ወርቅነሽ ደምሰው
በኢትዮጵያ በደኖች መመናመን ምክንያት የሚፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጆች ጤንነት ከሚያደርሰው ጉዳት ባሻገር ምርትና ምርታማነትን በመቀነስም ተፅዕኖው ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡በዚህም የተነሳ በከርሰ ምድርና በከባቢ አየር ላይ እየታየ ያለው የተፈጥሮ ክስተት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ይገኛል፡፡
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችሉትን ያልታሰቡ የድርቅ አደጋዎች ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል አማራጭ የሌለው መፍትሔ በመሆኑ ህብረተሰቡን በችግኝ ተከላ ፣ አፈር ጥበቃ፣ በውሃ አያያዝ፣ በመስኖ ልማትና የተፋሰስ ልማት በማሳተፍ በተፈጥሮ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶች የመቋቋም ሰፊ ሥራዎች ማከናወን ይጠበቃል፡፡ የተራቆተ የደን ሀብት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ለመልክዓ ምድሩና ለአየር ንብረቱ ተስማሚ የሆኑ አማራጮች መጠቀም የግድ ይላል፡፡
እንደባለሙያዎች ምክር የተፈጥሮ ሀብት ማልማት የአካባቢውን ልምላሜ ከመመለስ ባሻገር ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ ደርቀው የነበሩ ምንጮች ውሃ እንዲይዙ በማድረግ እርጥበታማ አየር እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ሆኖም ግን በሀገሪቱ ቀደም ባሉት ጊዜያት የተፈጥሮ ሀብቶች በማልማት እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው በመቅረቱና ሥራዎች ባለመሰራታቸው አብዛኞዎቹ አካባቢዎች መጎዳታቸው ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአካባቢ ልማት ሥራ ላይ ያለው ተሳትፎ አበረታች እየሆነ በመምጣቱ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡በየተፈጥሮ ሀብት ልማት እንቅስቃሴ አበረታች ተሞክሮ ካላቸው ክልሎች አማራ ክልል ይጠቀሳል፡፡እኛም የክልሉን እንቅስቃሴ የቃኘንበትን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
በክልሉ ከተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ውስጥ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች አበረታች ውጤት የታየባቸው መሆኑን በክልሉ በግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ተወካይና የደን ባለሙያ አቶ እስመለአለም ምህረት ይገልጻሉ፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በክልሉ ቀደም ባሉት ጊዜያት የተፋሰስ ልማት እቅድ በማውረድ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡
ክልሉ ለዞን፣ ለወረዳ ፣ ለቀበሌና ተፋሰስ በማውረድ ነበር የልማቱ ሥራ የሚከናወነው፡፡በአሁኑ ጊዜ ግን ከላይ ወደታች የነበረው እቅድ የማውረድ አሰራር ቀርቶ ከላይ እስከታች የሚያሳትፍ ዕቅድ በማዘጋጀት የልማቱን ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ውጤታማ የሚያደርግ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለመግባትም ጊዜ ተወስዶ ተከናውኗል፡፡
በእቅዱ ትኩረት አቅጣጫ መሠረት በተፋሰስ ልማቱ እስካሁን ሲሰራ የነበረውንና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከታች አጥርቶ በመያዝ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
በዘንድሮ ዓመት በተፋሰስ ልማት ይሰራባቸዋል ተብለው በእቅድ ከተያዙት መካከልም 8ሺህ209 አካባቢ ተፋሰሶች የተለዩ ሲሆን፣በዕቅዱ አዲስና ነባር ስራዎች ተካተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በተፈጥሮ ሀብት ልማት ዙሪያ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የሰው ኃይል ልየታ ሥራ ነው ፡፡
በዚህም በዘንድሮ ዓመት ወደ 4ነጥብ5 ሚሊዮን የሰው ኃይል ለማሳተፍ ቢታሰብም እስካሁን መለየት የተቻለው 3ነጥብ 4 ሚሊዮን ወይም 75 በመቶ የሚሆን የሰው ሀይል ነው:: የሰው ሀይል የልየታ ሥራው በአብዛኛው ቢጠናቀቅም በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ይሆናል:: ይህ በተፈጥሮ ሀብት ሥራ ላይ የሚሰማራው የሰው ሀይል እንደ እርከን፣ የተራራ ልማት ሥራዎችና በመሳሳሉት ላይ የሚሳተፍ ሆኖ የሰው ኃይል ልየታው እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ከታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ እስከ መጋቢት አካባቢ ሊሄድ የሚችል ሲሆን፤ በዋናነት ከጥር 15 እስከ የካቲት 30 ይጠናቀቃል ተብሎ ታሳቢ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
