
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአገሪቱ ዘመናዊ ፖሊስ ማደራጀት ከጀመረ ከአራት ዓመት በኋላ በ1939 ዓ.ም የተቋቋመ አንጋፋ ነው። ኮሌጁ በእውቀት እና በክህሎት የበቃ ሠራዊትና ተልዕኮውን በአግባቡ የሚወጣ የፖሊስ አመራር ለማሟላት የተመሠረተ ተቋም ነው። መጀመሪያ አዲስ አበባ ከተማ አባዲና አካባቢ ነበር መቀመጫው።
በ1967 ዓ.ም ደግሞ አሁን ወደሚገኝበት ሰንዳፋ ተዘዋውሯል። በ2007 ዓ.ም ደግሞ ከኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አድጓል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማደግ አስፈላጊ ሂደቶችን መስፈርቶችን አሟልቷል።
ይህ ተቋም ለ34 ዓመታት በ42 ዙር ለአገር ትልቅ ውለታ ያበረከቱና በማበርከት ላይ ያሉ የአገር ባለውታና አይረሴ የፖሊስ ዕጩ መኮንኖችን አሰልጥኗል። በተጨማሪም አጫጭር እና ረጃጅም የትምህርት መርሐ ግብሮችን ሲሰጥ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት በሰርተፍኬት፣ ዲፕሎማ እና ዲግሪ የትምህርት መስኮች እያሰለጠነ ሲሆን በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹በክርሚኖሎጂ እና ክርሚናል ጀስቲክስ›› የማስተርስ መርሐ ግብር ተማሪዎችን ያስመርቃል። በቅርቡም ሠላም እና ደህንነት ብሎም ፖሊስ ማናጅመንት የማስተርስ መርሐ ግብር ለመጀመር የትምህርት ሥርዓት ነድፏል።
ኮሌጁ ከመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር በተጨማሪ በተልዕኮና መደበኛ ባልሆነ የትምህርት ሥርዓት ብሎም በማታ መርሐ ግብር እያስተማረ ይገኛል። በማታ መርሐ ግር እስከ ሦስተኛ ዙር ተቀብሎ እያስተማረ ነው። ሠራዊቱም ባለበት ቦታ ሆኖ ለመማር የሚያስችለው ሁኔታ ተለይቷል። በአሁኑ ወቅትም ከክልልና እና ፌዴራል 7000 የፖሊስ አባላት በተልዕኮ ለማስተማርም ፍላጎት የተለየ በመሆኑ እንደ አገር ለዚህም ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ከሆኑት አቶ መስፍን አበበ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮችና የተቋሙን ሁኔታ አስመልክቶ ያደረግነውን ቆይታ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ፖሊስ ዝግጁነት ከቀጠናው አገራት እና ዓለም ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ፖሊሶችን የማብቃት ብቃት እንዴት ያዩታል?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡– ያለንበት ቀጣና ጂኦ ፖለቲክስ በጣም አስቸጋሪ እና በጣም ተለዋዋጭ ባህሪ ያለው ነው። ሁልጊዜ ሳናንቀላፋ ንቁ ሆነን ራሳችንን እያበቃን እድንጠብቅና እረፍት የማይሰጥ ቀጣና ነው። በብዙ ምክንያች ሁሌም ራሳችንን አዘጋጅተን እንድንጠብቅና እንደ ፖሊስ ተቋም ይህን ታሳቢ ያደረገ የወትሮ ዝግጁነት ሥራ እየተከናወነ ነው። ይህን የማብቃት ስልጠና አቅም ግንባታ ሥራው የሚሰጠው ደግሞ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነው።
ማንኛውንም ዓይነት አደጋዎች ጥፋት ለመከላከል የሚያስችል ብቃት እና ዝግጁነት ያለው ኃይል ሆኖ እንዲቆይ ወቅቱን ያገናዘበና ሁኔታዎችን የገመገመ ብሎም ሚዛን የጠበቀ ሥራ በጽናት እየሰራን ነው የሚል እምነት አለኝ።
