ዳንኤል ዘነበ
«ጠዋትና ማታ ድንጋይ ስር ቁጭ ብለው፣ በዙሪያቸው ሳር እየጋጡ ከሚጮሁ የቤት እንስሳት አጠገብ፣ በድንጋይ ስር ከሚሹለከለኩ ተሳቢ ነፍሳት ጋር ፀሐይና ንፋስ እየተፈራረቀባቸው በዳስ ስር ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። ትምህርት ቤቶቹ በቆላማ ስፍራ የሚገኙ ከሆነ ደግሞ ፀሐይዋ የሚቀመጡባትን ድንጋይ ስለምታግል፣ ተማሪዎቹ ‹ድንጋዩን ጭቃ ቀብተው› በመቀመጥ ችግራቸውን ለማቅለል ይሞክራሉ»፤ ይህ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሺህ በላይ በሚገኙት የዳስ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ተማሪዎች የጋራ ታሪክ ነው።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ በሶማሌ ክልል ከ 980 በላይ፣ በአማራ ክልል ከ9ሺህ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከደረጃ በታች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነገሡት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በአሁኑ ዘመን ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተብሎ የሚጠራውና ዘመናት የተሻገረው ተቋም መቋቋሙ ይወሳል፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረ 100 ዓመታት ቢሻገርም፤ ዛሬም ከዳስ ውስጥ መውጣት ያልቻለ መሆኑ ቁጭት ይፈጥራል። «በሕይወት ላይ ትምህርት ያላስተካከለው ለውጥ ምን አለ? የዘመኑ እኛነታችን ራሱ የትምህርት ውጤት ነው፡፡ የትምህርት መስክ ጠቦ መታየት የለበትም፡፡ እያንዳንዷ የሕይወት እንቅስቃሴ የምትበለፅገውና የምታድገው በትምህርት ነው!» ደራሲ ሲሳይ ንጉሡ በሰመመን መፅሀፍ እንደገለፀው፤ ትምህርት የሀገር እድገት መሠረት የመሆኑን ያህል ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶታል ማለት ያዳግታል።
ዘመናዊ ትምህርትን ዘመናት ቢያልፉትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚገኙ ብዙ ሺ ተማሪዎች ከዳስ አልወጡም። በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ለሚታየው ሰፊ ክፍተት ዋነኛው ተጠያቂው ማን ይሆን? መልሱ ‹መንግስት እንደሚሆን አያጠራጥርም።ለዚህ ደግሞ መንግስት የዳስ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ አልመስራቱን የሚያመላክት ነው።
የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር በ2012 ዓ.ም የዳስ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ለማሻሻልና ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ እቅድ መያዙን አስታውቀው ነበር። በዚሁ በጀት ዓመት በህብረተሰብ ተሳትፎ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት የሚያስችል እቅድ ማዘጋጀት ቢቻልም፤ ተግባራዊነቱ በሚጠበቀው ፍጥነት እየሄደ አለመሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በሀገሪቱ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ፤ የመማሪያ ክፍሎቹ ትክክለኛ መስኮቶች፣ የአየር ማስገቢያና ማስወጪያ ያላቸው፤ ዕድሜን ያማከሉ ዴስኮችና ወንበሮች፣ ንፁህና አስተማማኝ የመፀዳጃ ክፍሎችና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል። የቤት ውስጥና የውጭ የመጫወቻ ቦታዎችና ቁሳቁሶች፣ የማረፊያ ቦታዎችና ፍራሾች፣ ለአሳላጮች በቂ የሆኑ ተገቢ መጻሕፍትና መምሪያዎች እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕጻናት ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ይጨምራሉ።
የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር በተማሪዎችና በመምህራን ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ የሚሆነው የሁሉም ባለድርሻዎች ተሳትፎ ሲታከልበት በመሆኑ፤ ህብረተሰቡ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ በእርግጠም የህብረተሰቡ ተሳትፎ በሌለበት በመንግስት አቅምና በጀት ብቻ ጉድለቶቹን ማሟላት እንደማይቻል መረዳት አያዳግትም።
በፌዴራልና በክልል ደረጃ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ስራ ለማከናወን እቅዶች ቢኖሩም፤ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን ችግሩን እንዲገዝፍ ያደረገው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በህብረተሰቡ ዘንድ “የችግሩ ባለቤት መንግስት፤ መፍትሄ አብቃዩም መንግስት ነው» የሚለው እሳቤ፤ ትምህርት ቤት የመገንባት ሃላፊነትን የመንግስት ብቻ አድርጎ የመቁጠር አመለካከቶች በስፋት ይስተዋላል።
