መርድ ክፍሉ
በአዲስ አበባ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች በክረምት ወራት ብቻ የሚከናወን ተግባር የነበረ ሲሆን፤ ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በብዛት ይሳተፉበት ነበር። በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የክረምት ትምህርት፣ የትራፊክ አገልግሎት፣ ለተቸገሩ ሰዎች አልባሳት ማሰባሰብና የደም ልገሳ ይከናወን ነበር። በቅርብ ግን መንግሥት ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትኩረት በመስጠት በበጋና በክረምት ወራት የሚከናወኑ ተግባራትን በመለየት ወደ ሥራ ገብቷል። የኢዲስ አበባ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ምን እንደሚመስል የከተማው የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት አቶ አብርሃም ታደሰ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ምን ይመስላል?
አቶ አብርሃም፡- የአዲስ አበባ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከዓመት ዓመት ለውጥ እያመጣ ያለ ሥራ ነው። ተቋሙም እንደ አዲስ ተደራጅቶ ሥራ ከጀመረ ቅርብ ጊዜው ነው። በዚህ መሰረት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላለፉት አስራ አምስትና አስራ ስድስት ዓመታት በክረምት ወቅት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ነበሩ። በተለይ በትምህርት ቤት በዕረፍት ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ማዕከል ያደረገ ነበር።
አሁን ግን እጅግ መሻሻል አሳይቶ በከፍተኛ ሁኔታ ክረምትና በጋ የሚሠራ ሆኗል። በዚህም መሰረት ባለፈው ክረምት ወራት ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈው ከ560 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰጥቷል። እንደ አጠቃላይ በክረምትና በበጋ ወቅት ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት በቁሳቁስና በሙያም የተሰጠ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነበር።
በዚህም መሰረት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ አሁን በበጋው በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጥቅምት 20 ቀን እስከ ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም የሚቆይ አስራ ስድስት ፕሮግራሞች ያሉት መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል። በበጎ ፈቃድ ሥራው አንድ ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞች በማሳተፍ ከአምስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ሊሰበሰብበት የሚችል ወይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጥበት መርሐ ግብር ነው።
በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ የክረምት መርሐ ግብሩን እውቅና ተሰጥቶ ወደ አዲስ መርሐ ግብር ተገብቷል። በቀጣይ የገና በዓልን አነስተኛ ገቢ ካላቸው ጋር ለማሳለፍ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ የሀብትና ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ ነው።
በበጋው በጎ ፈቃድ አገልግሎት እስከ ሁለት መቶ የሚደርሱ ቤቶች የታደሱ ሲሆን፤ ከታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተጠናቀው ለነዋሪዎቹ ይሰጣሉ። ሃይማኖታዊ በዓላት መሰረት ተደርጎ ሥራዎች የሚከናወኑ ሲሆን፤ አጠቃላይ በዓመቱ የሚታዩ ክፍተቶችን መሰረት በማድረግ የበጎ ፈቃድ ሥራ ይከናወናል። በአዲስ አበባ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍ እያለና እያደገ የመጣ ቢሆንም ብዙ የሚቀሩት ሥራዎች አሉት።
አዲስ ዘመን፡- በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሠሩ ሥራዎች ምን ምን ናቸው?
