መርድ ክፍሉ
የወጣት ጥፋተኝነትን ለመተርጎም በመጀመሪያ /ወጣት/ የሚለውን የእድሜ ክልል መተርጎም አስፈላጊ ነው። ወጣት በሚባለው ፅንሰ ሀሳብ የሚገለፅ የዕድሜ ክልል በአገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ቀደም ሲል የነበረና አሁንም ያለ ቢሆንም የተለያዩ ማህበረሰቦችና ባህሎች ስለጉዳዩ ያላቸው ግንዛቤና አመለካከት እንደየራሳቸው ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ እድገታቸው የሚለያይ በመሆኑ ለወጣትነት አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም አልተገኘለትም።
በመሆኑም ሁሉም የሚያወጣውን ፖሊሲ ዓላማ መሰረት በማድረግ አመቺ ሆኖ በተገኘው ዕድሜ ላይ የተመሰረተ ትርጓሜ ይሰጠዋል። ለምሳሌ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከ15 እስከ 24 ዓመት ያለውን የእድሜ ክልል ወጣት በሚል ሲተረጎም፣ የዓለም ጤና ድርጅት ከ10 እስከ 24 ዓመት፣ የኢትዮጵያ የማሕበራዊ ደህንነትና ልማት ፖሊሲ ከ15 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ወጣት በማለት ይተረጉማሉ። የሌሎች አገሮችም የተለያዩ ተሞክሮዎችን ያስቀምጣሉ።
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በፌስቡክ ገፁ ስለ ወጣት ጥፋተኝነት ያሰፈረው መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ የወጣት ወንጀል አድራጊዎችን ጉዳይ የሚመለከቱ ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎችና ፖሊሲዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ሕገ-መንግሥት፣ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ፣ የማህበራዊ ደህንነት ጉዳዮች ፖሊሲ፣ የወንጀል ሕግ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ በዋናነት ይጠቀሳሉ። ይሁንና የወጣት አጥፊዎችን ምንነት በተመለከተ በሕገ-መንግሥቱም፣ በወንጀል ሕጉም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በግልጽ ትርጓሜ አልተሰጠውም።
በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት ስንመለከት ህፃን ማለት ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው ነው። የአንድ ህፃን የወንጀል ህግን የመተላለፍ ችሎታ የወንጀል ኃላፊነት በመባል ይታወቃል። የኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ ሥርዓትም ለህፃናት የወንጀል ኃላፊነት ፅንሰ-ሀሳብ ዕውቅና የሚሰጥ ነው።
የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን ለወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሂደት ሲባል ለሦስት ምድብ ከፍሎአቸዋል። ከ9 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ህፃናት ሲሆኑ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 52 መሠረት የወንጀል ኃላፊነት የሌለባቸው በመሆኑ ቤተሰቦቻቸው ወይም ሌሎች የቅርብ አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ በፅሁፉ ተቀምጧል።
ሁለተኛው ደረጃ ከ9 እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህፃናት በወንጀል ውስጥ ተካፋይ ሆነው በተገኙ ጊዜ እንደወጣት አጥፊ ተቆጥረው የወንጀል ተጠያቂነት ያለባቸው መሆኑን የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 53 ይደነግጋል። ይሁንና እነዚህ ወጣት አጥፊዎችን በተመለከተ የምርመራውንም ሆነ የፍርድ ሂደቱን በተመለከተ ከአዋቂዎች በተለየ መንገድ በልዩ ድንጋጌዎች የሚመራ መሆኑን ፅሑፉ ያሰፍራል።
በመጨረሻም በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከ15 እስከ 18 ዓመት የዕድሜ ክልል አንቀጽ 56 መሠረት የወንጀል ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን እንደ አዋቂ ተቆጥረው በመደበኛው ፍርድ ቤት ጉዳያቸው የሚታይ ነው። በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን በተመለከተ የዕድሜያቸውን ትንሽነት ፍርድ ቤቱ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቅጣቱ ሊቀልላቸው እንደሚችል በዚሁ ድንጋጌ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
ስለዚህ በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ከ15 ዓመት የበለጠ ዕድሜ ያለው ነገር ግን 18 ዓመት ያልሞላቸው ህፃናት እንደ ወጣት አጥፊ የማይቆጠሩና ለወንጀል ተጠያቂነት ሲባል እንደ አዋቂ የሚቆጠሩ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ስለዚህ በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ ወጣት አጥፊ ማለት ከ9 እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሆነ/ች ሆኖ የወንጀል ድርጊት የፈፀመ/ች ህፃን ማለት ነው።
የወጣት አጥፊዎች አያያዝስ ምን
መምሰል አለበት?
