አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ሲካሄድ የህዝብ ጥያቄ የእኩልነት እንጂ ነጻ የመውጣት ጥያቄ እንዳልነበር የሕግና ፖሊሲ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ብርሃነመስቀል አበበ ገለጹ። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከማንነት ወደ አስተሳሰብ ፖለቲካ መሸጋገር እንዳለበትም ጠቁመዋል።ዶክተር ብርሃነመስቀል ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት በዚትዮጵያ ቀድሞ በነበሩትስርዓቶች በአንድ ቋንቋ፣ እምነትና ባህል ላይ በተመሰረተ የአንድ ህዝብና አገር ግንባታ ምክንያት የህዝቦች ማንነት ተጨፍልቆ ቆይቷል። ይሄን ተከትሎም የማንነት ጥያቄ ጎልቶ እንዲደመጥ ሆኗል። ይህ ማለት ግን ነጻ የመውጣት ጥያቄ ሳይሆን በማንነት እኩል የመሆን ጥያቄ ነው።
“የብሔር ፖለቲካ ነጻ አገር የመመስረት ወይም አገር የመሆን ፖለቲካ ነው። በኢትዮጵያ ያለው የማንነት ፖለቲካ ነው፤” የሚሉት ዶክተር ብርሃነመስቀል፤ በአንጻሩ ማንነትና ቋንቋዬ ይከበር፣ እኩልነት ይኑር፣ አልገለል፣ ራሴን በራሴ ላስተዳደር፣ የሚሉ ጥያቄዎች ማንነቴ እኩልነት ይኑረው የሚል እንጂ ነጻ ልውጣ ማለት አለመሆኑን አብራርተዋል።
“ሲጀመር የነበረው የእኩልነት ጥያቄ እንጂ ነጻ የመውጣት ጥያቄ አይደለም። ማን ከማን ነጻ ይወጣል፣ የጋራ አገር ነው ያለን፤” ሲሉም ይጠይቃሉ። በኦሮሞና አማራ መካከል ያለው አስተዳደር በቋንቋ፣ በባህልና በሌሎችም ምክንያቶች አድሏዊነት ካለ፤ ኦሮሞው መብቴ ይከበር ማለቱ የእኩልነት እንጂ ነጻ የመውጣት ጥያቄ ማቅረቡ አለመሆኑን ለአብነት በማንሳት ያስረዳሉ።
እንደ ዶክተር ብርሃነመስቀል ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝቦች አንዱ ካንዱ የተዋጋበት ሁኔታ የለም። ሥርዓቶች ግን ችግር መፍጠራቸውን ሁሉም ያምናል። ህዝብ ደግሞ እነኛን ስርዓቶች እንዴት እናስተካክላለን እንጂ እንዴት እንባላለን ብሎ ጠይቆም አያውቅም። ከዚህ አኳያ ህዝቡ ያልጠየቀውን የህዝቡ ስነልቡና ውስጥ መክተት ስህተት ነው። እናም እኩልነት ከተረጋገጥ የማንነት ፖለቲካ በአስተዳደርና ፖሊሲ አማራጮች ላይ በተመሰረተ የአስተሳሰብ ፖለቲካ ሊተካ፤ ሽግግሩም ወደ አስተሳሰብ ፖለቲካ ሊገባ ይገባል።
ምክንያቱም የማንነት ጥያቄ የሕግ፣ የፖሊሲና የተቋማት ጉዳይ ምላሽ ሲያገኝ በሰዎች የተለያዩ ማንነቶች ላይ የተመሰረቱ መገለሎች ስለሚወገዱ ህዝቦች መከባበርና መቀባበል ውስጥ እንዲገቡ ያስችላል። የማንነት ፖለቲካም ያበቃል። ከዛ በኋላ አድሏዊነት ካለ ጉዳዩ የፖለቲካ ሳይሆን የፍርድ ቤት ስለሚሆን ሰዎች ፍርድ ቤት ሄደው ችግሮቻቸውን ይፈታሉ። ይህ ሲሆን ፖለቲካው የማንነት ሳይሆን የአስተሳሰብ መሰረት ይይዛል። አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታም ፖለቲካው ከማንነት ወደ አስተሳሰብ እንዲሸጋገር መስራትና መደላድል መፍጠር ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2011
ወንደሰን ሽመልስ