ደምስ ይግዛው (እጩ ዶ/ር)
በጀርመን የሀንጋሪ አይሁዶች ማሰቃያ ካምፕ (ኦሸዊትዝ) ሰለባ የነበረው ዶክተር ሚክሎስ ኒዝሊ «የናዚ ጭፍጨፋ በኦሸዊትዝ» በተሰኜው መጽሐፉ ገጽ 49 የናዚ ጀርመን መንግሥት በኦሸዊትዝ አቅራቢያ የሚገኘውን የቢርክናው መንደር ሙሉ በሙሉ በመውረስና ነዋሪዎችቹን ወደ ሌላ ቦታ በማስፈር የኦሻዊትዝ የማጎሪያና የጭፍጨፋ ካምፕን መሰረተ ይለናል (ኒዝሊ፣63) ። በዚህ ካምፕ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳዊያን በአንድ ባቡር ታጭቀው ለቀናት በረሃብና በውሃ ጥም እየተሰቃዩ ከተጓዙ በኋላ በቦታው ደርሰው ከተሳፈሩበት ባቡር እንዲወርዱ ከተደረገ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በዚህ ካምፕ በጅምላ በመርዝ ጋዝ ይገደላሉ (ዝኒ ከማሁ)።
በሌላ በኩል አይሁዳዊያን ከሀንጋሪ፣ ከፖላንድና ቼክ እንዲሁም ፀረ ናዚ አቋም የነበራቸው አውሮፓውያንንና ጂፕሲዎች (ዘርን ማፅዳት በሚል ስበብ) ወደዚህ የግድያ ካምፕ በባቡር ተጓጉዘው እንዲመጡ በማድረግ በድብደባ፣ በመርፌ በሚሰጥ ክሎሮፎርም፣ ኢ-ሰባአዊ በሆነ የጉልበት ሥራ፣ በመርዝ ጋዝ፣ በኤሌትሪክ ሞገድና በበሽታ ግድያ ከተፈፀመ በኋላ አስክሬናቸው በካንፑ ውስጥ በተሰሩ ግዙፍ የማቃጠያ ምድጃዎች እንዲቃጠል ይደረጋል (ኒዝሊ 67)። ሌላው የግድያ ዘዴ ደግሞ እስረኞችን በጥይት በጅምላ መፍጀት ነው ይለናል (ዝኒ ከማሁ)።
በርግጥ ኦሽዊትዝ ብቸኛው የናዚ የጭፍጨፋ ካምፕ አልነበረም። የሀንጋሪና የፖላንድ አይሁዶች የተጨፈጨፉበት እንደክራኩ እና ሉባሊን እንዲሁም ከቼክ ሪፑብሊክና ከመላው አውሮፓ የመጡ አይሁዳዊያንና ፀረ-ናዚ አቋም የነበራቸው ግለሰቦች የተፈጁባቸው እንደ ኢቤንሴ፣ ሜልክ አዶርኖ፣ ሙታሰንና ሊትስማንስታደት የመሳሰሉት የመጨፍጨፊያ ማጎሪያዎች ካምፖች ጥቂቶቹ ናቸው (ኒዝሊ፣149)።
ወደ እነዚህ ማጎሪያ ጣቢያዎች የመጡ አይሁዶች የወርቅ ጥርስ ይወልቃል፣ ጫማና ልብሳቸው ይወሰዳል፣ ፀጉራቸው ለፈንጂ መስሪያ አገልግሎት እንዲውል ይላጫል በመጨረሻም በግፍ ተገድለው እንዲቃጠሉ ይደረጋል (ኒዝል – 41)።
በናዚ የማጎሪያና የጅምላ ጭፍጨፋ ካምፖች ግድያው የሚፈፅመው የናዚ ጀርመን «SS›› በተባሉ የናዚ ሂትለር ታማኝ ወታደሮች ነው ። የሟቾችን ሬሳ የማቃጠል ተግባር ደግሞ ከራሳቸው ከታሳሪዎቹ በተመለመሉና “ሶንዶር ኮማንዶ” እየተባሉ በሚጠሩ ቡድኖች ነው።
የእነዚህ ሶንዶር ኮማንዶዎች እድሜ አራት ወራት ሲሆን ይህ ጊዜ ሲሞላ ይገደሉና በተራቸው በሌሎች እንደ አዲስ በሚመለመሉ ኮማንዶዎች እንዲቃጠሉ ይደረጋል። በተለይ በኦሽዊትዝ ግድያውን የሚያስተባብሩትና የሚፈፅሙት ዶ/ር ሜንጌል፣ ሻለቃ ዶ/ር ኬሊ፣ ሙስፊልድና ሞሌ እንደነበሩ የመፅሐፉ ደራሲ ዶክተር ሚክሎስ ኒዝሊ ይገልፃሉ።
በዚህ የናዚዎች ዘግናኝ የጅምላ ጭፍጨፋ ከ5-6ሚሊዮን የሚገመቱ የቼክ፣ሀንጋሪና ፖላንድ አይሁዳውያን ዜጎች በግፍ ተጨፍጭፈው አልቀዋል። (ኒዝሊ፣124)
