ዘላለም የሳጥን ወርቅ
ሊያ ወደ ጭፈራ ቤቱ ስትገባ የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” ሙዚቃ ተለቆ ነበር፡፡ እየተውረገረገች ወደ ውስጥ ገባች፤ በአይኗም በጥርሷም በመላ ሰውነቷ እየሳቀች፡፡
ብዙ አይኖች ተከተሏት፡፡ ቄንጤኛ ናት፤ ስታወራ… ስትስቅ በቄንጥ ነው፡፡ ስታኮርፍ… ስትቆጣ በዚህ ሁሉ ውስጥ ታምራለች። ማንም ያያታል፡፡ በትንሽ በትልቁ የሚስቅ ደግ ፊት አላት። ብዙ ታሪኮች የተደበቁበት ገጽ፡፡
በህይወቷ ውስጥ የመጡትን መከራዎቿን በሳቅ ነው የምትረሳቸው፡፡ መደነስ መጨፈር ትወዳለች፡፡ ቀሪው ህይወቷ በሲጋራ እና ጫት በመጠጥም የሚያልፍ ነው፡፡ እንዲህ በመሆኗ ሳትቆጭ የቀረችበት ጊዜ የለም፡፡
ረጅም ናት… እንደ ሰንደቅ፤ ቀለም የጠጣ ጸጉሯ ከተመጠነ አይንና አፍንጫዋ ጋር ሲታይ ከግሪክ ጣኦቶች አንዷን ትመስላለች። በጥንቃቄ የሚኳል አይንና ከንፈር አላት፡፡ እንደ ባላባት መሬት የሰፋ ዳሌ እንደ ስንጥር የቀጠነ ወገብ እና እንደ በጋ ሰማይ የጠራ ባት አይን ከማያስከድኑ ተፈጥሮዎቿ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በቴዲ ዘፈን ኢትዮጵያ ብላ ሳታበቃ አንድ ሰካራም ዳሌዋን ሲተሸሸ አገኘችው፡፡በቃ ለእሷ ወንዶች እንዲህ ናቸው፡፡አንድም ቀን እውነቷን ፈልጎ የመጣ የለም፡፡አብዛኞቹ ደንበኞቿ አላቂ ውበቷን ፈልገው የመጡ ናቸው፡፡
በውበቷ … በቁመናዋ የተማረኩ፡፡ በወንድ ልጅ ያልተበሳጨችበት ጊዜ የለም፡፡ ቢቻላትና አቅሙ ቢኖራት ወንዶች ከማይደርሱበት ስዋራ ስፍራ ራሷን ማኖር ትፈልጋለች። የእስካሁኑ የሴት ልጅ ስቃይ በወንድ ልጅ የመጣ ነው ትላለች። ቡና ቤት ስለተገኘች ክብረ ቢስ አድርጎ የሚያያት ብዙ ነው። ይህም ያበሳጫታል፡፡ ውስጧ ለምንም ያልነገረችው ማንም ያላዳማጣት ብዙ እውነት አለ፡፡ ሳያውቋት ሳይረዷት ባለችበት ሁኔታ የሚወቅሳት ብዙ ነው፡፡
ሀጢያተኛ ሲሉም ሊወግሯት ድንጋይ ያነሳሉ፡፡ ግን እሷ ይሄን አይደለችም፡፡ ከሆነችው … እየሆነችው ካለችው ሌላ ሰው … ሌላ ሴት ናት፡፡
የሚያዳምጣት … እህ የሚላት ቢኖር የምትነግረው ብዙ ነገር ነበራት፡፡ በግራ እና በቀኝ ደጅ የጠኑ በርካታ ወንዶች አየች፡፡ እዛም ..እዛም ሴት የሚያሽኮርምሙ፣ በተገለጠ ጭን …ባልተሸፈነ እምብርት ለሃጫቸውን የሚያዝረከርኩ ሆዳሞችን፡፡ ባንኮኒ ተደግፈው ከሚጠጡት ውስጥ አንድ ጎልማሳ በጥቅሻ ጠራት፡፡ ፊት ነሳችው፡፡
ከጋሽ ሽመልስ በስተቀር አብዛኞቹ አልጋ ተጋሪዎቿ ለዝሙት የሚመጡ ናቸው፤ ጋሽ ሽመልስ ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ታሪካቸውን ባይነግሯትም ባለትዳር እንዳይደሉ ግን ታውቃለች፡፡ ሚስታቸው የስድስት ወር ህጻን ልጃቸውን ይዛ ከቤት እንደጠፋች እና ዛሬም ድረስ የት እንዳለች እንደማያውቁ ነግረዋታል፡፡ጋሽ ሽመልስ ስትላቸው ስለማይወዱ እንደ ጓደኛ ቆጥራ አንተ ነው የምትላቸው።