አቶ አብርሃም፡- አሁን የሚሰጡት አገልግሎቶች በመርሐ ግብር ደረጃ በዝርዝር የተቀመጡ ናቸው። ብዙ መርሐ ግብሮች በበጎ ፈቃድ ይከናወናሉ። በዚህም ወደ አስራ ስድስት መርሐ ግብሮች የሚከናወኑ ሲሆን፤ የመጀመርያው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሠራ ሥራ ነው። በሰብዓዊ አገልግሎት፣ በትምህርት ድጋፍና ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች የመደገፍ ሥራ ይከናወናል።
በዚህ መሰረት በትምህርት ቤቶች የኮቪድ 19 መከላከል ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ የሚገኝ ነው። አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት የመደገፍ፣ የቤቶች ጥገና ከዚህ በፊት እንደነበረው ይከናወናል። በቤት ጥገናው ለአገር ባለውለታ የሆኑና አቅማቸው ሲደክም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ይካተታሉ።
የትራፊክ አገልግሎት፣ የሰላምና የፀጥታ ማስከበር፣ የኮቪድ 19 የግንዛቤ ሥራ፣ አቅም የሌላቸውን ሰዎች ነፃ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ፣ ‹‹ሙያዬ ለሀገሬ›› በሚል በመንግሥት ተቋማት ጭምር በነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል። በሌላ በኩል የፅዳትና ውበት ሥራ፣ የደም ልገሳ፣ የገቢ ግብር የማይከፍሉና ሲስተም ውስጥ ያልገቡትን በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት ልየታ የሚከናወን ይሆናል።
ባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብና ወደ ውጤት እንዲሸጋገሩ የማድረግ ሥራ ይሠራል፣ ‹‹በጎነት በሆስፒታል›› በሚል ታካሚዎችን ተራ በማስያዝ፣ በመደገፍና ሌሎች ሥራዎች ይከናወናሉ። ይህን ሥራ በማስፋት ፍርድ ቤቶችም ውስጥ ወጣቱ ተሰማርቶ የሚወጣውና የሚገባው ሰው ርቀቱን ጠብቆ እንዲገለገል ሰፊ ሥራ ለመሥራት ታስቧል።
በተጨማሪም የከተማ ግብርናም አንዱ በበጎ ፈቃድ የሚከናወን ሥራ ነው። በከተማ ውስጥ ያስፈልጋሉ የሚባሉና በህብረተሰብ ውስጥ ጉድለት ናቸው የሚባሉትን በጋራ በመቀናጀት የሚሠራ ይሆናል። ይህ ሥራ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቦታዎች ላይ የማስፋት ሥራ እየተከናወነ ነው።
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመጀመር ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ቤቶች በመጠገን፣ ደም በመለገስ፣ የፅዳት ሥራ በመሥራት እንዲሁም በጣና ሐይቅና በሌሎች ቦታዎች የነበረውን የእንበጭ አረም የመንቀል ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። በአፋር፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመንቀሳቀስ እየተሠራ ነው። አሁንም ለበዓል በኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ዙሪያ የቤት ጥገና መርሐ ግብር አለ። የአቅም ውስንነት ከሌለ በስተቀር በሁሉም ዘርፍ ሥራዎች ለመሥራት እቅድ አለ።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ምን ለመሥራት እቅድ ተይዟል?
አቶ አብርሃም፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የገና በዓል የሚሠራው በዓሉ ስለመጣ የሚሠራ አይደለም። ለገና በዓል የሚሠሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች በእቅድ መሥራት ከተያዙ ሥራዎች አንዱ ነው። ለምሳሌ በዚህ ቆይታ ውስጥ የሚደገፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ምን ያክል እንደሚሆን ተለይቷል።
ለእነሱም ምን ያክል ሀብት መሰብሰብ እንዳለበትም ታውቋል። ስለዚህ ከዚህ በኋላ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሠሩት አስራ ስድስት መርሐ ግብሮች ይከናወናሉ ማለት ነው። የሰብዓዊ አገልግሎት፣ ኮቪድ 19 የግንዛቤ ሥራ፣ የቤት እድሳት ሥራ እስከ አንድ ሺህ ድረስ ለመሥራት እንዲሁም በደረሱ ሰብል መሰብሰብ ሥራ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ተሰማርተው መሥራት ታቅዷል።
አካባቢዎችን በማፅዳትና በማስዋብ ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎችም በተከታታይ እየተሠሩ የሚቀጥሉ ናቸው። ነፃ የህክምና ድጋፎች አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መደገፍ፣ ተቋማትን የመጎብኘትና የማገዝ በተለይ የአረጋውያን፣ የሕፃናት፣ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ማዕከሎችን እየዞሩ የመደገፍ ሥራዎች ይሠራሉ።
በትምህርት ቤቶች ውስጥ የኮቪድ 19 የመከላከል ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ ነው። ከዚህ ባሻገር በጎ ፈቃደኞች ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በሁሉም አካባቢዎች የሰላምና የፀጥታ ሥራን ወጣቶች በባለቤትነት እንዲመሩት ይደረጋል።
የትራፊክ ደህንነት ሥራም በሰፊው እየተሠራ ያለ ሥራ ሲሆን፤ ሁሉም ሥራ በነበረበት የሚቀጥል ነው። ሥራዎቹ የሚቆራረጡ ሳይሆን የተፈቱ ችግሮችን በመቀነስ ያልተፈቱት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል።
በቅርቡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመለየት በበጎ ፈቃደኞች የሚሠሩትን ወደ ተግባር የማስገባት ሥራ ይጀመራል። የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እስከ ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ይሆናል። ከሰኔ አንድ ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይጀምራል።
አዲስ ዘመን፡- የበጎ ፈቃድ ፖሊሲና መመሪያ ዝግጅት ጋር በተያያዘ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምንድን ናቸው?