እንደ አገርና ህዝብ ያለብን አደጋ ምንድን ነው በሚለው ላይ፣ ከተልዕኳችን አኳያ የአገርና እና ሕዝብን ደህንነት መጠበቅ፣ ህገመንግሥትን በሚገባ የማስከበር ተልዕኮ ታሳቢ ያደረገና ይህን በብቃት ለመወጣት ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ከዚህ አኳያ አንዱ ለተልዕኮ ዝግጁ የሚያደርገው ሠራዊቱ በስልጠና ማብቃት ነው። በአስተሳሰብ እና እምነት የሚቆም ሠራዊት መገንባት ነው።
በአሁኑ ወቅት የፖሊስ እና መከላከያ ኃይል ምን እየሠራ እንደሆነ እየተመለከትን ነው። ትልልቆቹ ብዙ ጥፋት ሲያጠፉ በተቃራኒው ወጣት ሠራዊት አባላት በአንደበታቸው ከሚናገሩት በተጨማሪ የሚያደርጉትን በተግባር እያየን ነው። ይህ የሚሳየው ምን ያህል ለህገመንግሥቱ፣ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱና ለህዝብ ውግንና በፅናት እንደቆሙ የሚያሳይ ነው። መሰል አቋሞች የሚመጡት በፖሊስ ተቋማት ውስጥ በምንሰራቸው የማብቃት ሥራዎችና ዝግጁነት ነው።
ይህ ቢሆንም ከጉድለት የፀዳ ነው ማለት አይቻልም። በርካታ የአቅምና ትኩረት ውስንነት አሉብን። በተለያዩ ምክንያቶች ማድረግ የሚገባንን ባለማድረጋችን ያጋጠሙ ብዙ ጥፋቶችን ደግሞ እናያለን። ጥፋቶች የሚፈፀሙት ደግሞ ከአቅም አሊያም ከዝግጁነት ውስንነት ብሎም በትኩረት መስራት የሚገባን ካለማድረግ የሚመጡ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በስልጠና እና አቅም ግንባታ የሚስተካከሉ ሲሆኑ እነዚህን የበለጠ ትኩረት ሰጥተን መስራት እንዳለብን አመላካች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– የሌሎች አገራት እገዛ እና ድጋፍ የአገራትን የፖሊስ እና ደህንነት ተቋማት ሲጠመዝዙ ይስተዋላል። በኢትዮጵያ ይህ እንዳይሆን ምን እየተሰራ ነው?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡- ዋናው ነገር ከሌሎች የሚደረግ ድጋፍ በጥረት ላይ ተደማሪ ነው። ለአንድ ተቋም በተለይ እንደ ፖሊስ ለመሰሉ ህዝባዊ ተቋማት ወሣኝ የሚባሉት ህዝብ፣ አገር እና የተቋሙ የውስጥ አቅም ናቸው። ሌሎች ነገሮች በዚህ ላይ ተደማሪ ናቸው። በተረፈ እንደ አገር፣ መንግሥት ሆነ እንደ ህዝብ ያለው አቋም እነዚህ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነት የለንም።
ከነጉድለቱ እኛ ሀገራችን ማቅረብ በምትችለው ነገር የምንሰራው ሥራ በቂ ነው። ይህ ማለት የፖሊስ ተልዕኮ በበቃ የሰው ኃይል የሚፈፀም ብሎም ጽናትና እምነት ባለው የተቋም እሴቶች፣ ራዕይ ጠብቆ ዝግጁነት ባለው የሰው ኃይልና ሠራዊት የሚሰራና የሚፈጸም ነው። ከዚህ አኳያ ስናይ የሠራዊታችን አባላት ለማንኛውም ተልዕኮ እና ግዳጅና መስዕዋትነት ወደ ኋላ የሚሉ አይደሉም።
በራሳችን የውስጥ አቅም የምናደርጋቸው የማብቃት፣ አቅም ግንባታ፣ የሥልጠና ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው የፖሊስ ተልዕኮ የህዝብ ደህንነት፣ የህግ ማስከበር፣ የሕግ በላይነትን ማስጠበቅ የሚባሉት የአንድ አገር የግል ጉዳይ አይደሉም ድንበር ተሻጋሪና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳይ ናቸው። ወንጀል ድንበር ተሻጋሪ ነው።
በዓለም ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ብዙዎቹ ወንጀሎች በተለይም ትርፋማ የሆኑና በመደራጀት የሚፈፀሙ እንደ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ እፅ ዝውውር፣ ሽብር፣ ህገወጥ የፋይናንስ ዝውውር፣ ኮንትሮባንድና የመሳሰሉት ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ በተደራጀ አግባብ የሚፈፀሙት የረቀቁና ድንበር የሚሻገሩ ናቸው።