የወንድ ልጅ ጉድን ብታወራው አያልቅም፡፡ ቅምጥ አድርገዋት የሚመጡ ብዙ ናቸው፡፡ እንደሚስት የወር ደሞዝ እየቆረጡ … ቀለብ እየሰፈሩ በአሻቸው ሰዓት እየመጡ እብረዋት የሚያድሩ ሞልተዋል፡፡ አንዳንዶች ለስራ ወደ ሌላ ከተማ ሲሄዱ ይዘዋት ይሄዳሉ፡፡ ለማንም ግን ደስተኛ ሆና አታውቅም።መኖር ስላለባት ብቻ ታደርገዋለች፡፡
በሚያሳዩት እኩይ ባህሪ ከብዙ ወንዶች ጋር የደንበኝነት ውሏን አፍርሳለች፡፡ ስለከፈሉ ብቻ ሴትን ልጅ የገዙ የሚመስላቸው በማሰቃየት የሚደሰቱ በርካታ ወንዶች ገጥመዋታል፡፡
ሁሉም ወንዶች አንድ አይነት ናቸው። እውቀት እንጂ ጥበብ የላቸውም፤ ገንዘብ እንጂ እውነት የላቸውም። እውነት… እውቀት ቢኖራቸው ኖሮ ሚስታቸውን ቤት አስቀምጠው ሌላ ሴት ፍለጋ አይመጡም ነበር፡፡
የብዙ ወንዶች የደስታቸው ምንጭ ሃጢአት ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ከምሽት ደንበኞቿ ለማረጋገጥ ችላለች፡፡ ወደ ፊት ስለወንድ ልጅ የምትጽፈው ብዙ ነገር አላት፡፡ ከህልሞቿ አንዱ ወንዶችን መቅጣት ነው፡፡ በሴት ልጅ ላይ ላደረሱት በደልና ግፍ የእጃቸውን እንዲያገኙ ትሻለች፡፡ ቢሳካላትና ቢሆንላት ቀዳሚ ምኞቷ ስለሴት ልጅ መጮህ ነው፡፡
ያልሞላ ወንድ ያስጠላታል፡፡ ሞልቶ ያልፈሰሰ… ልፍስፍስ ወንድ አትወድም፡፡ ውበቷ ውስጥ ምን እንዳለ ሳያውቅ የሚከተላት ጠላቷ ነው፡፡ ሃሳቧ ሁሉንም ወንድ መቅጣት አይደል፤ ምትሃታዊ ፈገግታ ፈነጠቀች፡፡
ጥርሶቿ ወደማደሪያው ከመግባታቸው ለሃጩን ሲያስረከርክ አየችው፡፡ አንጀቷ ራሰ፡፡ ይፈልጓታል እንጂ አያገኟትም፡፡ መርጣ እንጂ ተመርጣ የማንም መሆን አትሻም፡፡ እንደቀሳሚ ንብ ዙሪያዋን እየዞረ አሸተታት፤ጠይም ቸኮሌት ገላዋ በአይኑ ላይ መጣ፡፡
ነገና ከዚህ በኋላ ባለው ህይወት ሁሉ እንደማይረሳት ታውቃለች፡፡ የሳቀችላቸው ወንዶች ሁሉ ዛሬ ላይ ባሪያዎቿ ናቸው። ምንም ያህል ገላዋን ሽጣ የምታድር ብትሆንም ስትፈልግ ካልሆነ ሲፈልጓት አትገኝም፡፡ ለጠራት ሁሉ አቤት ብላ አታውቅም። ነይ ብሎ ለላከባት ሁሉ አትሄድም፡፡
እንደአሰበችው ባይሆንም በዚህ ባህሪዋ ብዙ ወንዶች ሚስቶቻቸውን አየተው ከእሷ ጋር ሲዘሙቱ እያየች ትዳርን ጠላችው፡፡ በዛ ላይ መጥፎ የልጅነት ታሪክ ያላት ናት፡፡ ህይወት ከእግር እስከ ራሷ በብዙ የፈተነቻት እንስት፡፡
ቤተሰብ የላትም። አባቷ ምን አይነት እንደሆነ አታውቅም፡፡ ከእናቷም ጋር እስከ አስራ አምስት ዓመቷ ድረስ ብቻ ነው የኖረችው፡፡ እናቷን በሞት ስታጣ የህይወት አቅጣጫ ተቀየረ፡፡ ለመኖር ስትል ብዙ መስዋዕት ትከፍላለች፡፡ በመጨረሻም ራሷን በዚህ አስከፊ ህይወት ውስጥ አገኘችው፡፡
እናቷ ሀኪም እንድትሆንላት ነበር ሃሳቧ፡፡ የእናቷን ህልም ባለማሳካቷ ሁሌም ትቆጫለች፤ ዘላለማዊ ቁጭት፡፡ ወጣት በፈገግታዋ ድባቅ ተመቶ አጠገቧ ተደፍቷል፡፡ እንደ ዛሬ ደስ ያለው አይመስልም፤ ምራቁን በአምሮት አሁንም …. አሁንም እየዋጠ በጆሮዋ የማይሰማ ነገር ያንሾካሹካል፡፡
