ዳንኤል ዘነበ
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ በነገሡት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን መጀመሩን ታሪክ ይነግረናል።
በሀገሪቱ ጉዳይ ሰፊ ጥናቶች በማድረግ የሚታወቁት የፖለቲካና ታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ጆን ማርካኪስ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ የንግስና ዘመን መጀመሩን አረጋግጠዋል። ፕሮፌሰር ጆን «ምኒልክ ዘመናዊ ትምህርት ቤትን በመክፈት በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የትምህርት ዘር የዘሩ ናቸው፡፡
ትምህርት ቤቱም የተሠራው ንጉሠ ነገሥቱ በሰጡት የግል ገንዘብ ነው» ብለዋል። በሀገሪቱ ሲፈራረቁ የነበሩ መንግሥታት የዘመናዊ ትምህርትን መሰረት የጣሉትን አጼ ምኒሊክ ዱካ በመከተል፤ ባለፉት 110 ዓመታት ሲሰሩ የነበሩት ስራዎች ተደማምረው ከዛሬ ደጃፍ አድርሰውታል።
መንግስታት ያደርጉ ከነበረው ጥረት ጎን ለጎን፣ የውጭ ሀገር በጎ አድራጊ መልዕክተኞችና የተለያዩ ግለሰቦች ትልቅ አበርክቶዎች ነበሯቸው። ከእነዚህ መካከል በአሜሪካዊው መልዕክተኛ ጃክ ስሚዝ እና በባለቤታቸው የተመሰረተው ተስፋ በጎ አድራጎት ድርጅት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። የተስፋ በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጥላሁን አበጋዝ ከድርጅቱ አመሰራረት በመጀመር በጎውን አሻራ እንዲህ ይተርካሉ።
አሜሪካዊው ሚሽነሪ ጃክ ስሚዝ በአዲስ አበባ አራት ኪሎና ፒያሳ አካባቢ ወላጅ የሞተባቸው፣ በጎዳና ይኖሩ ለነበሩ ህጻናትና ታዳጊዎችን ይደግፍ ነበር። ጃክ ስሚዝ ራሳቸው እየተንከባከቡ፣ ትምህርት ሲሰጡ ቆዩ።
በዚህ መልኩ ድጋፍ ማድረጉ ውጤቱ እምብዛም አለመሆኑን በመረዳት ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ተስፋ ድርጅትን አቋቋሙ። እ.ኤ.አ በ1971 ተስፋ ድርጅት የደሃ ደሃ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገልገል ተቋማዊ ቅርጽን በመላበስ በጎ ተግባሩን በተደራጀ መልኩ ሊጀምር መቻሉን ያስረዳሉ።
የውጭ ሀገር ሚሽነሪው ጃክ እና ባለቤታቸው የመሰረቱት ድርጅት በአዲስ አበባ ለሚገኙ የደሃ ደሃ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም በጎዳና ለሚኖሩ እና ወላጅ አልባ ህጻናት አለኝታነቱን ማሳየቱን አጠንክሮ መቀጠሉን ይጠቅሳሉ።
ጃክ ስሚዝ ዶክተር ሚናስ ህሩይ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወደ ድርጅቱ እንዲመጡ በማድረግ፤ የተስፋ ድርጅትን አቅም በማጎልበት ድርጅቱን ቀስ በቀስ እየሰፋ በመምጣት ወደ ህጻናት ማሳደጊያነት ማሸጋገር መቻሉን ይገልጻሉ።
«በቀዳማዊ ኃይለስላሴ አየር ጤና አካባቢ ላይ በተሰጠው መሬት የህጻናት ማሳደጊያውን በተደራጀ መልኩ ለማከናወን አስችሎታል።
በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች ተግባሩን በመቀጠል፤ በ1977 ዓ.ም በሀገራችን ተከስቶ በነበረው ድርቅ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችን በመቀበል አሳድጎ፣ አስተምሮ ለቁም ነገር እንዲበቁ ያደረገበት አጋጣሚ በታሪክ የሚታወስ ተግባር ነው» ይላሉ።