ስለዚህ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እነዚህን ወንጀለኞች በጋራ ነው መዋጋት ያለበት። ምናልባት ቀኝ ገዥ የነበሩ አገራት ለጥቅማቸው ሲሉ በተለየ ሁኔታ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት ቢኖራቸውም እንደ ዓለም በሁሉም አካባቢ ወንጀለኞች መደበቂያ እንዲያጡ ካልተደረገ የወንጀል ውጤቱ ዓለምን ያጠፋል። ስለዚህ ወንጀልን ለመዋጋት የዓለም አገራት የጋራ ትስስር አላቸው።
ኢትዮጵያም ወንጀል በመከላከል ረገድ ከምስራቅም ሆኑ ምዕራብ የሚገኙ የተለያየ አመለካከት ካላቸው በርካታ አገራት ጋር በጋራ ትሰራለች። ዓለም አቀፍ የፖሊስ አሶሴሽን፣ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ፖሊስ ቺፍስ አሶሴሽን እንዲሁም ሁለትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር ከጀርመን፣ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ ጋር እየሠራን ነው።
በአገር ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም በሰው ኃይል ግንባታዎች የሚያግዙ ሥራዎችን ለማከናወን ሥምምነቶችን በመፈራረም በጋራ እየሠራን ነው። ወንጀልን ለመከላከል በግል መቆም እንደማያወጣ እኛም ሆኑ እነርሱ እናውቃለን። ስለዚህ በህብረት እየሠራን ስለሆነ ጥሩ ለውጦች አሉ። ኮረናን በመከላከልም ሆነ የፖሊስ ተቋማትን በማሳደግና በማዘመን ረገድ በተቋማትና አገራት ደረጃ ከተለያዩ አገራት ጋር እየሰራን ነው። በቴክኖሎጂ ረገድም ድጋፍም እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ቴክኖሎጂ መሠረት በማድረግ ወንጀል እየተፈጸመና የፖሊስን አቅም የሚፈታተኑ ወንጀሎች እየተበራከቱ ነው። በዚህ ረገድ ቴክኖሎጂ የመታጠቅና መፈፀም አቅምን ከማሳደግ አኳያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ምን እየሰራ ነው?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡– መጪው ጊዜ የቴክኖሎጂ ዘመን ነው። እንደባለፈው ዘመን በጥንት የፖሊስ አሰራር ለመጪው ዘመን አያዋጣም። አሁን የምንከተለው ዕድገት አገርን ኢንዱስትራላይዝ የማድረግና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመታጠቅ ሁኔታ ግድ እየሆነ ነው። በመሆኑም የፖሊስ አሠራር ይህን መከተል አለበት። ቀደም ሲል በነበረው የፖሊስ አሠራር ለማስቀጠል ማሰብ ውጤታማ አያደርግም። አገር አዘምኖ ፖሊስን ኋላቀር አድርጎ መጓዝ አይቻልም።
ለምሳሌ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተጀመሩትና በቱሪዝም ዘርፍ ያለን ሃብት በደንብ አውቆ አገሪቷ የቱሪስቶች ማዕከል እንድትሆንና ተመራጭ አገራት ተርታ እንደተሰለፈች ይታወቃል። ስለዚህ በቱሪዝም እየተሰራ ያለው ነገር ሲያድግ ሌላውም ሊታሰብበት ይገባል። ቱሪዝም እና ቱሪስት በጣም የተሳሰሩ ናቸው።
ቱሪስቶች በጣም ነፃነት ይፈልጋሉ። ስለዚህ ቱሪስቶች በሚበዙበት አካባቢ ህግ የማስከብር ሥራው የፖሊስ ግርግር አይፈልግም። በመሆኑም መሰል የፖሊስ ግርግር ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ ይጠበቃል። ዘመናዊ ከተሞች በተሰሩ ቁጥር ዘመናዊ የፖሊስ ሥራ መታከል አለበት። በመሆኑም እጅግ የረቀቁ የዘመኑን የፖሊስ ቴክኖሎጂ በሁሉም ቦታ ማግኘት ተገቢ ነው። ይህን የመታጠቅ፣ የመጠቀም ብሎም በቴክኖሎጂ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ቀድሞ አውቆ ማስቀረትን ታሳቢ በማድረግ መሥራት ግድ ይላል።