አቶ አብርሃም፡– ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ አንፃር ስንመለከት ፖሊሲው በፌዴራል ደረጃ የሚዘጋጅ ነው። ፖሊሲውን ለማዘጋጀት 2009 ዓ.ም ላይ ሥራው ተጀምሮ የነበረ ሲሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሲንከባለል ቆይቷል። መጀመሪያ ላይ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚል የነበረ ሲሆን፤ ክረምትን መሰረት አድርጎ ሲዘጋጅ የቆየ ነው። አሁን ግን በጎ ፈቃደኞች በሚል እየተዘጋጀ ነው። በጎ ፈቃደኛ ሲባል ከሕፃን እስከ አዋቂ ድረስ የሚያጠቃልል ነው።
ማስፋት እቅድ አለ። የመስጠትና የመደገፍ ባህልና ልምዱን ያዳበረ ሕፃን ካለ በቀላሉ በጎ ፈቃደኛ ማግኘት ይቻላል። ሁሉንም ያሳተፈ የበጎ ፈቃድ ፖሊሲ ያስፈልጋል። ፖሊሲው ባለመኖሩ ብዙ ጉዳቶች አሉ። በጎ ፈቃደኞች የኢንሹራንስና ለሰጡት አገልግሎት የሚሰጣቸው ሰርተፍኬት እንዲያገኙ ለማድረግ ሰፊ ክፍተቶች አሉ።
ስለዚህ ፖሊሲው በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል የሚል እምነት አለን። የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የፖሊሲ ዝግጅቱን እየሥራ ይገኛል። የሰላም ሚኒስቴርም በተባባሪነት የፖሊሲ ዝግጅቱ ላይ እየተሳተፈ ነው።
እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ ሥራ የራሱ ፍኖተ ካርታ እንዲኖረው ለማስቻል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል። ከኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ፍኖተ ካርታውን ለማሠራት ዝግጅት እየተከናወነ ነው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መመሪያ እንዲኖር ለማድረግ ጥናቶች ተጠናቀዋል። ከዚህ ባሻገር በጎ ፈቃደኞችን ለማሳተፍ የሚያስችል ማንዋልም ተዘጋጅቶ እየተጠናቀቀ ነው። ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሠራር የሚያስፈልጉና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መመሪያዎች እየተዘጋጁ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ወጣቱ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ አምጥተዋል?
አቶ አብርሃም፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ቢኖር የከተማውን ወጣት በአንድ መድረክ ያሰባሰበ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይሄ በመሆኑ ወጣቱ የአካባቢውን ችግር በራሱ የመፍታት አቅሙ ከፍተኛ ሆኗል። በርካታ የበጎ ፈቃድ ማህበራትም እየተመሰረቱ ይገኛሉ።
ወጣቱ በሚኖርበት አካባቢ የሚገኙ አቅመ ደካሞችን እየደገፈና እየረዳ ይገኛል። በዚህ ሂደት ውስጥ ችግሮቻቸውን ለይተው አይተው የመፍታት ልምዳቸው እያደገ ነው። ሁለተኛ ወጣቱ እርስ በርስ ሲገናኝ የሚለዋወጡት ተሞክሮዎች አሉ።
እነዚህ ሁኔታዎች ተደማምረው በወጣቱ ስነልቦና ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለ ነገር ነው። በርካታ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ለመሥራት የማሰባሰቢያ መድረክ ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ ነው።
ስለዚህ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በበጎ ፈቃድ ሥራ በማዋላቸው ብዙ ውጤታማ ሥራ መሥራት ተችሏል። ወጣቶችን ለማሰባሰብና ስብዕናቸውን ለመቅረፅ ጭምር ድጋፍ አድርጓል። ሌላው እየጠፋና እየከሰመ የመጣው የአብሮነትና የመተጋገዝ እሴት ተመልሶ እንዲመጣም አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- በወጣቱ የተመሰረቱ የበጎ ፈቃድ ማህራትን የመደገፍ ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ አብርሃም፡– በወጣቱ የተመሰረቱ የበጎ ፈቃድ ማህበራትን ለመደገፍ ባለው ውስን አቅም የተለያዩ ድጋፎችና እገዛዎች ይደረጋሉ። በሁሉም ክፍለ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምንነት፣ ባህሪና አጠቃላይ በቂ እውቀት እንዲይዙ ለማድረግ ስልጠናዎች እየተሰጡ ናቸው።
