በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተገነቡና አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ከ50 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አንዳንዶቹ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቁ ተማሪዎችን በመቀበል ያስተናግዳሉ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት አብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎች ግን መብራትና ውሃን ጨምሮ በመሰረተ ልማት እጥረት የተነሳ የመማር ማስተማሩን ስራ በአግባቡ ማከናወን አለመቻላቸውን ያማርራሉ፡፡
ይህንንም በተመለከተ በህዝብ ተወካዮ ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በእንጅባራ፣ ሰላሌና ጎንደር የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመገኘት ምልከታ አድርጎ ነበር፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም በምልከታው በየተቋማቱ ችግሮች መኖራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
የሰው ሀብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ክፍሌ ለማ እንደሚሉት፤ ጥናት ያደረጉባቸው ቦታዎች ከግንባታ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ለተቋራጭ ገንዘብ በጊዜው አለመከፈልና የግንባታ መጓተት፣ በየተቋማቱ የሚሰጠው የመውጫ ፈተና በተማሪዎች ተቀባይነት ማጣት፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የውሃ አቅርቦት ማነስ እንዲሁም በትምህርት ክፍሎች ውስጥ ያለው የብሄር ስብጥር ተመጣጣኝ አለመሆን በዩኒቨርሲቲዎቹ ለሚነሱ ችግሮች ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው፡፡
በፌዴራል ደረጃ የተዘጋጁ ዲዛይኖች በፍጥነት አለመሻሻል ለግንባታ መጓተት ምክንያት ነው የሚሉት አቶ ክፍሌ፤ ግንባታዎች ከተያዘላቸው ጊዜ በላይ ተቋራጮች ሲያጓትቱ እርምጃ አለመውሰድና በሌላ በኩል ችግሮቹ ወደ ፍርድ ቤት በሚወሰዱበት ወቅት አፋጣኝ እርምጃ አለመውሰድ በግንባታ ስራዎች ላይ መጓተት እንደፈጠረ በምልከታው መታየቱን ይጠቁማሉ፡፡
ለአዳዲስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚቀርበው የሃይል አቅርቦት አነስተኛና የተቆራረጠ መሆኑ እና አፋጣኝ መፍትሄ አለመሰጠቱ የማስተማር ስራው ላይ እክል መፍጠሩን በመጥቀስ፤ ለጊዜያዊነት ጀኔሬተር የቀረበ ቢሆንም በእንጅባራና በሰላሌ ጀነሬተሮቹ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን በምልከታው መታየቱን ይገልፃሉ፡፡
እንደ አቶ ክፍሌ ገለፃ፤ ምልከታ በተደረገባቸው ሁለቱ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች በቂ የቤተ ሙከራ ግብዓቶች ሳይኖሩ ሁሉም ነገር ከተሟላላቸው ዩኒቨርሲቲዎች እኩል የመውጫ ፈተና እንድንፈተን መደረጉ ፍትሀዊ አይደለም የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ አዳዲስ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከግንዛቤ የከተተ የፈተና አሰጣጥ ባለመኖሩም በተማሪዎች ዘንድ ቅሬታ እየተፈጠረ ነው፡፡
የተማሪዎች ምደባ የብሄር ስብጥር በጠበቀ መልኩ ቢካሄድ ተማሪዎቹ የሚገጥማቸው የቋንቋም ሆነ የሌላ ማበራዊ ችግር እንደሚፈታ የሚጠቁሙት አቶ ክፍሌ የተወሰኑ ተማሪዎች አንድ ዲፓርትመንት ውስጥ እንዲመደቡ መደረጉ እያጋጠመ ላለው የፀጥታ ችግር መንስኤ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ከፍተኛ የውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ለኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ኮርፖሬሽን ስራው ቢሰጥም እስካሁን ስራው ባለመጀመሩ ተማሪዎቹ ለችግር መዳረጋቸውን በምልከታው መታየቱን ጠቁመዋል፡፡ ተቋሙ በጊዜያዊነት የሚጠቀምበት ከከተማው የሚመጣው የውሃ መስመር በብልሽት ምክንያት በመቋረጡ ተማሪዎች ችግር ውስጥ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡
የ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ከተማ መስቀላ፤ በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሃይል አቅርቦት አነስተኛ በመሆኑ አቅራቢያ ካሉ ከተሞች ሃይል በመሳብ በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ፡፡ ለዩኒቨርሲቲዎቹ ሃይል ለማሟላት ከመብራት ሃይል አገልግሎት ጋር ውል ተገብቶ ገንዘብ ቢከፈልም እስካሁን ሃይል አለመቅረቡን በመጥቀስ፤ ያለውን ችግር ለመፍታት ስራዎች ቢጀመሩም መዘግየታቸውን ይጠቁማሉ፡፡
በአዳዲስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ጀነሬተር ቢሰጥም አቅራቢው ከዋናው መስመር ጋር የሚያገናኘው ገመድ ዋጋው ጨምሯል ገንዘብ ይጨመርልኝ ማለቱን በመጥቀስ፤ ግዥ ኤጀንሲ ደግሞ ውል በገባው መሰረት ማቅረብ አለበት በማለቱ ገመዶቹ እስኪገዙ መዘግየቱን ይናገራሉ፡፡ የሃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ዘላቂ የሃይል አቅርቦት የሚያስፈልግ ቢሆንም የኢትዮጰያ ኤሌክትሪክ ሃይል የትራንስፎርመር ችግር ስላለብን ከውጭ ገዝቶ እስኪያስገባ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ግንባታ የሚያዘገዩቱን ተቋራጮች ውል ሲቋረጥም በአፋጣኝ በአዲስ የማይተኩት በህግ የተያዘው ጉዳይ ሳይጠናቀቅ ለአዲስ መስጠት ስለማይቻል መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ የውሃ አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት በየክልሎቹ የሚገኙ የውሃ ስራዎች ኢንተርፕራይዞች የውሃ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ እንደሚገኙ በመጥቀስ፤ ወደ ተቋማቱ ለማድረስ የበጀት እጥረት እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ በሰላሌ ያለው ጉዳይ የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ኮርፖሬሽን ጉድጓዱ ካለበት እስከ ተቋሙ ድረስ ለማምጣት በገጠመው ችግር ስራው በፍጥነት አለመከናወኑን ያመለክታሉ፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደሚሉት፤ የሚታዩት ችግሮች በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚስተዋል ነው፡፡ የመብራት መቆራረጡ አገራዊ ችግር ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ሜጋ ዋት የሚሆን ሃይል ያስፈልጋል፡፡ መብራት ሃይል የሚያስፈልገውን ሜጋ ዋት ባለማቅረቡ ምክንያት ከየአካባቢው አንድ ነጥብ አምስት ሜጋ ዋት በመሳብ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ለተቋማቱ የተሰጡት ጀነሬተሮችም ችግሩን መፍታት አይችሉም፡፡
የመውጫ ፈተና ለማስተግበር በአገሪቱ ሁሉም ተቋም ተመሳሳይ አቅም ላይ መገኘት የለበትም የሚሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ የመውጫ ፈተና የሚሰጠው የስራ ገበያውን የሚቀላቀል ተማሪ ቢያንስ ማወቅ ያለበትን ጉዳይ አውቋል ወይ የሚለውን ለመለየት በመሆኑ ይህንን ታሳቢ በማድረግ የሚዘጋጅ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ አዳዲሶቹ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በግብዓትና በሰው ሃይል በደንብ የተደራጁ ባለመሆናቸው እዛ ገብቶ የሚማር ተማሪ የራሱ የሆነ ክፍተት የሚፈጥርበት በመሆኑ የሚካካስበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡
ዶክተር ሳሙኤል እንደሚሉት የመውጫ ፈተና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ ለማረጋገጥ፣ ለማጎልበትና ለመቆጣጠር ጠቃሚ ነው፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ደግሞ የመምህራን ልማት ስራ ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም የመምህራን ልማት ላይ ከተሰራ ተማሪውን በመቀየር ጥራት ማምጣት ስለሚቻል ለዚህ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 20/2011
መርድ ክፍሉ