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የሚደገፉ ወንጀሎችን ከማክሸፍ ረገድ እንዴት ትገለፃለች?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡- በዚህ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም በጣም ኋላቋር ነው። ወንጀለኞች ቴክኖሎጂ በመታጠቅ በንፅፅር ይቀድማሉ። በሳይበር እና በሶሻል ሚዲያ የሚፈፀም ወንጀል እየረቀቀ ነው። ለአብነት በቴሌ ላይ እየተሰሩ ያሉ ወንጀሎችን በሚሊዮኖች እና ቢሊዮኖች ኪሳራ አደረሱ ሲባል ይሰማል። ይህን ከወንጀለኞች ሰምተን እንጂ ቀድመን አውቀን የማስቀረት አቅም የለንም። ይህን በሚገባ ተገንዝበናል።
በመሆኑም ፖሊስ ቴክኖሎጂን በመታጠቅ ወንጀልን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችለው አቅም እንዲኖረው እየተሰራ ነው። ቢፈፀምም በፍጥነት ማወቅ አለብን። በቀጣይም የቴክኖሎጂ የትምህርት ክፍል የቴክኖሎጂ ፖሊሲንግ የመከፈት ውጥን ያለ ሲሆን በዚህም ምርምር ማድረግ፣ ባለሙያ የማፍራት እና ቴክኖሎጂ የመታጠቅ አስፈላጊነት ታምኖበት እየተሠራ ነው። እስካሁን ያለው በጣም ኋላቀር ነው። ቴክኖሎጂ በእርግጥ አቅም፣ እውቀትና ብዙ ነገር ይጠይቃል። ስለዚህ በዚህ ላይ በሰፊ መሥራት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– ፖሊስን በቴክኖሎጂ እና እውቀት ማስታጠቁ እንደተጠበቀ ሆኖ ህዝባዊነትና ፖሊሳዊ ሥነምግባር መላበስና ሌላው መለያው ነው። ከዚህ አኳያ በሥነ ምግባር ጥሰት በመፈፀም ዜጎች በደል ይፈፀምብናል ሲሉ ቅሬታ ይሰማል። እርስዎ ምን ይላሉ?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን ፡- የሥነ ምግባር ጉዳይ በፖሊስ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ለዚህ ጥናት አያስፈልግም ህዝብን ቅር የሚያሰኙ ነገሮች ይፈፀማሉ። በመሆኑም ይህን እያረሙ መሄድ ይገባል። ይሁንና ግን ነገሮች በተገቢው ሚዛን መታየት አለባቸው።
የእኛ ተቋምና ፖሊሶቻችን ካለው ተልዕኮ ስፋት፣ ተልዕኮውን ከመፈፀም ከሚከፍሉት መሥዕዋትነት ካለባቸው ድካም፣ ጭንቀት እና ከሚደረግላቸው አንፃር ሲመዛዘን በየትኛውም ሚዛን ጤናማ አዕምሮ ያለው ቆም ብሎ ከስሜት ነጻ ሆኖ ቢያመዛዝን ከየትኛው ዓለም ከሚፈፀም አኳያ የእኛ ፖሊስ የተሻለ ነው።
የእኛ ሥነምግባር ምንጩ አንዱ የህዝቡን ባህልና እሴት የተገነባው በሃይማኖትና በጠንካራ ባህል ነው። በሁለተኛ ደረጃ በትምህርት ቤት ውስጥ የምናደርገው ግንባታ ትልቅ ነው። እነዚህ ልጆች ፖሊስ ከሆኑ በኋላ የፖሊሳዊ ሳይንስ ግንባታ እንደተጠበቀ ሆኖ ሥነ ባህሪ የምንገነባበት የኢንዶክተሬሽን መሰረታችን ህገመንግሥቱ ነው። ሌላው ህዝባዊ እሴት ነው። ሦስተኛው ደግሞ ዓለም አቀፍ የፖሊስ እሴት ነው።
ይህ ሁሉ ፖሊስ እራሱን ለህዝብ ፍላጎት አሳልፎ እንዲሰጥ የሚያዘጋጁ ናቸው። በዚህም በብዙ ቦታ ራሳቸውን መሥዕዋት እያደረጉ ነው የሚሰሩት። ብዙ ግርግርና ትርምስ ባለበት ቦታ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት። ሁሉ ሰው ባለው ልምድ ቢገመግም መልካም ነው።
ጥፋት ባለበት ቦታ ፖሊስ የሚያድነው ለመግደል ሳይሆን ተጠርጣሪን ለመያዝ ነው። ከአቅም በላይ ሲሆን ግን የሚወስዳቸው እርምጃዎች ይኖራሉ። ኃይለኛ ረብሻ እና ግርግር በተፈጠሩባቸው ቦታዎች ራሳቸውን ለጥቃት ጭምር ሰውን ሳይጎዱ ለመከላከል ነው የሚሞክሩት። ስለዚህ ማንኛውም ዜጋ መገንዘብ ያለበት ይህን ሚዛናዊ ሆኖ ማየት አለበት። በዚህ አገር ፖሊሶች በብዙ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየተገደሉ ጭምር አይገድሉም። ትልቅ አውቶማቲክ መሳሪያ ይዞ ፖሊስ በቀስት እና ተራ መሳሪያ ይገደላል። ይህን ሚዛናዊ ሆኖ ማየት አስፈላጊ ነው።