ለወጣት አጥፊዎች ልዩ አያያዝ አስፈላጊ ከሆኑበት ምክንያቶች ዋነኛው ወጣት አጥፊዎች የድርጊታቸውን ውጤት በመረዳት በኩል በአካልም ሆነ በአስተሳሰብ ከአዋቂዎች አንፃር ያልበሰሉ በመሆኑ እንደ አዋቂዎች የድርጊታቸውን ውጤት ለመረዳት አለመቻላቸው ሲሆን ሌላው መደበኛው ሂደት ከአዋቂዎች እኩል የሚያያቸው በመሆኑ ህፃናቱን ላልተፈለገ ውጤትና መገለል ሊያጋልጥ የሚችል በመሆኑ ነው።
ወጣት አጥፊዎች ህፃን እንደመሆናቸው መጠን የተለየ የመማር ችሎታ ያላቸው በመሆኑ ቅጣት ሳይሆን በትምህርታዊ አያያዝ የመለወጥ አቅማቸው ከአዋቂዎች ይልቅ የተሻለ በመሆኑ ልዩ አያያዝ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ነው።
በተለይ ወጣቶች መደበኛውን ባህሪና ፀባይ ያልያዙ በመሆኑ ከአዋቂዎች ይልቅ ከችግሮቻቸው ለመሻሻል ተስፋ ሰጭ ናቸው። ስለዚህ ወጣት አጥፊዎችን ከቅጣት ይልቅ በትምህርትና በማረም አምራችና ንቁ ዜጋ ለማድረግ ይቻላል። ይህ አስተሳሰብም በተለያዩ የአገራችን ሕጎች እና ፖሊሲዎች የተንፀባረቀ ሲሆን በዋነኛነትም ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ እና የወንጀል ሕግና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ የሚጠቀሱ መሆናቸውን በጠቅላይ አቃቤ ህግ ማህበራዊ ገፅ ላይ የሰፈረው መረጃ ያሳያል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 36 ላይ የሕፃናት መብቶችን በጠቅላላው እና የወጣት አጥፊዎችን አያያዝ በተመለከተ በልዩ ሁኔታ ተመልክቶ ይገኛል። አንቀጽ 36/2/፡- “ሕፃናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ በመንግሥታዊ ወይም በግል የበጐ አድራጐት ተቋሞች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በአስተዳደር ባለስልጣኖች ወይም በሕግ አውጭ አካላት የሕፃናት ደህንነት በቀደምትነት መታሰብ አለበት“ በማለት ሕፃናትን የሚመለከቱ ጉዳዮች በሚስተናገዱበት ጊዜ የሕፃናቱ ደህንነት በተቀዳሚነት ሊታሰብ እንደሚገባ ከሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን አንቀጽ 3/1/ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ተቀምጧል።
በተጨማሪም በዚህ አንቀጽ ላይ የተመለከተው “የአስተዳደር ባለስልጣኖች“ የሚለው ቃል የዐቃቤ ሕግ፣ የፖሊስ እና መሰል ተቋሞችን የሚያካትት መሆኑን መረዳት ይቻላል። በሌላ በኩልም በሕገ መንግስታችን አንቀጽ 36/3/ ላይ በማረሚያ ወይም ማቋቋሚያ ተቋሞች የሚገኙ ወጣት አጥፊዎች ከአዋቂዎች ተለይተው መያዝ እንዳለባቸው በግልጽና በማያሻማ መልኩ መቀመጡን ፅሁፉ ያትታል።
የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ታምራት ኪዳነ ማርያም እንደሚናገሩት፤ ወጣት ጥፋተኛ ሲባል እድሜያቸው ከዘጠኝ ዓመት በላይ የሚገኙና እስከ አስራ አምስት አመት ያሉት ታዳጊዎች ወንጀል መሰል ነገር ውስጥ ሲገኙ ነው። አያያዛቸው እንደ አዋቂ ሰው መሆን የለበትም። አዋቂ ሲባል ለወንጀል ችሎታ ያለው ማለትም እድሜው ከአስራ ስምንት በላይ የሆነ ሰውን ያካትታል።