በህብረተሰቡ ዘንድ ሰርፆ ያለው እሳቤና የተቀረፁት በጎ ያልሆኑ አመለካከቶች የችግሩ መነሻ ሲሆኑ፤ መታረቅ ከቻሉም የችግሩ መፍቻ ቁልፍ እንደሚሆኑ፤ ከሰሞኑ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ሰፊ ሽፋን ሲሰጣት የነበረችው ወጣቷ ኢንጂነር አክሱማዊት አብርሃ ተሞክሮ ማሳያ ይሆናል። ወጣቷ ኢንጂነር አክሱማዊት አብርሃ፤ በጎንደር ከተማ የሚገኘውን በቀይ አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ሁለት ብሎክ የመማሪያ ህንጻዎች አስገንብታ ለአገልግሎት እንዲበቃ አድርጋለች።
ወጣቷ ኢንጂነር የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላ የነበረበትን ትምህርት ቤት አስታውሳ፤ የእውቀት በረቷን ከውድቀት መታደግ እንደሚገባት በማመን ነበር ወደ ተግባር የገባችው። በውጭ ሀገር የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የመማሪያ ብሎኮቹን በማስገንባት ለማስረከብ በቅታለች። የመንግስትን ሸክም ያቀለለ ተግባር የፈፀመችው ወጣቷ አክሱማዊት፤ በተጨማሪም በየካቲት ወር 2013 ዓ.ም በከተማው በሚገኙ ሌሎች ሁለት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማሪያ ህንጻዎችንና ቤተ-መጻህፍት በመገንባት ደረጃቸውን ለማሻሻል ቃል ገብታለች፡፡
የወጣቷ አክሱማዊት ተግባር የትምህርት ዘርፍ ሽንቁርን የመድፈን ኃላፊነት የአንድ ወገን አድርጎ የመቁጠር እሳቤ የሚያርቅ ይሆናል። በሀገሪቱ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ ለሙሉ ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የህብረተሰቡ አብራክ የሆነው በውጭ ሀገር የሚገኘው ዲያስፖራ ጉዳዬ ብሎ ተሳትፎ ማድረግ የውዴታ ግዴታ መሆኑን ማሳያ ይሆናል።
በሌላ በኩል በሀገሪቱ በቀጣይ ትምህርት ዓመት የዳስ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ለማሻሻልና ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ የያዘው እቅድ የሚሰምረው የሀገሪቱ ባለሀብቶች ሰፊ ተሳትፎ ሲታከልበት እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። በሀገሪቱ የሚገኙ ባለሀብቶች የበኩላቸውን ሚና መጫወት ቢችሉ፤ ሊመጣ የሚችለውን ውጤት የአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ተሳትፎ ትልቅ ማሳያ ይሆናል።
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ባለ ስምንት ክፍል ትምህርት ቤት በብሎኬት በመገንባት ችግሩን ለማቃለል የበኩሉን ሚና ተወጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ የዳስ ውስጥ ትምህርትን በማስቀረት ወደ ተሻለ የመማሪያ ክፍል ለማሸጋገር መሰራት እንዳለበት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከመግለጽ ባለፈ በተግባር ተሳትፎ በማድረግ ነበር ጥሪውን ያቀረበው። አትሌት ሀይሌ ትምህርት ቤቶቹን ለመስራትና ማህበረሰቡን ለማገዝ ያነሳሳው እነዚህን የመማሪያ ዳሶች በቴሌቪዥን መስኮት መመልከቱ ተከትሎ እንደሆነ ነበር የገለጸው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዋግ ኸምራ አስተዳደር ብቻ 874 የዳስ መማሪያ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን ከ1500 በላይ ተማሪዎች የሚማሩበትም መሆኑን ነው፡፡ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ቆላማ የማዕከላዊ ጎንደር አካባቢዎች፣ ሰሜን ወሎና ኦሮሚያ ብሄረሰብ አስተዳደር ደግሞ በስፋት ይገኝባቸዋል።
የፌዴራል ሆነ የክልል መንግስታት በሁሉም ክልሎች ያሉ የዳስ ትምህርት ቤቶችን እና ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ወደ ስታንዳርድ ትምህርት ቤቶች የመቀየር ከባድ የቤት ስራን ለማከናወን ባለሀብቱ የሀይሌን መንገድ መከተል ሲችሉ እንደሆነ መረዳት ይገባል።
ከኃይሌ ተሞክሮ መገንዘብ የሚቻለው የዳስና የዛፍ ጥላ ስር ትምህርት ቤቶቸችን በህብረተሰቡ ተሳትፎ የማስቀረት ውጥኑ እውን የሚሆነው መገናኛ ብዙሃን በተገቢው ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲችሉ እንደሆነ ነው። ስለዚህ መገናኛ ብዙሃን በሀገሪቱ የሚገኙ የዳስና የዛፍ ጥላ ስር ትምህርት ቤቶች ፈልፍሎ መረጃዎችን በማውጣት ለባለሀብቱም ሆነ ለህብረተሰቡ ተገቢውን መረጃና ግንዛቤ በመፍጠር የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁሞ ማለፍ ይገባል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2013