አቶ ገብረመድህን አርአያ የቀድሞ የሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ የኢኮኖሚ ኃላፊ የነበሩ ናቸው። የድርጅቱን (ህወሓት) አካሄድ በመቃወም በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በወቅቱ ለነበረው ወታደራዊ መንግሥት እጃቸውን በመስጠት ከጥቂት ጊዚያት በኋላ ደግሞ ኑሮአቸውን በአውስትራሊያ በስደት ያደረጉ የትግራይ (ዓድዋ) ተወላጅ ናቸው።
ግለሰቡ ከዓመታት በፊት (እ.ኤ.አ 2012) ኢሳት ለተባለው የመገናኛ አውታር የሰጡትን ቃለ መጠይቅ መሰረት በማድረግ ከመገናኛ አውታሩ ድረገጽ You tube በማውረድ በህወሓት ማጎሪያና ጭፍጨፋ ካምፖች የተፈፀመውን ዘግናኝ ታሪክ እንደ ሚከተለው ይቀርባል።
እንደ አቶ ገብረመድህን ገለፃ « በወቅቱ ህወሓት ሓለዋ ወያነ (የወያኔ እስር ቤት) ወይም 06 (ባዶ ሸድሸተ -ባዶ ስድስት) ብሎ በማቋቋም በተለያየ የትግራይ አካባቢዎች ማጎሪያና ጭፍጨፋ ካምፖች እንደነበሩት ይገልፃሉ። እንደግለሰቡ ገለፃ እነዚህን የማጎሪያና የጅምላ የመጨፍጨፊያ ካምፖች የመሰረተው ህቡር ገ/ኪዳን በሚባል ታጋይ (አሁን በስኳር ኮርፖሬሽን ግዥ ክፍል ቡድን መሪ እና የህወሓት የቁጥጥር ኮሚሽን አባል ሆኖ ሲሰራ የነበረ) እንደሆነ ያብራራሉ።»
እንደ
አቶ ገብረመድህን አርአያ
ገለፃ እያንዳንዱ እስር
ቤት (ሓለዋ ወያኔ
– 06) የተቋቋመበት ዓላማ የወልቃይት
አማሮችን በጅምላ ለመፍጀትና
የህዝቡን መሬት ለመንጠቅ፣
ህወሓትን የሚቃወሙ የትግራይ
ተወላጆችን ለመግደል እንደሆነ
ያብራራሉ። የግለሰቡ ገለፃ
እንደሚከተለው አጥሮ ይነበባል።
1 .ፃዒ ሓለዋ ወያነ፡-
ይህ የማጎሪያና የመግደያ ካምፕ በትግራይ፣ ዓድዋ ልዩ ስሙ ማይ ቂንጣል በሚባል አካባቢ የተመሰረተ ነው። ይህ እስር ቤት ከምድር በታች የተሰሩ 150 ክፍሎች (cells) አሉት። ቤቶችም 3 ሜትር ከመሬት በታች ተቆፍረው የተገነቡ ናቸው። በእያንዳንዱ እስር ቤት(cells) ከ100-150 ሰዎች ተጨናንቀው እንዲታሰሩ ይደረጋል። በእዚህ የማጎሪያ ካምፕ ሰዎች የሚገደሉት በቶርቸርና በጢስ በማፈን (chamber of gas) ነው ።
ይህ እስር ቤት በዋነኝነት የወልቃይት አማሮችን ዘር ለማጥፋት ታቅዶ እንደተገነባ ይገለፃሉ። በዚህ እስር ቤት በተከናወነው የግድያ ዘዴ እስከ 1973 ዓ.ም ድረስ ወደ 15 ሺ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች እንደተገደሉበት አብራርተዋል።
2. ዓዲ መሐመዳይ ሀለዋ ወያነ፡-
ይህ የማጎሪያና የመግደያ ካምፕ በትግራይ ሽሬ አውራጃ ልዩ ስሙ ሽራሮ በሚባል አካባቢ የተገነባ ። በዚህ የማጎሪያ ካምፕ ከመሬት በታች የተገነቡ ብዙ የእስር ቤት ክፍሎች (cells) እንደነበሩና ታሳሪዎች ደግሞ በሙሉ የወልቃይት ፀገዴና ጠለሞት አማሮች (ወንዶች፣ ሴቶችና ህፃናት) ናቸው በማለት ይናገራሉ።