በተፈጥሮ ሀብት ከሚሠሩት ሥራዎች ውስጥ የማሳ ላይ እርከን፣ የተራራ ልማት ስራዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ ሥራዎች በአንዴ የሚጠናቀቁ ሳይሆን እንደ የአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ይከናወናሉ፡፡አንዳንዶቹም ዓመቱን ሙሉ የሚሠሩ፣ከፊሎቹ ደግሞ በአንዴ የሚያልቁ ናቸው:: በተፋሰስ ልማት ሥራ 328ሺህ 534 ሄክታር መሬት ላይ ለመስራት ታቅዶ አሁን ላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በ2012 በተፈጥሮ ሀብት ልማት የተከናወኑ ሥራዎች በጣም ጥሩ በመሆኑ፣ በተፋሰስ ልማት 361ሺህ 926ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 254 ሺህ 278 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል:: የልማት ሥራው በታቀደው መሠረት እየተተገበረ በነበረበት ወቅት ድንገት በተከሰተው ኮቪድ 19 ወረርሽ ምክንያት በተለይ የበልግ አምራች የሆኑት የሰሜን ሸዋ፣ የምስራቅ ጎጃምና የደቡብ ወሎ አካባቢዎች ሰብል ሥራውን ጨርሰው ወደ ተፈጥሮ ሀብት ልማት በሚገቡበት ወቅት መከሰቱ እቅዳቸውን ሳይፈጸሙ የቀሩ ቢሆንም ፤ ሥራዎች ከመጓተታቸው በስተቀር የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡በጸጥታ ምክንያት በሀገሪቷ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባይታወጅ እና በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያቶች ሥራዎች ባይስተጓጎሉ ኖሮ በነበረው የህዝብ መነቃቃት፣የክትትልና ትኩረት የበለጠ አፈጻጸም ማስመዝገብ ይቻል ነበር፡፡
ሥራውን መልሶ ለማስጀመር ለችግኝ ጣቢያና ለግብርና ሠራተኞች ግንዛቤ በመፍጠርና ለጽዳት አገልግሎት የሚውሉ እንደ ሳኒታይዘርና ሳሙና በማስራጨት አርሶ አደሩ በግሉ ማሳ ላይ የሚያስራውን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ተረባርቦ ለመመለስ በተደረገ ጥረት የተወሰነ መሻሻሎች ታይተዋል። በቡድን የሚሰሩ ሥራዎች ላይ እስካሁንም ችግሮች መኖራቸውን ዳይሬክተሩ ያብራራሉ፡፡
በተፈጥሮ ሀብት ልማት ከሚሠሩት ሥራዎች ውስጥ የማሳ ላይ የአፈር ክለት በመከላከል፣ በጎርፍ የሚወሰደውን ደለል ለመቀነስ ተጠቃሽ መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በተራራ ላይ ልማት ቤንችና እርከን የሚባሉ ይጠቀሳሉ፡፡የተራራ ልማት የሥራ እድል መፍጠሪያ በማድረግ በተለይ ቤንች እርከን ሥራን ከፍራፍሬና ከደን ጋር አያይዞ ወደ ምርታማነት ለመቀየር እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡
ከዚህም ተጨማሪም የተለያዩ የአፈር ገደል የሆኑ ቦታዎችን ወደነበሩበት የመመለስና ትርፍ ውሃ ባለበት አካባቢ ትርፍ ውሃውን የማስወገድ ሥራዎች የሚሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል። እነዚህ ሥራዎች በእያንዳንዱ ሲዘረዘር በጣም ሰፊ በመሆናቸው የማሳ ላይ ልማት የአፈር እርከንና የተለያዩ ሥራዎች የሚያካትት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተራራ ላይ ልማት የተራራ ላይ የእርከን ሥራና አነስተኛ የውሃ መያዝ መዋቅር እንዲሁም በቦረቦሮ አካባቢ ክትርና ቦረቦር ቅርጽ ማስተካከል የመሳሰሉት መጥቀስ የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በተመሳሳይም በደን ልማት ሥራ የደን ተከላ የሚካሄዱ ሲሆን፤ የተከላ ቦታ ልየታ በተከናወነባቸው ቦታዎች ችግኝ ማፍላትና ተከላ ማካሄድ የመሳሰሉት ሥራዎች ይሰራሉ:: ባለፈው ዓመት በክረምት ወቅት በርካታ የችግኝ ተከላ ሥራ ተካሂዳል::
በዚህም ከተተከሉት 1ነጥብ 5 ቢሊዮኑ ችግኝ ውስጥ እስካሁን ወደ 1ነጥብ 316 ቢሊየን አካባቢ የአረምና የኮትኳቶ ሥራ በመስራት እንክብካቤ እየተደረገ ሲሆን፤ አፈጻጸሙም 83 በመቶ ደርሷል:: የዘንድሮ የዝናቡ ሥርጭት ከበድ ያለ ስለነበረ የአረምና የኮትኳት ስራው በሁለት አይነት መንገድ ነው የተከናወነው፡፡ የመጀመሪያው ክረምቱ እየባሰ ስለሄደ ችግኝ የተተከለበት አካባቢ ጉድጓዱ ውሃ የመያዝ ወይም የመሸከም ሁኔታ ስለነበረ እሱን የማስወገድና ከተወገደ በኋላም አፈር የመሙላት ሥራ ነው፡፡
