት ግንባታ ሥራ ተሠርቶ የሚመጣ ነገር ሲሆን፤ ባለፉ ታሪኮች፣ ህዝብ ከህዝብ ጋር በነበሩ ግንኙነቶች፣ ባለፉ የጦርነት ታሪኮች፣ የሰላም፣ የመተሳሰብ፣ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲሁም መልካምና መጥፎ የሆኑ የታሪክ ግንኙነቶች የሚፈጥሩት አብሮ ቆይታነት የሚያመጣው የብሄር ግንባታ የሚባለው ሃሳብ ነው። የአገር መውደድን የሚያዳብረው በታሪክ ሂደት ውስጥ በሚኖረው መልካምና መልካም ያልሆኑ ግንኙነቶች የማጠናከርና የማላላት ነገር ነው። ከዚህ ጋር የተያያዙ ብዙ ጉዳዮች እየተነሱ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ አገረና ብሄረ መንግሥት ግንባታ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለው ጉዳይና በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት የተሠሩ ሥራዎች ምንድናቸው የሚለው ሁኔታም በየመድረኮቹ እየተዳሰሱ ይገኛሉ። በሦስት ሺህ ዓመት ታሪክ ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኔ አገር ነው ብሎ እንዲያስብ የተሠራው ሥራ ምንድነው? እና የተሠሩት ሥራዎች ውስጥ ምን ጉድለት አለ? የሚለው በስፋት ሙግት እየተደረገበት ይገኛል።
ለምሳሌ ብዝሀነትን ከመፍጠር አንፃር ሁሉም በጋራ የኔ ነው ብሎ እንዲያስብ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል ትልቅ ጉዳይ ነው። ያሉትን መልካምና መጥፎ አጋጣሚዎች በመለየት ሌሎች ትስስሮችን በማጠናከር ለጋራ እሴቶች ዋጋ እየሰጡ የአንድነት መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት ሊመጡ የሚችሉ ለውጦች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።
የወጣቶች ሚና ምን መሆን አለበት የሚለው ጉዳይ በስፋት ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ ወጣቱ እኩልነትን የተቀበለ እንዲሆን፣ ብዝሀነትን የተቀበለ እንዲሆን እንዲሁም የተጠናከረ የአገረ መንግሥትና የብሄር ግንባታ እንዲኖር እኩልነትን መቀበል የግድ ያስፈልጋል። አንዱ የበላይ አንዱ ትንሽ የሚሆንበት ነገር ትክክል አይደለም ብሎ የሚታገል ወጣት ህብረተሰብ ያስፈልጋል።
ለኢ-ፍትሐዊነት የሚታገል ወጣት እስካልተገነባ ድረስ የምናስበው የአገርና የብሄር መንግሥት ግንባታ ሊሳለጥ አይችልም።
ሌላው ኢኮኖሚ፣ እድገትና ብልፅግናው ደሀ ከተኮነ በትንንሽ ነገሮች ግጭት ውስጥ የሚገባ በመሆኑ የኢኮኖሚ አቅም እያደገ በመጣ ቁጥር በትንንሽ ጉዳዮች መጋጨት አይኖርም አገራዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዴት መግባባት እንደሚቻል መታሰብ ይጀምራል። ስለዚህ አገሪቱ እንድታድግና እንድትበለፅግ ዜጎች መሰረታዊ ጉዳዮች የማያጥሯቸው እንዲሆኑ ለማድረግ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አጠናክሮ መሠራት አለበት።
ወጣቱ ምክንያታዊ እንዲሆን በየሰበቡ መጋጨት የለበትም። ብሄር ለይተው ለማጋጨት የሚሞክሩ ኃይሎችን መቃወም አለበት። ይህ ካልሆነ በትንንሽ ጉዳዮች ግጭት ውስጥ ከተገባ ከፍተኛ ቁርሾ ውስጥ ይገባል። በህዝቦች፣ በብሄሮች፣ በተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ በተለያየ አገር ነዋሪዎች እና በእምነቶች መካከል ቁርሾዎች እንዲባባሱ ያደርጋል።
ስለዚህ ወጣቱ ምክንያታዊ መሆን አለበት። ሊያጋጩ የሚችሉ ጉዳዮችን ለምን ብሎ መጠየቅና ማስቆም አለበት። ከዚህ ውጪ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ታሪኩን፣ ባህሉንና ትስስራቸውን የሚረዳ ወጣት መሆን አለበት።
ለዚህም ምክንያት ላይ የተመሰረተ ከሆነ ለአገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ነው። እነዚህ ጉዳዮች ከወጣቱ ምን ይጠበቃል በሚለው ምዕራፍ ውስጥ በሰፊው እየተዳሰሰና ውይይት እተደረገበት ያለ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡– ውይይቱ በተካሄደባቸው ክልሎች ወጣቱ የፅንፈኞች አስፈፃሚና የጦርነት ተማጋጅ እንዳይሆን የተነሱ ነገሮች ነበሩ?