ይሁንና ሰው በመሆኑ መቶ በመቶ ፍፁም ባለመሆኑ መሳሳት ሊኖር ይችላል። ሆኖም እነዚህ መታረም እንዳለባቸው በኦፕሬሽን ወቅት የተፈፀመውን ሁኔታ በጥልቅ ግምገማ ይታረማል። እንደ ሁኔታውም ቅጣት ሊኖር ይችላል።
ከህዝብ ጋር ያለን ሥራና ትስስር ደካማ ነው። በኮሚዩኒቲ ፖሊስ ብዙ ነገር ለመሥራት እየተሞከረ ነው። ይህ ከፍተኛ በጀትና ብዙ የሰው ኃይል የሚጠይቅ ነው። በዚህ ላይ በጥልቀትና በተከታታይ ባለመስራታችን ክፍተቶች አሉ። የሆነው ሆኖ ግን ከነድክመቱም ቢሆን ህዝብ ከማንኛውም በላይ የፖሊስን ልፋት ይገነዘበዋል።
አዲስ ዘመን፡– የፖሊስ ሠራዊት መሥዋዕትነት በዚህ ደረጃ የሚገለፅ ከሆነ ጥቅማ ጥቅሞችን ከማስከበር አኳያ ምን ተሰርቷል?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡– ከዚህ አኳያ ብዙ ክፍተቶች አሉ ብዙም ሰርተናል። በመሠረታዊነት የአገር አቅም ይወስነዋል። እኛ አገር፣ ህዝብ እና ህገመንግሥት ሁሉን ነገር እንጠብቃለን። ሁለመናችን ነው የምንሰጠው። የጎሳ ግጭት፣ ሽብርና ሌላ ችግር ሲፈጠር ፖሊስ ራሱን መስዕዋት አድርጎ ዜጎችን ይታደጋል። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ይህ እሴት ራሳችንን እንዳናይ ያደርገናል። ስለዚህ ያልተደረገልን ሊደረግልን ይገባል ብለን መከራከር ላይ ሠራዊቱም ብቻ ሳይሆን መሪዎችም ጭምር ደካማ ነን። ስለዚህ ለሠራዊቱ መደረግ በሚገባው ላይ በጽናት በሚገባ መሥራት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– የፖሊስ ሠራዊት አባላት ሕይወታቸውን ስለሚገብሩ በሌላው ዓለም የሕይወት ኢንሹራንስ አላቸው። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታስ?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡- አሁን እያነሳሁት ያለው እዛ ደረጃ ሳይደርስ ነው። የዕለት ተዕለት ቀለቡ በአግባቡ እንደ ሰው ቢሆን መልካም ነው። ከባድ ስፖርት ይሰራል፣ ብርድ እና ፀሃይ ላይ ይቆማል፣ ሥራው ለአደጋ የተጋለጠ ነው። ፎቶ ኮፒ ላይ የሚሰራ ሰው ጨረር አለው ተብሎ የወተት እና ሌላ ጥቅማ ጥቅም አለው። በብርድ ጊዜ ‹‹ሬንጀር›› ለብሰው ይቆማሉ፤ ልብሱ የሚሞቅ ይመስላል ግን አይደለም። ፀሓይ ይፈራረቅባቸዋል። ፀሓይ እና ብርድ እየተፈራረቀባቸው ሙሉ ቀን በተመደቡበት ቦታ ይገኛሉ። ፍዝዝ ድክም ብለው ሙሉ ሰዓት ሥራቸውን ይሰራሉ።
ስለዚህ የህይወት ዋስትና ለእኛ ቅንጦት ነው። በሳምንት አንድ ቀን ሥጋ ጠብታ ሊበላበት የሚችልበት ነገር የለውም። የእኛ የወር ቀለባችን 850 ብር ነው። ወደ ቀን ሲመነዘር 28 ብር ነው። በ28 ብር ቁርስ፣ ምሳ እና እራት እንዲበሉ ይጠበቃል።
በአንድ ወቅት የመስክ ጉብኝት ወጥተን ነበር። የፖሊስ ደመወዝ ያኔ 300 ብር ነበር። የደመወዛቸውንና ቀለባቸውን አዋጥተው መጨረሻ የሚተርፋቸው 32 ብር ነበር። ይህን የምትነግረን የነበረው አንዲት ሴት ፖሊስ ናት። እኔ ሴት ነኝ። በተልዕኮ ከወንዶች እኩል ማናቸውም ግዳጅ ላይ እሳተፋለሁ። የወር አበባ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፤ ‹‹ሞዴስ›› ያስፈልገኛል ብላ ነበር።
ሴት ፖሊስ ናት ለፀጉሯ ቅባት ያስፈልጋታል። ታዲያ በዚህ 32 ብር እንዴት ሊበቃ ይችላል? ስለዚህ ይህ በቂ አይደለም። ግን የተሰጠን ነገር በማብቃቃት የአገርን ደህንነት፣ ኢኮኖሚ ችግር ታሳቢ በማድረግ እነዚህ ነገሮች ባለመሟላታቸው ሠራዊቱ ሥራ አልሰራም አይልም። ግን ሥራውን እየሠራ የሚያስፈልገውን ይጠይቃል።