ጃክ ስሚዝ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ዶክተር ሚናስ ህሩይ ከሌሎች ኢትዮያውያን ጋር በመሆን ድርጅቱ ወደ ትምህርት ተቋምነት ያሳደጉት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት በስፋት ተደራሽ እንዲሆን ከማድረግ በተጓዳኝ፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ በሥነ-ምግባሩ የዳበረ የተማረ ዜጋ በመፍጠሩ ረገድ፣ ወዘተ በትምህርት ዘርፍ ተስፋ ድርጅት በጎ አሻራቸውን ያሳረፈ መሆኑን ረጅሙ ጉዞው ሲፈተሽ የሚገኙ ውጤቶች መሆናቸውን ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ፤ የሰው ልጅ ከድህነት የመውጫ አንዱና ዋነኛው ቁልፍ በትምህርት እንደሆነ በመገንዘብ ወደ ትምህርት ተቋምነት ሙሉ ለሙሉ መቀየሩን ተከትሎ፤ በህጻናት ማሳደጊያ የሚገኙትን ጨምሮ በከተማው የደሃ ደሃ ቤተሰብ ልጆችን በመመልመል፤ መሰረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶ ትምህርታቸውን በተሟላ መልኩ እንዲከታተሉ ነበር የተደረገው።
በአዲስ አበባ አየር ጤና አካባቢ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ በተገነባው ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ተግባሩን በመጀመር፤ ባለፉት ዓመታት ብዙ ሺህ ተማሪዎችን አስተምሮ ለቁም ነገር አብቅቷል።
ተስፋ ድርጅት ወደ ትምህርት ተቋምነት ሲቀየር በኬጂ ደረጃ ነበር። ነገር ግን በአጭር ጊዜ ራሱን ከፍ በማድረግ ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትነት አሳደገ። ብዙም ሳይቆይ ወደ ሁለተኛ ደረጃነት በማደግ በመዲናዋ በድህነት ምክንያት ትምህርታቸውን መማር ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘመናዊ ትምህርትን ተደራሽ ማድረጉን እንደገፋበት ይናገራሉ።
የተስፋ ድርጅት አበርክቶውን ሳይገደብ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በማቋቋም አስረኛ ክፍል ተምረው ውጤት ላልመጣላቸው ችግረኛ ተማሪዎችን በመቀበል የሙያ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እድል መፍጠር ተችሏል።
ከዚህ አኳያ በሀገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ተስፋ ድርጅት ብዙ ርቀት የተጓዘ ስለመሆኑን አመላካች መሆኑን ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል በዘመናዊ ትምህርት ተደራሽነት ላይ አንዱ ችግር በድህነት ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አለመቻል መሆኑን የሚያነሱት አቶ ጥላሁን፤ ተስፋ ድርጅት በትምህርት ቤቱ በእንዲህ አይነት ችግር መማር ያልቻሉ ልጆችን በመቀበል አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ይገልጻሉ።
በዚህ ረገድ ድርጅቱ በሁለት መልኩ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ያመለክታሉ። የመጀመሪያው ሙሉ አገልግሎት የሚባለው ሲሆን፤ በድርጅቱ ወጪ የአልባሳት፣ የምግብ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገላቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚደረግበት ነው። ግማሽ አገልግሎት የሚባለው ሁለተኛው ነው።
ተማሪዎቹ ለትምህርታቸው የሚረዳቸውን ቁሳቁሶችን ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚማሩትን ያካትታል።
በዚህ መልኩ ድጋፍ የሚያደርግላቸውን 50 ተማሪዎችን በየዓመቱ በመቀበል ከኬጂ ጀምሮ እስከ አስረኛ ክፍል በድርጅቱ ትምህርት ቤት እንዲከታተሉ ይደረጋል።
