መርድ ክፍሉ
በአገሪቱ ውስጥ የንግግርና የሙግት ባህል ብዙም የጎለበተ አይደለም። የትኛውም አይነት ጉዳዮች በንግግር፣ በሙግትና በሀሳብ ያሸነፈው እንዲገዛ እድል የመስጠት ወይም በንግግርና በሙግት የማለፍ ባህሉ በጣም ደካማ ነው። አብዛኛውን ነገር በአገሪቱ በመንግስት ይሁን በግል ተቋማት እንዲሁ በቤተ እምነት አመራሮች መካከል፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች መካከል፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በገዥው መንግስት መካከል የሚኖሩ ጉዳዮች በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ላይ የሚታዩ ችግሮች ከስር ጀምሮ የንግግርና የሙግት ባህሉ አለመዳበር ጋር የተያያዘ ነው።
የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ስራዎችን በመስራት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሰፊ ወጣት ህብረተሰብ በማስተባበር አገሪቱ ሰላማዊ እንድትሆን እና የዴሞክራሲ ባህሏ የጎለበተና የበለፀገ አገር የመፍጠር ሂደት ውስጥ የወጣት ህብረተሰብ ሚና ከፍተኛ እንዲሆን የሚያስችሉ አዳዲስ ስራዎችን ለመስራት ተዘጋጅቷል።
በዚህም መሰረት ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ ያሰበው የንግግርና የሙግት መድረክ ማዘጋጀት ነው። የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፅህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት አክሊሉ ታደሰ በሚያዘጋጀው መድረክ ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል። ማብራሪያውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የመድረኩ አላማ
የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ወጣቱ ህብረተሰብ የመነጋገርና የሙግት ባህሉ ማደግ አለበት የሚል እምነት አለው። ስለዚህ የንግግርና የሙግት መድረኮች መዘጋጀት ለውጥ ያመጣል በሚል እሳቤ ለማዘጋጀት እቅድ አውጥቷል። የሚዘጋጁት የንግግር መድረኮች ‹‹ምክንያታዊ የሆነ የወጣቶች ውይይት›› የሚል ሃሳብ አላቸው። የመድረከቹ አላማ በተማረ ወጣት ውስጥ የመነጋገር፣ የመወያየትና የመከራከር ባህል ለማሳደግ ነው።
\ሌላው የመድረኩ አላማ የንባብ ባህልን የማሳደግ ነው። የወጣቱ የንባብ ባህል በሚፈለገው ደረጃ ያደገ አይደለም።
የብዙ አገራት ልምድ በሚታይበት ወቅት ሰው በየግሉ አንብቦ የተለያዩ ሀሳቦች በማውጣጣት በጠረጴዛ ዙሪያ የሚነጋገርበት መድረክ ሲኖር የማንበብ ባህል እያደገ ይመጣል። ማንኛውም ሰው የንግግር መድረክ ከተዘጋጀለት አንብቦ ይመጣል። ያነበበውን ከሌሎች ጋር ይከራከርበታል።
የተለየ ሀሳብ ሲያጋጥም ተከራክሮ ለማሸነፍ ብዙ መፅሀፍቶችን ያገላብጣል። የንባብ ባህሉ ያደገ ህብረተሰብ በአገር እድገት፣ ሰላም በመፍጠር ውስጥና ብልፅግና በማምጣት ረገድ የማይተካ ሚና ይኖረዋል። አዕምሮን ለማሳደግ የንባብ ምግብ ያስፈልገዋል። የንባብ ባህል በሚፈለግ መንገድ እያደገ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን የሚኖሩት የንግግር መድረኮች የክርክርና የውይይት መንፈስ የማዳበርና የንባብ ባህልን አብሮ ለማሳደግ የታለመበት ነው።
ሶስተኛው ዓላማ በአገሪቱ የሚኖሩት ወጣት ህብረተሰብ በምክንያትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሀሳብ እንዲሰጥ ይፈለጋል። በአገሪቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት እና ከዛም በፊት በነበሩ ጊዜያት ብዙዎቹ ክርክሮች ያልተፈለጉ ችግሮች አምጥተዋል። ወጣቱን እንደመሳሪያ በመጠቀም የተለያዩ ግጭቶች ተፈጥረው ነበር።