ድህነቱን እኛ ብቻ መሸከም የለብንም። በእርግጥ ደግሞ አንዱ መታወቅ ያለበት ነገር ሠራዊቱ ብዙ ነው። ለሠራዊቱ የሚጨመረው ጭማሪ እንደ አገር ካለው ሠራዊት አኳያ ሲባዛ በመንግሥት በጀት ላይ የሚያመጣው ለውጥ በጣም ትልቅ ነው። ፖሊስ ሲታሰብ መከላከያ ታሳቢ ይደረጋል። ስለዚህ የሚጨመረው ነገር የአገር ነገር የማዛባት ባህሪ ይኖረዋል ከሚል እሳቤ አንጻር እኛም ራሳችንን ያዝ እናደርጋለን። ሠራዊቱም ጥያቄውን እየጠየቀ ስራውን ይሰራል። በቂ ካምፕ፣ በቂ መኖሪያ እና በቂ የሥራ መሳሪያዎች የሉም። ይህ ሊታሰብበት ይገባል።
ግን በዚሁ አጋጣሚ ማመስገን የምፈልገው ነገር አለ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ መንበረ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በርካታ ለውጦች አሉ። ለመጀመሪያ በተለየ ሁኔታ ባለፈው ዓመት ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል። በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ መንገድ ድጋፍ ተድርጓል። አሁን ያሉንን ጉድለቶች ለሟሟላት ድጋፍ እየተደረገ ነው። ይህ ጥሩ መነሳሳት ፈጥሯል። መንግሥት እንዲገነዘበው የምናደርገው ጥረት ፍሬ እያፈራ ነው።
ቀደም ሲል ግን ተንኮልም ነበር። ጤናማ ያልሆኑ መንግሥታት ፖሊስ ጠንካራ እንዲሆን አይፈልጉም። ፖሊስ በግልጽ ህግና ህግን መሰረት በማድረግ ብቻ ህግ ማስከበር፣ ሁሉንም እኩል በማየት በህግ ብቻ ስርዓትን የማስከበር ኃላፊነት አለበት። ጠንካራ ፖሊስ በዜጎች ላይ የሚፈጸም ወንጀልን እና ደባ ለመከላከል በፅናት ይቆማል። ስለዚህ ሙሰኞች እና አጥፊዎች፣ ህገ ወጦች፣ አምባገነኖች ህግን ሲጥሱና ዜጎችን ሲበድሉ በጽናት ከፊታቸው ይቆማል። ሙሰኞች እና አጥፊዎች፣ ህገ ወጦች፣ አምባገነኖች ጠንካራ የፖሊስ ተቋም እንዲኖር አይፈልጉም።
በአፍ ይናገራሉ። በተግባር ደካማ ዋስትና የሌለው፣ የሆነ ነገር ብታደርግ የሆነ ነገር እንደምትደረግ እንድታውቅና እንዲገባህ ያደርጋሉ። በዚህ ምክንያት ጠንካራ ፖሊስ እንዳይኖር እነዚህ ለፖሊስ የሚያስፈልጉ በግል ፖሊስ ለለፋበት የሚያገኝ፣ እንደ ተቋም በራስ የሚተማመን እንዳይኖረው አድርገው ቆይተዋል። አንዳንዴ ስንመለከተው መንግሥትና መንግሥት የሚመራው የፖለቲካ አካል ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲወገንና የእነርሱ ተላላኪ ሆኖ እንዲቆይ የተሰራው ሥራ ተቋሙን ሽባ አድርገውት ቆይተዋል።
አዲስ ዘመን፡–መንግሥታት እና ሥርዓቶች ሲቀያየሩስ በፖሊስ ሥራና ተቋም ላይ ተፅዕኖ አላሳደረም?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡- ፈጥሯል! በታሪክ እንደምንሰማው በንጉሡ ዘመን ምንም እንኳን ፖሊስ የንጉሡ አገልጋይ ቢሆንም ጠንከር ያለ የፖሊስ ተቋም እንደነበር እንሰማለን። በደርግ ዘመን ፖሊስ የማዳከም ሥራ እና ከወታደሩ ዝቅተኛ ሆኖ እንዲታይ የማድረግ ጫና ነበር። ፀጥታ እና ሕግ የማስከበር ሥራውን በወታደር ከዛ ያለፈውን ደግሞ በአብዮት ጥበቃ እንዲሠራ በማድረግ ፖሊስን ሽባ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል። ምክንያቱም ትክክለኛው የወንጀል ምርመራና መከላከል ሥራዎችም አልነበሩም።
አብዮት ጥበቃ የመከላከል ሥራውን ይዞ ነበር። የምርመራ ሥራውን ደግሞ ውስን የደርግ ኃይላት ከአብዮት ጥበቃው ጋር ይዘውት ነበር። ሰው እንደፈለጉ የሚገሉበትም ሁኔታ ነበር። ስለዚህ ፖሊስ በጣም ተዳክሞ ነበር።
በኢህአዴግ ዘመን የነበረውን የፖሊስ ኃይል ሙሉ ለሙሉ በማፍረስ በእውቀት የተገነባ ሳይሆን በትግሉ ዘመን በነበረው ታጋይ አስተሳሰብ እንዲመሩና እንዲያደራጁ ነው የተደረው። ለፖሊስ እውቀትና ብቃት የነበረው ትኩረት ሲበዛ ደካማ ነበር።