የአስረኛ ክፍል ውጤታቸውን መሰረት በማድረግ ወደ ቴክኒክና ሙያ የሚገቡትን በራሱ በተስፋ ድርጅት ተቋም፤ ወደ መሰናዶ በመግባት እስከ ዩኒቨርሲቲ የሚጓዙ ከሆነ ደግሞ የሚደረግላቸው ድጋፍ ሳይቋረጥ የሚቀጥል መሆኑን ነው ያመላከቱት።
መንግስት በሀገሪቱ የዘመናዊ ትምህርት ተደራሽነቱን ለማሳደግና ጥራትን መሰረት ያደረገ የመማር ማስተማር ሥርዓት እውን ለማድረግ የያዛቸው እቅዶች መኖራቸውን የሚያነሱት አቶ ጥላሁን፤ መንግስት የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ማስፋፋት፣ በሃገሪቱ በገጠር የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዲገኝ የማድረግ፣ ለሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ትኩረት በማድረግ አዳዲስ ቴክኖሎጂን የሚፈጥሩ ዜጎች ማፍራት የሚሉ እቅዶች ይጠቀሳሉ።
ተስፋ ድርጅት እነዚህን እቅዶች ወደ ተግባር በመቀየር ተጨባጭ ስራዎችን ማከናወኑን መቻሉን ያብራራሉ። በተጨማሪም ተስፋ ድርጅት አቅሙን ከፍ በማድረግ ዩኒቨርሲቲ መክፈት የደረሰ መሆኑን ያነሱት አቶ ጥላሁን፤ የትምህርት ተቋማቱ ከአዲስ አበባ ባሻገር፣ በደሴ፣ በጋምቤላ፣ በአሶሳ ከተማዎች ላይ በመክፈት በድህነት ምክንያት ከትምህርት ዓለም የራቁ የደሃ ደሃ ህብረተሰብ ልጆችን በማስተማር የትምህርት ተደራሽነቱ ላይ ሰፊ ሥራ መስራት እንደተቻለ ነው ያስታወቁት።
ከእነዚህ በተጨማሪ ‹ሪፍት ቫሊ› የተሰኘ ፕሮጀክት በመንደፍ በባቱ ከተማ ዝዋይ ሀይቅ አጠገብ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በሀዋሳ ከተማ ዳር ሲንታሮ በሚባለው አካባቢ ከኬጂ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። የእነዚህ ትምህርት ቤቶች መከፈት ለብዙ ሺህ የደሃ ደሃ ህብረተሰብ ክፍሎች ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን በተመሳሳይ መሰራቱን ያስረዳሉ።
በሀገራችን በድህነት ውስጥ የሚገኙ ህጻናትና ታዳጊዎች በተገቢው መንገድ ተምረው ከችግራቸው እንዲወጡ በማድረግ ስኬታማ ስራን በመስራት፤ በዘመናዊ ትምህርት ተደራሽነት ላይ የጎላ አስተዋፅኦን አበርክቷል።
መንግስት የትምህርት ተደራሽነቱ ላይ ብሎም ጥራቱን ለማስጠበቅ የሚያደርጋቸው ጥረቶችን ማገዝ ሲቻል በትምህርትን ዘርፍ የሚፈለገው ውጤት ይመጣል።
ከተስፋ ድርጅት ተሞክሮ በመውሰድ መሰል ድርጅቶች፤ ግለሰቦች መሰል ተግባራትን በማከናወን አበርክቶ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በመንግስት በኩል ደግሞ በተለያዩ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ላይ የሚታየውን የእውቀት ብክነት እንዴት መታደግ እንደሚቻል ተሞክሮ መውሰድ ይኖርበታል።
በተስፋ ድርጅት ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚማሩ ተማሪዎች ከቴክኒክ ሙያ ይሁን፤ ከዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በፍጥነት ወደ ስራ ዓለም እንዲሸጋገሩ ይደረጋል። ድርጅቱ ስራ የሚፈልግ ክፍልም አለው። ከተለያዩ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ካምፓኒዎች ግንኙነት አለው።
በክፍሉ አማካኝነት ለተመራቂ ተማሪዎቹ ስራ እስከ ማስቀጠር የዘለቀ ተግባር የሚያከናውን መሆኑን ይናገራሉ። መንግስት የተስፋ ድርጅትን ተሞክሮ ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል። ይህም ተመርቆ በስራ ማጣት የሚባክነውን እምቅ ኃይል በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል እድል የሚፈጥር መሆኑን ነው ያመላከቱት።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 2013