አዋቂ ሰው ወንጀል ፈፅሞ ሲገኝ በሚያዝበት መንገድ ወጣት አጥፊ መያዝ የለበትም። ወጣት ጥፋተኞች አያያዛቸው የተለየ መሆን አለበት። በሰሩት ወንጀል የተፈረደባቸውም ከሆነ ሊታሰሩም የሚገባው እንደማንኛውም ሰው ተቀላቅለው መታሰር የለባቸውም። ለብቻቸው መቀመጥ አለባቸው።
ወጣት ጥፋተኞችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሕግ ወጣቶቹ ካሉበት ስህተት የሚታረሙበትን መንገድ የሚያስቀምጥ ነው። ሕጉ ጥፋተኞቹን መቀጣጫ ማድረግ ወይም ቂም በቀል የሚወጣባቸው አይደለም። የሕጉ ትኩረት በዚህ እድሜያቸው ወንጀል ውስጥ ሊገቡ የቻሉበትን ምክንያት አጣርቶ ለወደፊቱ ከወንጀል የሚርቁበትን መላ መፈለግ ላይ ያተኩራል።
የሥነ ልቦና ችግር ወይም አንድ ማህበራዊ ችግር ወደ ወንጀል እንደሚከታቸው ይታሰባል። ወጣት ጥፋተኞች ልምድ ስለሌላቸው ወደ ወንጀል እንደሚገቡም ይገመታል። የአገሪቱ ሕግ ችግራቸውን መፍታት ላይ የሚያተኩር መሆኑን ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያ ሕግ ወጣት ጥፋተኞች ከመቅጣትና ከማረም የበለጠ ችግራቸውን በመቅረፍ ማስተማር ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው። በዚህም ብዙ ዓይነት የጥንቃቄ ስራዎች ያሉ ሲሆን በሕጉ ቅጣት ብቻ ሳይሆን የወጣት ማሳደጊያ ማስገባት ወይም ፀባይ ማረሚያ ማስቀመጥ እንደ አማራጭ እንደሚወሰድ አቶ ታምራት ያብራራሉ። ሌላው ደግሞ ወጣት ጥፋተኞችን ለወላጆቻቸው በመስጠት በጥብቅ ክትትል እንዲቆጣጠሯቸው ማድረግ እንደሚቻል በመጥቀስ፤ በሚማሩበት ትምህርት ቤት ቁጥጥር ማድረግ ሌላኛው አማራጭ መሆኑን ያስረዳሉ።
ወጣት ጥፋተኞች የሚዳኙት በመደበኛው ሕግ ወይም በመደበኛው የሕጉ አፈፃፀም የሚከናወን አይደለም የሚሉት አቶ ታምራት፤ አዋቂዎች ወንጀል ሰርተው ሲገኙ ዳኛ አንድ ጊዜ ከፈረደ በኋላ የፈረደውን መልሶ ማየትም ሆነ ማሻሻል አይችልም። ስህተት እንኳን ቢኖር ሊሻሻል የሚችለው በይግባኝ ብቻ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ነገር ግን በአንዳንድ ልዩ ሁኔታዎች ውስጥ የወጣት አጥፊዎች ፍርድ ይካተታል። በወጣት አጥፊዎች ጉዳይ የዳኛ ስራ የተወሰነው ቅጣት የሚያርማቸው ካልሆነ ሊለውጥ እንደሚችል ይናገራሉ።
እንደ አቶ ታምራት ማብራሪያ፤ ወጣቶች በሽብር ስራዎች ላይ የተሰማሩ ከሆነ በዋናነት መጠየቅ ያለበት ለሽብር ስራ ያሰማራቸው ሰው ነው። ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችን በጦርነት ማሰማራት በአለም አቀፍ ህግ የተከለከለ ነው። በዚህም ወጣቶቹን የመለመሉ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑ ሲሆን በጦርነትም ሆነ በሽብር ተግባር የተሰማሩ ወጣቶችም ከተሰማሩበት ተግባር እንዲታረሙ ተመጣጣኝ ቅጣት ሊወሰንባቸው ይችላል።