ታግሎ ያሸነፈው የፖለቲካ ባለቤት አካል ነበር። በመርህ ገለልተኛ ሆኖ ህገመንግሥት መጠበቅ ቢኖርበትም በተግባር ተቃራኒ ነው። በፅናት በሙያ እና በተሰጠው ኃላፊነት እንዳይሰራ ሆን ተብሎ ደባ ሲሰራ ነበር። በበጀት የማዳከም ሥራ ነበር።
በጀት የሚመደብልን የነበረው ምርጫ ሲመጣ ነበር። ምክንያቱም በምርጫው ወቅት ገዥው ፓርቲ የሚፈልጋቸው ነገሮች ማስከበር እንዲቻል ነው በተዘዋዋሪ ሲደረግ የነበረው። የማይፈልገውን የማዳከም ሥራ በሠላማዊ ጊዜ ፖሊስን የማብቃት፣ ህዝብን የማሳተፍ መርሆች እንዲተገበር እና በቂ ስልጠና፣ በጀትና ሃብት
እንዲኖር አይደረግም። በተልዕኮም በሙያ ነፃነትም እንዲሰራ አይደረግም ነበር። በዚህ የተነሳ ደካማ ነበር።
ከለውጡ በኋላ በተፈጠሩ ነገሮች እውነተኛ ጠንካራ ፖሊስ እንዲመጣ በንፅፅር የፖሊስን ተልዕኮ የተረዳ መሪ ቢኖር የተፈጠረው ‹‹አድቫንቴጅ›› ህዝብ ልዕልና ለማረጋገጥ የፖሊስን ተልዕኮ በህግና ህግ ብቻ መፈፀም እንዲችል ህገ መንግሥታዊ ተጠያቂነትና ህገ መንግሥታዊ እሴቶችን መሠረት አድርጎ እንዲሠራ ከመፈለግ አኳያ እምነቱ ስላለ በሃብት ራሳችን እንድንችል አይተን የማናውቀው ድጋፍ ተደርጎልናል።
ይህ በግለሰብ ደረጃ ፖሊስ ዘንድ የሚደርስ፤ እንደ ቡድን ለምንሠራቸው ሥራዎች ድጋፍ ያያዘ ነው። በሠራዊት አልባሳት፣ መኖሪያ ካምፕ፣ ምግብ፣ ትምህርት እና ስልጠና ራሳችን እንድንችል ነው ይህ የተደረገው። እስከ ዛሬ እንደ ፌዴራል ፖሊስ የራሳችን ማሰልጠኛ ተቋም የለንም። የምናሰለጥነው ከወታደራዊ ካምፖች በተውሶ ነበር። በየዓመቱ እስከ 5000 ፖሊስ እናሰለጥናለን። በራሳችን መልክ ወደ ተሻለ ለውጥ እንዳንገባ ሳይደረግ መቆየቱ ምን ያክል ትኩረት እንዳልተሰጠው ያሳያል።
ስለዚህ ከለውጡ በኋላ ብዙ ለውጦች ቢኖሩም ግን ገና ችግሮች አሉ። ለምሳሌ ቴክኖሎጂ ለእኛ እንደ ቅንጦት የሚታይ ግን እጅግ አስፈላጊ ነው። አሁን ያለው አሠራር መለወጥ አለበት። ለህግ ማስከበር ሥራው የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎች ገና መሠራት አለባቸው።
ቀደም ሲል በተለያዩ መስፈርቶች የፖለቲካ ኃይሉ የሚፈልጋቸው ዓይነት ሰዎችን የመመልመል ተጽዕኖ ነበር። በመርህ ፖሊስ ጥሩ ስብዕና፣ መልካም ዜግነትን፣ ጽናት፤ ታዛዥነትን፣ ፖሊሳዊ የአካል ብቃት ይጠይቃል። እነዚህ ሳይንሳዊ መስፈርት ናቸው። ከዚህ በዘለለ ግን አመለካከት የሚለው የተመረጡ ለአገዛዙ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን በማስገባት ሲስተሙን ቆላልፎ ለመያዝ ሲሰራ ነበር። በተግባርም ስንቸገርበት የነበረው የገዥ ኃይል አመለካከት እና የገዥ ኃይል አካል እንደ መስፈርት ይጠይቅ ነበር።
ይህ በፌዴራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ ሙያውን አዳክሞት ቆይቷል። አመለካከት በሚል እንደ ፈረስ ጋሪ የተወሰነ ነገር ብቻ ማሰብ የሚችሉ ሰዎች ብቻ እንዲሰባሰቡ የማድረግና የህግ የበላይነት፣ ህግመንግሥት መጠበቅና የህዝብ ወገንተኝነት ቀርቶ ገዥውን ፖለቲካና ፍላጎትና የአስተሳሰቡ አለቆችን የመጠበቅ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ ይህ ሁሉ በደል በፖሊስ ላይ ሲሠራ አመራር ነበሩ። ለምን ዝምታን መረጡ?