እነዚህ የተፈጠሩት ችግሮች በምክንያት ላይ የተመሰረተ ንግግር ዝቅተኛ መሆኑን ማሳያ ነው። በማንኛውም ጉዳይ ላይ ጥልቅ እውቀት አለመኖርና በአንድ ጉዳይ ላይ ለምን ብሎ መጠየቅ አለመቻል ችግር እየፈጠረ ነው።
በአገራዊ ጉዳይ ላይ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች እውቀት ያስፈልጋል። በእውቀትና በምክንያት የሚደረግ ንግግር ለአገር እድገትና ሰላም እንዲሁም ለአገረ መንግስት ግንባታ የሚኖረው አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛ ነው። የሚኖሩት የንግግር መድረኮች አላማ በምክንያትና በእውቀት የሚመራ የወጣት ህብረተሰብ በመገንባት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
አራተኛው ዓላማ በአገሪቱ ውስጥ የፅንፈኝነት አስተሳሰብ እየዳበረ ይገኛል። ፅፈፈኝነት እየዳበረ እንዲመጣ ካደረጉት መካከል ህብረተሰቡ ከራሱ ሀሳብ ውጪ አለመቀበልና ቡድኖች ከራሳቸው ሀሳብ ውጪ ያለን ሀሳብ ጆሮ መስጠት ስለሚሳናቸው ነው። በየትኛውም ሀሳብ ላይ በጋራ ሆነው የሚነጋገሩበት መድረክ እየጠፋ በሚመጣበት ወቅት የፅንፈኝነት አስተሳሰብ እያደገ ይመጣል።
በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩት በተለይ በተማሩት ሰዎች አካባቢ የሚታየው ጫፍ የመያዝ ነገር እና በሚይዙት ጫፎች መካከል ያለው ስፋት ከባድ ችግሮችን እያመጣ ነው። የማይታየውን የመሀል ክፍተት መመልከት የሚቻለው ንግግር ሲኖር ነው። በንግግር የሌላውን ሃሳብ ለማዳመጥና የራስን ሃሳብ ማስረፅ የሚቻለው የንግግር መድረኮች ሲዘጋጁ ብቻ ነው።
ንግግር ፅንፍ የወጣን ሀሳብ ለማቀራረብና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የሚያደርግ ነው። ስለዚህ በሚዘጋጁ የንግግር መድረኮች ፅንፍ የተያዘባቸውን ሀሳቦች እየገታ የመሀል አስተሳሰቦችን በመፍጠር መቻቻልና መደማመጥ እንዲመጣ ያደርጋል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ በትልልቅ ጉዳዮች ጭምር እንደ ዜጋ መስማማት የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት ያቅታል ማለት ነው።
የተማረው ወጣቱ ህብረተሰብ በጋራ ጉዳዮች በተለይ የሀይማኖት፣ የብሄር፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የታሪክና የልምድ ብዝሀነት ባለባቸው አገራት ውስጥ ሰብሰብ የሚያደርግና አንድነት የሚፈጥር መድረክ ከሌለ አገረ መንግስቱ አደጋ ሊገጥመው ይችላል። የፅንፈኝነት አስተሳሰብን ለማጥፋት የንግግር መድረክ ወሳኝ ሚና አላቸው።
አምስተኛው ዓላማ ደግሞ ወጣቱ ህብረተሰብ የመፍትሄ አካል እንዲሆን ለማድረግ የንግግር መድረክ አስፈላጊ ነው። የንግግር ባህል እያደገ ሲመጣ የሙግትና ነፃ የሆነ ሁኔታ ሲፈጠር በአንድ ጉዳይ ላይ ሰዎች መነጋገር ይችላሉ።
መነጋገር ሲችሉ ሀሳባቸውን ያዋጣሉ፣ ይከራከራሉ እንዲሁም የተሻለ የሆነውን ይመርጣሉ ከዛም ወደ መፍትሄ ይመጣሉ። በተጨማሪም ከወጣቱ ምን ይጠበቃል? ወደሚል ሀሳብ መምጣት ይቻላል። ትችት የሚያበዛና ችግር ብቻ የሚያወራ ከሆነ አገር በማሳደግ ሂደት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ሚና ሊጫወት አይችልም። በማንኛውም ጉዳይ ላይ ውይይቶች ሲደረጉ የመፍትሄ ሃሳብ በዛው የማመንጨት ሁኔታ ይፈጠራል።
የሚደረጉ የውይይት መድረኮች ከወጣቱ ምን ይጠበቃል የሚለውን ሀሳብ መያዝ አለባቸው።