ይህ የስልጠና ሥራ ተከታታይነት ባለው መልኩ የሚቀጥል ሲሆን፤ በግንዛቤና በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ውጤታማ መሆን ይችላል። በሌላም በኩል የንፅሕና መጠበቂዎችና አስፈላጊ የሚባሉ ድጋፎች ይደርጋሉ። በቀጣይ ልምድ ያላቸውን ምሁራንና በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን በመጋበዝ ወጣቶችን የማንቃት ሥራ በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የወጣቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሁም በስልጣን እርከኖች ላይ ውክልና እንዲኖራቸው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ አብርሃም፡- ቢሮው ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተጨማሪ የወጣቱ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከዚህ አንፃር ብዙ ጠንካራ ሥራዎች ተሠርተዋል ባይባልም ለውጦች ግን መጥተዋል። ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።
ይሁን እንጂ በርካታ ወጣቶች አሁንም ድረስ ሥራ የሚፈልጉ ናቸው። የተወሰኑ ወጣቶች ሥራ የማማረጥ ሁኔታ ቢኖርም ብዛት ያላቸው ወጣቶች በኢኮኖሚ ውስጥ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ገበያው የሚፈጥራቸው አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ያሉ ሲሆን፤ በእነዚህ ውስጥ የሚገቡ ወጣቶች እንዳሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ዕድሎች ሊፈጠሩሏቸው የሚገቡ ወጣቶች አሁንም ድረስ አሉ።
በቅርቡ 28 ሺህ ወጣቶች በአረንጓዴ ልማት ሥራ የተሰማሩ ሲሆን፤ ወደ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በመመደብ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በፊትም በፐብሊክ ሰርቪስ ውስጥም ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ተቀጥረው ህዝቡን እንዲያገለግሉ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።
አሁንም በአምስት ወራት ውስጥ በርካታ ወጣቶች በተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ሆነዋል። በቀጣይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች በማምጣትና አዳዲስ ዘርፎችን ለመፍጠር ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የወጣቱ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጨምር ምን ምን ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ?
አቶ አብርሃም፡– ቀደም ብሎ የነበረው የወጣቶች ተሳትፎ እውነት ለመናገር ለይምሰል የተደረገ ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ በአስፈፃሚው አካል ውስጥ የወጣቱን ተሳትፎ ብንመለከት በጣም ዝቅተኛ የነበረ ነው። አሁን ያለው አመራር በወሰደው ዕርምጃ በአዲስ አበባ ከተማ የአስፈፃሚ አካል ውስጥ የወጣቱ ተሳትፎ 70 በመቶ ደርሷል።
የሴቶችንም ተሳትፎ ብንመለከት በጣም ዝቅተኛ የነበረ ነው። በቅርቡ በተደረገ ሥራ የሴቶች ተሳትፎ 30 በመቶ ማድረስ ተችሏል። በህግ ተርጓሚው አካል ውስጥ የወጣቱ ተሳትፎ 29 በመቶ ነው። በህግ አውጪው ደግሞ የወጣቱ ተሳትፎ ከ10 በመቶ በታች ነው።
ለዚህ ደግሞ የወጣቱ ተሳትፎ ማነስና መድረኩን የሚፈጥሩት አካላት ለወጣቱ ክፍት አለማድረጋቸውን ያሳያል። ባለፉት ምርጫዎች ወጣቶች በምርጫ የነበራቸውን ተሳትፎ ስንመለከት በጣም ዝቅተኛ ነበር።
ወጣቱ በመራጭነት የተሻለ ተሳትፎ የነበረው ቢሆንም በተመራጭነት የነበረው ተሳትፎ በጣም ዝቅተኛ ነበር። በእነዚህ መድረኮች ወጣቱ ሊመጣ ካልቻለ ህግ አውጪው አካል ላይ መሳተፍ አይችልም።
በፊት መስፈርት በማስቀመጥ ወጣቱ በፖለቲካው መድረክ ተሳታፊ እንዳይሆን ዕድል ይዘጋበታል። በአሁን ወቅት ግን በርካታ ወጣቶች ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው። በቀጣዩ ምርጫ ወጣቱ ተሳታፊ እንዲሆን ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በጣም እናመሰግናለን
አቶ አብርሃም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2013