ወጣት አክሊሉ፡- በመድረኮቹ ከአጀንዳው ጋር ተያይዞ የተነሱ ሃሳቦች ነበሩ። በተለይ ከእውነታዎች ጋር ተያይዞ በአገር ውስጥ ያሉት የህዝቦች አንድነትና በጋራ የመኖር ትስስርና ተከባብሮና በሰላም የመኖር ጉዳይ በአገሪቱ ባሉ አካባቢዎች እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ ተነስቷል።
አንዱ የተጠናከረ ምክንያታዊና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብ ባለመፍራቱ ምክንያት ችግሮች ተነስተዋል የሚለው ድምዳሜ ላይ ተደርሶበታል። ሁለተኛው የአገረ መንግሥት ግንባታ እውቀትና የአገርና የብሄረ መንግሥት ግንባታ ላይ የተሠራው ሥራ የላላ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እየመጣ ያለ ጉዳይ ነው የሚል ሃሳብ ተነስቷል።
በአገሪቱ ሰው በማንነቱ የማይጠቃበትና ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ ለመፍጠር ወጣቱ ምን ማድረግ አለበት እንዲሁም በመተከል ያለው ሁኔታ ከዚህ አንፃር ምን ይመስላል። በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ በተለይ ሰላም ለማስፈን ምን እየተሠራ ነው። ሰላምና እኩልነትን ወደ ጎን በመተው እኔ የበላይ መሆን አለብኝ ብሎ የተንቀሳቀሰው የህወሓት አጥፊ ቡድን ያለበት ሁኔታ ምን እንደሚመስል እና እነዚህን ሁኔታዎች እንዴት መታገል ይቻላል የሚለው ላይ ወጣቱ እየተወያየበት ያለ ነገር ነው።
በሁሉም ከተሞች አካባቢ የነበረው መግባባት ለአገር ሰላም፣ ለአገር አንድነት፣ ዜጎች ወደተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው በማንነታቸው ጥቃት ሳደርስባቸው በነፃነት እንዲሠሩ ያለው ሁኔታ በወጣት ውስጥ እየሰረፀ ይገኛል።
ወጣቱ ለዚህ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በየመድረኮቹ መተማመን እየተደረሰበት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በቀጣይስ የመድረኮቹ ሁኔታ በምን ዓይነት ሁኔታ ይካሄዳል?
ወጣት አክሊሉ፡- በየመድረኮቹ የሚገኙት ምሁራን በሃሳብ ደረጃ ብዙ ነገር የሚያነሱና የሚመሩት በመሆኑ መድረኩ ላይ ለመሳተፍ የኦን ላይን ምዝገባ ይከናወናል። እስከአሁን 91 በመቶ የሚሆነው በየመድረኩ የሚሳተፈው ወጣት የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ የያዙ ናቸው። በቀጣይ እየታሰበ ያለው የመጀመሪያው ዙር እንደተጠናቀቀ ለሁለተኛው ዙር ዝግጅት ይከናወናል።
ለምሳሌ የቀጣይ አጀንዳ ምን ይሁን የሚለው በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ምሁራን ሃሳብ እየተሰበሰበ ነው። ሁለተኛው ዙር አብዛኛው ምዝገባ በኦንላይን የሚከናወን ይሆናል።
ሁለተኛውም ዙር ልክ እንደ መጀመሪያው በተመሳሳይ ሁኔታ ይከናወናል። የመጀመሪያው ዙር ውይይት በወረዳ ከተሞች ላይ መካሄድ ሲጀምር ሁለተኛው ዙር በክልል ከተሞች ይጀምራል። ለዚህም አስፈላጊ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
የአንደኛውም ዙር አፈፃፀም በማየት ሁለተኛውን ዙር ላይ ምን ያክል ወጣቶች መሳተፍ አለባቸው የሚለው ይወሰናል። የምሁራን ተሳትፎና ፅሑፍ ዝግጅቱ የበለጠ እየተጠናከረ ይሄዳል።
አዲስ ዘመን ጥር 07/2013