ሌላው በወጣት ጥፋተኞች ላይ የሚወሰን የሞት ፍርድ በሚመለከት ‹‹የሞት ፍርድ በአለም አቀፍ ደረጃ ከአስራ ስምንት ዓመት በታች በሆኑት ላይ ተፈፃሚ አይሆንም። በኢትዮጵም ህግ በተመሳሳይ ከአስራ ስምንት ዓመት በታች በሆኑ ታዳጊዎች ላይ የሞት ፍርድ አይፈፀምም።›› ይላሉ። በምሳሌነትም በአሜሪካን አገር ከአስራ ሰባት ዓመት በላይ በሚገኙ ወጣት አጥፊዎች ላይ እንደሰሩት ወንጀል የሞት ፍርድ ሊበየን ይችላል።
ነገር ግን ይህ ሁኔታ አለም አቀፍ ህግን የሚፃረር ነው። ከአሜሪካ በስተቀር የትኛውም አገር ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሚገኙ ወጣቶች ላይ የሞት ቅጣት አይወሰንም። የሚወሰኑ ቅጣቶች ለወጣቶቹ ተመጣጣኝ መሆን አለበት። ህፃናትን ለሽብር የሚያሰማሩት ላይ ጠበቅ ያለ ርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ያመለክታሉ።
በ2003 ዓ.ም በተዘጋጀው የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ እንደሚያመለክተው፤ በማንኛውም የፍርድ አሰጣጥ ሂደት እና ፍርድ ከተሰጠም በኋላ ወጣት ወንጀል አድራጊዎች የሚደረግላቸው አያያዝ ወጣቶቹ ከገቡበት የተሳሳተ መንገድ እንዲወጡ፣ ቀና አስተሳሰብን እንዲያዳብሩ፣ ሠላማዊና ለሕግ ተገዢ የሆነ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ዘዴ የተከተለ መሆን ይኖርበታል። በዚህ ረገድ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ዋነኛ ዓላማ ወጣቶቹን ማስተማር እና በሂደትም ከቤተሰብና ከማኀበረሰቡ ጋር የተሣካ ውህደት እንዲፈጥሩ ማስቻል መሆን ይኖርበታል።
ወጣት ወንጀል አድራጊዎች በሕግ ፊት ሁለም እኩል ነው በሚል ምክንያት በፍርድ ቤት ቀርበው እንዲመሰክሩ፣ ጥፋታቸውን እንዲያምኑ፣ መስቀለኛ ጥያቄ ሊቀርብባቸው ወይም በአቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ሊገደዱ አይገባም።
እንደ ወንጀል ፍትህ ፖሊሲው፤ በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ አማራጭ የመፍትሔ እርምጃዎች ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት የሚሰጣቸው ተቋማት በፌደራል እና በክልሎች ደረጃ እንዲቋቋሙ ይደረጋል። ተቋማቱ ተግባራዊ የሚደረገውን አማራጭ የመፍትሔ እርምጃ አግባብነት፣ ለወጣቱ የተለየ ሁኔታ ተስማሚ መሆኑን እና ወጣቱ ከፈፀመው የወንጀል ድርጊት ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው።
በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ አማራጭ የመፍትሔ እርምጃዎች አግባብነት፣ ይዘት፣ ዓይነት እና ዝርዝር አፈፃፀምን አስመልክቶ በመስኩ የሚሻሻልና የሚቀረፁ ሕጎች፣ መመሪያዎች እና ፕሮግራሞች በሕገመንግሥት ውስጥ የተካተቱትን ወይም በሕገመንግሥቱ መሠረት ዕውቅና ያገኙትን የወጣት ወንጀል አድራጊዎች መብቶችን እና ልዩ ጥበቃዎችን ባገናዘበ መልኩ መሆን ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2013