በዚህ ማጎሪያ ካምፕ በወንዶች ብልትና በሴቶች ጡት እስከ 5 ኪሎ ግራም የሚመዝን ክብደት ያለው ነገር በማንጠልጠል ግፍ የተፈፀመበት ነው። እስር ቤቱ አርባ አምስት (45 ) ጠባቂዎች ወይም ገዳዮችን ያካተተ ነበር። በዚህም ግፍ የተሞላበት የእስረኞች ስቃይ ማማ ብዙ ሺህ አማሮች በጅምላ እንደተጨፈጨፉ ቃለ ምልልስ አድራጊው ገልፀዋል።
3. ወርዒ ሓለዋ ወያኔ፡-
እንደ አቶ ገ/መድህን ኣርዓያ ገለፃ ይህ እስር ቤት በትግራይ፣ ዓጋመ አውራጃ ልዩ ስሙ ኣዴት በሚባል አካባቢ የተመሰረተ ሲሆን ዋና አላማውም የቀድሞ መንግሥት ሠራዊት ምርኮኞችን ለመግደል ታልሞ የተፈጠረ ማጎሪያና መግደያ እደሆነ ይገለፃል። በእዚህ እስር ቤት ግድያ ይፈፀም የነበረው በኪኒን መልክ በሚሰጥ መድሃኒት፣ በጋለ ብረት ሆድን በመተኮስና ያበዱ ውሾች በሚገደሉበት ሳይናይድ በተባለ መርዝ ነበር ብለዋል። በዚህ እስር ቤት እስከ ሰባት መቶ ሰባ (770) የሚደርሱ የቀድሞ መንግሥት ወታደሮች የተፈጁበት እንደነበር ያስረዳሉ።
4. ቡንበት ሓለዋ ወያነ
ይህ እስር ቤት ሕንፍሽፍሽ ፈጥራችኋል የተባሉ የህወሓት ታጋዮች በ1969 ዓ.ም የተፈጁበት ነው። ይህ እስር ቤት ሰላሳ ገዳይና ጠባቂ አባላት ነበሩበት።
5. ሱር ሓለዋ ወያኔ
ይህ ማጎሪያ ካምፕ ስሙ ከቡንበትነት ወደ ሱርነት የተቀየረና በትግራይ፣ ሽሬ አውራጃ ልዩ ስሙ ሸራሮ አፅርጋ በሚባል አካባቢ የሚገኝ አደገኛ እስር ቤት ነው። በዚህ እስር ቤት ሁለት በሁለት ካሬ ሆነው ( 2×2) ከመሬት በታች ተቆፍረው በተሰሩ ክፍሎች እስረኞች ይታሰራሉ። በአንድ ክፍል እስከ 200 ሰዎች ይታሰሩበት ነበር። በዚህ እስር ቤት ከአስር እስከ አስራ አምስት ሺህ ( ከ 10 -15 ሺ ) በላይ አማራዎች በግፍ እንደተፈጁበት ቃለ ምልልስ አድራጊው ይናገራሉ።
6. ዓዲ በቕሊዒት ሓለዋ ወያነ
በእዚህ እስር ቤት ግድያ የሚፈጽመው በመርዝና በሚስጥር በሚሰጥ መርፌ ነው።
7. ዓይጋ ሓለዋ ወያነ
የራሱ ታሪክ ያለው፤ ለወልቃይት ፀገዴ ቅርብ የሆነና ብዙ የዚህ ኣካባቢ አማራዎች የተፈጁበት እስርና መግደያ ቤት ነው።
8. ባህላ ሓለዋ ወያነ
ይህ እስር ቤት የትግራይ አርበኞች እና የወለቃይት ፀገዴ አማሮች የተፈጁበት ነው። ሲሉ ገልፀዋል።
9. ፍየል ውሃ ሓለዋ ወያነ
ይህ እስር ቤት በወለቃይት ፀገዴ የሚገኝ ሲሆን ከ15-20 ሺህ አማሮች የተፈጁበት ነው።
10. ግህነብ ሓለዋ ወያነ
ይህ እስር ቤት በሽሬ አውራጃ ማይ ገባ አካባቢ (አሁን ወልቃይት ስኳር ፋብሪካ የሚገነባበት) በቃሌማ ወንዝ ዳርቻ የሚገኝ ሲሆን 200 የጉድጓድ እስር ቤቶች የነበሩበትና አብዛኛው ጨለማ ቤቶችን ያካተተ ሲሆን ሟች ራሱ መቃብሩን የሚቆፍርበት ነው።
በእዚህ እስር ቤት አብዛኛው እስረኛ በጨለማው ምክንያት የሚታወርበት እንዲሁም የሴቶችና ወንዶችን ብልትን በመተኮስ የሚገደልበት ነው። በብዙ ሺህ የወልቃይት አማራዎች እንደተገደሉበት ይገመታል። በዚህ እስር ቤት ከ1969-83 ዓ.ም. እስከ አርባ ሺህ የሚገመቱ የወልቃይት አማሮች የተገደሉበት ነው።