ሁለተኛው ክረምቱ እየወጣ ሲሄድ ደግሞ የአረምና የኮትኳቶ ሥራ ወይም ዙሪያውን በመሸፈን አፈሩን የማነሳሳትና በራሱ ላይ ልባስ ማድረግ የመሳሰሉትና እስካሁን እየተሰሩ ያሉት የተሻሉ ናቸው፡፡የመስክ ምልክታና ክትትል እንዲሁም ከዞን ባለሙያዎች ጋር በቅርበት እየተከናወነ ያለው ሥራም በበጀት አመቱ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
በተፋስስ ልማት በትኩረት ከሚሰሩ ሥራዎች አንዱ ግድቦች ማልማት ሲሆን፣በክልሉ ባሉት በርካታ ግድቦች የተፋሰስ ልማት ሥራዎች በተሰራባቸው ወይም ገና በሚሠራባቸው አካባቢ ቅድሚያ በመስጠት የሥነ አካላዊ ሥራዎች መስራት የሚል መርህ ይጠቀሳል፡፡በተለይም ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ደለልን የመከላከሉ ሥራ የአባይን ፣ የአዋሽንና የተከዜን ግድቦች ለመታደግ ያግዛል፡፡ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ወደ ሥራ የተገባ በመሆኑም ውጤታማ እንደሚሆን ይጠበቃል ፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ልቅ ግጦሽ በማስቆምም ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡በዚህም ትኩረት የተሰጠው ለእንስሳት ምግብነት የሚውል መኖ ማዘጋጀት ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት በተራቆቱና በቦረቦር መሬቶች ላይ ለእንስሳት መኖ የሚሆኑ የተለያዩ የሣርና እጽዋት ዝርያዎች እንዲተከሉ በማድረግ ለእንስሳቱ መኖ ማቅረብ ተችሏል፡፡በተሻለ መንገድ በተሰራበት አካባቢ ልቅ ግጦሽን ማስቀረት ተችሏል ፡፡
አሁን ላይ በአንዳንድ ቀበሌዎች ልቅ ግጦሽ ማስቆም ተችሏል፡፡ይህ ደግሞ የሰብል ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል፡፡ የአፈር ክለት እየቀነስ መምጣቱም የዝናብ ውሃ መጥጦ በማስቀረት አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡በተለይም የህብረተሰቡ አስተሳሰብ በተቀየረባቸው አካባቢዎች ለተፈጥሮ ሀብት ልማት የሚሰጠው ትኩረትና እንክብካቤ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ አንዱ የሌላውን በማየት በሂደት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው ቸልተኝነት ተወግዶ በሁሉም አካባቢ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል የሚል እምነት ተይዟል፡፡
የህብረተሰቡን ለተፈጥሮ ሀብት የሚሰጠውን ትኩረት ከፍ እንዲል ለማድረግ የተፋሰስ ልማት ተቋማት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተውጣጥተው በተመረጡ የኮሚቴ አባላት በማወያየት ወደ አንድ ሀሳብ እንዲመጡ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ህብረተሰቡ እየለሙ ባሉና ወደፊት በሚለሙ የተፋሰስ ልማቶች ላይ ካልተስማማ ተግባራዊ ማድረግ ስለማይቻልም በክልሉ የአሰራር ሥርአት ተዘርግቷል፡፡በተዘረጋው አሰራርም ህብረተሰቡ ህገ ደንብ በማውጣት የልማት ሥራውን ያከናውናል፡፡በየጎጡ የማወያየት ሥራም ይከናወናል፡፡
ተጠቃሚነት አንጻር ለአብነት በተፋሰሱ ልማቱ ተሳታፊ የሆኑ 150 ሰዎች በ500 ሄክታር መሬት የእንስሳት መኖ የሚያለሙ ከሆነ ሁሉም አባላት መኖውን አጭደው እኩል እንዲካፈሉ ቅድመ ሁኔታ ተመቻችቷል ፡፡ ቀደም ሲል ከብት ያለው የተፋሰሱ አባል ብቻ መኖውን የሚወስድበት አሰራር ነበር፡፡በአሁኑ ግን ከብት ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው እኩል እንዲካፈሉ ተደርጓል፡፡ከብት የሌላቸው ላላቸው በመሸጥ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡እንዲህ ያለው ፍትሐዊ አሰራር ሁሉም እኩል ለተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ትኩረት እንዲሰጡ ያስችላል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎችን በመስራት ረገድ ከሚነሱት ችግሮች ውስጥ አንዱ ህብረተሰቡን በአንዴ አሳምኖ ወደ ሥራ መግባት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የተፋሰስ ተቋማት በመገንባት፣ አስተሳሰብን በመቀየር ግንዛቤ መፍጠር ጊዜ እንደሚወስድ ይናገራሉ፡፡ ግንዛቤው ከተፈጠረ በኋላ ግን ውጤቱ አመርቂ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልማት ሥራው በአንድ አካል ጥረት ብቻ ውጤታማ እንደማይሆን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች እገዛ አስፈላጊ መሆኑን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ውጤታማ ሥራዎችን በማሳየት እንዲበረታቱ ቢያደርጉ የላቀ ውጤት ይመዘገባል የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2013