ከነፈገግታዋ ጆሮዋን ለአፉ ሰጥታ “ምን አልከኝ አለችው፤ እንዲሰማት ከሙዚቃው በላይ እየጮኸች፡፡ ‹‹ለገንዘብ እንዳታስቢ ዛሬ ከአንቺ ጋር ጥሩ ሌሊት ማሳለፍ እፈልጋለው›› በሚንተባተብ ድምጽ እየተወለካከፈ አወራት፡፡
“ምን ያህል ትከፍለኛለህ የንጋት ኮከብ የሚመስሉ አይኖቿን ጥላበት
“የፈለግሽውን” በኩራት መለሰላት፡፡
“የፈለኩት ገንዘብ ባይኖርህስ በመናደድ እና በመታገስ ስሜት ደግማ ጠየቀችው፡፡
“እንዴት አይኖረኝም ሀብታም እኮ ነኝ፡፡
በእያንዳንዱ ምሽት ትበሳጫለች፡፡ ወንዶች ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ የተመኘችውን ያክል ምንም ነገር ተመኝታ አታውቅም።
“ሴቶች ነጻ ይወጡ ዘንድ ወንዶች ገንዘብ ስለማይገዛቸው ብዙ ነገሮችን ማወቅ አለባቸው፡፡ በሃሳቧ ለዚህም ከገንዘብ ሌላ ምንም የሌላቸው ሀብታም ወንዶች የሚማሩበት ትምህርት ቤት እንደሚያስፈልጋቸው አመነች፡፡
“ምነው ዝም አልሽ ተጫወቺ እንጂ ሚስት ያለኝ መስሎሽ ነው የለኝም፡፡ ደግሞ ቢኖረኝስ አንዴ ዳሌዋን አንዴ በኩል ያሸበረቀ አይኖቿን እያየ፡፡
የብሽቀት ሳቅ እየሳቀች “በማሰብ የሚኖሩ ወንዶች ያስደስቱኛል፡፡አንተን ጨምሮ ይሄ ሁሉ ወንድ ማሰብ የተሳነው ነው፡፡ ማሰብ የሚችል አእምሮ ሚስቱን ቤት አስቀምጦ ሌላ ሴት አያሽኮረምም” አለችው፤ ቡጢ ከሰነዘረብኝ ብላ ራሷን ለመከላከል እየተዘጋጀች፡፡ ከመናገር ወደ ኋላ ስለማትል ብዙ ጊዜ ተጣልታ ታውቃለች፡፡ ጠርሙስ ተወርውሮባት ያውቃል፡፡
በዚሀ መሀል ነበር ከወጣቱ ጋር እንደቆመች ከርቀት በምልክት የጠራትን ሰው ያየችው፡፡ የአራት ዓመት አልጋ ተጋሪዋ ሽመልስ ነው፡፡ ወጣቱን በቆመበት ትታ ዳሌዋን እያውረገረገች ወደ ጠራት ሰው ሄደች፡፡
ወጣቱ በተቀየመ ፊት በአይኑ ተከተላት፡፡ ከአንድ መላጣ ሽማግሌ ላይ ስትጠመጠም አያት፡፡ ደሙ ፈላ፡፡ በነፍሱ በስጋውም ወዷታል፡፡ እንዴት ያድርግ ታገኝ እንደሁ ብሎ ዓመት ከመንፈቅ ጠበቃት፡፡ አላየችሁም፡፡ በሽማግሌው ወሬ እየተፍለቀለቀች ፊት ነሳችው፡፡
ሊያ ከሽመልስ ጋር ሲጠጡ አምሽተው ወደ ያዙት ክፍል ሲገቡ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሆኖ ነበር፡፡ጠዋት ሽመልስ ወደ ቤቱ ሲሄድ ሊያ ተኝታለች፡፡ አርፍዳ ስትነሳ አንድ የወንድ ልጅ የኪስ ቦርሳ አገኘች፡፡
ባለቤቱን ለማወቅ ቦርሳውን ስትከፍተው ያየችው ግን የህይወት ዘመኗን አስደንጋጭ ነገር ነበር፡፡ ትንፋሽ አጠራት። እየሞተች ራሷን አገኘችው፡፡ እጆቿ ተንቀጥቅጠው ቦርሳውን ጣሉት፡፡ አይኖቿ ቦርሳ ውስጥ ካለው የእናቷ እና የጋሽ ሽመልስ ፎቶ ላይ ተተክለው ነበር፡፡
… ወያባ ነብስ…
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2013