11 ዓዲ ጨጓር ሓለዋ ወያነ
ይህ እስር ቤት ብዙ አማራዎች እና ፀረ ህወሓት አቋም የነበራቸው የትግራይ ተወላጆች የተገደሉበት ነው። በ1970 ዎቹ መጀመሪያ ሕንፍሽፍሽ(ትርምስና ማደናገር) ፈጥራችኋል በሚል ታጋዮች የተገደሉበት እስር ቤት ነው።
- በለሳ ማይ ሓማቶ ሓለዋ ወያነ
ይህ እስር ቤት በትግራይ ዓድዋ አውራጃ ገርሑ ስርናይ አካባቢ ልዩ ስሙ ዕገላ በተባለ ቦታ የተመሰረተ ነው። ብዙ የወልቃይት አማራዎች እንዲሁም ፀረ ህወሓት አቋም የነበራቸው የትግራይ ተወላጆች የተገደሉበት ነው። በዚህ እስር ቤት ሃያ አምስት አባላት የነበሩት ገዳይ ነበረው።
በእዚህ እስር ቤት እስረኞች የሚመረመሩት በግርፋት፣ በዕሳት እና የጋለ ብረት በማቃጠል፣ አስተኝቶ ከግንድ ጋር በማሰር (ራቁትን)፣ በወንድ ብልትና በሴት ጡት አሸዋ በማንጠልጠል የሚከናወን ነበር። እስከ ሚያዝያ 1972 ዓ.ም ድረስ በአረጋዊ በርሄና ስብሀት ነጋ ፍርድ ሰጭነት 153 የትግራይ አርበኞች፣ 232 ታጋዮች ህንፍሽፍሽ ፈጥራችኋል የተባሉ እንደ እነ ወርቅ ልዑል፣ ግራዝማች ታደሉ፣ የመሳሰሉት የተገደሉበት ነው። ሟቾች በአንድ ጉድጓድ በጅምላ የሚቀበሩበት እስር ቤት ነበር ይሉናል።
ዓዲ ውእሎ ሓለዋ ወያነ- በዚህ እስር ቤት በብዙ ሺህ አማራዎች ተገድለዋል ዓስገራ ሓለዋ ወያነ
ይህ እስር ቤት በአፋር ክልል አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ብዙ ዜጎቻችን የተፈጁበት ነው።
ማርዋ ሀለዋ ወያነ
ይህ እስር ቤት ዓድዋ ገርዑ ስርናይ ኸውያ አካባቢ የሚገኝ እስር ቤት ነው።
የዱጋ ዱግኒ ማጎሪያ ማሰቃያና ግድያ ካምፕ
ይህ የማጎሪያና ማሰቃያ ካምፕ (concentration camp) በቀድሞ የሽሬ አውራጃ አስገደ ወረዳ ዱጋ ዱግኒ ቀበሌ በሚገኘው ተራራ ስር ከመሬት በታች በ2 ሜትር ጥልቀት ተቆፍሮ የተሠራ እስር ቤት ነው ። የስቃዮች ሁሉ ማማ በሆነው በዚህ የማጎሪያና መጨፍጨፊያ (መግደያ) እስር ቤት በምሽግ መልክ የተሰሩ በርካታ ክፍሎች (cells) ሲኖሩት በአንድ ክፍል ከ70-80 ሰዎች ተጨናንቀውና ተፋፍገው ያለመኝታ ወይም በፈረቃ በመተኛት ስቃይንና ሞትን የሚጠባበቁበትና የወልቃይት ፀለምትና ፀገዴ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን አበሳ፣ ስቃይና የሞት ፅዋ የጨለጡበት ነው። ይህ ማጎሪያ ካምፕ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ግፍ ሲፈፀምበት የቆየና በተለይ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ከ3500 የሚልቁ የወልቃይት ወንድና ሴት ሽማግሌና ህፃናት ዜጎቻችን የማቀቁበት በጣት የሚቆጠሩት ከመትረፋቸው በስተቀር አብዛኛዎቹ በስቃይ ተገድለው ሬሳቸው ወደ ገደል የተወረወረበት ነው።
ዘመን ህዳር 29/2012 ዓ.ም