ወጣቱ የመፍትሄ ሰው መሆን ከቻለና ምክንያታዊ የሆነ ወጣት ከተፈጠረ በመፍትሄ ሀሳቦች የራሱን ሚና መጫወት የሚችል ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል። እነዚህ ሁሉ ሲደመሩ ለአገር የሚኖራቸው ፋይዳ ምንድነው የሚለው ሲታይ አገሪቱ ሰላም የሰፈነባት፣ የተረጋጋች፣ የዴሞክራሲ ባህሏ ያደገና የበለፀገች አገር በማድረግ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
እንደ ብልፅግና ወጣቶች ሊግ አገሪቱ ሰላም የሰፈነባት እንድትሆን፣ የዴሞክራሲ ባህል ያደገባት እንዲሁም ድህነትን ለመቅረፍ በህብረተሰብ ውስጥ የመነጋገር ባህል እንዲጎለብት በማድረግ ለአገር በሚጠቅም ጉዳይ መተባበር ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ የወጣት አደረጃጀቱ ትልቅ ሚና አለው በሚል ሀሳብ መድረኮቹ ተዘጋጅተዋል። እነዚህን ጥቅሞች ለማስገኘት የሚዘጋጀው መድረክ ወጣቶች ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የሚወያዩበት ይሆናል።
የመድረኩ አዘገጃጀት
የወጣቶች ምክንያታዊ የውይይት መድረክ በየሶስት ወሩ የሚከናወን ሲሆን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች የሚካሄድ ነው። በሂደት የውይይት መድረኩ በገጠር አካባቢዎችም የሚከናወን ይሆናል። መድረኩ ወጣት ምሁራን የሚሳተፉበት ሲሆን በክልል፣ በዞንና በወረዳ ከተማዎች ውይይቱ የሚከናወን ይሆናል። ውይይቱ በመጀመሪያ በክልል ከተማዎች የሚጀመር ሲሆን በመቀጠል በዞን ከተማዎች ላይ እንዲሁም በመጨረሻ በወረዳና በወረዳ መዋቅር ተጠሪ በሆኑ ከተማዎች ላይ ይካሄዳል።
እስካሁን ባለው ዳሰሳ ከአንድ ሺ አንድ መቶ በላይ ከተማዎች ላይ የውይይት መድረኩን ለማካሄድ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን በመድረኩ ለማሳተፍ ታስቧል። የውይይት መድረኩ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ በአንድ ሺህ አንድ መቶ ከተሞች ላይ የሚከናወን ሲሆን በሁለተኛው ዙር በተቀሩት ከተማዎችና የገጠር አካባቢዎች ይካሄዳል።
የመጀመሪያው ዙር የወጣቶች ምክንያታዊ ውይይት መድረክ አጀንዳ ‹‹የአገረ መንግስት ግንባታና የወጣቱ ሚና›› የሚል ሲሆን የሊጉ መዋቅር ከታች ጀምሮ ሁለት ወራት የፈጀ ዝግጅት አድርጓል። በፌደራል ደረጃ የሚመለከታቸው ተቋማት በተለይ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴርና ከክልሎች ጋር በመተባበር የሚከናወን ነው። የውይይት መድረኩ በነፃነት ውይይት የሚከናወንበት ሲሆን የትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ወጣቶች በጋራ የሚነጋገሩበት ይሆናል።
የትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ያለው ሀይል፣ የትኛውም እምነት ተከታይ እንዲሁም የትኛውም ብሄር አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮች አሉት። የአገር ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና እንዲሁም አገረ መንግስት ግንባታ ላይ አንድ የሆነ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ውይይቱ ይረዳል።