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡– አዎ! አሁን ይህን መስፈርት መከተልና መተግበር ከመሠረታዊው መርህ፣ እኛ እንደ ፖሊስ ልንመራበት ከሚገባን መርህ ይቃረናል። አንደኛ የህዝብ ፖሊስና መከላከያ የሕዝቡን ተዋፅኦ መምሰል አለበት። የሕዝቡን ተዋፅኦ አለመምሰል በተለይም በየደረጃው ያለው አመራር በህዝቡ ያለንን ተዓማኒነት ሙሉ ለሙሉ አጥፍቶታል። ምን ሀቀኛ ነገር ብንሠራ ህዝቡን አይመስልም። መሪዎቹን ነው የሚመስለው ስለዚህ ይህን ነገር ማስተካከል አለብን ብለን ደጋግመን በማናጅመንትና ከዚያም በታች ባሉን ሁኔታዎች እንወያያለን። ግን የምትሰማው በልክ ነው። ምናልባትም በተናገርከው ነገር ትገመገምበታለህ፣ ትወቀርበታለህ፣ ሂስ ተቀብለህ ትኖራለህ።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ እንደ አመራር ይህ ፈተና ደርሶብዎታል?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡- በትክክል! ከምሰራባቸው የተለያዩ ቦታዎች ላይ የተነሳሁትና ከብዙ መሥሪያ ቤት የቀየርኩት በዕድገት አይደለም። በእንዲህ ዓይነት ባህርያቴ በመወገድ ነው። ‹‹ኮምፕሌን›› አላደርግም። ምክንያቱም ሲስተሙ የፈጠረው ነገር ነው። ሁል ጊዜ ራሴን አስተካክዬ መታገል ነው ያለብኝ የሚል እምነት አለኝ።
ስለዚህ በዚህ ባህሪዬ እስካሁን ያሉሁበት ቦታ ቢያንስ መከላከል ባልችል እኔ ያንን መጥፎ ነገር ባለመስራት መጥፎ ነገር የሚሰሩትን እኔ ባለሁበት መስመር ላይ ትክክል የሆነ ነገር እንዲሠሩ በማድረግ ጥፋት ቀንሷል። ተፅዕኖ መፍጠር በቻልኩበት እንዲስተካከል አደርጋለሁ። ይህ የእኔ መርህ ነው።
እኔ እንደ መርህ፣ አስተሳሰብ ጥሩ እምነት ነበረኝ። የሥርዓቱ ጥፋት እምነቱን ያለመተግበር፣ የተፃፈውን የምንነጋገርበትን የምንወያይበትን አለመፈፀም በተቃራኒው ሆኖ መገኘት ነበር ጥፋቱ። ስለዚህ የምንታገለው በተቃራኒው በሚፈፀመው ነገር ነው። ስለዚህ ይህ ነገር መታረም አለበት፣ የፖሊስ ተቋም የፖለቲካ ኃይል ተቋም መሆን የለበትም፣ የፖሊስ ፖለቲካው ህገመንግሥት ነው። ስለዚህ ፖለቲካ ይቅርብን በማለት በየጊዜው እንከራከራለን። ያው ትገመገምበታለህ። እኔ አለሁ ብዙም የሆንኩት ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፡– ተጨማሪ መልዕክት አለዎት?
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡– እንደ አገር አሁን የደረሰብን ፈታኝ ሁኔታ ለሁላችንም የሚያሳምመን ነው። እንደ ፖሊስ እና መከላከያ በጣም ነው ያሳመመን። ከዚህ ህመማችን ድነን ዳግም የዚህ ዓይነት ነገር ሊፈፀምባት የማይችል የፀናች ታሪኳን በተደማሪ የበለጠ የምታሳድግ አገር ለመገንባት ነው ጥረት እያደረግን ያለነው። በዚህ ወቅት እንደ ህዝብም እንደ ሠራዊትም እየተከፈለ ያለው መስዕዋትነትም የምንኮራበት ነው። በእኛ ዘመን ለተፈፀመው ጥፋትና ምናልባትም የእኛን ስም ይዘው ያሉ አካላት የጥፋት ኃይል መሳሪያ ለሆኑትም በጣም የምናፍርበትና ዳግም ይህ እንዳይከሰት ተምረን ራሳችን በተሻለ የምናበቃበት ነው።
ለህዝባችን፣ ለሠራዊታችን፣ በተለይም በግንባር ለነበሩ የሰሜን ዕዝ፣ የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል አባላትም ሆነው ምናልባትም በትግራይ ፖሊስ ውስጥ ሆነው የጁንታውን ተልዕኮ ባለመቀበል ከእኛ ጋር ሆነው ለታገሉት የሠራዊታችን አባላት ጭምር ትልቅ ክብር አለኝ። ህዝባችን ላደረገልን ድጋፍም ትልቅ ክብር አለኝ።
በጋራ ሆነን አገራችንን የመለወጥና መንግሥት ያሰባቸውን የብልፅግና እቅዶች ለማሳካት ሁልጊዜም ከመንግሥት ጎን ለመቆም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች አገር ለመገንባት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ገለልተኛ ሆነን ልናገለግላቸው የምንቆም መሆናችንን እየገለፅኩ ለሚደረጉልን ድጋፎች ሁሉ ላመሰግን እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7/2013