በአገሪቱ አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ የሚደረገው የንግግርና የሙግት መድረክ የትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ወጣቶች በጋራ መጥተው ውይይት የሚያደርጉበት ነው። የተማሩ ወጣቶች በመድረኩ በስፋት ተሳታፊ ይሆናሉ።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከመንግስትና ከግል መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ወጣቶች እንዲሳተፉ ተመቻችቷል። የመወያያ ፅሁፍ በማቅረብ ሂደት ውስጥ በተመሳሳይ መንገድ የትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እንዲሳተፉበት እየተደረገ ነው። የመድረኩን ሀሳብ በአግባቡ ማስጨበጥ የሚችሉና አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር እያዛመዱ ወጣቱ ትምህርት እንዲጨብጥበትና በነገው ህይወቱ ሚዛናዊ እንዲሆን እንዲሁም እውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዋፅኦ ማድረግ እንዲችል አላማውን ሊያሳኩ የሚችሉ ሰዎች የተመለመሉበት ሁኔታም አለ።
በሁለተኛውና በሶስተኛው ዙር የውይይት መድረኮች ላይ ተሳታፊዎችን መመዘኛ በማስቀመጥ በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ የመመልመል ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። በመድረኩ ፅሁፍ የሚያቀርቡ ሰዎች በውድድር እንዲመረጡ ይደረጋል።
በተቀመጠው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥሩ ትንታኔ ማቅረብ የሚችሉ ሰዎች እንዲመጡም ያስችላል። በተጨማሪም የውይይቶቹ አጀንዳዎችም ምሁር ወጣቶች ተሳታፊ ባደረገ መልኩ ምርጫ ይደረጋል። የብልፅግና ወጣቶች ሊግ በአመለካከቱ ለአገር አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችል የአገረ መንግስት ግንባታውን የተጠናከረ እንዲሆን አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችል ማህበረሰብ እንዲፈጠር ለማድረግ አንድ ኃላፊነት አለበት። አገር ሰላም እንዲሆንና ዴሞክራሲ እንዲዳብር ሁሉም ወጣት ኃላፊነት አለበት።
የብልፅግና ወጣቶች ሊግ መድረኩን ለማዘጋጀት ኃላፊነት የወሰደ ሲሆን በቀጣይ ሁሉም አካላት ከማዘጋጀት ጀምሮ ተሳታፊ እንዲሆኑ ይመቻቻል። የዚህ ድምር ውጤት ሰላም የሰፈነበት፣ የተረጋጋችና ዴሞክራሲያዊ ባህል የጎለበተባት አገር ለመገንባት የሚያስችል እንዲሆን ጥረት ይደረጋል። ውይይቱ ከታህሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የሚከናወን ሲሆን በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማና በሱማሌ ክልል ተካሂዷል። በተከታታይ በሌሎች ክልል ከተማዎች ላይ መድረኩ የሚቀጥል ይሆናል።
ለውይይቱ ከተማዎች መነሻ የተደረጉት ስራው ሰፊ በመሆኑ ነው። የሊጉ መዋቅር ያለው እስከ ወረዳ ድረስ ሲሆን ቀበሌ ላይ የተጠናከረ መዋቅር የለም። ሁሉንም በአንዴ መድረስ ያልተቻለው የአቅምና የመዋቅር ችግር ስላለ ነው። መድረኩ የምሁር ወጣቶች ተሳትፎ የሚፈልግ በመሆኑ ከተማዎች ላይ እንዲደረጉ በመወሰኑ ነው። በመድረኩ ለሚነሱ የተለያዩ ጥቄዎች ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ የሚሰጡ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ይገኛሉ። ነገር ግን ጥያቄዎች ተነስተው የሚመለሱበት መድረክ አይደለም። በዋነኝነት በጉዳዮች ላይ ያሉ አተያዮችን ማስተካከልና ለጉዳዮች ድርሻ የሚወሰድበት እንዲሁም መንግስትም ያሉ ችግሮችን ለይቶ የሚፈታበት ይሆናል።
የተካሄዱት መድረኮች
በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ በኦሮሞ ባህል ማዕከል ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ከ300 በላይ ወጣቶች በተሳተፉበት ተካሂዷል። መድረኩ ‹‹የሀገረ መንግስት፣ ብሄረ መንግስት ግንባታና ዓለም አቀፋዊ ልምዶች›› የሚል ርዕስ ላይ ትኩረት አድርጓል። ወጣቱ ሲቃወምም ሆነ ሲደግፍ በምክንያት ሊሆን እንደሚገባ የሚያመላክቱ ዓለም አቀፋዊ ልምዶችም በቀረቡ ፅሁፎች ተዳሰዋል።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አመራር በመድረኩ የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱ ያለወጣቱ ምክንያታዊነትና ንቁ ተሳትፎ ዋጋ እንደሌለው ተናግሯል። ወጣቶች በተጀመረው ለውጥ ውስጥ የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ እውቀት እና ልምድን መሰረት ያደረገ ምክንያታዊነት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። መድረኩም በዋናነት እውቀት እና ልምድን መሰረት ያደረገ ምክንያታዊነትን መፍጠር ያለመ መሆኑንም አስታውቋል። ለወጣቱ መሰል መድረኮች መዘጋጀታቸው አስፈላጊነታቸው የጎላ መሆኑም በመድረኩ ላይ ተነስቷል። በውይይቱ ከወጣት አደረጃጀትና ከንግዱ ማህበረሰብ የመጡ እንዲሁም ምሁራን እና የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ወጣቶች ተሳታፊዎች ነበሩ።
ምክንያታዊ የወጣቶች የውይይትና ሙግት መድረክ በአማራ ክልል ደረጃ በባህር ዳር ተካሂዷል። በመድረኩ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ ምሁራን ወጣቶች እየተሳተፋበት ሲሆን ‹‹የሀገረ መንግስት ግንባታና የወጣቱ ሚና›› በሚል ርዕስ ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። የሀገረ መንግስት ግንባታ ምንነት፣ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደትና ትምህርት የሚወሰድባቸው ጉዳዮች፣ የሌሎች ሀገራት የሀገረ መንግስት ግንባታ ልምዶች፣ ለውጡና የሀገረ መንግስት ግንባታ እርምጃዎች እንዲሁም የተጠናከረ የሀገረ መንግስት እውን ማድረግ ይቻል ዘንድ የወጣቱ ሚና የሚሉት ነጥቦች ተዳሰውበታል። ብዝሀነትን ጠብቆ አንድነት የሚጠናከርበት፣ ሰላምና ብልጽግና የተረጋገጠበት፣ ዜጎች በእኩልነት ተንቀሳቅሰውና ሰርተው ህይወታቸውን የሚመሩባትን ኢትዮጵያ ማጠናከር ይቻል ዘንድ ሀገረ መንግስቱ ሊቆምባቸው የሚገባው ምሰሶና የወጣቱ ሚናም በሰፊው የተመከረበት ነበር።
በተጨማሪም የምክንያታዊ ወጣት መድረክ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ የተካሄደ ሲሆን ‹‹ሙሉ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለሀገራችን ወጣቶችና ለክልላችን እናረጋግጣለን›› በሚል መሪ ቃል ነበረው። ያለፉት ስርዓቶች ብሄር ብሄረሰቦችን አሳታፊ ያላደረጉና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ሙሉ ለሙሉ ያላጎናፀፈ እንደነበር በመድረኩ ተጠቅሷል። አሁን ላይ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ሀገራዊ ጉዳዮች እና ውሳኔዎች ውስጥ የመሳተፍ መብትን አግኝተዋል። በመድረኩ በሀገረ-መንግስት እና በብሄረ-መንግስት ፅንሰ ሀሳብና ዓለም አቀፋዊ ልምዶች ዙሪያ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። መድረኩ ከለውጡ ማግስት አንስቶ መንግስት እየሰራቸው የመጡ ስራዎችን በማስገንዘብ በቀጣይ ሊሰሩ ስለታቀዱ ስራዎች ለማሳወቅ ይረዳል ተብሏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013